በዚህ ወቅት ብዙ ወላጆች የሚቸገሩበት ጉዳይ የልጆች ስልክ፣ ታብሌት ወይም ኮምፒዩተር ይዞ መቆየት ነው። የልጆችን ስክሪን የሚያዩበትን ሰዓት መወሰን እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ መልኩ ውጪ እንዲጫወቱ፣ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ ጥሩ እንቅልፍ እንዲያገኙ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል። ሌላው ዋነኛው ነጥብ ደግሞ የዓይንን ጤንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው።
የስክሪን ብርሃን ዓይንን እንዴት ይጎዳል
ብዙ ወላጆች የሞባይል እና ሌሎች ስክሪኖችን ለረጅም ጊዜ ማየት ጉዳት እንዳለው ሲጠይቁ ይሰማል። ከዚህ በታች አንዳንድ የሚጠበቁ እና አስደንጋጭ ውጤቶችን እንመለከታለን።
1. ብዙ ጊዜ በቤት ውስጥ መሆን እና ሩቅ ነገርን ያለማየት ችግር (Short Sightedness)
– አንደኛው ችግር ስክሪን ብዙ ጊዜ መጠቀም ልጆችን ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የፀሐይ ብርሃን ለዓይን ጤንነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ልጆች ውጪ እንዲጫወቱ ማድረግ ከአካላዊ ጤናቸው ባለፈ ለዓይን ጤንነትም ጉልህ ሚና ይጫወታል።
– እንዲሁም ሌሎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት ልጆች በቤት ውስጥ ብዙ ሲቆዩ የሩቅ ነገርን ያለማየት ችግር (Short Sightedness) ተጠቂ ይሆናሉ። ምክንያቱ በትክክል ባይታወቅም የተለያዩ መላምቶች አሉ። ከእነዚህም ተመራማሪዎች በፀሐይ ጨረር ውስጥ ያለው ዩቪ ብርሃን ለጤናማ ዓይን እድገት
አስፈላጊ እንደሆነ አሳይተዋል። ተያይዞም ባለፉት 30 ዓመታት በሩቅ ነገሮችን ያለማየት ችግር (Short Sightedness) በልጆች ላይ እጅጉን እንደጨመረ ታይቷል።
2. የዓይን መድከም
ዓይናችን እረፍት ይፈልጋል። ልጆች ደግሞ አንድ ነገር ሲይዙ ቶሎ ላይተዉ ስለሚችሉ ለብዙ ሰዓታት በአንድ ነገር ላይ አፍጥጠው ሊቆዩ ይችላሉ። ትኩረት የሚፈልግ ነገር በተለይ ከስክሪን የሚወጣው ብርሃን ዓይንን የበለጠ ያደክማል።
3. የዓይን መድረቅ እና መቆጣት
ረጅም ሰዓት ስክሪን ላይ ማሳለፍ የዓይን ድርቀት እና መቆጣትን ያስከትላል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በማንኛውም ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎች ስክሪን ላይ ሲቆዩ ትኩረታቸው ስለሚወሰድ ዓይናቸውን ብዙ አይከድኑም፤ ይህም የዓይን መድረቅን ያመጣል። ለጥሩ እይታ ዓይን ላይ ቀጭን የእምባ ሽፋን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ችግር ሕፃናት ላይ ሲሆን ይብሳል ምክንያቱም ለአዋቂ ዓይን ተብሎ የሚሰራ ስክሪን ስለሚጠቀሙ።
4. የዓይን ትኩረትን ለመቀያየር መቸገር
አንድ ነገር ላይ ለረጅም ጊዜ አትኩሮ መቆየት እይታን አስተካክሎ ሌሎች ነገሮችን ለማየት በተለይ የርቀት እይታ ላይ ያስቸግራል። ይህ ጊዜያዊ ችግር ነው፤ በጥቂት ሰዓታት፣ ቀናት አሊያም ሳምንታት ውስጥ ወደ ቀድሞ እይታ ይመለሳል።
5. ከእይታ በላይ እንቅልፍ ላይ ያለው ችግር
የእንቅልፍ ጊዜን መሻማት ሌላኛው ሕፃናት ላይ የሚፈጥረው ችግር ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከስልክ፣ ታብሌት፣ ኮምፒዩተር ወይም ሌሎች
ባለ ስክሪን ዕቃዎች የሚወጣው ሰማያዊ ጨረር በተለይ ማታ ማታ መጠቀም የአእምሮን የእንቅልፍ ሥርዓት ያዛባል። እነዚህን የስክሪን መብራቶች አእምሮአችን እንደ ቀን ስለሚያይ ሰውነት የእንቅልፍ ጊዜውን ይለውጣል። በተጨማሪም የቪዲዮ ጌሞች ስለሚያጓጉ ልጆች የእንቅልፍ ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገው ይቀመጣሉ።
ምን ማድረግ አለብን?
• ስክሪን የሚጠቀሙበትን ጊዜ መገደብ
ልጆች በዚህ እቅድ እንደሚመሩ ማረጋገጥ
– ልጅዎ ውጪ እንዲጫወት ማበረታታት
– ስልክ ወይም ታብሌት መጠቀም የማይችሉባቸውን ቦታዎች መለየት
– በተለይ ከመኝታ በፊት መኝታ ቤት ውስጥ ስልክ እንዳይጠቀሙ ማድረግ
– ወላጆች ለልጆች ሞዴል መሆን አለባቸው፤ እነርሱም ቢሆን ስልክ የሚጠቀሙበትን ጊዜ መገደብ አለባቸው።
ምንጭ፦ ከዶክተር ጤና ፌስቡክ ገፅ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014