ከሞት ባሻገር ያለው የእድር ተግባር በዓለም ከተማ

እድር በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አለያም ተወላጆች በመደራጀት ማህበራዊ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያቋቁሙት ተቋም ነው። በተለይም ሰዎች ድንገተኛ ኀዘን ሲያጋጥማቸው በኢኮኖሚም ሆነ በሥነልቦና የሚተጋገዙበት አደረጃጀት እንደሆነ ይገለጻል። የአካለ ወልድ የአማርኛ ፍች መዝገበ ቃላት እንደሚያብራራውም እድር የቃሉ ትርጓሜ ብድር መክፈል ወይም ወንፈል ማለት ነው። ወንፈል ማለት ደግሞ አንዱ ለአንዱ የሚተጋገዝበትና ብድሩን የሚከፍልበት ሂደት ነው።

ከዚህ ስያሜው በመነሳትም እያንዳንዱን ድንገት ክስተት በተለይ ሞት ሲፈጠር ወጪዎችን በጋራ እንዲሸፈን የሚደረግበት፣ ኀዘንን የማስረሳት ሚናንም በስፋት የምንጫወትበት ጥምረት እንደሆነ ይነሳል። በእድር ወቅት መዋጮ የሚከናወነው በተለያየ መልኩ ሊሆን ይችላል። እንደ አካባቢው ሁኔታም ይወሰናል። አንድ ሰው መከራ ሲደርስበት የእድሩ አባላት በየወሩ የገንዘብ መዋጮ ስለሚያደርጉ ከእዚያ ላይ በሕግና መመሪያቸው መሠረት ወጪ አድርገው የሚገዛውን ይገዛሉ። በገንዘብ ደረጃ የሚሰጥ ከሆነም እንዲሁ ያደርጋሉ። ከዚያም ባለፈ በኀዘኑ ቤት ተገኝተው ለኀዘንተኛ የሚሆኑ ምግብና መጠጥ ቡናን ጨምሮ ያዘጋጃሉ። በተወሰነላቸው ሰዓትም ተግባራቱን ፈጽመው ወደየቤታቸው ይሄዳሉ።

አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የእድሩ አባላት የሚኖርባቸው ግዴታ እንጀራ፣ እህል (ጥራጥሬ፣ ሽሮ በርበሬ፤ የቡና እና ሌሎች መዋጮን ማድረግና በጉልበት ሥራዎችን ማገዝ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻርም እድር በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ወይም ተወላጆች ማህበራዊ ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱበት ኀዘናቸውን ትተው መጽናናትን የሚያገኙበትና ማህበረሰብ እንዲደሁም የእርስ በእርስ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከሪያ ሕብረት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

እድር የራሱ መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ ያለው መሆኑ ደግሞ በሕግ መገዛት ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው ማህበረሰቡ እንዲረዳ የሚደረግበት መሆኑም ይገለጻል። ምክንያቱም በእርሱ አማኝነት ብዙ ልምምድ የሚያደርጋቸው ነገሮች ይፈጠራሉ። ለመሆኑ ይህ እድር በሰሜን ሸዋ አካባቢ ምን አይነት መልክ አለው ስንል የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ዕሴት ልማት ባለሙያን እየሩስ ጌታቸውንና የአካባቢው ሰዎችን አነጋግረናል።

በመጀመሪያ ሃሳባቸውን ያጋሩን ለረጅም ጊዜ በከተማዋ በእድር ሰብሳቢነት የሠሩት በሻህ ወረደ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የአካባቢ ሰዎች ብዙ ጊዜ ድንገት ኀዘን ሲገጥማቸው የሚመጡ ዘመድ አዝማዶችን እና እንግዶችን በቀላሉ ለማስተናገድ ይቸገሩ ነበር። የመከራው የእህል ውሃው ወጪም በምንም መልኩ በአንድ ሰው መሸፈን የማይቻል ነው። እናም የመስተንግዶውን ጉዳይ የሚሸፍን እንደሚያስፈልግ ታመነበት። ጉዳዩ የሕብረት መሆን እንዳለበት ሲታሰብም ስም ተሰጥቶት ወደ ትግበራው ተገባ። ይህንንም እድር የሚል ስያሜን ሰጡትም።

በሻህ እንደሚሉት ሞት ወይም ኀዘን በዚህ ጊዜ ይመጣል ተብሎ አይጠበቅም። በዘህም ኀዘን የደረሰበት ሰው ለኀዘኑ ወይም ለመከራው አስፈላጊ ወጪዎችን ለመሸፈንና ለእንግዳ የሚሆን መስተንግዶ ለማዘጋጀት ችግር ይገጥመዋል። እናም ይህንን ችግሩን ለመፍታት የጐረቤት ሰዎች አጋዥነት የግድ ይላል። የዘመድ አዝማድ ደራሽነትም እንዲሁ ግድ ያስፈልገዋል። ይህንን ያዩ የሀገር ሽማግሌዎችም በመሰብሰብ ይህንን ሁሉ ጫና የሚያቃልል ማህበራዊ ሕግጋት ያለው አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ ተማመኑ። እድር በሚል ስያሜም ተቋም መሠረቱ። አሁን በመርሀ ቤቴ ወረዳም ይኸው እድር ሰፊ ሥራ እየተከናወነበት ይገኛል።

ዓለም ከተማ ላይ የነበረው የመጀመሪያው እድር የቅዱስ አማኑኤል እድር ነበር። የተመሠረተውም በ1943 ሲሆን፣ የመርሀ ቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ስትመሠረት እንደሆነም ይነገርለታል። እንዲመሠረት ያደረጉት ግለሰቦችም አቶ አስራቴ እና ባላባራስ ስሜ ሃይሌ የሚባሉ ግለሰቦች ስለመሆናቸውም ይገለፃል። ሲመሠረት ኀዘን ለደረሰበት ሰው ማስተዛዘኛ ከእድሩ አባላት የሚሰበሰበው የእንጨት፤ የንፍሮ እህል እንዲሁም 10 ሳንቲም ነበር። ኀዘንተኞቹ እንግዶቻቸውን በዚሁ አስተናግደው ይሸኛሉ ይላሉም።

በሻህ በዓለም ከተማ በሁለተኛ ደረጃ የተቋቋመው እድር በ1982 ዓ.ም የተቋቋመው የመድሃኒአለም እድር ነው። እንዲቋቋም የሆነበት ምክንያት አሁንም ያለው የቅዱስ አማኑኤል የመረዳጃ እድር እንቅስቃሴውን አቁሞ የነበረ በመሆኑ ነው። በ1984 ዓ.ም የእድሩ አባላትም ዓለም ከተማ ተመልሰው ሲሰበሰቡ ቤተሰብ ሞቶብናል ክፍያ ይፈፀምልን የሚሉትን ለማስተናገድ የእድሩ የመክፈል አቅም አለመኖር ተከትሎ በተፈጠረ ችግር ምክንያት የተመሠረተ እድር ስለመሆኑም አቶ በሻህ ይናገራሉ።

የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ዕሴት ልማት ባለሙያ እየሩስ እንዳሉን፣ እድር በየቦታው የተለያዩ ክዋኔዎች ይኖሩታል። እንደ ሁኔታው ጥቅሞቹም ዘርፈ ብዙ ሆነው ይታያሉ። ስለሆነም አንድ አካባቢን መምረጥ ግድ ይለናልና በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷ የሆነችውን መርሀ ቤቴ ወረዳ (ዓለም ከተማ)ን እንመልከት። በዓለም ከተማ የሚገኙት እድሮች መሠረት ያላቸውና ለብዙዎች ተምሳሌት የሆኑ ናቸው። አመሠራረታቸውም እድሜ ጠገብ ነው። ስለዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የማህበረሰቡን ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች በሚል በቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ።

ዋና እድር ሲባል ከቃሉ እንደምንረዳው የመጀመሪያ፣ የበላይ እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን አጣምሮ ይይዛል። ኀዘን የደረሰበት የእድር አባል በአብዛኛው ዋና እድሮች የሚተገብሩት ተግባር በቀላሉ ለመገመት የማይቻል ነው። ለምሣሌ በዋና እድሮች የሚሸፈኑት ክፍተቶች የቁሳቁስ አቅርቦት፣ የእህል ይህም ሲባል የንፍሮ እህልና እንጀራ አስከሬን የማጓጓዝ ሥራ፣ የቀብር ቁፋሮ ሥራ በመጨረሻም በቀብር ሥርዓቱ ላይ የአባላት መገኘት አለመገኘት ቁጥጥር ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ እድር የተለያየ ስያሜ ሲኖረው የሴት፤ የወንድ የሚባሉት ዋንኞቹ ናቸው። የሴት እድር በበለጠ ሴቶች የሚሳተፋበትና የበላይ አመራር ሆነው የእድሩን ሕግና ደንብ የሚያስፈፅሙበት ነው። በተጨማሪም በሴት ባልትና የተዘጋጀ በርበሬ፣ ሽሮ፣ የወጥ ክክ ቡና እና እንጀራ አዘጋጅተው መከራ ለደረሰበት የእድር አባል ይሰጣሉ። እንደዚሁም የሴት የእድር አባላት ወጥ በመሥራት እና ቡና በማፍላት እንዲሁም ሌሎች እንደ እድሩ ሕግና ደንብ የሚሠሩ ሥራዎችን በመሥራት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ባለመከራውን የሚያግዙበት ሥርዓት ነው። ይህንን ሥራ ሲያከናውኑ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን እንደ ስኒ፣ ትልቅ ሻይ ጀበና፣ ወጥ መሥሪያ ብረት ድስትና ትሪ ሳህን በማሟላትም ጭምር ነው።

የሴቶች እድር ከዋና እድርና ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በዚሁ ተግባርና ኀዘነተኛዋ ቤት ፍራሽ፣ ትራስ፣ አልጋ ልብስና፣ የወለል ምንጣፍ በመውሰድ እና የእድሩ አባላትም ከሦስት ቀን በፊት ኀዘነተኛው ካላሰናበቷቸው በስተቀር እስከ ሶስት ቀን ድረስ በመከራው ቤት በመገኘት የተለያዩ ሥራዎችን በመተጋገዝና በመከባበር መሥራታቸው ነው።

የሰፈር እድር ወይም ፈጥኖ ደራሽ እድር፦ የሚባለው በአንድ አካባቢ ወይም ጎጥ ባሉ ሰዎች አማካኝነት የሚመሠረት ነው። እድሩ በሰፈር ወይም በጎጡ ውስጥ የሚኖሩ ለመግባባትና ለመተዋወቅ በጣም የቀረቡ ሰዎች ዘመዶቻቸውን በተለያየ አጋጣሚ ስለሚያውቋቸውና ያሉበትንም አካባቢ ስለሚረዱ ኀዘን በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ የሚደርሱ መሆናቸውን ለመንገርም ነው። እናም በዚህ እድር ውስጥ ያሉ ሰዎች የተለያየ ቦታ በመሄድ ለምሳሌ፦ በገጠር ቀበሌዎች ያሉትን ዘመዶችን ይጠራሉ፣ በስልክ የሚጠሩትን ስልክ ቁጥር ከኀዘነተኞቹ አለያም ሌሎች ሰዎች በመቀበል ደውለው ኀዘን እንዳጋጠመ ይናገራሉ።

ኀዘን የደረሰበትን ግለሰብ ቤት በዋናነት በመቆጣጠርና እንደ አስፈላጊነቱና እንደ እድሩ ሕግና ደንብ ተጨማሪ ተግባራትን በማከናወን ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት የእድር አይነት ነው። በተጨማሪም ይህ የእድር አይነት አካባቢ ለመጠበቅ ለምሣሌ፦ በሰፈር ውስጥ የማይታወቁና ፀጉረ ልውጥ ሰው ሲኖር በመከታተል ያሉበት ሁኔታ አስጊ ከሆነ ለጥበቃ ኃይሎች ይጠቁማል። የበለጠ በመከታተል ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋልም። ከዚያም ባሻገር የተጣላን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ያስታርቃል። ለአካባቢውም ጥበቃ በማድረግ ልማትን ያፋጥናል።

አንድ ቀበሌ፦ ሁለትና ከዚያ በላይ ቀበሌ ለቀበሌ ተከፋፍሎና ተወስኖ የተቋቋመ የእድር አይነት ሲሆን በእድሩ ውስጥም የሚሳተፉት አካላት በአንድ ቀበሌ እድር ብቻ ይሳተፋሉ። ሁለትና ሦስት በሞሉ እድሮች ላይ መግባት አይፈቀድም። ምክንያቱ ደግሞ ሩቅ ከሆነ ቦታ መጥተው የጊዜና የሰው ሃይል ብክነት እንዳይፈጠር ለማስቻል ነው። በመሆኑም የቀበሌ እድር በዓለም ከተማ የተቋቋመው በ2004 ዓ.ም እንደነበረ ሁለቱም ያነጋገርናቸው አካላት ይናገራሉ።

እድሩ በከተማው ውስጥ ያሉ የተለያዩ የእድር አይነቶች በቀበሌ እድር ውስጥ በማካተት ወደ አንድ መስመር እንዲመጡ በማድረግም እንደ እቅድ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው። ይህ ደግሞ እድሩን ከጊዜና የሰው ኃይል ብክነት ማቅለል ባሻገር በአጭርና በተቀላጠፈ መልኩ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ስለመሆኑም ያነሳሉ።

ከዚህ አንጻርም በመርሐ ቤቴ ወረዳ ያሉ እድሮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ያብራራሉ። አንዱና ዋነኛው ወጪን መጋራትና ኀዘንን ማስረሳት ነው። ሌላኛው ደግሞ በእድሩ ደንብ ውስጥ በማካተት አካባቢን ማልማት ነው። የአካባቢ ጥበቃ ቡድን በማቋቋም ጭምር እድሮች ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። ከብቶች እንዳይወሰዱ፣ ደን እንዳይደርቅና ያለአግባብ እንዳይጨፈጨፍ ይጠብቃሉ። ምንም ነገር እንዳይሰረቅ ከማድረግም አልፈው የሰረቀ ቢገኝ ባወጡት ደንብ ይቀጣሉ። የሃይማኖት ተቋማትን በጉልበትና በገንዘብ ይደግፋሉ። የታመሙና የተቸገሩ ሰዎችን ይረዳሉ። የሕዝብ ተሣትፎን በሚጠይቁ የመንግሥት ልማቶች ላይም በስፋት ይሳተፋሉ፡፡

በወረዳው እድሮች ከተመሠረቱበት ከ1943 እስከ 1980ዎቹ ድረስ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን አብዛኛው ተሳትፏቸው በኀዘን ላይ ብቻ የታጠረ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ ሁኔታውና እንደ አስፈላጊነቱ በኀዘን ካለው ትብብር ውጭ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነ የባህል እሴት ባለሙያዋ እየሩስ ያነሳሉ።

ዕድር ግለሰቦች ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚገዙበትን በራሳቸው ውዴታ ደንብ አቅደውና አፅድቀው ያደራጁት እንደመሆኑ መጠን ለዚያ የመገዛት ሁኔታቸው የሰፋ ነው። በመሆኑም እንደ እድሩ ስፋትና የገንዘብ መጠን የሕግና ደንባቸው ሁኔታ ይለያያል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ወርሃዊ ክፍያ አፈፃፀም ሕግ፤ የመረዳጃ ገንዘብና የእንጀራ ክፍያ ሕግ፤ የአዲሱ ገቢዎች ገንዘብ አከፋፈል ሕግ፤ ስለሞቱ ሰዎች መረጃ አቀራረብ ሕግ፤ ከሌሎቹ አቻ እድሮች ስለሚኖር ትብብር እቃ የመዋዋስ ደንብ፤ ስለ እድር ሥርዓተ ተኮር አፈፃፀም በእድሩ ደንብ ውስጥ ተዘርዝሮ የተጻፉ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።

የእድርተኛው ግለሰብ እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም እና ልጅ ተመዝግበው እንዲቀመጡ በእድሩ ደንብ ተደንግጓል። እድሩን ስለማውረስና ስለመወከል፤ ስለ ክብረ በዓል አከባበር ደንብ ፀድቆ ተካቷልም። የእድሩ አባላት የሆኑ በኤች አይ ቪ ኤድስ ለተያዙ የገንዘብ ርዳታ የአፈፃፀም ደንብ፤ በደንቡ ውስጥ ወሰን የተደረገለት ጉዳይም ነው። የእድር መሪዎች የሥራ ድርሻ፤ የእድሩ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀትና የሥራ አገልግሎት ምን እንደሚመስል በእድር ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ አብዛኞቹ ሕግና ደንቦች በእድር አመራሮች የሚፈፀሙ ናቸው። ከአመራሮች አቅም በላይ ሲሆንና ደንቡን ለማስፈፀም የሚያስቸግር ጉዳይ ሲገጥም ለጠቅላላ ጉባዔው ቀርቦ የሚወሰንበት አለ። በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ካለ ብዙም ባያጋጥም ነገር ግን እንደ ክሱ መጠንና ይዘት በቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤት እንዲታይ ደንቡ አካቶ ይዟል።

በመርሐ ቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ያሉ እድሮች ለከተማዋ ሕብረተሰብ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ለምሣሌ፦ በእድር ውስጥ በመግባትና በመደራጀት በከተማው ውስጥ የተለያየ ቀበሌዎች በመዘዋወር ችግኝ በመትከል፣ የከተማውን መንገዶችና የተለያዩ ቦታዎች በማፅዳት፤ ለአየር ብክለት መንስኤ የሚሆኑትን ከማስወገድ የከተማውን ውበት ከመጠበቅ አንፃር አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። አባትና እናት የሞቱባቸውን ህፃናት፤ አረጋውያንን እንዲሁም መጠለያ የሌላቸውን አቅመ ደካሞችንም ይደግፋሉ። ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለአብነት በጦርነት ጊዜ ስንቅ ያዘጋጃሉ፤ ተፈናቃዮችን ሀብት በማሰባሰብ ይደግፋሉ፤ ማናቸውንም በሕብረት የሚከወኑ ተግባራት በመተግበር የእርስ በእርስ ማህበራዊ እና ሀገራዊ መስተጋብራቸውን ያጠናክራሉ ሲሉም ባለሙያዋ ያብራራሉ።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You