ብዙ ጊዜ ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚሰጠው ትርጓሜ ግልጽ ያልሆነና የተሳከረ ነው። የሀገር መገለጫ በሆኑት እሴቶቻችን ላይ ያለን የአረዳድ ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ ሊሆን የቻለው የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዲላላ በሚፈልጉ፣ በትውልድ መካከል መከፋፈል በመፍጠር ሀገሪቷ ችግሮቿ እንዲበዙ ሌት ተቀን በሚሰሩ ሰዎች መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጀመሩት የለውጥ ሂደት መካከል ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ብዙ ጊዜ በንግግራቸው ሲነሱ ይደመጣሉ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የዜግነት ፖለቲካ እና የማንነት ፖለቲካ ጨምሮ በርከት ያሉ ምጦች ሀገሪቷን እየተፈታተኗት ይገኛሉ። እነዚህን ችግሮች በቶሎ መስመር እንዲይዙ ካልተደረገ የታሰበውን ዓላማ ለማሳካት ትልቅ እንቅፋት መሆናቸው ባያጠራጥርም አሁን ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ የሚገባው ግን የተፈጠረውን ችግር ማባባስ ሳይሆን ውጤቱ ላይ መሆን ይኖርበታል።
የላላ አገራዊ አንድነት ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ምንም ሚና እንደሌለው በመረዳት በሰላም ተቻችሎ በመኖር የነበረንን እሴት ለማሳደግና የምንፈልገውን እድገት ለማምጣት አገራዊ አንድነትን መገንባት ግድ ነው። ይህም በሃሳብ አንድ መሆን የግድ ባይባልም ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግባባት እና ኢትዮጵያዊ አንድነት ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ሁሉም የፖለቲካ ተዋናይ ሊያምን ይገባል። በዚህም ለችግሮች ሳይሆን ለቀጣይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ መስመር እንደ መዘርጋት ይቆጠራል።
በቀጣይ የሚካሄደው የ2013 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት የሚረጋገጥበት እንዲሆን መስራት ይገባል። ይህም ከሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ይጠበቃል። በመሆኑም በኢትዮጵያ እየኖርን ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጠለሽ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክርና ከተጋረጠብን ፈተና የምንወጣበትን መፍትሄ ማስቀመጥ ላይ ልናተኩር ይገባል።
ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር እሳቤ የተሰኘውን ሰባተኛ መጽሐፋቸውን ሲያስመርቁ እንደተናገሩት፤ ችግሮቻችን ላይ አሊያም ምጡ እና ጭንቀቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ውጤቱ ላይ አተኩረን መሄድ ይኖርብናል። “ኢትዮጵያ እንድትበታተን እና እንድትፈርስ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ። በዚህም ብዙ ጊዜ ችግር ሲፈጠር ይስተዋላል። ነገር ግን ችግሩን በይቅርታ አልፎ ውጤቱ ላይ መድረስ ይገባል። ከምጡ እና ስቃዩ በኋላ ስላለው መልካም ነገር ትኩረት አድርጎ መሻገር ይቻላል።” ብለዋል።
በርግጥ በተበታተነ ሁኔታ ስለኢትዮጵያ አንድነት፣ ትልቅነት መሥራት አስቸጋሪ ማድረጉ አይቀርም። ምንም አስቸጋሪ ቢሆንም ግን በአገሪቱ ጫፍ እየወጡ ያሉት የፖለቲካ መጓተቶች የሀገሪቷን አንድነት በመፈታተን የሚያደርሱትን አደጋ ከወዲሁ በመገመት ልዩነቱን በማጥበብ ወደ አገራዊ አንድነት ለማምጣት መስራት ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ ሁሌም ምጥና ጣር ቢበዛባትም እንደብረት እየጠነከረች በፈጣሪዋና በህዝቦቿ ጥረት ከሚግጥሟት ፈተናዎች በማይታመን ሁኔታ ትንሳዔዋ እየደመቀ የምትሄድ ሀገር መሆኗን ሁሉም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ከለውጡ ወዲህ ያጋጠሟትም ፈተናዎች ይህን ሃሳብ የሚያጠናክሩ ናቸው። ህወሓት ለ27 ዓመታት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ሃገር የመበታተን ራዕይ በመያዝ አገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ አጥፊና በታታኝ ኃይል በቅርቡ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ህልውናው ያከተመ ቢሆንም የቡድኑ ርዝራዦች የህግ ማስከበር ዘመቻውን ለማጠልሸትና ሀገራዊ አንድነትን እንደጎዳ አድርገው በቀጠሯቸው ሚዲያዎች ሲያራግቡ ይደመጣሉ። ውስጣችንን ለምናውቀውና ላለፉት 27 ዓመታት በህወሓት ግፍና መከራ የቀመሰ ሰፊው ኢትዮጵያዊ ግን የህግ ማስከበር ዘመቻው አሁን ላይ ያለውን ችግር የሚያባብስ ሳይሆን የወደፊቱ አንድነታችን የሚጠናከርበት ሁኔታን የፈጠረ ክስተት መሆኑን ይረዳል ።
አሁን ኢትዮጵያ በውስጣዊና በውጫዊ ችግሮች ተከባ ትገኛለች። በመተከልና በትግራይ ክልል ገና ሙሉ ለሙሉ ያልተረጋጋ የጸጥታ ችግሮች አሉ። የኑሮ ውድነቱም እንዲሁ የብዙዎችን ወገብ እያጎበጠ ነው። በሌላም በኩል ሱዳን ድንበራችን በሃይል ወራ ይዛለች። በህዳሴው ግድብም እየደረሰው ያለው ዓለም አቀፋዊ ጫና ሌላው የኢትዮጵያ ፈተና ነው። ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ ምጦች ነገ ብልጽግናዋ የተረጋገጠ አዲስቷን ኢትዮጵያ ይወልዳሉ። ዜጎች የሚያፍሩባት ሳይሆን የሚኮሩባት ኢትዮጵያ እንድትወለድ ይረዳሉ። የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በጥላቻ የሚታያዩባት ሳይሆን በጋራ የሚያለሟት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን መንገድ ይጠርጋሉ። ስለዚህም ዛሬ ኢትዮጵያ በችግሮች የተከበበች ብትመስልም እንደሁልጊዜው ሁሉ ፈተናዎችን ሁሉ አልፋ ለለልጆቿ መመኪያ መሆኗ አይቀርም። ስለዚህም የዛሬው ትውልድ ችግሮች ላይ ከማተኮር ተሻግሮ የነገዋን ኢትዮጵያ ለማየት በትጋት መስራት አለበት።
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም