አዲሱ ገረመው
አገራችን ካፈራቻቸው ምርጥና ዘርፈ ብዙ ከያኒያን መካከል አንዷ ናት፤ ዓለምጸሐይ ወዳጆ። ወደ ኪነ ጥበብ መድረክ መውጣት ከጀመረችም ሃምሳ ዓመታትን አስቆጥራለች።
በ13 ዓመቷ ወደ ኪነ ጥበብ አለም የተቀላቀለችው አርቲስቷ እድሜዋን ሙሉ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ባህልና ታሪክ ማበብ ስትደክም ኖራለች። ጸሐፌ ተውኔት፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይ፣ የዘፈን ግጥም ደራሲ ናት። ለዚህም ሥራዎቿ በኪነ ጥበብ ሰዎች ዘንድ ጉልህ እማኝ ሊሆኑ ይችላሉ።
በጸሐፌ ተውኔትነት ከ20 በላይ ድርሰቶች አሏት። በአዘጋጅነት በአገራችን ሴት የመድረክ አዘጋጆች ቁንጮ ናት ይሏታል። ከአዘጋጀቻቸውም መካከል አማቾች፣ ያልተያዘ፣ የፌዝ ዶክተር በአብነት መጥቀስ ይቻላል። በትወና በኩልም በተለይ አገር ቤት በነበረችባቸው ወቅቶች ሀምሌት፤ የቬኑሱ ነጋዴ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ ሞረሽ፣ አንድ ጡትና ሌሎች ዘመን ተሻጋሪ ተውኔቶች ላይ በአብዛኛው ተሳትፋለች።
ዓለምጸሐይ፤ በመድረክ ላይ በወከለቻቸው ገጸባሕሪያት ሁሉ በሚያስደንቅ ጥበብ በመጫውት ተግባሯ ትታወቃለች።በትረካ ተውኔቶች ባከገር፣ በክላሲካል ድራማዎች ሙሉ በሙሉ በግሩም ሁኔታ እንደተካነች ይነገርላታል።
ከአራት መቶ በላይ የዘፈን ግጥሞችን ሰርታለች። ከእነዚህ ውስጥም አንዳንዶቹ እንደ ብሄራዊ መዝሙር የሚዜሙ ናቸው። በገጣሚነቷ ማረፊያ ያጣ ችሎትና የማታ እንጀራ የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትን አበርክታለች። ይህንን ያደረገችው በአገር ቤት እያለች ነው። ብሔራዊ ቴአትር ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶችና በባለሙያነት ሠርታለች። በዓለም አቀፍ የቴአትር ተቋም በኢትዮጵያ ጸሐፊ በመሆን አገልግላለች። በባህል ሚኒስቴር የህጻናት ቴአትር ኃላፊ በመሆን አገልግላለች።
በተለይ በኢትዮጵያ የህጻናት ቴአትር ጅማሬ ላይ አለምጸሐይ የአምበሳውን ድርሻ ተወጥታለች። ይሄ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የህጻናት ዝማሬ ላይም እንዲሁ ብዙ አሻራ አሳርፋለች።
ከዚህም ባሻገር ባለፉት 30 ዓመታት ከኢትዮጵያ ወጥታ በሰሜን አሜሪካ ስትኖር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሥነ ጥበብንና ባህልን ሊያስተዋውቁና ሊያስፋፉ የሚችሉ በርካታ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች። በዚህም መሠረት በሰሜን አሜሪካ የጣይቱ የባህል ማዕከልን አቋቁማለች። እንኳን ግለሰብ በመንግስት ደረጃ ትልቅ አቅም ሊጠይቅ የሚችሉ ሥራዎችን ስትሰራ መቆየቷም ይታወቃል።
በጣይቱ ባህል ማዕከል አማካኝነት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሮችን አዘጋጅታለች። አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶችን በማሰናዳት አነቃቂ ንግግሮችን አድርጋለች። የበቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በማውጣት በዋሽንግተን ዲሲ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ቤተ መጻህፍትና የጥናት ማዕከል አቋቁማለች። በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከዛም አልፎ ጥቁር አፍሪካዊያን እንደ ቤታቸው የሚቆጥሯቸውንና የሚሳተፉባቸውን መድረኮች ማመቻቸት ችላለች።
አሁን ደግሞ አገር አቀፍ ራእይዋን ለማሳካት እየሰራች ትገኛለች። ከህዝቧ ጋር በመሆን ከዳግማዊ ምኒልክ ሀውልት አጠገብ የቀድሞ አራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ውስጥ ያለውንና 117 ዓመት ያስቆጠረውን የቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል መኖሪያ ቤት ቅርስነቱን እንደጠበቀ አስጠግኖ ለባህል ማዕከል እንዲያገለግል በመስራት ላይ ትገኛለች።
የእርፍት ውሎ
ለነገሮች ስስ በመሆኗ የምትስቀውን ያህል እምባም ያጠቃታል። ኪነ ጥበቡን ይዛ በስደት አለምን ዞራለች።በዚህ መንከራተት ውስጥ በህይወቷ ላይ ብዙ ጫናዎች ደርሰውባታል። ጥበብ ቀናዒ ናት ስትባል ብቻነትን ትፈልጋለችና አለምጸሐይም ብቻዋን ጊዜ ወስዳ ህዝብ ከሚያውቀው የመድረክ ላይ ጀግና በተጨማሪ አገሯን በከፍታ ላይ ሊያስቀምጡ የሚችሉ በጎ ተግባራትን ሰርታለች። በተለይ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ።
ለነፍሷ ደስታን የሚሰጡት የእረፍት ጊዜ ክዋኔዎቿ ማንበብና መጻፍ ናቸው። የማንበብ ፍቅሬ ተአምር ነው የምትለዋ አርቲስቷ፤ ድካም ከበዛበት ሥራ በኋላ ቢያንስ ሁለት ገጽ ማንበብን የግድ ብላ ከንባብ ጋር መቆራኘቷን ትናገራለች። ከዚህ ባሻገር በተለይ ሲከፋት ተቀምጣ ከነ እምባዋ ትጽፋለች። ይህ ስሜት እንደ ትንፋሽ ይወጣልኛል ነው የምትለው። የምትተነፍሰው ደግሞ ስትጽፈው ነው።
የኪነ ጥበብ ሱሰኛ ሆና በመፈጠሯ አንዳንድ ጊዜ ለፈጣሪ የደብዳቤ ይዘት ያለው ጽሁፍ ሳይቀር ትጽፋለች። ሰርታ የጠገበች ስለማይመስላት የእረፍት ጊዜ ሊሆናት የሚገባውን ጊዜ በራሱ ለዚሁ ሙያ ታውላለች። የእንቅልፍ ሰዓቷን ሳይቀር ቀንሳ ነው ሥራ የምትሰራው። አለምጸሐይ በንዴቷም ሆነ በደስታዋ ወቅት ከንባብና ጽህፈት ባሻገር ሙዚቃ ትሰማለች። ፊልሞችንም እንዲሁ ትመለከታለች።
መልዕክት
“ኢትዮጵያ ከምናውቃት በላይ ትልቅ አገር ናት። የዛኑ ያህል ከነገስታቶቻችን ጀምሮ የውጭ ጠላቶቿ ኃይለኞች ናቸው። በወራሪዎችና ከኋላ ባሉት መርዞች ደግሞ ውስጣችን የገባውን የመከፋፈልና የጥላቻ ጽንስ ልብ ያለማለት ነገር አለ። ማን ከኋላ እንደሚገፋን አናስበውም፤ ማን የህች አገር እንድትፈርስ እንደሚመኝ ስለማንረዳ ነው እንጂ እንኳን ለትውልዷ ለሌላ ትውልድ የሚበቃ ታሪክ አለን። የሚያኮራ ነገር አለን። ቋንቋችን፣ አልባሳታችንና አጠቃላይ ብዝኃነታችን ውበት እንጂ መጠቃቂያችን መሆን የለበትም” ስትል አለምጸሐይ ለትውልዱ ከአደራዋን ጭምር መልእክቷን ታስተላልፋለች።
በተለይ ትውልዱ በእርጋታ እንዲያስብና ከመለያየት የሚገኝ ውጤት እንደሌለ በማሰብ የጋራ ህብረት መፍጠር እንዳለበት ትመክራለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013