በጋዜጣው ሪፖርተር
የአፍሪካ ጄንደር ኢኖቬሽን ላብ በኢትዮጵያ የፆታ እኩልነት በቅርብ ጊዜ ጥናት አድርጎ ባገኛቸው ቁልፍ የጥናት ውጤቶች እንዲህ ይላል። ‹‹ሴቶች ከወንድ አቻዎቻቸው ያነሰ ሥራ የማግኘትና የመቀጠር ዕድል ያላቸው ሲሆን፣ ሥራ የማግኘት ዕድል ቢኖራቸው እንኳ ከወንዶቹ ያነሰ ሰዓት (በሳምንት) ለመሥራት ይገደዳሉ›› ይላል። በተጨማሪም ‹‹ሴቶች ከወንድ አቻዎቻቸው ያነሰ በመደበኛ ሥራ ተቀጥሮ የመሥራት ዕድል ያላቸው ሲሆን፣ በአብዛኛው ከግብርና ጋር ባልተያያዙ የሥራ ዘርፎች ተቀጥሮ የመሥራት ዕድላቸው ሰፊ ሆኖ ይታያል። በዋነኝነት በምርት ግብዓቶች ልዩነት ምክንያት የሴቶች የግብርና ምርታመነት ደረጃ ከወንድ አቻዎቻቸው አንሶ ይታያል። ሴቶች ከሥራ ፈጠራ እና ከግል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያገኙት ገቢ ከወንድ አቻዎቻቸው በእጅጉ ያነሰ ለመሆኑ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት ነው።
እንደ ዕድሜ፣ የጋብቻ ሁኔታ እና የትምህርት ደረጃን ከመሳሰሉ ጥቂት ወሳኝ ባህሪያት ውጪ በቅጥር ገቢ ዙርያ በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት በግልፅ የሚያብራሩ ምክንያቶች አይገኙም። ሰፋ ተደርጐ ሲታይ እንደ ፆታ ላይ የተመሠረተ መድሎ፣ ሴቶች ለቴክኒካል ሥልጠናዎች ያላቸው ተደራሽነት ውስን መሆን እንዲሁም ሴቶች መደበኛ ባልሆነ የሥራ ዘርፎች በብዛት መገኘት ዓይነት ምክንያቶች ለተፈጠረው ልዩነት የተሻለ መንስኤ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ። በኢትዮጵያ የሴቶች የሰዓት ገቢ ከወንድ አቻዎቻቸው በ44 በመቶ ያነሰ ነው። ፆታዊ እምነቶች (norms) ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወደሆኑ ባህርያት ሊለወጡ ይችላሉ። በፆታ ዙርያ ለረጅም ጊዜ በማኅበረሰቡ ተይዘው የቆዩ እምነቶች በተለይም ሴቶችና ወንዶች እንዴት ዓይነት ባህሪ ሊጐናፀፉ እንደሚገባቸው የሚደነግጉ እምነቶች ሴቶች በሚመርጧቸው ምርጫዎች እና ዕርምጃዎች ላይ የራሳቸው የሆነ ጫናን ማሳረፋቸው አይቀሬ ነው።
ይህ ከላይ የተዘረዘረው የጥናት ውጤት ሴቶች ምን ያህል ጫና እያደረባቸው እንደሆነ በጨረፍታ ለማሳየት የቀረበ ነው። ሆኖም በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆነው እንኳን ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያላቸው ብርቱ ሚና አይተኬ እየሆነ መጥቷል። ሴትነት በተለይም እናትነት በተፈጥሮ ውስጥ የሚለገስ ልዕልና ነው። ወንድ ቢሆንም፣ አባትነትን በእናትነት ፋንታ ከተፈጥሮ ቢለገስም አባትነት የእናትነትን ያህል ጣዕም እንደሌለው አሳምሬ አውቃለሁ። እርግጥ ነው መሰዋዕትነቱ፣ ስቃዩና ሕመሙም ግዝፍ ነስቶ የሚታይ ዕውነታ ነው። ይህ በተፈጥሮ ውስጥ የሚለገስ እናትነት የተሰኘ ክብር በማሕፀን ተከልሎ የሚቀርና የአብራክን ክፋይ ወልዶ ከመሳም የዘለለ አንድምታ የሌለው አይደለም፤ የልቦና ውቅር ማዕቀፍም የተቸረው እንጂ። ሴትነት ትውልድን ከማስቀጠል ተፈጥሯዊ ኃላፊነት የላቀ ነው። እናትነት ደግሞ ምስጢሩ ዕልፍ የሆነ ተፈጥሯዊ ፀጋ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚወደድ ሁሉ በአንስታይ ፆታ የመጠራቱም ሚስጢር ከፍቅር የመነጨና ማንም እንዲህ ይሁን ብሎ ሳይበይነው የተግባባንበት ነው። ሕዝቡ ሀገሩን ኢትዮጵያ እናቴ ሲል ይደመጣል። አባት ሀገር ኢትዮጵያ የሚል ካገኛችሁ እሱ ፍቅሩ ስለሀገሩ የነጠፈበት፤ ስለ እናቱ የተዛባበት እንደሆነ መጠርጠር መልካም ነው።
አሁን በኢትዮጵያ ሴቶች ከምን ጊዜውም በተሻለ የኃላፊነት ከፍታ እና ስብጥር ላይ የሚገኙበት ወቅት ነው። እናቶች ሁሌም የሰላም ዘብ እንደሆኑ ባይካድም በተቻለ መጠን ሁሉ ከሰላም ሰባኪነት የወጣ አካሄድ ሲከተሉ ያየንበት ዘመንም አሁን ነው። በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ከሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች እኩል ሰላም እንዲወርድ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። ወንድ በጉልበቱ ሊፈታው የሚሞክረውን ችግር ሁሉ ሴት በጥበብ የመፍታት አቅሟ የተመሰከረ ነውና።
በሀገር ደረጃ ሲታይ የዝቅተኛ ኑሮ ተጠቂና የደረሰ ችግር ሁሉ ገፈት ቀማሽ እናቶች የሰላምን ጣዕም የሚውቁትን ያህል የጦርነትን ክፋት አሳምረው ያውቁታል። እንዲያውም ብዙ ታላላቅ ወንዶች ጠቢብ ሲባሉ እንዲኖሩ ካደረጋቸው አንድ ምክንያት ሴትን ለማዳመጥ በከፈቱት ጆሯቸው ስፋት ነው።
ለዚህ አሁን ከአከበርነው የዓድዋ ድል ጋር አያይዘን ወደኋላ መለስ ብለን ማየት ብንችል እቴጌ ጣይቱን መጥቀስ እንችላለን። እቴጌዋ ለሰላም ሩቅ መንገድ የሚሄዱ ነገር ግን ቆራጥና ጀግና ሴት ነበሩ። ውሳኔዎችን ከግልፍተኝነት በፀዳ ሰክኖ በጠለለ ጥበብ ይወስኑ እንደነበር እማኝ አመክንዮዎችን እያነሱ መተንተን ይቻላል። እንዲያውም ለዓድዋ ድል አንዱ ምሶሶ እቴጌ ጣይቱ ናቸው ብንል ይጋነንብን ይሆን? ይህን የምለው የእናቶችን ጠቢብነትና ኃላፊነትን ያለ ነፍጥ የመወጣት ችሎታ ለማሳየት ጭምር ነው፤ የሰላሙ መንገድ አልሆን ሲል ደግሞ ነፍጡን በጥበብ የመጠቀም አቅምንም ከዚሁ ሳንቀጣ መመልከት የሚያስችለን አስረጅ ታሪክ ነው።
አሁንም ይህ ዘመን ዘለል ሥራ ቀጥሏል። ትውልድ በመቀጠሉ ብቻ ሳይሆን ብቃት በመቀጠሉ ጭምር ዛሬም ትላልቅ ኃላፊነትን ተሸክመው ትላልቅ ድርጅቶችን እየመሩ ያሉና አለፍ ብሎም ሀገርን በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እያራመዱ ያሉ ሴቶችና እናቶች ያሏት ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያ። ሴቶችን በተለይ እናቶችን አንድ የሚያግባባ ቋንቋ አለ – ሰላም። አሁን የምናወጋው እናቶች ከላይ በጠቀስነው ጥናት እንኳን በተጠቀሱ ችግሮች ውስጥ ሆነው ለሰላም፣ ለልማትና ለዕድገት ያበረከቱት አስተዋፅዖ ይህን ያህል ከሆነ እኩል ምህዳር ቢፈጠር ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት የሚያዳግት አይደለም። እናም ሴትነት በተለይም እናትነት እንዲህ ነው አንሶ የመግዘፍ፣ ጠቅኖ የመጉላት እና ጠብቦ የመስፋት ጥብብ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም