አፍሪካውያን እንደ ህዝብ ጠንከራ ህዝቦች ናቸው ፤ በህዝብ ብዛታቸው፣ በቆዳ ስፋታቸው ባላቸው ልዩ የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም በሌላውም ከራሳቸው አልፈው ለሌላ ዓለም የሚተርፉ ህዝቦች ናቸው። በቋንቋ፣ በእምነት፣ በቀለም የተለያዩ ቢሆንም በአፍሪካዊነታቸው የሚኮሩና ጠንካራ ስነልቦናና ትስስር ያላቸው ህዝቦች ናቸው።
የአፍሪካ ህብረትንም ሲመሰርቱ በተባበረ ክንድ ለመደጋገፍ ፣ለመረዳዳት እና እንደ አፍሪካ አፍሪካን በየዘርፉ ወደፊት ለማራመድ ነው። የውስጥም ሆነ የውጭ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት አስበው ነው። በአንድነት ተሳስበውና ተባብረው ለማደግ በማሰብ ጭምር ነው።
የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችም ተመካክረውና ተራርመው ለመፍታት ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን በማፈላለግ በዋናነት በራስ አቅም በኢኮኖሚ ፈርጣማ አህጉር ለመመስረት ጭምር ነው።
በዚህ መንገድ ብዙ አፍሪካዊ ጉዳዮቻቸውን በአፍሪካውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ተወጥተዋል። የሰላም መደፍረስ ሲያጋጥም በቦታው ፈጥኖ በመድረስ ለሰላም ማስከበር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ተባብረውና ተረዳድተው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን ፈተዋል፤ ተቋቁመዋልም።
ይሄ ማለት ግን ከሌላው የዓለም ህዝቦች የተለዩና የተገነጠሉ ናቸው ማለት አይደለም። በሚያገናኙ፣ በሚያስተሳስሩ ተግባራት ላይ ሁሉ ይተባበራሉ፤ አብረው ይቆማሉ፤ አብረው ወደፊት ለመራመድ በተለያዩ የዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ይጓዛሉ።
ነገር ግን ማንነታቸውን በማያከብርና ሉዓላዊነታቸውን በሚጎዳ ጉዳይ ላይ ደግሞ አይደራደሩም። በአፍሪካ ውስጥ በተለያዩ ሀገሮች መካከል አለመግባባት ሲፈጠርም አፍሪካ ህብረት ችግሮችን ለመፍታት ይሞክራል። ችግር ፈጣሪዎችን ያወግዛሉ፤ ጣልቃ ይገባል፤ ያስተካክላል።
ይሄ የነበረ አሁንም ያለ ነው። ወደፊትም በአህጉሩ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታ ይቀጥላል።
ከዚህ እውነታ በመነሳትም ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብፅና ሱዳን ጋር ለሚነሳው ሃሳብ የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያን ይፈታ የሚል ጠንከራ አቋም አላት። በዚህም አቋሟ አብዛኞቹ አፍሪካውያን ተስማምተውና ተግባብተው ወደ ተግባር ገብተዋል።
ግብፅጽ ግን አፍሪካዊ ጉዳዮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን ሃሳብ ከማጠናከር ይልቅ አንዴ የዓለም ባንክና አሜሪካ በታዛቢነት ይግቡ። ሌላ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያደራድሩን ስትልና ስትወተውት ቆይታለች። ግብፅና ሱዳን የተለያዩ ሴራዎችን በመሸረብ አሁንም የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያን የሚለውን ወደ ጎን በማድረግ አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረት እና ኮንጎ በአዳራዳሪነቱ እንዲገቡ እና በአራትዮሽ ድርድሩ እንዲካሄድ መወትወት ቀጥለዋል። ምን ያለበት ምን አይችልም እንደሚባለው የአበው ተረትም ያለአንዳች ሴራ ህግንና ስርዓትን ተከተሎ የተጀመረን ድርድር እንደ አዲስ ለማስጀመር መሞከር ጤነኛነት እንዳይደለ ግልጽ ነው።
አሁንም የኢትዮጵያ አቋም የአፍሪካውያን ጉዳይ የሚፈቱት በአፍሪካውያን ናቸው የሚል ነው። የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የኮንጎ ፕሬዚዳንት ናቸው። እሳቸው ሀገራቸውንም አፍሪካ ህብረትንም ወክለው ይሳተፋሉ። ስለሆነም አፍሪካዊ ወንድማማችንትን መርህ በመከተል በፍተሐዊነት ማግባባት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጪ ያለውን አካሄድ ኢትዮጵያ በፍጹም አትቀበልም።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ታላቅ ክብር አላት። በመሆኑም የአፍሪካ ህብረት በደቡብ አፍሪካ በኩል የጀመረው የሦስትዮች ውይይት ሳይጠናቀቅ ሌላ አካል ይግባበት የሚለውን ሃሳብ አትቀበለውም።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ፤ ኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በሚያደርጉት የሦስትዮሽ ውይይት ላይ መግባባት ካልቻሉ ጉዳዩን ወደየሀገራቱ መሪዎች በመውሰድ ለማስወሰን የሚያስችል ስምምነት አላቸው። በመሆኑም የየሃገራቱ መሪዎች በማያውቁት እና ፍቃድ ባልሰጡበት ሁኔታ ሌላ አደራዳሪ አካል መፈለግ አግባብ አይደለም። ተገቢነትም ተቀባይነትም የለውም። አሁንም ወደፊትም አዋጪውና ብቸኛው መንገድ አፍሪካዊ ችግሮቿን በአፍሪካውያን መፍታት ብቻ ነው
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013