የ ስሪ ዲ ሞዴል ጠበብቱ ወጣት

የዛሬው የወጣቶች ገጻችን እንግዳ የቤቶን ዲዛይን መሥራች እና ሥራአስኪያጅ አርክቴክት እና የአርባን ፕላኒንግ ባለሙያ በረከት ብርሀኑ ነው። ‹‹ቤቶን›› የሚለው ቃል በጀርመንኛ የሲሚንቶ አርማታ ወይንም ኮንክሪት የሚል ትርጉም ያለው ነው። በአማርኛ ቋንቋ የእርስዎን ቤት የሚል ትርጉምን ይይዛል።

ቤቶን ዲዛይን ከሚሠራቸው ሥራዎች የተቋማት የብራንዲንግስ ሥራና ማማከር፣ የሕንጻዎች የተለያዩ ፕሮጀክቶች ስሪ ዲ ሞዴሎችን መሥራት እንዲሁም የተጠናቀቁ ሕንጻዎችን ተረክቦ የፊኒሺንግ ሥራ ወይንም የኢንቲሪዬር ዲዛይን ሥራን ማከናወን ይገኙበታል።

በረከት ወደዚህ ሥራ ከመግባቱ በፊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት የስሪ ዲ ሞዴል ትምህርት የሚወደው እና ሲማርም ከከፍሉ ተማሪዎች በተሻለ ጥሩ ውጤት ያለው መሆኑን ያስታውሳል። መምህሩ የነበረው አማኑኤል ገዛኸኝ ለዘርፉ ጥሩ እይታ እና ፍቅር እንዲያድርበት እንዳደረገው ይናገራል። በኮቪድ ወረረሽኝ ወቅት የተማረውን ትምህርት በተግባር የሚተርጎምበት ዕድል በማግኘቱ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ፕሮጀክቶችን ተቀብሎ በመሥራት አቅሙን ማዳበር ችሏል።

እንደ ሀገር ከአብዛኛው ሰው አፍ የማይጠፋው እና በብዙዎች ዘንድ ወጣቶች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ የሚሰነዘረው ሀሳብ እና ጥያቄ ሥራ አገኘህ? ወይም ሥራ አገኘሽ? የሚለው ጥያቄ ነው። አንድ ወጣት ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በቶሎ ሥራ ማግኘቱ ቀጣይ የሕይወት ጉዞውን በመቀጠል ሕልሙን ለማሳካት ያግዘዋል። ስለዚህ በአካባቢያቸው የሚያገኟቸው ሰዎች ተመራቂዎች ሥራ ማግኘታቸውን በተደጋጋሚ ሊጠይቋቸው ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ለሁሉም ወጣቶች ቀላል የሚባል ነገር አይደለም፡፡

እንደተመረቁ የራስን ተቋም ገንብቶ ገበያውን መቀላቀል ቀላል የማይባል መሆኑን የሚገልጸው የድርጅቱ መሥራች እና ሥራአስኪያጅ ወጣት በረከት፤ የአመራር ክህሎትን መገንባት፣ ድርጅት እንዴት እንደሚመራ ማወቅ፣ ቢዝነስን እንዴት ማስኬድ እንደሚቻል መረዳት እንዲሁም ከሰዎች ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነትን መፍጠር ከትምህርት ቀጥታ ወደ ሥራ ለሚገባ ሰው ትንሽ አስቸጋሪ ነው ይላል።

‹‹ከትንሽ በመነሳት ከባለቤቴ ጋር አንድ ላይ ሆነን መጀመራችን ሥራዎችን እና የሚመጡ ኃላፊነቶችን እየተከፋፈልን እየተጋገዝን መሥራታችን ዛሬ ላይ እንድንደርስ አስችሎናል›› ይላል።

በረከት እና ባለቤቱ ጺዮን ዘውዴ የተዋወቁት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በነበሩበት ወቅት ሲሆን፤ ባለቤቱም እንዲሁ የአርክቴክት ባለሙያ ናት።

‹‹ሥራውን በጀመርንበት ወቅት ተቀባይነት ስላልነበረው ግንዛቤ ከመፍጠር ነበር የተነሳነው። ስሪ ዲ ሞዴል ያለውን አስፈላጊነት፣ ምንነት ማስረዳት በጣም ከባድ ነበር›› የሚለው በረከት አሁንም ገና በማደግ ላይ ያለ ዘርፍ እንደሆነ ይናገራል።

ስሪ ዲ ሞዴል የተለያዩ ድርጅቶች፣ ሕንጻ ባለቤቶች እንዲሁም የሪል ስቴት አልሚዎች በመገንባት ላይ ያለ ሕንጻቸውን እና ቢሯቸውን በቀላሉ ማሳየት እንዲችሉ ያስችላል። ለሜጋ ፕሮጀክቶችም እንዲሁ ማስተማርያ እና ማሳያ በመሆን ያገለግላል።

ሥራቸው አሁን ላይ ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን የሚጠቁመው በረከት፣ ብዙ ተቋማ ሞዴላቸውን በዚህ መልኩ በመሥራት ለሰዎች በቀላሉ ማሳየትና ለደንበኞቻቸው ማስረዳት እንደሚችሉ እየተረዱ መጥተዋል። ስለዚህ አሁን ላይ ያለው ተቀባይነት ጥሩ ነው። ከተለያዩ ተቋማት ጋርም መሥራት ችለናል ይላል።

በእስካሁኑ ጎዞው ቤቶን ዲዛይን ከ90 በላይ ከሚሆኑ ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ችሏል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብን እንዲሁም የአዳማ የንፋስ ማመንጫን ዲዛይኖች ስሪ ዲ ሞዴል ሠርቷል። በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ከሚገኙ ከተለያዩ ሪልስቴት አልሚዎችና ተቋማት ጋር በመሥራትም ጥሩ ደንበኝነትን በመፍጠር ለቀጣይ የሥራ ጉዞው ስንቅ ሰንቋል።

በረከት ሥራቸውን እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚያከናውኑ ሲያስረዳ ስሪ ዲ ሞዴል እንዲሠራላቸው ለሚፈልጉ ደንበኞቻችን መጀመርያ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ልከውልን በሥራው ስንስማማ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በስምምነታችን መሰረት ሰርተን እናስረክባለን። ለኢንቲርዬር ዲዛይን ከሆነ ደግሞ እየተጠናቀቁ የሚገኙ ሳይቶችን ሄደን ቦታው ድረስ በመመልከት ሳምፕሎችን በማሳየት እና ከደንበኞቻችን ጋር ስብሰባዎችን በማድረግ ፍላጎታቸውን ለመረዳት እንሞክራለን። ከዚያም ወደ ሥራ እንገባለን ይላል።

ቤቶን ዲዛይን በበረከት እና በባለቤቱ ጺዮን ከተመሰረተ ሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል። ከትልልቅ ተቋማት ጋር አብሮ ከመሥራት ባሻገር ለሌሎች በዘርፉ ለሚገኙ በርካታ ወጣት ባለሙያዎች ሥራ እድል መፍጠር ችሏል። በእዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥም ወደ 40 ለሚጠጉ ቋሚ ሰራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል።

40 ከሚጠጉት ቋሚ ሰራተኞችን ውስጥ አብዛኛዎቹ አርክቴክቶች ሲሆኑ ሜካኒካል ኢንጂኒየሮች፣ የእንጨት ሥራ እና የተለያዩ ባለሙያዎችም አሉን ለሚለው በረከት፣ በወጣትነት ዕድሜህ ሥራ መሪ በመሆን በስርህ በርካታ በእድሜ ተቀራራቢ የሆኑ ወጣት ሠራተኞችን ማስተዳደር መምራት አልከበደህም? የሚል ጥያቄ አቅርበንለት ነበር። ‹‹ወጣት ሆኖ የሥራ ኃላፊ መሆን ቀላል ባይሆንም ዋናው ዓላማችን ሥራችንን ማሳካት ስለሆነ እንደ ቡድን ሆነን በአንድነት ነው የምንሠራው።›› ሲል መልሷል።

በሥራ ሂደት ሥራዎችን በሚፈለገው ፍጥነት መሥራት አለመቻል አልያም በሀሳብ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሊፈጠሩ ቢችሉም ትኩረታችንን ሥራችን ላይ ስለምናደርግና በቡድን ስሜት ስለምንሠራ ይህ ነው የሚባል ችግር አልገጠመንም ሲልም አክሏል።

እኔ ሥራውን ስጀምር እውቀት እና በምሠራው ሥራ ላይ ክህሎት ቢኖረኝም እንዴት ማስኬድ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር የሚለው በረከት እስካሁን ለመጣበት መንገድ ላሳካቸው እቅዶች እና በሥራው ውጤታማ እና ስኬታማ ለመሆኑ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን ጭምር ያመሰግናል። ስኬት እንደ ግለሰቡ ትርጉሙ ይለያያል የሚለው በረከት እንደ አንድ ወጣት ዓላማን መረዳት አለባቸው ሲል ይመክራል። ወጣቶች በዙርያቸው ያለውን ችግር በመረዳት ያላቸውን አቅም በመጠቀም ያንን ችግር ለመፍታት መሞከር እንደሚገባቸውም ይገልጻል።

ሁሉም ወጣቶች ባሉበት ዘርፍ ላይ ጠንክረው እየተማሩ ራሳቸውን በእውቀት እና በክህሎት ማሳደግ ይኖርባቸዋል። ስኬት ላይ ትልቁ ነጥብ ፍጹም መሆን ሳይሆን የየእለት እድገታችን ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። ከትላንት ዛሬ ምን አሻሽለናል፣ ምን ጥሩ እየሠራን ነው የሚለው ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል። ሥራን በጉልበት ብቻ ሳይሆን በጥበብ መሥራትን ልንማር ይገባል ሲልም ያክላል፡፡

በረከት ትምህርቱን በትኩረት ተከታትሎ፣ ከተመረቀ በኋላም ጊዜ ሳያባክን ያለውን ክሕሎት እና እውቀት ይዞ ወደ ሥራ በመግባት ከትዳር አጋሩ ጋር አሁን ያለበት የስኬት ደረጃ ላይ ደርሷል። አብሯቸው የሠራቸው ተቋማት ቁጥር 90 ይድረሱ እንጂ ድርጅቱን ካቋቋመ የተቆጠሩት ሁለት ዓመታት ብቻ ናቸው።

ከዚህ በኋላም በርካታ ሥራዎችን የመሥራት አቅድ ያለው ሲሆን ቤቶን ዲዛይንን እንደ ሀገር በስፋት እንዲታወቅ ከማድረግ ባለፈ የሀገር ውስጥ ተሞክሮውን ይዞ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር በመጓዝ መሥራት የሥራ አስኪያጁ በረከት የወደፊት እቅድ ነው። ያለውን የሥራ ጥራት ይዞ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ የስሪ ዲ ሞዴል ዲዛይኖችን የሚሠሩ ተቋማት አንዱ ለመሆን አልሟል።

በአፍሪካ ደረጃ ተጠቃሽ የሆነ ድርጅት የመውለድ ውጥኑ ሰምሮ የበረከት ሕልም እንዲሳካ የዝግጅት ክፍላችን ምኞት ነው።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You