
በደቡብ ስፔን በሚገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ በጡረተኛ ግለሰብ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ምክንያት የተፈጠረውን ፀረ ስደተኛ አመፅ ተከትሎ በአጠቃላይ 14 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ተጨማሪ ፖሊስ ተሰማራ። ባለፈው ረቡዕ በቶሬ ፓቼኮ ከተማ የ68 ዓመት አዛውንት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተጠረጠሩ ሶስት የሰሜን አፍሪካ ተወላጆች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የጸጥታ ችግሩ የተከሰተው፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የሚገኙባት እና በ40 ሺህ ሰዎች የሚኖሩባትን ከተማ ነዋሪዎች ያበሳጨ አንድ ቪድዮ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ነው። ጡረተኛው ግለሰብ እና ፖሊስ የተሰራጨው ቪዲዮ ከክስተቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው የተናገሩ ቢሆንም ወንጀለኞችን እንዲያነቁ እና ጥቃት እንዲደርስባቸው የሚደረጉ የማህበራዊ ሚዲያ ጥሪዎች በፍጥነት ተበራክተዋል።
በትር የያዙ ቡድኖች በቶሬ ፓቼኮ ጎዳናዎች ሲዘዋወሩ ታይተዋል።”አሁኑኑ አስወጧቸው” የሚል ስያሜ ያለው አንድ ቀኝ አክራሪ ቡድን በሰሜን አፍሪካውያን ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ጥሪ አቅርቧል። ስደተኞች ላይ አዲስ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሱ ተጨማሪ የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች በዚህ ሳምንት በሶስት ቀናት ውስጥ ተስፋፍተው ውስጥ ታይተዋል።
የሰሜን ምስራቃዊቷ ማታሮ ከተማ ውስጥ የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት የተጠረጠረ የአክራሪ ቡድኑ መሪ አባል በቁጥጥር ስር ውሏል። ባለፈው ረቡዕ በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው 68 ዓመቱ ዶሚንጎ ቶማስ ዶሚንጌዝ፤ ዘወትር እንደሚያደርጉት ጠዋት ላይ እየተራመዱ ሳለ ተገፍትረው መሬት ላይ መጣላቸውን እና መመታታቸውን እንደተናገሩ ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨ ፎቶ የግለሰቡ ፊቱ ክፉኛ እንደቆሰለ አሳይቷል። ፖሊስ፤ የጥቃቱ መንስኤ ግልጽ አለመሆኑን አስረድቷል። አዛውንቱ ዶሚንጌዝ ገንዘብ ወይም ንብረታቸውን እንዲሰጡ እንዳልተጠየቁ እና አጥቂዎቹ የሚናገሩትን ቋንቋ እንዳልተረዱት ተናግረዋል።
በሙርሲያ ግዛት ከአካባቢው እና ከሀገሪቱ ፖሊስ ኃይሎች ተወጣጡ 130 የጸጥታ ኃይሎችን በማሰማራት የፖሊስ ስምሪት እንዲጠናከር ተደርጓል። የስፔን መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ አዛውንቱን ግለሰብ በማጥቃት ተጠርጥረው የታሰሩት ሶስት እድሜያቸው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ የሞሮኮ ተወላጆች ናቸው። ተጠርጣሪዎቹ በሙሉ የከተማዋ ነዋሪ እንዳልሆኑም ተዘግቧል።
አንደኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከባስክ ግዛት ባቡር ተሳፍሮ ወደ ፈረንሳይ ድንበር ለመሻገር ሲዘጋጅ ነው። በጣም የከፋው ሁከት በተከሰተበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፤ ጭምብል የለበሱ ሰዎች የተካተቱበት የወጣቶች ቡድኖች በተሽከርካሪዎች እና ንግዶች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። ቀኝ አክራሪ ቡድኖች እና በሰሜን አፍሪካ ተወላጆች መካከልም ግጭቶች እንደተከሰቱ ተዘግቧል።
ጋዜጠኞች፤ በርካታ ወጣቶች ጠርሙሶችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በአድማ በታኝ ፖሊሶች ላይ ሲወረውሩ ተመልክተዋል። የቶሬ ፓቼኮ ከንቲባ ፔድሮ አንጌል ሮካ፤ “የስደተኞች ከቤታቸው እንዳይወጡ እና ከአመፀኞችን እንዳይጋፈጡ” ጠይቀዋል።
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ስደተኞች በአካባቢው በተስፋፋው የግብርና ዘርፍ ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአሁን በኋላ በከተማው ውስጥ ደህንነት እንደማይሰማቸው ተናግረዋል። ከንቲባው ስደተኞች ቶሬ ፓቼኮ ውስጥ ከ 20 ዓመታት በላይ መኖራቸውን ገልጸዋል።
የቀኝ አክራሪ ቡድን የቴሌግራም ቡድን ተጠቃሚዎች፤ በሌሎች የስፔን አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በዚህ ሳምንት ለሶስት ቀናት ሰሜን አፍሪካውያን “ለማደን” ወደ ከተማዋ እንዲጎርፉ ጥሪ እንዳቀረቡ ተዘግቧል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፈርናንዶ ግራንዴ ማርላስካ፤ ግጭቱ የተከሰተው በከፍተኛ ቀኝ ዘመም ቡድኖች እና በስፔን ሶስተኛው ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነው ቮክስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፀረ ስደተኞች ንግግር ምክንያት ነው ብለዋል።
የቮክስ ፓርቲ መሪ ሳንቲያጎ አባስካል ለተፈጠረው ሁከት ተጠያቂ አለመሆናቸውን በመግለጽ፤ ባለፈው ሳምንት ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ሰዎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ የፈቀዱትን “የማስ ኢሚግሬሽን” ፖሊሲዎች ተጠያቂ አድርገዋል። አባስካል ስለ ስደተኞች ሲናገሩ፤ “ድንበሮቻችን ሰርቋል፣ ሰላማችንን ሰርቋል፣ ብልፅግናችንን ሰርቋል” ብለዋል።
የሙርሲያ ዐቃቤ ሕግ በክልሉ የቮክስ ፕሬዚዳንት ሆሴ አንጌል አንቴሎ ላይ የጥላቻ ወንጀል ምርመራ ከፍቷል። ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር ይህ ጥቃት የተከሰተው በስፔን ሁለት ዋና፤ ‘ፖፑላረ ፓርቲ’ እና ሶሻሊስት ፓርቲ’ “ጥፋት” ነው ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “በቶሬ-ፓቼኮ እየተመለከትን ያለነው ነገር ሁላችንንም የፈተነን [ክስተት] ነው። መናገር፣ በፅናት ርምጃ መውሰድ እና አንድ የሚያደርጉን እሴቶችን መከላከል አለብን። ስፔን የመብቶች እንጂ የጥላቻ ሀገር አይደለችም” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም