ጽጌረዳ ጫንያለ
በግቢው ውስጥ ያሉ ቅጠላቅጠሎች ዓመቱን ሙሉ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ለመሆኑ ልምላሜያቸው ይመሰክራል።እናት ከጓሮዋ ቀንጠብ አድርጋ ልጆቿን የምትመግብ ለመሆኑም በጓሮው አትክልት ስፍራ የሚታየው ክፍት ቦታ ያሳብቃል።አባትም ቢሆን ከጓሮው እየቀነጠሰ ለንግድ የሚያቀርበው ነገር እንዳለው በጫት ጥቅጥቅ ያለው ሰፊ መሬቱ ያስረዳል።በዚያ ላይ ራቅ ራቅ ብሎ እንደ ጎጆ ቤት በየቦታው የሚታየው ጎተራም ቢሆን አርሶ አደሩ እህል አምራች እንደሆነ ይመሰክራል።በተመሳሳይ በግቢው በስተቀኝ በኩል የሚታየው በረትም የእንስሳት ልማት ላይም የሚሰራ እንደሆነ አርሶ አደሩ ሳይናገር እንግዳው የሚያውቅበት ነው።
ለመሆኑ የት ገብታችሁ ነው ይህንን ያያችሁት ማለታችሁ አይቀርም።በኮሮኮንች መንገድ እየተዳፋን ከጅማ ወደ ገጠራማዋ ክፍል ዲዴ ወረዳ ኢላላ ቀበሌ በምትባል ሥፍራ ነው።ቤቶቹ ራቅ ራቅ ያሉ ናቸው። አካባቢው ዝናብ የሚለየው አይመስልም።ምክንያቱም የሁሉም ሰው ግቢ በሚባል ደረጃ አረንጓዴ ይታይበታል።በተለይ የኮባ ቅጠልና ዛፍ እንዲሁም የጓሮ አትክልቶች ማንም ሳይተክል እንዳያልፍ የተባለ ይመስላል።የእነ አፊስ አባዱላ አባቦኩ ቤትም በዚህ ሁኔታ ያማረና ነፋሻ አየርን የሚያጎናጽፍ ነው።
ይህ ታታሪነታቸው ለገበሬው የእፎይታ ምንጩ እንደሆነም በደንብ ያስገነዝባል።ምክንያቱም የአርሶ አደሩ የወራት የልፋትና የድካም ውጤት ይታይበታልና። በእርግጥ ውጤቱ ለለፋው አርሶ አደር ብቻ አይደለም።ግቢው ውስጥ እረፍት ሽቶ ለሚገባው ሁሉ ነው።እኛም ልናርፍ ይመስል ባለቤታቸው ከውጪው ቤቱ እንደሚሻል ስትነግረን እኛም የመረጥነው ንጹህ አየር ለመማግ ውጪውን ነበር።በዚያ ላይ አቀባበላቸው በራሱ የተለየ ምግብ ነበር።ለነገሩ ኦሮሞ በባህሉ ምርቃት ቁርሱ፣ ምሳውና እራቱ ነው ይባል የለ፡፡
እርሳቸውም ገና እግራችን በራቸው ላይ ሲደርስ ወደ እርሳቸው ቤት ጎራ እንደምንል ሲረዱና ማንነታችንን ስንነግራቸው ፊታቸው እንደፀሐይ ጮራ እያበራ ‹‹ሃሳባችንን ለመጋራት እዚህ ስለመጣችሁ አላህ ይስጥልን›› በማለት ምርቃታቸውን አዥጎደጎዱልን።ነገር ግን ቋንቋቸው ብዙም አልገባንም ነበር።ምክንያቱም አርሶ አደሩ ከኦሮምኛ ቋንቋ ውጪ አማርኛ ብዙም አይናገሩም።ይሁንና የግብርና ባለሙያ ምን እንዳሉን በሚገባ ያስረዳን በመሆኑ ምስጋናችንን ተቀብለንም ወደ ውስጥ ዘለቅን።
ቤታቸው በጣም ትልቅና በዘመናዊ መንገድ የተሰራ ነው።በዚያ ላይ የእስልምና ዕምነት ተከታይ በመሆናቸው ጅባ ተነጥፎበት ግቡ ግቡ ያሰኛል።ባለቤታቸውም ብትሆን ከውጪው ይልቅ ውስጡ እንደሚሻል ጋብዛን ነበር።ሆኖም ምቾቱ ይበልጥ በግቢው ያምራልና ውቡን አየር እየተቀበልን ምርጫችንን ከቅጥር ግቢያቸው ባለ በርጩማ ላይ አድርገን ወደ ወጋችን ገባን።
ትርጉሙ በአስተርጓሚያችን የግብርና ባለሙያው ቢሆንም እያንዳንዱን ሳያስቀር መንገሩን ቀጥሏል። እኛም በሁለት ቋንቋ እየሰማን ነው ይህንን የምናወጋችሁ። መጀመሪያ ላይ ስለሚሰሩት ነገር ከመጫወታችን በፊት የከተሜ ሰው እና ባለሙያ ወደ እኛ ዘንድ ሲመጣ ከምንም በላይ እንደሰታለን። ምክንያቱም ችግራችንንም ደስታችንንም እንነግረዋለን። እነርሱም ለመንግሥት ይነግሩልናል ብለን እናምናለን። ለዚህም እንኳን ደህና መጣችሁ ማለታቸውን ነገረን።እኛም ምስጋናችንን ተቀበልን። ከዚያም ወደ ሥራ ባህላቸው ስለገቡ ያሉንን እንንገራችሁ።
እንደ ጅማ ባሉ አካባቢዎች ላይ ስንዴ ዘርቶ ወደ ጎተራ መክተትና መጠቀም መቼም አይታሰብም። ዘርታችሁ እዩት ቢባሉም ማንም ሰው በቀላሉ ለመቀበል ያስቸግረዋል።ምክንያቱም በማህበረሰቡ ዘንድ መሬቱ ለስንዴ አይሆንም ተብሎ ታምኖበታል።ይሁን እንጂ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ይህንን ሞክሮ አረጋግጧል።ከባሌ አካባቢ ሴናቴ የተሰኘውን ስንዴ በማምጣትም ገበሬው ቢዘራው ምን ያህል ትርፋማ እንደሚሆን እያንዳንዱ ቤት በመሄድ አስረድቷል።ይሁንና ብዙዎቹ ለመቀበል ተቸግረዋል።እንግዳችን ግን ባለሙያ ያለውን በቶሎ የሚቀበሉ ስለነበሩ የመጀመሪያው ሰው በመሆን ምርታማነቱን አረጋግጠዋል።
በእርሳቸው ዘንድ መሬት አይሆንም የሚባል ነገር አይታሰብም። የሰጡትን እንደሚያበቅል ነገር ግን እንክብካቤን እንደሚፈልግ ይታመናል።ስለዚህም ግቢያቸው የማይዘሩትና የማይተክሉት ነገር የለም። በተለይ በባለሙያ የሚመጣ ነገር ደግሞ የበለጠ እንደሚጠቅማቸው ያውቃሉ። በመሆኑም የተባሉትን አድርገው ከጠበቁት በላይ ምርት ይሰበስባሉ። ለአብነትም ሴናቴ የተሰኘውን የስንዴ ዝርያ ዘርተው በግማሽ ሄክታር 15 ኩንታል ሰብስበዋል። ባቄላ፣ ገብስና ጤፍም ዘርተው እንዲሁ ምርታማ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የባለሙያ እገዛ የሰጣቸው እንደሆነ ያምናሉ።እንደውም ከስንዴው በፊትም ገብስ ዘርተው በሄክታር 20 ኩንታል መሰብሰብ እንደቻሉም አጫውተውናል።
የግብርና ምርትን በባለሙያ እንዴት መጠቀም መማር ከተቻለ ምርታማ የማይኮንበት መንገድ አይኖርም የሚሉት እንግዳችን፤ ምጥጥኑ ላይ የተሻልን መሆንም እንችላለን። ለዚህ ደግሞ እኔ ምስክር ነኝ።ከጊዜ ወደጊዜ በአዝርዕቱ ብቻ ሳይሆን በአትክልትና ፍራፍሬው እንዲሁም በጫቱ ቤቴን ደጉሜ ለገበያ አቀርባለሁ። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የግብዓት እጥረት ያጋጥማል።ለምሳሌ እንደ አረም መድኃኒትና ማዳበሪያ።ይህ ከተሟላ፣ ባለሙያው ካገዘ ገበሬው ዘመናዊነትን እንዳይላበስና ምርታማ እንዳይሆን የሚያግደው እንደማይኖርም አስረዱን።
የግቢው አትክልትና ፍራፍሬ ላይ አይናችንን ተክለን ተሻግረንም የእንስሳቱን ብዛት ብንመለከትም ከአንደበታቸው እንዲያወጡት ግን ግድ ሆነብንና ‹‹ለመሆኑ ምን ምን ይሰራሉ?›› አልናቸው።እርሳቸውም ‹‹ያው እንደምታዩት የመጀመሪያ የገቢ ምንጬ ጫት ነው።ከዚያ እንስሳትን በማደለብ እሸጣለሁ።አትክልትና ፍራፍሬዎቹም ገቢ ያመጣሉ።በተጨማሪ ስንዴና ገብስ እንዲሁም ባቄላም ቤቴን ከመደጎሙ አልፈው የገቢ ምንጬ ናቸው።ዛፍም ቢሆን በመትከል ገቢዬ ብቻ ሳይሆን ለቤት መስሪያ እንዳልቸገር አድርጌያለሁ ›› ሲሉ መለሱልን።ቀጥለውም ስለ ኑሯቸው፤ ቤተሰባቸው፤ ውሏቸውና ምኞታቸው እንዲሁም ቀጣይ እቅዳቸው ብዙ አወጉን።
ከሥራ ባህላቸው ሲጀምሩ ሁልጊዜ በማለዳው ተነስተው ወደ ሥራቸው ከመሄዳቸው በፊት ከሁሉ የሚቀድመውን አምላካቸውን እንደሚያመሰግኑ፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሥራ የሚባረከው በጸሎትና በአላህ ጭምር ነው ብለው ስለሚያምኑ እንደሆነ አጫወቱን። ከዚያ ስለቀን ውሎ ከትዳር አጋራቸው ጋር በመሆንም ስለቤታቸው እንደሚመክሩ፤ ልጆቻቸውም ቀን ምን መሥራት እንዳለባቸው ሥራ እንደሚያከፋፍሉ ቀጥለው ደግሞ ቁርስ በልተው ለቤተሰቡ ተፈላጊውን መልዕክት አስተላልፈው እንደሚወጡም ነገሩን።
የሥራ ጅማሯቸው ከግቢ የሚነሳ በመሆኑም ጫቱንና አትክልቶቹን መኮትኮት እንደሚጀምሩ ፤ ዝናብ ካልጣለ ውሃ ማጠጣት እንደሚገቡ ይናገራሉ።ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ ወደ ውድማ ይሄዳሉ።የእርሻ ሥራቸው ካለቀ ደግሞ ከከብቶቻቸው ጋር ውሏቸውን ያደርጋሉ።በእርግጥ ይህ ተግባር የእርሳቸው ሳይሆን የልጆቹ ነው።ነገር ግን ከስራ ጋር መራራቅ ስለማይሆንላቸው የማይገቡበት የለምና ልጆቻቸውን ጭምር ያግዛሉ።ይህ ሁሉ ሥራ ሲጠናቀቅ ደግሞ ማህበራዊ ጉዳይ ካላቸው ወደዚያ ይሄዳሉ።
እርሳቸው ከግቢ ውጪ ሆነው ሲሰሩ የትዳር አጋራቸው ደግሞ በቤት ውስጥ ብዙ ተግባራትን ያከናውናሉ። ጠዋት ሲወጡ ሲያደረጉት የነበረውን ማታም ሲመጡ በደስታ እንደሚደግሙት ያስረዳሉ። በእስልምናው ቁጭ ብሎ መጫወቻ፣ የሆድ የሆድን ማውጊያ ጫት በመሆኑም ወደዚያ ከመግባታቸው በፊት መክሰስ ይሰጣሉ። ከዚያ ቡና አፍልተው አብረው አልያም ከሌሎች እንግዶች ጋር በመሆን ደስታቸውን እንዲያጣጥሙ ያግዟቸዋል።
አርሶ አደር አፊስ አባዱላ አባቦኩ በቤታቸው ውስጥ ስለሚከወኑ ነገሮች ሁሉ ከቤተሰባቸው ጋር ምክክር ያደርጋሉ።በተለይም በልጆቻቸው ዙሪያ ለባለቤታቸው ብቻ የሚተውት አይደለም።የእርሳቸውን ድርሻ በሚገባ ይወጣሉ። ይመክራሉ፤ ይከታተላሉም።ከዚያ ሻገር ሲልም ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ያደርጋሉ።በዚህም ከአራተኛ ክፍል እስከ ኮሌጅ የደረሱ ልጆች እንዲኖራቸው ሆነዋል።ቀደም ሲል አባወራ ብቻ ፈላጭ ቆራጭ የነበረው አስተሳሰብ ያሉበት አካባቢ ገጠር ቢሆንም እርሳቸው ጋር ይህ ቦታ የለውም።ስለዚህም እርሳቸውም ባለቤታቸውም በቤታቸው ጉዳይ በእኩል ያገባኛል ስሜት ነው የሚሰሩት።
እንግዳችን ከቤታቸው አልፈው ለሰፈሩ መኩሪያና መካሪ ዘካሪ ናቸው።አስታራቂም ሲፈለግ ከእርሳቸው ውጪ የሚጠራ የለም።በሰላምም ጉዳይ፤ በአገራዊ ጉዳይ እንዲሁም በልማት ጉዳይ ሁሉም ሰው ያውቃሉ ብሎ ሲለሚያስባቸው እርሳቸውን ያማክራል።ይሁን ካሏቸውም ያደርጋል።እንደውም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስንዴውን አምጥቶ ሲያከፋፍል ማህበረሰቡ ለመቀበል ተቸግሮ እያለ መፍትሄ የሰጡት እርሳቸው መሆናቸውን የግብርና ባለሙያው ያነሳል።
ከተሜውና አርሶ አደሩ
አርሶ አደር ለከተሜው ሰው የህይወቱ ቤዛ ነው።ከተሜውም እንዲሁ ለአርሶ አደሩ የህይወት እስትንፋስ ዘሪ ነው።ነገር ግን ይህ ምልከታ በሁላችንም ዘንድ በእኩል አልሰረጸም የሚሉት አርሶ አደር….፤ ገብስ ዘርተን ምርት እንዲሰጠን የአቅማችንን እንሰራለን፤ ፍሬው ለሚሰጥ ፈጣሪ ደግሞ አደራውን እናስረክባለን፤ እንለምናለንም። ሁሉ ነገር ከግብ ሲደርስና ሲሰበሰብ ደግሞ ምርታችንን ለመሸጥ ገበያ እንወጣለን።
የሚገዛው ከተሜው በመሆኑ በአለን ዋጋ ተገበያይተን የምንፈልገውንና ከእኛ ዘንድ የሌለውን ከዚያው ሸምተን እንመለሳለን።ስለዚህም እኛና ከተሜው ተመጋጋቢ ነን ማለት ነው።አንዳችን ለሌላችን የምንሆን ሰዎች ነን። ስለዚህ ከተሜው ለእኛ እኛም ለከተሜው መድኃኒት ነን። ተደጋግፈን ተዋደንና ተሳስበን ነው የምንኖረው።ይህ ደግሞ የአብሮነትና ትብብር ገመዱን ካላጠነከርነው አደጋችን የከፋ ይሆናል። እናም አንዳችን ለአንዳችን አደጋ መሆናችንን እናቁም ሲሉ ይመክራሉ።ለዚህም ምክንያታቸው የኑሮ ውድነቱ ከነጋዴው ይልቅ ገበሬው ላይ እያረፈ መምጣቱን በማየታቸው ነው።
የገበሬ ራቱ ልፋቱ
መኪና ያለ ነዳጅ እንደማይሄድ ሁሉ እኛም በደንብ ካልበላንና ካልጠጣን ምንም ማድረግ አንችልም።ለዚህ ደግሞ መስራት አማራጫችን ሳይሆን ግዴታችን እንደሆነ ያስገነዝበናል።እየቀመሱ ለሌላም እየሰጡ ቤተሰባዊነትን ማጠናከር ጭምር የሚመጣው በሥራ ብቻ ነው።የማይሰራን ሰው አይደለም ጎረቤት ቤተሰብም አይወደውም፤ አያስጠጋውምም።ለማኝ ሆኖ የሰው እጅ የሚጠብቅ ይሆናልም።ይህ ደግሞ ለገበሬ መጥፎ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ ነገር ነው።እናም ለገበሬው ቁርሱም እራቱም ልፋቱ ነው ይላሉ።ባይሰሩ ኖሮ እርሳቸውን ጨምሮ ሰባት ቤተሰብን ማስተዳደር የማይታሰብ እንደሆነም ያስረዳሉ።
መልዕክት ለአካባቢ ሽማግሌዎች!
በአካባቢው ጤፍ፣ ባቄላ፣ ገብስና ስንዴ በብዛት ይመረታል። የአገሬው ነዋሪም ሰርቶ ለመለወጥና ለማደግ ደፋ ቀና የሚል ነው። ታዲያ ይህን ምርት ለማምረት፣ ለመሰብሰብና ለሚፈልገው ለማድረስ የሀገር ሰላም ከምንም በላይ ወሳኝ ነው። ልጆችም ተምረው አሰቡት ደረጃ የሚደርሱት ሀገር ሲኖር ነው። ስለዚህ ልጆች ወደ ጥፋት እንዳያመሩ ቤተሰብ መምከር አለበት። ሁሉም ነገር እንዳሰብነው መልካም እንዲሆንም የአካባቢው ሽማግሌዎች አደራ አለባቸው። ይሁን እንጂ በተሰጣቸው የአገር አደራ ልክ እየሰሩ ነው ለማለት እቸገራለሁ ይላሉ።ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚያነሱት በእነርሱ ጊዜ የነበረውን አስተዳደግ ነው።
‹‹በእኛ ጊዜ ልጅ የሚያድገው በጎረቤት ቁጣና ክትትል ነው።ዛሬ ግን ነገሮች ተቀይረው ቤተሰብ ጭምር ልጆቹ በሌላ ሰው እንዲነካበት አይፈልግም።ይህ ደግሞ እያራራቀን ይገኛል።እናም ቤተሰብ በተለይ የአካባቢው ሽማግሌዎች የቀደመውን የመዋደድና የመከባበር ባህል ለማምጣት ከቤታቸው ጀምረው መስራት አለባቸው›› ይላሉ።ቤቱ በአባወራው ባህል መሰረት ከተመራ አካባቢው ጤና ያገኛል።ሰላምም ይሰፍንበታል።ስለዚህም በተሻለ ነገ ልጆቻችንን ለማሻገር ዛሬ ላይ ኃላፊነታችንን እንወጣ፤ አደራችንን እንፈጽምም ሲሉ ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2013