አስናቀ ፀጋዬ
አዳዲስ ቢዝነሶችን ለመጀመር ደፋር ናቸው። ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር ከቶ አያውቁም። ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከሀገር ውጪ ተሰደዋል። በስደት በሄዱበት ሳዑዲ አረቢያም ህይወት በእጅጉ ፈትኗቸዋል። በመኖሪያ ፍቃድ ችግር ምክንያትም ለእስር ተዳርገዋል። ከስምንት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደሀገራቸው ተመልሰውም ድለላና ሌሎች ንግዶችን ሞክረዋል።
በአንድ አጋጣሚ የተዋወቋቸው ሰው ከፈታኙ የእምነበረድ ማውጣት ስራ ጋር እንዲጋፈጡ አድርጓቸዋል። ይህንኑ ቢዝነስ ጥቂት እንደሰሩ ተሰላችተው ስራውን ለመተው ከጫፍ ከደረሱ በኋላ ከአንድ ህንዳዊ ጋር በመገናኘታቸው ወደዚህ እልህ አስጨራሽ ስራ ዳግም ተመልሰዋል። ከብዙ ውጣውረድ በኋላም በአሶሳ ከተማ የራሳቸውን የእምነበረድ ማምረቻ ፋብሪካ አቋቁመው ስራቸውን በትጋት ቀን ከሌት እያከናወኑ ይገኛሉ። የዲ አር ቢ ኢንተርናሽናል እምነበረድ ፋብሪካ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ፀጋዬ።
አቶ ዳዊት ውልደታቸውና እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ በተለምዶ ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአንድ እስከ ሁለተኛ ክፍል በዓለም ብርሃን ትምህርት ቤት እንዲሁም የሦስትና የአራተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በራስ አበበ አረጋይ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ከአምስተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ስላልመጣላቸው ለአንድ ዓመት ያህል የራሳቸውን የህይወት መሥመር ሲፈልጉ ቆዩ። በዚሁ አንድ ዓመት ውስጥም የማትሪክ ውጤታቸውን ለማሻሻል ሞከሩ። ሆኖም ሊሳካላቸው ባለመቻሉ ሌላ መንገድ መፈለግ ጀመሩ።
አቶ ዳዊት ከራሳቸው ጋር ሲመክሩ ከቆዩ በኋላ ኑሮን ለማሸነፍና ራሳቸውን ለመደጎም ሲሉ በ1985 ዓ.ም ወደ ሳኡዲ አረቢያ ተሰደዱ። በሳኡዲ አረብያ በነበራቸው ቆይታ ቋንቋውን እያወቁት በመሄዳቸው ከግብፆች ጋር በመሆን የኤር ኮንዲሽኒንግ፣ ማቀዝቀዣዎችና የልብስ ማጠቢያ ቴክኒሺያን በመሆን ሰሩ። በዚሁ ስራም በሳውዲ አረቢያ ለስምንት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በመኖሪያ ፍቃድ ችግር ምክንያት ስምንት ወር ታሰሩ። ከአስር ከተለቀቁ በኋላም ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
በስደት ከቆዩበት ሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ይሄ ነው የሚባል ስራ ማግኘት አልቻሉም። ለጊዜውም አንዳንድ ተባራሪ አየር ባይር ንግዶችን መስራት ጀመሩ። ሆኖም ንግዱ ሊያዋጣቸው ባለመቻሉ እንደገና ወደ ሳኡዲ አቀኑ። ወደ ሳውዲ አረቢያ ዳግም ከተመለሱ በኋላ ግን ልክ እንደበፊቱ የሚያስደስት ነገር አላገኙም። ቀድሞውኑ ብዙ ነገሮች ተበላሽተው የነበረ በመሆኑ ዳግም ወደ ሳኡዲ አረብያ ላለመመለስ ወስነው ወደ ሀገራቸው መጡ። ወደ ሀገራቸው ዳግም ከተመለሱ በኋላም አዲስ አበባ ላይ የድለላና የአይር ባየር ስራዎችን መስራት ጀመሩ።
በችግር ክፉኛ የተፈተኑት አቶ ዳዊት በአንድ አጋጣሚ ጓደኛቸው ቃሊቲ ኢንዱስትሪ መንደር አካባቢ ያላቸውን ቦታ እንዲገዟቸው ይወተወቷቸው ጀመር። እርሳቸውም ጓደኛቸውን ለማስደሰት ብለው 50 ሺህ ብር ብቻ እንዳላቸውና ቀሪውን 100 ሺህ ብር በሌላ ጊዜ እንደሚከፍሉ ተስማምተው ቦታውን በ150 ሺህ ብር ገዟቸው።
ከአረቦች ጋር በመሆን ኦርዮን የተሰኘ ድርጅት በጋራ አቋቁመውም በገዙት ቦታ ላይ ቼሪ ስናኮችን /ብስኩቶች/ በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ። በዚህ ሂደትም በተለይ በ2000 ዓ.ም ምርቱን በስፋት ለገበያ በማቅረብ ማትረፍ ቻሉ። ይሁን እንጂ ስራው እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ከዚሁ ስራ ጎን ለጎን በአነስተኛ ማሽኖች የፈርኒቸርና ስቴኪኒ ማምረት ስራ ጀመሩ።
ብዙም ሳይቆይ ግን የቼሪ ስናክ ማምረት ስራው እየከሰረ መጣ። ከዚሁ ስራ ጎን ለጎን የጀመሩት የፈርኒቸርና የስቴኪኒ ስራውም ተቀዛቀዘ። በዚህ መሃል አንድ የጭነት መኪና የነበራቸው ሲሆን ከቤንሻንጉል ክልል ድንጋይ እየጫነ አነስተኛ ገቢ ያስገባላቸው ነበር። በአጋጣሚ በ2001 ዓ.ም በክረምት ወቅት መኪናቸው ድንጋይ ሲጭን ጭቃ ይይዘዋል። የቀጠሩት የመኪናቸው ሹፌርም መኪናው ተበላሽቶ እንደቆመ ይነግራቸዋል። እርሳቸውም መኪናቸውን ለማሰራት ከአዲስ አበባ ወጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ መንዲ ተጓዙ።
ወደ መንዲ ከመጡ በኋላ የቁፋሮውን ካምፕ ለማየት መሄድ ቢፈልጉም በጭቃው ምክንያት መድረስ ባለመቻላቸው የመኪናውን ሜካኒክ አሰናብተው ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀራቸው ተመልሰው አነስተኛ ከተማ ላይ አደሩ። መኪናው ተሰርቶ ከመጣ በኋላም ድንጋይ ጭኖ ወጣ። ከተማ አድረው ወደ አዲስ አበባ ሊመለሱ ሲሉ ያደሩበት ቤት ባለቤት በመንዲ አካባቢ ተቆፍሮ የሚወጣው የእምነበረድ ማዕድን ባለቤት መሆናቸውን ተረዱ።
የእምነበረዱ ባለቤት በአጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ የመሄድ ሃሳብ የነበራቸው በመሆኑ ከእርሳቸው ጋር አብረው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ስለ እምነበረድ ቢዝነስ ማውራት ጀመሩ። አቶ ዳዊትም ሰውየው የማዕድን ማውጣት ስራውን በኋላ ቀር መንገድ እንደሚያከናውኑ ተገነዘቡ።
በጊዜው አቶ ዳዊት አብዛኛዎቹ ስራዎቻቸው ቆመው የነበሩበት ወቅት በመሆኑ ወደዚህ ቢዝነስ ለመግባት ብዙም አላመነቱም። ስለቢዝነሱ ሲያሰላስሉ ካደሩ በኋላ በማግስቱ ከሰውየው ጋር ተገናኝተው ቃሊቱ ያላቸውን ቦታና ስራዎቻቸውን አስጎበኟቸው። በጋራ የእምነበረድ ማምረት ስራውን ለመስራትም ተስማሙ።
አቶ ዳዊት በወቅቱ እጃቸው ላይ ጥሬ ብር ባለመኖሩ የጭነት ተሽከርካሪያቸውን ሸጡ። ከሽያጩ በተገኘው ገቢም ለማርብል ማውጫ የሚያገለግል ማሽን ማሰሪያ ዋለ። ትልቅ ማሽን መንዲ ላይ በመትከልም ጓደኛቸው እብነበረዶችን እየቆራረጡ በሽያጭ ወደ አዲስ አበባ ለእርሳቸው መላክ ቀጠሉ። እርሳቸውም እምነበረዶቹን ተቀብለው ዳግም እየቆራረጡ ለገበያ በማቅረብ የራሳቸውን ገቢ ማግኘት ቻሉ።
በእንዲህ ሁኔታ የቀጠለው የአቶ ዳዊትና የስራ ጓደኛቸው የእምነበረድ ስራ እንደ አጀማመሩ ሊዘልቅ አልቻለም። መንዲ ላይ የማርብል ማምረቻ መጋዘን ለማሰራት አዘው ስም ሳይዞር ውክልና የነበራቸው ቢሆንም መጋዘኑን ሰርተው ማጠናቀቅ ግን አልቻሉም። በዚህ ሳቢያም እንደገና ከባንክ 400 ሺህ ብር ተበድረው መጋዘኑን ገንብተው አጠናቀቁ።
ሆኖም በዚህ ሂደት ጓደኛቸው ካዷቸው። እምነበረዶችንም ለሌሎች ሰዎች ማቅረብ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ዳግም ከችግር ጋር ተጋፈጡ። የአራት መቶ ሺህ ብር ብድሩንም መክፍል ሳይችሉ ቀሩ። መጨረሻ ላይ ከአቢሲኒያ ባንክ ባገኙት የ1 ሚሊዮን ብድር ያለባቸውን እዳ መክፈል ቻሉ። ይህንንም ብድር ለመክፍል ዳግም ሌላ ጫና ውስጥ ገቡ። እንደገና ወደ ህብረት ባንክ ከሄዱ በኋላ መጋዘኑን አስይዘው ብድር ወሰዱ። የተወሰነ ገንዘብ ከፍለውም ቀሪውን መያዝ ቻሉ።
በዚህ የእምነበረድ ቢዝነስ የተሰላቹትና የደከሙት አቶ ዳዊት ይህን ቢዝነስ በመተው ወደ ዱባይ አልያም ወደ ጁባ ሄደው አነስተኛ ስራ ለመስራት ራሳቸውን በማዘጋጀት ላይ ሳሉ ከአንድ ህንዳዊ ኢንጂነር ጋር ተዋወቁ። በዚህ መሀልም ቀደም ሲል ባህርዳር ላይ የነበረ የእምነበረድ ደምበኛቸው ፐርፎርማ ሰጥተው እምነበረድ አዘው ይጠባበቁ የነበረ በመሆኑ እምነበረድ እንደሚፈልጉ ይነግሯቸዋል። እምነበረድ እጃቸው ላይ በመኖሩ 250 ሺህ ብር ቀብድ ተቀብለው ይሰጧቸዋል። በዚህ ጊዜ ቀደም ሲል ጓደኛቸው የሰሩት አይነት ማሽን ጀምረው 60 በመቶ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ለማጠናቀቅ ወኔ አጥተው ነበር። በዚህ አጋጣሚ ከህንዳዊ ኢንጂነር ጋር በመገናኘታቸው የጀመሩትን ፋብሪካ እንዲጨርሱላቸውና 25 ከመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው ነገሯቸው። ህንዳዊውም በሃሳባቸው ተስማሙ። የጀመሩትን የእምነበረድ መቁረጫ ማሽንም ጨረሱ።
አቶ ዳዊት በማሽኑ እምነበረድ መቁረጥ ከጀመሩ በኋላ ለፍሊንስትሰቶን ሆም እምነበረድ አቅርበው 500 ሺህ ብር ገቢ አገኙ። በዚህም ተበረታተው ከ2003 ዓ.ም ወዲህ በዚሁ የእምነበረድ ቢዝነስ ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን አድርገው መስራት ቀጠሉ። የስደት ሃሳባቸውንም ሰረዙ። በዚሁ ባገኙት ብርም ተመሳሳይ ሁለተኛ ማሽን አሰሩ። በዚህ መሃል የእርሳቸውና የቀድሞ ጓደኛቸው ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት አቅንቶ የነበረ ሲሆን በሽምግልና በተወሰደባቸው ገንዘብ ምትክ ጥሬ እቃ መቀበል ጀመሩ። ጥሬ እቃውን እየተቀበሉም በማሽኖቻቸው እምነበረዱን ቆርጠው ለገበያ ማቅረብ ተያያዙ።
ዛምራ ኮንስትራከሽን የሰራውን የየካ ክፍለ ከተማ ህንፃ ኮንትራት ወስደው ሙሉ የማርብል ስራ ሰርተው ተጨማሪ ገቢ አገኙ። ባገኙት ገንዘብም ከጣልያን ሀገር ሌላ ዘመናዊ የእምነበረድ ማሽን ገዝተው አመጡ። የሀገር ውስጥ ማሽኖቻቸውንም ለጀማሪ እምነበረድ አምራቾች ሰጥተው በአዲሱ ማሽን መጠቀም ጀመሩ። እንደገና ከቻይና ሀገር ሁለተኛ አዲስ የእምነበረድ ማሽን ገዝተው ወደሀገር ውስጥ አስገቡ።
ጥሬ እቃ ከጓደኛቸው ተቀብለው ከመስራት ይልቅ በራሳቸው ማዕድኑን አውጥተው ሙሉ ስራውን የመስራት ፍላጎት የነበራቸው አቶ ዳዊት ወደ መንዲ በማቅናት ከክልሉ የማዕድን ማውጣት ፍቃድ አግኝተው ወደስራው ገቡ። ተጨማሪ ማሽኖችንም ገዝተው አስገቡ። ጥሬ እቃ በራሳቸው እያመረቱ ወደ አዲስ አበባም መላክ ጀመሩ። በሂደትም የእምነበረድ ማምረት ስራውን እያስፋፉ መጡ። ከውጪም የእምነበረድ ሞያተኞችን አስመጡ። ለሌሎች ፋብሪካዎችም ጭምር ጥሬ እቃውን መሸጥ ቀጠሉ።
ልማት ባንክ ባወጣው የሊዝ ፋይናሲንግ ፕሮጀክት መሰረትም 20 ከመቶውን እርሳቸው 80 ከመቶውን ደግሞ ባንኩ እንደሚሸፍን ስምምነት ተደርጎ ተጨማሪ የእምነበረድ ማሽኖችን ገዙ። በ2012 ዓ.ም በአሶሳ ከተማ በገነቡትና ዲ አር ቢ ኢንተርናሽናል በተሰኘው እምነበረድ ፋብሪካ ውስጥም ማሽኖቹን ተከሉ። ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ለፋብሪካው ግንባታም ባጠቃላይ ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ብር ወጪ አደረጉ።
በሦስት ፈረቃ በማሰራት ከ100 እስከ 200 ሰራተኞችን ቀጥሮ የማሰራት አቅም ያለው ፋብሪካቸው በአሁኑ ወቅት 60 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል። ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ ልዩ ልዩ የእምነበረድ ምርቶችንም ያመርታል። በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም በቀን እስከ 800 ካሬ ሜትር እምነበረድ የማምረት አቅም ይኖረዋል። አንዱን ካሬ ባለሦስት ሴንቲ ሜትር የእምነበረድ ምርቱን በ1 ሺህ ብር ዋጋ እንዲሁም ባለሁለት ሳንቲ ሜትሩን በ900 ብር ለገበያ ያቀርባል። ጥሬ እቃውንም ወደ ውጪ ሀገር መላክ ጀምሯል።
‹‹ከዚህ ሁሉ ልፋት በኋላ ወደኋላ መመለስ የለም›› የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በቀጣይ ከፋብሪካው በሚገኘው ተረፈ ምርት የቀለም ፋብሪካ የማቋቋም በተለይ ደግሞ ጂፕሰምና ኳርትዝ የማምረት እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህም ስራ በሂደት ላይ እንደሚገኝና ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ግራናይት የማምረት ስራ እንደሚጀምሩም ይጠቁማሉ። እምነበረዱንም ሆነ የግራናይት ስራውን በተሻለ ቴክኖሎጂ በማምረት ለገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸውም ያስረዳሉ።
ምርቶቹንም በስፋት ወደውጪ ሀገር የመላክ ፍላጎት እንዳላቸውና በተለይ ደግሞ ለዱባይ፣ ህንድና አሜሪካ የማቅረብ እቅድ እንዳላቸውም ይጠቅሳሉ። ሌሎች ንኡስ እምነበረድ አምራቾችን በመፍጠር ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል የመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸውም ይናገራሉ። በተለይ የእምነበረድ ክምችት በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ ወጣቶችን በማደራጀት ማሽንና ጥሬ እቃ በማቅረብ እንዲያመርቱና እንዲጠቀሙ የማድረግ ውጥን እንዳላቸው ያመለክታሉ። በቀጣይ ዓመት አንድ ማሽን የመጨመር ፍላጎት እንዳላቸውም ይገልፃሉ።
‹‹በዚህ የእምነበረድ ስራ ተሳክቶልኛል›› የሚሉት አቶ ዳዊት የዚህ ስራ መጨረሻው ሃብት ማካበት ሳይሆን እርሳቸው በከፈቱት የእምነበረድ ፋብሪካ ብዙ ሰዎች ሰርተው መኖርና መጠቀም የሚችሉበትን ኢንዱስትሪ አስፋፍተው ማለፍ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግም ሌት ተቀን እንደሚለፉ ይጠቅሳሉ። ያሰቡት ህልም ከግብ ባይደርስ እንኳን ቤተሰባቸው አልያም አብረዋቸው የሚሰሩ የስራ ባልደረቦቻቸው እንደሚያስቀጥሉት ይገልፃሉ። በዚህ ውጣውረድ ሁሉ ፈጣሪያቸው እንደረዳቸውም ይመሰክራሉ።
‹‹የእምነበረድ ማምረት ስራ እጅግ ፈታኝ ከመሆኑ አኳያ ሌሎችም በተመሳሳይ ገብተው እንዲሰሩበት ለመምከር እቸገራለሁ›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ዳዊት እርሳቸው ወደዚህ ስራ የገቡት ምንም አማራጭ ስላልነበራቸው መሆኑን ያስረዳሉ። እስካሁን ባለው ሂደትም ሁሉንም ፈተና እንደተወጡ ይናገራሉ። በመሆኑም ስራው ትርፍ አለው ብለው ሌሎች ገብተው እንዲሰሩበት እንደማይመክሩ ይገልፃሉ። ይሁንና የእምነበረድ ማምረት ስራ ገበያው አሁንም ድረስ ያልተሰራበትና ክፍት ከመሆኑ አኳያ ድፍረቱና ብርታቱ ካላቸው ሊሰሩበት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። የእምነበረድ ስራ ከተፈጥሮ ጋር ትግል መግጠምን የሚጠይቅ አንዴ ማግኘት ሌላ ጊዜ ደግሞ ማጣት የተለመደበት ዘርፍ እንደሆነም ጠቅሰው፤ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሰዎች ስራውን ከታች ጀምሮ አይተውትና ተፈትነውበት ሊያልፉ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013