በብዙ ሴቶች ላይ የወር አበባ በሚታይባቸው ወቅቶች ከባድ የህመምና ምቾትን የሚነሱ ስሜቶች ይስተዋላሉ። የአመጋገብ ባለሙያው እና የአኗኗር ዘይቤ መስራች ዶክተር ሮሂኒ ፓቲልን ሴቶች በወር አበባ ወቅት መውሰድ ያለባቸውና የሌለባቸው ምግቦችን በተመለከተ ጠይቀናቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተውናል። መልካም ንባብ።
“የወር አበባ በራሱ አይጎዳም፣ ነገር ግን ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡት ህመሞች ወይም ሌሎች የማይመቹ ምልክቶች ስለሚኖሩ በዚህ ወቅት ከሌላው ወቅትም በተሻለ መልኩ ልጃገረዶች/ሴቶች/ ለጤናማ የአመጋገብ ስርአትና ለንፅህና አጠባበቅ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።” ብለዋል። ይህ በዋነኝነት ምክንያቱ በወር አበባ ወቅት ተገቢ ያልሆነ የአመጋገብ ስርአትን መከተል በራሱ የራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ተቅማጥ.. ሊያስከትል ስለሚችል የአመጋገብ ስርዓት ባለሙያው ሴቶች በዚህ ወቅት ሊመገቡዋቸው የሚገቡ ጥቂት የምግብ ዓይነቶችን እንዲሁም በወር አበባ ወቅት መጠቀም የሌለባቸውን ዶክተር ፓቲል እንዲህ አስቀምጠዋል።
ሴቶች በወር አበባ ወቅት ሊመገቧቸው ከሚገቡ የምግብ ዓይነቶች መካከል ቅጠላ ቅጠሎች እና ፍራፍሬዎች ዓይነት ናቸው። በወር አበባ ወቅት በሰውነታችን ውስጥ ያለ አይረን መቀነስ ስለሚያጋጥም ብዙውን ጊዜ ይህ ወደ ሰውነት ህመም፣ ድካም እና ራስ ማዞር ስለሚያመራ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶችን እንዲሁም በውሃ የበለፀጉ ፍራፍሬዎችን እንደ ሐብሐብ እና ዱባ፤ የስኳር ፍላጎቶች ካሉዎት ደግሞ ጣፋጭነት ያላቸውን ፍራፍሬዎች ይመገቡ።
ሞቅ ያለ የዝንጅብል ሻይ የማቅለሽለሽ ስሜትን በማስወገድና በውስጡ የስቃይ ስሜትን የሚፈጥሩ ጡንቻዎችን በማስታገስ ጥሩ ስሜት እንዲሰማዎት ይረዳዎታል።
ዶሮ እና ዓሣ እነኚህን በፕሮቲን እና በኦሜጋ 3 ቅባት የበለፀጉ ምግቦችን አመጋገብዎ ላይ ማከሉ ለጠቅላላው ጤናዎ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። በይበልጥ ግን እነኚህ ምግቦች በአይረን እና ፕሮቲን የበለፀጉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በወር አበባ ወቅት መጠቀሞ በሰውነት ውስጥ የሚኖርን ሀይል የማጣት ስሜት ያጠፋል።
ምስር በጣም ጥሩ የፕሮቲን ምንጭና በአይረን የበለፀገ ስለሆነ በዚህ ወቅት መመገባችንን ተመራጭ ያደርገዋል። ለውዝ እና ጥቁር ቸኮሌት በማግኒዥየም እና በአይረን የበለፀገ ስለሆነ በየቀኑ ከእነዚህ ውስጥ በወር አበባ ወቅት አንድ እፍኝ መውሰድዎን ያረጋግጡ።
ለውዝ በኦሜጋ 3 የሰባ አሲዶች የበለፀገ እና ትልቅ የፕሮቲን ምንጭ ያለው ነው። ለውዝን ብቻውን ለመብላት ካልፈለጉ በፍራፍሬዎች ውስጥ ይጨምሩት። ውሃ መጠጣት አስፈላጊ ለመሆኑ ፍፁም ማብራሪያ ባያስፈልገውም ሁላችንም በዚህ ወቅት በቂ ውሃ መጠጣት በወር አበባ ወቅት የሚታዩ የህመም ምልክቶች የሆኑትን እንደ የሰውነት ድርቀት፤ የራስ ምታት… የመያዝ እድልን ይቀንሳል።
በወር አበባ ወቅት ማስወገድ ያለብዎት ነገሮች ጨው እና ቅመም ያላቸው ምግቦች በጨው እና በሶዲየም የበለፀጉና የታሸጉ ምግቦችን ማስወገድ ይኖርቦዎታል። ከመጠን በላይ የጨው ፍጆታ መጠቀም በወር አበባዎ ውስጥ ወደ እብጠት እንዲመራ የሚያደርገውን የውሃ ማቆየትን ያስከትላል። በተጨማሪም ጨጓራዎን ሊያበሳጭ እና የአሲድ ቅባቶችን ሊያስከትል ስለሚችል ቅመም የበዛባቸውን ምግቦችንም ያስወግዱ።
ቡናና የአልኮል መጠጦች የሆድ ድርቀት፤ የምግብ መፈጨት ችግርን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ እንደ ቡና፣ ኃይል ሰጪ መጠጦች (አልኮል) ወዘተ ያሉ መጠጦችን ያስወግዱ።
ከላይ የተሰጡ ምክሮችን በአግባቡ ከተጠቀመን የተፈጥሮን ፀጋ በአግባቡ ያለስቃይ አስተናግደን መሸኘት እንችላለን። ጤናችን በእጃችን ነውና በአመጋገባችን ስቃያችንን እንቀንስ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013