አንተነህ ቸሬ
የሕይወታቸው ጥሪ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳትና መንከባከብ ነበር። በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በዘላቂነት ለመለወጥ ከልጅነታቸው ጀምሮ በትጋት ሲሰሩ የኖሩ ሰው ናቸው። የተሻለ ኑሮ መኖር የሚያስችሏቸውን ብዙ እድሎችን ቢያገኙም ‹‹ድሆችን መርዳት የማያስችለኝ ስራ አልሻም›› ብለው ትኩረታቸውን በሕይወት ጥሪያቸው ላይ አድርገው ብዙ ደክመዋል።
ተሳክቶላቸውም በመንግሥት ሆስፒታል ህሙማንን በመርዳት ጀምረው ‹‹ብርሃን የማኅበራዊ ልማት ስልጠናና ማማከር ማዕከል›› የተሰኘ ድርጅት አቋቁመው ከ52ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ኑሯቸው በዘላቂነት እንዲሻሻልና እንዲለወጥ እስከማድረግ የዘለቀ ስኬት አስመዝግበዋል። ሰዎችን ከድህነት የማላቀቅ ስራቸው ዘላቂ፤ ችግሩም ከመሰረቱ እንዲቀረፍ የሚያስችሉ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትንም አደራጅተዋል። ብዙ ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ቴሬዛ›› እያሉ ይጠሯቸዋል … በሠናይ ተግባራቸው ለብዙኃን ደሃዎች ፍጡነ ረድኤት መሆን የቻሉት፣ የድሆች ጀምበሯ ዶክተር ጀምበር ተፈራ!
ጀምበር የተወለደችው ወላጆቿ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በስደት ላይ በነበሩበት በ1935 ዓ.ም ማዳጋስካር ውስጥ ነው። አያቷ ስመ ጥሩ አርበኛ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ (አባ ንጠቅ) ናቸው። ከፋሺስት ኢጣሊያ መባረርና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ሕፃኗ ጀምበር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከታተለች በኋላ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አቅንታ በክላሬንደን የሴቶች ትምህርት ቤት (Clarendon School for Girls) ተማረች። በመቀጠልም በተንብሪጅ ዊልስ የነርሲንግ ትምህርት ቤት (Tunbridge Wells School of Nursing) የነርስነት ትምህርት አጥንታ በ1957 ዓ.ም ተመረቀች። በሕክምና ሙያ መሰማራት ችግረኞችን ለመርዳት ጥሩ እድል እንደሚፈጥርላት ታምን ነበር።
ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መስራት ጀመረች። በስፍራው ለድሆች በነፃ ሕክምና ይሰጥ ስለነበር ድሆችን የመርዳት ልዩ ፍላጎት የነበራት ሲስተር ጀምበር ስራውን በከፍተኛ ፍላጎት መስራት ጀመረች። ይሁን እንጂ ለታካሚዎች የሚሆን በቂ ግብዓት ስላልነበር ሲስተር ጀንበር ከቤተሰቦቿ እየጠየቀች አንሶላ፣ ብርድ ልብስና የንጽሕና ቁሳቁሶችን ለታካሚዎቹ ለማቅረብ ትጥር ነበር።
በኋላም ለታካሚዎቹ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማሟላት የሚያስችል ጥናት በማድረግ 32ሺ ብር እንደሚያስፈልግ ለሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች አሳወቀች። ሆስፒታሉ መመደብ የሚችለው 24ሺ ብር ብቻ እንደሆነ ሲነገራት ሲስተር ጀምበር ‹‹ቀሪውን እኔ ከሰው ጠይቄ አሟላለሁ›› በማለት ታካሚዎችን የመርዳት ልባዊ ፍላጎቷን አሳየች። ከቤተሰቦቿና ከሌሎች ሰዎች ጠይቃ 10ሺ ብር አገኘች።
የሆስፒታሉ ክፍሎች እንዲታደሱና ለየክፍሎቹ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች እንዲሟሉ አደረገች። የሥራው ውጣ ውረድ ግን ቀላል አልነበረም። ለሦስት ዓመታት በዘለቀው አገልግሎታቸው የሆስፒታሉ ኃላፊ እስከመሆን ደርሳለች።
ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከአውቶብስ ተራ አካባቢ አሁን ወደሚገኝበት ስፍራ ሲዛወር የሚሰጠው አገልግሎት ድሃ-ተኮር መሆኑን ስላቋረጠ ሲስተር ጀምበር ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመልቀቅ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ማገልገል ጀመሩ። አዲስ በተከፈተው የጤናና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ውስጥ ተመድበው የአምቡላስ፣ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ እንዲሁም ለስጋ ደዌ ተጠቂዎችና ለሌሎችም ችግረኞች ስልጠና የመስጠትና የማቋቋም ስራዎች እንዲከናወኑ አደረጉ። በማኅበሩ ካከናወኗቸው ተግባራት አንዱ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መመሪያ (First Aid Manual) ማዘጋጀታቸው የሚጠቀስ ነው።
በቀይ መስቀል ማኅበር እያገለገሉ ሳሉ የቀዳማዊ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት በወታደራዊ አስተዳደር ተተካና የአዲስ አበባ ከንቲባ ከነበሩት ባለቤታቸው ዶክተር ኃይለጊዮርጊሥ ወርቅነህ ጋር ታሰሩ። አራት ሕፃናት ልጆቻቸውን ትቶ መታሰር እጅግ ከባድ ስለነበር በመታሰራቸው እጅግ አዝነው ነበር።
እስር ቤት የተመለከቱት የእስረኞች የጤናና ንጽሕና ሁኔታ እጅግ አስደነገጣቸው። ስለሆነም በሚያውቋቸው ሰዎች እርዳታ አማካኝነት እስረኞች የሚታከሙበት ክሊኒክና የጤና ባለሙያዎች የሚሰለጥኑበት ማዕከል እንዲቋቋም አደረጉ። በዚህም ከእስረኞችና ከወህኒ ፖሊሶች የተውጣጡ ከ85 በላይ ግለሰቦች በጤና ረዳትነት ለመመረቅ በቅተዋል። በተጨማሪም የወሊድ እና የምክር አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው እስረኞችም ሕክምናና ምክር ይሰጡ ነበር።
ከ13 ዓመታት እስራት በኋላ ከእስር ቤት ወጡ። ምንም እንኳ ያለጥፋታቸው ቢታሰሩም መታሰራቸው ቂም አላስያዛቸውም፤ ‹‹የራሴን ሕይወት መኖር አለብኝ›› ብለው ተስፋ እንዲቆርጡና ድሆችን የመርዳት ሃሳባቸውን እንዲተው አላደረጋቸውም። ከእስር ቤት እንደወጡ ጥሩ ደመወዝና ጥቅም የሚያስገኙ ስራዎች ቢቀርቡላቸውም እርሳቸው ግን ‹‹ድሀን መርዳት የማያስችለኝ ስራ ካልሆነ ይቅርብኝ›› በሚለው አቋማቸው ጸኑ። ብዙም ሳይቆይ አንድ የኖርዌይ ግብረ ሰናይ ድርጅት የድሀ ማኅበረሰቦችን ችግር ለመፍታት የሚያከናውነውን ስራ ተቀላቀሉ።
የነሲስተር ጀምበር የማኅበራዊ ችግሮች መፍቻ ተግባራት፣ በተለይ ለድሃዎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያከናወኑት የቤት ግንባታ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት ቻለ። ድርጅቱ የኮንትራት ጊዜውን ሲያጠናቅቅም ሲስተር ጀምበር በጉዳዩ ላይ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችል ትምህርት እንዲማሩ ባለቤታቸው ምክር ሰጧቸው። እርሳቸውም በባለቤታቸው ሃሳብ ተስማምተው በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እድል አገኙ። የጥናትና ምርምር ስራቸውን አከናውነው ካጠናቀቁና በመሠረታዊ የጤና ክብካቤ (Primary Health Care) ከዩኒቨርሲቲው ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎችን ካገኙ በኋላ ቀደም ሲል ስራው ይካሄድበት የነበረውን አንድ ቀበሌና አራት ሺ የተጠቃሚ ቁጥር ወደ ሦስት ቀበሌዎችና 30ሺ ሕዝብ በማሳደግ ስራውን ቀጠሉ።
‹‹የተቀናጀና አካታች የከተማ ልማት መርሐ ግብር (Integrated Holistic Approach Urban Development Project (IHA-UDP))›› በተሰኘው መርሐ ግብራቸው ለችግረኛ ወገኖች የመዋዕለ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲቋቋሙ፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የትምህርት፣ የጤናና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት እንዲገነቡ፣ ወጣቶች እንደየዝንባሌያቸው ችሎታቸው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አገልግሎት እንዲሁም አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ደግሞ እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል። በርካታ ሴቶች በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን አሻሽለዋል። የአዕምሮ ሕሙማን ጨምሮ አካል ጉዳተኞች እንክብካቤ አግኝተውና ስልጠና ወስደው በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ አድርገዋል።
ዶክተር ጀምበር በአንድ ወቅት ስለበጎ አድራጎት መርሐ ግብራቸው ሲያስረዱ እንዲህ ብለው ነበር …
‹‹ … የዓለም ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ በ1970 ዓ.ም. አንድ ጥናት አካሂዶ ነበር። ጥናቱም በተክለ ሃይማኖት አካባቢ ስምንት የመጨረሻ ደሃ ቀበሌዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ነበር። ከእነዚህም ቀበሌዎች መካከል በቀድሞው ከፍተኛ ሦስት ቀበሌ 41 ውስጥ የኖርዌይ ሕፃናት መርጃ ድርጅት በድህነት ቅነሳ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች ትኩረት ያደረገ የተቀናጀ ሥራ ለአምስት ዓመታት ያህል ለማከናወን ከመንግሥት ጋር ተስማምቶ ወደ እንቅስቃሴ ገብቶ ነበር። አራት ሺህ ሕዝብ በሚኖርበት በዚሁ ቀበሌ ይህንኑ ተግባር ለማከናወን ድርጅቱ የማኅበራዊ ኑሮ ባለሙያ፣ መሐንዲስ፣ የጤና ሙያተኛና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ሲቀጥር እኔ በጤና ባለሙያነት ተቀጠርኩ።
በሙሉ አቅማችን ሥራውን ከመጀመራችን በፊት ዓለም ባንክ ካወጣው መረጃ በተጨማሪ የራሳችን የዳሰሳ ጥናት ማካሄድ ስለነበረብን እያንዳንዱን ቤተሰብ ‹ምን ትፈልጋላችሁ?› እያልን ጠየቅን። ከሁሉም ቤተሰቦች ያገኘናቸው ምላሾች የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት፣ የሥራ አለማግኘት … የሚሉ ናቸው።
ከቀረቡት ችግሮች በመነሳት ሳይጠገኑ ለረጅም ዓመታት የቆዩ፣ በጊዜ ብዛት የተነሳ ሊፈራርሱ የተቃረቡና ለሰው ልጅ መኖሪያ ከማይሆኑ የቀበሌ ቤቶች መካከል መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው እንዲጠገኑ፣ የከፋ ጉዳት ያለባቸው ደግሞ ፈርሰው እንደገና በአዲስ መልክ እንዲገነቡ ተደርገዋል። ለልጆች ትምህርት ቤት፣ ለእናቶች ደግሞ የገቢ ምንጭ በመፍጠር እንዲቋቋሙ ሲደረግ በጤናው ዘርፍም በእናቶችና ሕፃናት ጤና ክብካቤ ዙሪያ ትርጉም ያለው ሥራ ተሠርቷል። በሽታን በመከላከል ረገድም ውጤት ተገኝቶበታል።
ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር የነበረው ስምምነት፣ የማቋቋሙን ሥራ ካከናወነ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመንግሥት አስረክቦ ለመሄድ ነበር። ነገር ግን ይህ ስምምነት በመንግሥት በኩል አልተከበረም ነበር።
በዚህም የተነሳ መንግሥት ቃሉን ስላላከበረ ወይም ፕሮጀክቱን ለመረከብ ፈቃደኛ ሆኖ ስላልተገኘ ድርጅቱ ሥራውን ለማቆም ተገደደ። ሥራው የቆመው በ1979 ዓ.ም. ነበር። ድርጅቱ ሥራውን ሲያቆም እኛም እየተበተንን ነበር። ሆኖም ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኔ ፕሮጀክቱን ተረክቤ የማቋቋሙን ሥራ ቀጠልኩበት። በፊት ከነበረው ቀበሌ በተጨማሪ ቀበሌ 30፣ ቀበሌ 42 እና ቀበሌ 43 የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አደረግኩ።
በዚህም ብቻ ሳልወሰን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ሁለት ቀበሌዎችም በፕሮጀክቱ እንዲታቀፉ በማድረግ አገልግሎቱን አስፋፋሁ። በዚህም የተነሳ በተክለሃይማኖት አካባቢ በአራት ቀበሌዎች፣ እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሁለት ቀበሌዎች ለሚገኙ ችግረኛ ወገኖች መዋለ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተቋቁሞላቸዋል። ልጆቹ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ጥሩ ውጤት ሲያመጡ መሰናዶ ትምህርት ቤትና ዩኒቨርሲቲ እንዲቀጥሉ ሲደረግ፣ ውጤት ያልመጣላቸው ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ገብተው እንደየሙያ ዝንባሌያቸው እንዲሠለጥኑ ተደርጓል።
በዚህ ዓይነት አካሄድ በርካታ ችግረኞችና ጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ታዳጊ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ተደርጓል። ልጆቹ ከመዋለ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃና ከዛም ዩኒቨርሲቲ ገብተው እስከሚመረቁ ድረስ ወጪያቸውን የሚሸፍነው ድርጅቱ ነው።
ይህ ዓይነቱ ፕሮጀክት ታዳጊ ወጣቶችን ከመርዳት አልፎ ብዙ አቅመ ደካማ አረጋውያንም እንክብካቤ ያደርግላቸዋል … በተክለ ሃይማኖት አካባቢ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ውስጥ ከ5000 በላይ ቤቶች (በአዲስ ግንባታ፣ በከባድና በቀላል ጥገና) ተሠርተዋል … በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሁለት ቀበሌዎች ለሚገኙ 80 ቤተሰቦች ባለአራት ፎቅ ባለአንድ የመኝታ ክፍልና ስቱዲዮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተሠርተውላቸዋል … በጤናው ረገድ በዋናነት በእናቶችና ሕፃናት ጤንነት ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው። ነፍሰ ጡር እናቶች እስከሚወልዱ ድረስ የሕክምና ክትትል ይደረግላቸዋል።
ከወለዱም በኋላ ሕፃኑ አምስት ዓመት እስከሚሞላው ድረስ አስፈላጊ ክትባት እንዲያገኝ፣ በሦስት ዓመት ደግሞ መዋለ ሕፃናት እንዲገባ ይደረጋል። ለዕድገቱና ለጤንነቱ ተስማሚ የሆነ ምግብም ይሰጠዋል። በአጠቃላይ መሠረታዊ የጤና ክብካቤ እንዲተገበር በማድረግና በንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ ውጤት ተገኝቷል … ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ (99 በመቶ የሚሆነውን) የምናገኘው እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ ሆላንድ፣ አሜሪካና ካናዳ፣ ከሚገኙ ለጋሾች ነው … ››
የስራቸውን ፍሬያማነት የተገነዘቡ ብዙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከዶክተር ጀምበር ድርጅት ልምድ መቅሰም በመፈለጋቸውና ስራውን ቋሚ በሆነ አካዳሚያዊ ዝግጅት ለማጠንከር በማሰብ ‹‹የከተማ ልማት ሰራተኞች ኢንስቲትዩት›› የተሰኘ ተቋም ሊያደራጁ ተነሱ።
በባለቤታቸውና በወዳጆቻቸው ምክርና ድጋፍ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸውንም ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተገናኘ አከናውነው ተቋሙን መሰረቱ። በዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸው የድህነት ቅነሳ መመሪያ አዘጋጅተዋል። ተቋሙ ድህነትን አንድ ድርጅት ለመቀነስ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ይልቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትምህርትና ስልጠና ላይ በተመሰረተ አካሄድ በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የሰውን ሕይወት በዘላቂነት መለወጥ ስለሚኖረው ፋይዳና ስለሚያስፈልገው ጥረት ሲናገሩም እንዲህ ብለው ነበር …
‹‹ … አገራችን ድሃ አገር ናት። እኛ የሠራነው በጣም ጥቂት ነው። ሁሉም ሰው በየአካባቢው ያለውን የድህነት ሁኔታ መገንዘብ አለበት። ቤተሰቦች ልጆቻቸው ስለድህነትም ሆነ አገርን ስለመርዳት ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ አለበት። የሰውን ሕይወት መለወጥ ጊዜ ይፈጃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከባዱ ነገር ደግሞ አስተሳሰብን መለወጥ ነው።
‹ቤተሰቦቼም ድሃ ነበሩ፤ እኔም ድሃ ነኝ፤ ከዚህ የተለየ እድል የለኝም› ብለው የሚያምኑ ሰዎችን አስተሳሰብ መቀየር ትልቅ ጥረትና ትጋት ይጠይቃል … መንገድ ላይ ምጽዋት ሰጥቶ መሄድ ብቻ በቂ አይደለም፤ የሰውን ኑሮ በዘላቂነት መለወጥ ነው የሚያስፈልገው፤ ይህ ደግሞ ለመንፈስም፣ ለወገንም ለአገርም መልካም ነው። ከወቅታዊ እርዳታ ይልቅ ለዘለቄታዊ ልማት አስተዋፅኦ የማድረግ ባሕል ሊኖረን ይገባል።
አስተሳሰብ ከተቀየረ ድህነታችን ዘላቂ በሆነ መንገድ ይቀንሳል … ዓይናችንን ጨፍነን ካልሄድን በስተቀር ድህነታችን በሁሉም ቦታ ይታያል። ችግሩን ለመቅረፍ በግልም ሆነ ተደራጅተን መርዳት አለብን። እኛ ለስራችን ካስፈለገን ገንዘብ ውስጥ 99 በመቶ ያህሉን ያገኘነው ከውጭ ለጋሾች ነው። እርዳታ ሊያደርጉ የሚችሉ አካላት በአገር ውስጥም አሉ። እነዚህ አካላት ተደራጅተው መርዳት አለባቸው።››
ዶክተር ጀምበር በበጎ አድራጎት ዘርፍ እንዲሰማሩ ምክንያታቸው እናታቸው ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ዶክተር ጀምበር ለበጎ አድራጎት ተግባራቸው ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝተዋል። የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሰራተኞች ማኅበር፣ የማኅበረ ግዩራን ዘረ-ኢትዮጵያውያን (SEED)፣ የአፍሪካ እናት እንዲሁም የሴት ቢዝነስ ባለሙያዎች ማኅበር ሽልማቶች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። ዶክተር ጀምበር ከባለቤታቸው ከንቲባ ዶክተር ኃይለጊዮርጊሥ ወርቅነህ አራት ልጆችን አፍርተዋል። ዶክተር ጀምበር ባለቤታቸው በእስር ላይ ሳሉ የጻፉትን የሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸውን ጨምሮ ሌሎች መጽሐፍትን አሳትመዋል።
ከልጅነታቸው ጀምረው ችግረኞችን የመርዳት ፍላጎት የነበራቸውና ፍላጎታቸውንም በተግባር ያሳዩት የድሆች ጀንበሯ፣ ዶክተር ጀንበር ተፈራ፤ ባደረባቸው ሕመም ሕክምናቸውን ይከታተሉበት በነበረው የለንደን ቅዱስ ባርትስ ሆስፒታል ታኅሣሥ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በ78 ዓመታቸው አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013