ጨረፍታ ከሰለሞን ደሬሳ

‹ሰለሞን ደሬሳ› ሲባል ብዙዎቻችን በብዙ ዓይነት እናውቀዋለን:: አንዳንዶች ‹ሞገደኛ ጸሀፊ ነው› ይላሉ:: እንዲህ የሚሉት ብዕሩ ይዞ በመጣው አንድ አዲስ ዓይነት የአጻጻፍ ስልትና በጽሁፎቹም ሽንጡን ገትሮ መሞገት፣ ለምን? እያለ መጠየቅ፣ ‹አይሆንምን ትተህ ይሆናልን ያዝ› ዓይነት ፍልስፍና አራማጅ ነው:: በብዙ ነገሮቹም አንዳንዴ ጥያቄን፣ አንዳንዴም አግራሞትን የሚያጭር ብዕረኛ ነው:: አፈንጋጭነቱም ሆነ በሥነ ጽሁፍ ዓለም የታወቀበት ማንነቱ ግን ከአንድ የተለየ ምስል ጋር አዋዶታል:: እርሱ ግን ሁልጊዜም እንዲህ የምትል ፍልስፍና አለችው “ኪነ ጥበብ ለኪነ ጥበብነቱ” በቃ፤ በዚህችው መርህ ነው የሚጓዘው::

ሰለሞን ሙያው ምን ነበር? ብሎ እርሱን በአንዲት ቦታ ወይንም በውስን ስፍራዎች ማስቀመጥና መለካት ያስቸግራል:: በብዙ የድርሰት ሥራዎች አድናቆት የተቸረው ደራሲ ነው:: ሰለሞን ጋዜጠኛም ነው:: ከጋዜጠኝነቱ ጎን መምህርነትም አለበት:: ከራሱ ሥራዎች ተሻግሮ ሥነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ለብዙዎች መንገድ ጠቋሚ የሆነ ሀያሲ ነው:: በሥነ ግጥም አጻጻፍ ውስጥ ከነበረውና ከሚታወቀው ወጣ ብሎ የራሱን አዲስ ዓይነት መንገድ ያሰመረ ገጣሚ ነው:: ታዲያ በእነዚህ ሁሉ ያለፈው ሰለሞን ደሬሳ ‹ፈላስፋም› ጭምር እንደሆነ ይነገርለታል:: ‹ፈላስፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ገጣሚ መምህር ሀያሲ ሰለሞን ደሬሳ?› ብለን እንጠራው እንደሆን እንጃ…

ሰለሞን ደሬሳን ያበቀለች ለም አፈር ብዙ የጥበብ ልጆችን ያፈራችው የወለጋ አፈር ናት:: በምዕራብ ወለጋ ዞን ለጊምቢ ቅርብ በሆነችው ጬታ መንደር ውስጥ ነው:: ፋሽስቱ ኢትዮጵያን በወረረበት በ1930ዓ.ም ነበር የተወለደው:: ወላጅ አባቱ አቶ ዳንኪ ላንኪ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ የሺመቤት ደሬሳ አመንቴ ናት:: ታዲያ ሰለሞን መጠሪያው በእናቱ አባት ነው:: እንዲህ ብለን ብቻ እንዳናልፈው እዚህ ጋር ቤተሰቡ እንደ ኦዳ ካለ ትልቅ የታሪክ ዛፍ ስር የተቀመጠ ነው:: አያቱ(የእናት አባት) በጊዜው በሀገራችን ከነበሩ ጥቂት ምሁራን አንደኛው ናቸው:: በ1930ዎቹ በግብርና ሚኒስቴር ዳይሬክተር ነበሩ:: አባታቸው የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ገዢ ነበሩ:: ልጃቸው ይልማ ደሬሳ (የሰለሞን አጎት) በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በንግድና በትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ነበሩ:: በትልቁ የሚታወቁበት “የኢትዮጵያ ታሪክ በ16ኛው ክፍለ ዘመን” የሚለው መጽሐፋቸው ነው:: ሌላኛው አምባሳደር ብርሃኔ ደሬሳም አለ:: የይልማ ደሬሳ ልጅ የሆነችው ሃና ይልማ ደሬሳ ደግሞ፤ የሰለሞን ጓደኛ የነበረው የስብሃት ገ/እግዚአብሄር የመጀመሪያ ባለቤቱ ናት::

ጩታ ላይ የተወለደው ሰለሞን ደሬሳ፣ እዚህች የትውልድ መንደሩ ውስጥ ልጅነቱን የመቦረቅ ዕድሉን ግን አላገኘም:: ምክንያቱ ደግሞ፤ አዲስ አበባ ያሉ ዘመዶቹ ሊያስተምሩና ሊያሳድጉ ከወላጆቹ ተቀብለው ያመጡት ገና የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር:: አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ዕድሜው ለትምህርት ብቁ ሲሆን ትምህርት ቤት ገባ:: ቅሉ ሰለሞን ገባ እንጂ ትምህርቱ ግን አልገባ ብሎት ነበር:: እርሱም እንዳለው በልጅነቱ ያልዞረበት ትምህርት ቤት አልነበረም:: መድኃኒያለም፣ ዊንጌት፣ ተፈሪ መኮንን… እያለ ካልተጠበቀበት ደረሰ:: ታዲያ እንዲያ የስንፍናን ዳውላ የተሸለመ የመሰለው ሰለሞን ደሬሳ፣ ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የገባው በ16 ዓመቱ መሆኑን ስናውቅ መገረም አይጠፋም:: ከግጥሞቹ አስቀድሞ ብዙዎችን ያስገረመበት ነገር ምናልባትም ይኸው ይሆናል:: ዊንጌት በነበረበት ሰዓት ግን ከነ አሰፋ ገብረ ወልድ ጋር በመሆን የትምህርት ቤቱን መጽሄት ያዘጋጁ ነበር:: ዩኒቨርሲቲ በቆየባቸው ጊዜያትም የኮሌጁ መጽሄት አዘጋጅ ነበር:: በአንድ ወቅት ፍቅር ይዟት በፍቅር እፍ ላለች ለአንዲት ወጣት ግጥም ጽፎ፣ ለጻፈበትም የአሥር ሳንቲም ክፍያ አገኘ፤ በብዕሩ ፍቅርን የማለደበት ይህ ግጥሙ ለርሱም የመጀመሪያው ነበር::

ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ለመማር ያሰበውና የጀመረው በሥነ ጽሁፍና ፍልስፍና ትምህርት ክፍል ውስጥ ነበር፤ ለመግፋት ግን ሳይሆንለት ቀረ:: በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚገባበትን አጋጣሚ ስላገኘ ነበር:: በሬዲዮ ጣቢያው በዜና አንባቢነት ጀምሮ ከሦስት ወራት በላይ አልዘለቀም:: ምክንያቱም ወደ ውጭ ሀገር የሚወስደው የትምህርት ዕድል መጣለት:: ድምጹን አየር ላይ ማዋል ከመጀመሩ ራሱም በአየር ሄደ:: ሻንጣውን ሸክፎ ወደ ፈረንሳይ ሀገር አቀና:: ሰለሞን በፈረንሳይዋ ቱሉስ ውስጥ ትምህርቱን እየተከታተለ፣ በጎን ደግሞ በፓሪስና ሲያሰኘው በሌሎች የአውሮፓ መንደሮችም ጎራ እያለ መዝናናት ይወድ ነበር:: ዳሩ እዚያ ብቻ ሳይሆን እዚህ በዩኒቨርሲቲ ሳለም፣ እንደ ወንድሞቹ ከነበሩት ሁለቱ ወዳጆቹ፣ ከተስፋዬ ገሠሠና ስብሐት ጋር አብረው ብዙ አሳልፈዋል:: “ሲመሽ ሁላችንም ወደ አንድ ሰፈር ነበር የምንሄደው…ውቤ በረሃ::” ከውቤ በረሃ የሌሊት ወፎች መካከል አንደኛዎቹ ነበሩ::

ልክ እንደምንጽፈውና እንደምናወራው ቀላልና ፈጣን ባይሆንም፤ ሰለሞን ደሬሳና ፈረንሳይ ግን እጅና ጓንት ነበሩ ማለት ይቻላል:: የርሷን ባናውቅም ለርሱ ግን እጅግ ተመችታው ነበር:: የኋላ ኋላ ለደረሰበት የስኬት ደረጃ የፈረንሳይ እጆች የገዘፉ እንደሆኑም ጭምር ያወራላታል:: ሰለሞን እንዴትና በምን መንገድ ሊገናኛቸው እንደቻለ አጭርና ግልጽ መንገድ ባይኖርም፤ በጊዜው በአሜሪካ እውቅ ከነበሩት ቸስተር ሃይመስ እና ጀምስ ቦልድዊን ከተባሉት ሁለቱ ደራሲያን ጋር በፈረንሳይ ወዳጅነት ገጥመው ነበር:: ከእነርሱ ወገንም ሆነ ከሌላ በኩል ከብዙ ሙዚቀኞችና ሰዓሊያን ጋርም ቅርርብ መፍጠር ችሎ ነበር:: አኗኗር በተለይ አዋዋል ብዙ የሕይወት ለውጦችን ያስከትላልና የሰለሞን ጥብብ ከእነዚህ ውስጥ ሁሉ ትንፋሽ ተጋርቷል:: ከእነዚህ እውቅ የጥበብ ሰዎች ጋር መዋሉ ብቻ ሳይሆን በነበረው ተዝናኖት ወዳድነቱ ሲያደርጋቸው የነበሩ የስዕል ጋለሪዎችና መሰል የሥነ ጥበብ ጉብኝቶቹ ትልቅ ዐሻራ አኑረውበታል:: የሥነ ጥበብ ሃያሲነቱ ከሳለፋቸው ምልከታና ቅኝቶቹም ጭምር ያገኘው ነው:: የፈረንሳይ አድባር ቀንታው ነበርና ግጥም በፈረንሳይኛ ጽፎ ገሚሱ ለህትመት በቅተውለታል:: “በኔ ላይ ተጽእኖ ያሳደረብኝ የፈረንሳይ ሥነ ጽሁፍ ሳይሆን ፓሪስ መኖሬ ነው” አለ፤ ውስጡን ስለፈነቀለው የጥበብ ቅንጣት ሲናገር::

ሰለሞን ፈረንሳይ ሲደርስ ገና 20 ዓመቱ ነበር:: ከሚተዋወቃቸውና አብሮ ከሚውላቸው አንስቶ እንቅስቃሴዎቹ ግን ከዕድሜው የተሻገሩ ነበሩ:: “… እንዲያውም ላንድ ኢቫንጋርድ የፈረንሳይ ጋለሪ ማንም ሳይሾመኝ ስዕል አውቃለሁ ብዬ ገብቼ እንደ አማካሪም ሆኜ፤ ያኔ የመረጥኳቸው ሰዓሊዎች አሁን በዓለም የታወቁ አሉ:: …ከፈረንሳይ ጸሀፊዎች ጋርም ያለ እድሜዬና ያለ እውቀቴ እኩል ገብቼ ዋልኩኝ” ብሎም ነበር በአንድ ወቅት:: ሰለሞን ፈረንሳይ ውስጥ የነበረውን ሕይወት በጥቅሉ ስንመለከተው፤ አንድ የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝቶ እንደሄደ ተማሪ አነበረም:: ምናልባትም እንደ አንድ ቱሪስት አሊያም እንደ አንድ ዝነኛ ሰው ነበር ኑሮው:: ይህን ሁሉ ለማድረግ መቼም በአንድ ተማሪ ኪስ የማይታሰብ ነውና ብንጠይቀውስ? “ገንዘብ ብዙ አልነበረኝም:: በተለይ መጨረሻው ላይ ምንም አልነበረኝም:: ከትሬንታ ላይ ሌሊት ሌሊት አትክልት እያወረድኩ ነበር የምኖረው:: ግን አንድ ሳንቲም ኪሴ ሳይኖር እንደሚሊየነር ልጅ ነው ፓሪስን የኖርኩባት” ነው ምላሹ፤ ሌላኛው የሰለሞን ጥበብ ይሆናል::

እስካሁን ብዙ ነገሮችን እየጀመረ መጨረሻውን ለመድረስ የተሳነው ሰለሞን የጀመረውን የፈረንሳይ ትምህርቱንም ሳያከትም እብስ አለ:: ምክንያቱ ደግሞ ጓደኛው እስክንድር በጎሲያን አሜሪካ ውስጥ ሊያገባ ነው:: እርሱ ደግሞ ከሚዜዎቹ አንደኛው ነበርና ‹ደህና ሰንብች አውሮፓ!› ሲል ጥሎ አሜሪካ ገባ:: አሜሪካ እንደ ፈረንሳይ እንስፍስፍ ባትሆንለትም የምትጎረብጥ ግን አነበረችም:: ከሠርጉ በኋላ እዚያው ከዚያው እያማተረ የራሱን ብዙ መንገዶችን ለመቅደድ ሞክሯል:: ወደ ካሊፎርኒያ ግዛት ካመራ በኋላ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አማርኛን ማስተማርም ጀምሮ ነበር:: እዚያ ከነበረው ወዳጁ ጌታሁን አምባቸው ጋር ሆነው ድምጻቸውን በቴፕ እየቀዱም አማርኛ ቋንቋን ማስተማር ጀመሩ:: በዚያ ሆኖ ካበረከታቸው የሚነገርለት አንደኛው “ኢትዮጵያን ዲክሽነሪ” በተሰኘው የአማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃል ነው:: ከእርሱ ጋር ለ12 ሆነው ያዘጋጁትና ትልቅ ፋይዳ የነበረው ነው::

ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ መንግሥቱ ለማ እና ዮሐንስ አድማሱ በአንድ ወቅት ከሰለሞን ጋር በጣም የቅርብ ነበሩ:: ያገናኛቸው ድልድይም የሥነ ጽሁፍ ነበር:: እዚህ የብዕር ጀመአ ውስጥ የነበሩትን እያንዳንዱን ስንመለከት ‹እዚህ ማዶ› እና ‹እዚያ ማዶ› ልንላቸው የምንችላቸውና ሁሉም የየራሳቸው ቀለም ያላቸው ናቸው:: ታዲያ በዚህ ልዩነት መካከል እንደምን ተቻቻላችሁ አያስብልም ይሆን? “…ሳናስብበት ልዩነታችንን ተቀብለን የምንናበብ ይመስለኛል::” የሰለሞን የአሜሪካ ኑሮ ከሥነ ጽሁፍ ሥራዎች ያራቀው እንደነበር አልሸሸገውም ነበር:: “ሥነ ጽሁፍን ማስተማር እንጂ ለመጻፍ አልሆነም ነበር፤ ለምን እንደሆን አላውቅም” ይል ነበር:: አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈውም በመምህርነቱ ነበር::

የኋላ፤ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ምክንያት የሆነው ቀደም ሲል በ3 ወር ተሰናብቶት የሄደው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነበር:: በ1961ዓ.ም ጣቢያው አውጥቶት በነበረው የቅጥር ማስታወቂያ ፈተናውን አለፈና ከኢትዮጵያ ፈረንሳይ-ከፈረንሳይ አሜሪካ- ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ሦስት ማዕዘን ሠርቶ መጣ:: በኢትዮጵያ ሬዲዮም ከ1961ዓ.ም እስከ 63ዓ.ም ለሁለት ዓመታት ከሠራ በኋላ፤ ከ1963-64ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለአንድ ዓመት ቆይቷል::

ሰለሞን ደሬሳ በፈረንሳይ እና አሜሪካ ካሰባሰባቸው ተሞክሮና ልምዶቹ ጋር በሥነ ጽሁ ፍ አንድ ሰፋ ያለ መንገድ እንዲጀምር ራሱን ያካበተበት ትልቁ ስፍራ ጋዜጦችና መጽሄቶች ነበሩ:: በመነን መጽሄት ይጽፍ ነበር:: ‘ኢትዮጵያን ኦብዘርቨር’ ላይ በእንግሊዝኛ እየጻፈ ታትመው የወጡለት ሥራዎቹ ቀላል የሚባሉ አልነበሩም:: በአዲስ ሪፖርተር ላይም እንዲሁ ይሠራ ነበር:: ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ከብዕሩ ጋር ሲጎበኛቸው የነበሩ ህትመቶች ለደረሰበት ኃይልና ጉልበት ናቸው:: እኚህን መሰል ጉዞዎቹ ውስጡ አንድ ነገር ሽው ሳያደርጉበት አልቀሩም:: በጋዜጣና መጽሄት ላይ ያወጣቸው በነበሩ በተለይ የግጥም ሥራዎቹ ውስጥ ፈራ ተባ እያደረገ በጥቂት ጥቂቱ ኋላ ላይ የታወቀበትን የአጻጻፍ ስልት ይሞካክር ነበር:: ብዙ እየጻፈ ብዙ ልምድ ሲያካብት ግን ደፈር ብሎ ከመጽሐፍ መሃል ፈለቀቀው::

1964ዓ.ም ያሳተማት “ልጅነት” የተሰኘች የግጥም መድብል፣ ገጣሚው ሰለሞን ደሬሳ የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ አድርጋለች:: መድብሏ በሥነ ጽሁፍ ቤት ውስጥ ውዝግብ የፈጠረችም ጭምር ነበረች:: በግጥሞቹ አጻጻፍ የተማረኩና አንዳንዶች አድናቆትን አጎረፉለት:: በሌላ ወገን ደግሞ በተቃራኒው በትችት አብጠለጠሉት:: ‹የግጥም አወራረድ አበላሸ፣ ከፈረንጅ ያመጣው ነው› የሚሉም ወረዱበት:: አንዳንዶችም ‹ሱሪያሊስቶቹን ገልብጦ ነው› አሉ:: መሃል ላይ ቆሞ የሁሉንም ሲሰማ የነበረው ሰለሞን ደሬሳ ግን በአድናቆት ኩራትም ሆነ በትችት ፍርሃት ሳይንገዳገድ በራስ መተማመን ነበር:: “ለኔ እንደሚሰማኝ በስድ ንባብ የተጻፈው እንዲገባን፣ በግጥም የተጻፈው እንዲሰማን ነው” ይላል::

በ1991ዓ.ም ወደ ሀገር እንደተመለሰ ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “…እኔ በወጣትነቴ የጻፍኳቸው ለምሳሌ ልክ የዚህን ኮት እጅጌ አውልቄ ብሰበስበው እንዳለው ዓይነት ነው፤ ውስጡ ወደ ውጭ ይገለበጣል:: እኔም እንዲሁ ውስጤን ወደ ውጪ ለመገልበጥ ነው የሞከርኩት:: ልብ ማበጥ አይደለም…እኔ ድሮ ልዝብ ጥጋብ ነበረብኝ:: ሁለተኛ ደግሞ በቃ ያንኑ ከመደጋገም እስቲ አዲስ ነገር ደግሞ እንጨዋወት ከሚል የመጣም ይመስለኛል” ብሎ ነበር፤ ስለእነዚያ ‹አመጸኛ› ግጥሞቹ ሲናገር:: ብዙሃኑ የመቻሉን ጥግ በአድናቆት የሚገልጹት ቢሆንም፤ ዛሬም ድረስ ግን በርሱ የግጥም አጻጻፍ የጋራ ስምምነት መፍጠር ያልቻሉ አሉ::

“ዘበት እልፊቱ ወለሎታት” የተሰኘችውና በ1992ዓ.ም የታተመች ሁለተኛው የግጥም መድብል ናት:: በህትመትም ሆነ በሌላ ጎልተው ለመውጣት ያልቻሉ በርካታ የግጥም ሥራዎቹ ከየቦታው ተበታትነው እንደቀልድ እንዳመለጡት ብዙ ጊዜ ተናግሮ ነበር:: የአጫጭር ልቦለድ እና የተውኔት ሥራዎችም ነበሩት:: ስሙን ደማቅ ያደረጉ ሦስት የተለያዩ መጻሕፍትም አሉት:: በአብዛኛው ግጥሞቹ ውስጥ የምንመለከተው ‹ወለሎታት› የኦሮሚኛ የግጥም ስልት ሲሆን ቤት መድፊያ ፊደላቱ የማይመሳሰሉ በመሆናቸው ቤት አይመቱም:: እርሱም ይህንኑ አጻጻፍ ነበር ከአማርኛው ስልት ጋር ያዳቀለው::

ሰለሞን ደሬሳ በ1966ዓ.ም አካባቢ አሜሪካ ነበር:: የፖለቲካው ትኩሳት በጋለበት በዚያን ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ልሂድ አልሂድ እያለ ከራሱ ጋር ሲሟገት ነበርና በመጨረሻ “ደርግ መጣ እኔም አሜሪካ ቀረሁ” አለ:: ከዚህ በኋላ የሀገሩን አፈር የረገጠው ከ17 ዓመታት በኋላ ነበር:: የደርግ መንግሥት ገብቶ የደርግ መንግሥት ሲወጣ ነበር የተመለሰው:: ከመጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥበብ ቤተሰብና አድናቂዎቹን የተገናኘውም በ1991ዓ.ም ብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ውስጥ ነበር::

እንግዲህ ሕይወት ማለት የዛፍ ላይ መሰላል ማለት ናት:: አፈር ሆነው ከተፈጠሩበት አፈር ላይ አንስታ ከኑሮ ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ታደርሳለች:: ቅሉ ሁላችንም የምንወጣው አንድ ዓይነት ዛፍ አለመሆኑ ነው፤ የወይን፣ የማንጎ፣ የኮክ፣ ግራር፣ ወይራ፣ ባህርዛፍ…የሚያፈራ ወይንም የማያፈራ:: ሕይወት ከገፈተረችን መሰላል እንወጣለን፣ በቅርንጫፎቹ ዞር ዞር ብለን ተንጠላጥለንም ግራር ከሆነ ስነወጋ፣ ኮክም ከሆነ ስንበላው፤ ተንሸራተን ድንገት ካልተዘረርን ግፋ ቢል እስከ እርጅና እንዘልቃለን:: ቅሉ የወጣንበት ዛፍ ምን ቢረዝምና እስከ አናቱ ብንወጣ ከምድር ቢያርቅ እንጂ ከሰማይ አያደርስም:: እናም ዞሮ ዞሮ ከመሬት ከአፈሩ ነው:: ‹ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን› ብንል የምናልባት ነውና ለሁሉም አይሳካ ይሆናል:: ‹አፈር ነበርን አፈርም እንሆናለን› የሚል መጨረሻ ግን ለሊቅ ለደቂቁ የተጻፈ ነውና ፈላስፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ገጣሚ መምህር ሀያሲው ሰለሞን ደሬሳ መጨረሻው ይኸው ነበር::

በአሜሪካ የሚኒሶታ ግዛት ውስጥ ለረዥም ጊዜ ህመም ይዞት በሕክምና ሲታገል ቆይቶ ነበር:: ከተጣመደው በሽታ ክብደት የተነሳ የአልጋ ቁራኛ እስከመሆን ደርሶም ነበር:: ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ግን ከዚያች የኑሮ ዛፉ ላይ የሕይወት መሰላሉን እየረገጠ በክብር ወረደ:: የ80 ዓመት አዛውንት ሆኖ ወደ አፈሩ ሲገባ ዕድሜውን ሳያባክን በተሰጠው ጥበብ ሠርቶና ብዙ አፍርቶ ነበር:: “ገላና” እያለ ከሚጠራት አሜሪካዊቷ ባለቤቱም የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር:: “…የጠና የሀገር ፍቅር እንዳለኝ አይረሳ:: …ለመጻፍና ለመግጠም ስነሳ ደግሞ በልበ ሙሉነት መጻፍ የምችለው ስለ ኢትዮጵያ ነው:: ኢትዮጵያውያንን እወዳለሁ:: … ከመሞቴ በፊት ኢትዮጵያ መኖር እፈልጋለሁ:: ስሞት ግን የትም ብቀበር ቁብ የለኝም” እንዳለውም ግብዓተ መሬቱ የተፈጸመው በዚያው በሚኒሶታ ነበር:: “ቢሮክራሲ አልወድም፤ ከሞትኩ በኋላ እንኳን ገነት ለመግባት ‹ለጴጥሮስና ጳውሎስ ማመልከቻ አስገባ› ምናምን ብባል አይስማማኝም::”

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You