አዲስ አበባ(ኢዜአ)፡- ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት ምክንያት በአዲስ አበባ ዙሪያ በግዳጅ ላይ ያሉ የልዩ የጥበቃ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያዩ።
በዚህም የሰራዊት አባላቱ “ግዳጃችን በአንድ ቦታ ተረጋግተን መቀመጥ ስለማያስችለን በቀን የሚሰጠን አበልና ጥቅማጥቅም የወቅቱን የኑሮ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው” ሲሉም ጥያቄያቸውን አንስተዋል።
እንደ ሰራዊት አባላቱ፤ ከአሁን ቀደም ጥያቄያችንን በየደረጃው ለሚገኙ የአመራር አካላት አቅርበን ምንም ምላሽ በማጣታችን “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማሰማት መጥተናል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሰራዊት አባላቱ ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አውሰተው፤ እንደ ሌሎቹ የሙያ ዘርፍ ማለትም እንደ መምህራንና ሌሎች የመንግስት ሠራተኞች ጉዳይ ሁሉ በጥናትና በአሰራር የሚመለስ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰራዊት አባላቱ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሲሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ በካቢኔ ስብሰባ ላይ እንደሆኑና ነገሩን አስቀድመው ያላወቁ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ እንደሆነ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ የማህበራዊ ሚዲያውን ውዥንብር አስቀድሞ ማጣራት እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ ስለሰሞነኛው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ማንም ተቃዋሚ በሰላማዊ ሁኔታ እታገላለሁ” ብሎ አገር ውስጥ እስከገባ ድረስ ትጥቅ ይዞ መታገል እንደማይችል ተናገረዋል።
የሰሞኑ የግንባሩ ሊቀ መንበር ገለጻም “የአፍ ወለምታ እንዳይሆን መልሶ መፈተሽ ያስፈልጋል” በማለት ወደ ፊት በጉዳዩ ላይ በሰፊው እንደሚመክሩበት ገልጸዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያስፈልጋቸው የተደራጀ ሀሳብ፣ ስትራቴጂና ፖሊሲ መሆኑን ጠቁመው፤ “አሁን በስራ ላይ ያለውን ሐሳብ መሞገት የሚያስችል ምክንያታዊ የሆነ ሳይንሳዊ መሞገቻ አቅም እንጂ ክላሽ አይደለም” ብለዋል።