ኢትዮጵያውያን በነፃነታቸውና በሉኣላዊነታቸው ተደራድረው አያውቁም፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ ያኔ ምዕራባውያን መላውን ጥቁር ህዝብ ለማስገበርና ለም መሬታቸውን ለመቀራመት በተንቀሳቀሱበት የቅኝ ግዛት ዘመን እንኳ ኢትዮጵያ እጇን ያልሰጠች አገር ከመሆኗም ባለፈ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦችም የይቻላል መንፈስን ያላበሰችና የትግልን ወኔ ያስታጠቀች የነፃነት ተምሳሌት ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ አድዋ ሕያው ምስክር ነው፡፡
ይህ የተጋድሎ ታሪክ ታዲያ ከዚያ ወዲህም ቢሆን ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም፡፡ ሁሌም ቢሆን ለጥቅማቸው ሲሉ አፍሪካን የሚፈልጓት ብዙዎቹ ነጮች ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልማሱት ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ለዚህ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱና ዋነኛው ደግሞ በኢኮኖሚ ማዳከም ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወታደራዊ ጡንቻቸውን በማሳረፍ እና እርስ በርስ በማባላት እነሱ የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ለማድረግ የሄዱበት ሴራም ይጠቀሳል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለዚህ ሴራ ምቹ ሆና አታውቅም፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በየዘመኑ የመጡ መሪዎች የየራሳቸው ልዩነትና ባህርይ ቢኖራቸውም ለውጭ ሃይል የሚንበረከኩ አይደሉም፡፡ በተለይ የራሳቸውን አጀንዳ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን የሚፈልጉ ሃይሎች ይህን ባለማግኘታቸው ኢትዮጵያን ስትራቴጂያዊ ጠላት አድርገው እስከመውሰድ ደርሰዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኢትዮጵያን እድገት የሚገቱ ስልቶችን በመጠቀም የማዳከም ስትራቴጂያቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት ሲታቀድ ድጋፍ ከመከልከል ጀምሮ ግድቡ ተግባራዊ እንዳይሆን የተካሄዱ ሴራዎችና በተለያዩ አጋጣሚዎች በውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ድጋፎችን ለመከልከል የተደረጉ ጥረቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡
በተለይ በሃገራችን የመጣውን ሁለገብ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት የአንድነት ተስፋ ያላማራቸው የውጭ ሃይሎች ካኮረፉ የውስጥ ሃይሎች ጋር በመመሳጠር በሃገሪቱ አለመረጋጋት እንዲፈጠርና እርስ በርስ ያለው መስተጋብር እንዲሻክር በማድረግ ሀገሪቷን ለመከፋፈልና ለማበጣበጥ የሄዱበት ስልት ብዙ ጉዳት አስከትሏል፡፡
ይህ አይነቱ ስራ ደግሞ መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልፅ እንደነበረው በህወሃት ጁንታ መሪነት ሲካሄድ የቆየ ነው፡፡ ለዚህም በአሁኑ ወቅት በዚህ ቡድን ላይ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶች ከሞላ ጎደል መቆማቸው ማሳያ ነው፡፡
ይሁን እንጂ መንግስት በሃገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን አቅም ሁሉ በመጠቀም ጫና ለማሳደር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት ትንኮሳ እስከመፈፀም የተደረሰበት መንገድም በግልፅ ታይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሱዳን እና ግብጽ አማካኝነት እየተፈፀመ ያለው ትንኮሳ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም ህወሃት በስልጣን ዘመኑ በተለያዩ የውጭ ሃገራት የሰገሰጋቸው አባላቱ አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያን ህልውና ከማይፈልጉ ሃይሎች ጋር በመመሳጠርና ሆን ብለው መረጃዎችን በማዛባት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ የሚጠቀሙት ደግሞ በዋናነት ሚዲያውን ሲሆን በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተቋማትንም በተለያዩ መንገዶች በማሳሳትና እነሱ በሚፈልጉት መንገድ በመንዳት በኢትዮጵያ ላይ ጫና አንዲያሳርፉ መድከማቸውን ቀጥለውበታል፡፡
ይህ ሁኔታ ሰርግና ምላሽ የሆናቸው የኢትዮጵያ ጠላቶችም አጋጣሚውን በመጠቀም አቅማቸውን አሟጠው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸትና በተለያዩ መንገዶች ጫና ለማሳደር የሚደረጉ ጥረቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሰሞኑን በፀጥታው ምክር ቤት የቀረበውና በቁርጠኛ የኢትዮጵያ ወዳጆች የተቀለበሰው አቋምም ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
እነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያ ለቀጠናውም ሆነ ለራሷ ሰላምና እድገት ከምታደርጋቸው መልካም ስራዎች ይልቅ በጥቃቅን ጉዳዮችና ሆን ተብለው በሚፈበረኩ የውሸት አጀንዳዎች ሲዳክሩ ይስተዋላሉ፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያካሄደውችን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በክልሉ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የነበረው የሃይል አቅርቦት እንዲስተካከል ተደርጓል፤ በጁንታው ወድሞ የነበረው የቴሌኮምና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው ስራ እንዲጀምሩ ተደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ጁንታው የፈጠረውን ጭለማ በመግፈፍ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል 135 ረጂ ድርጅቶች በክልሉ ተሰማርተው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገነዘቡና የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ ሰባት የውጭ ሃገር ሚዲያዎችም ትግራይ ገብተው እንዲዘግቡ እድል ሰጥቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የውጭ ሚዲዎች የሚያነሷቸው የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች በመረጃ ላይ ተሞርኩዘው እንዲጣሩ መንግስት ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ የመንግስት በጎ ስራዎች ለነሱ ቦታ የላቸውም፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በትግራይ የተፈጠረውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ብሎም በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት የራሳቸው የግል ፍላጎት ያላቸው ሃይሎችን ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ሁላችንም የበኩላችንን ሃላፊነት ልንወጣ ይገባል፡፡ “ውሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሎቹም ይጓዛሉ” እንዲሉ በተጀመረው የሰብኣዊ ድጋፍ፣ የልማትና አገርን የማዳን ዘመቻ ትኩረታችንን በማድረግ ወደፊት እንጓዝ፡፡ ለዚህ ደግሞ አንድነታችንንና ትብብራችን ወሳኝ ነውና ለጋራ ሃገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ እንስራ!
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም