ኃይሉ ሣህለድንግል
ዴሞክራሲ የህዝቦች ጥማት ነው።ይህን መሰረት በማድረግም ነው ሀገር ለማስተዳደር የፈለገ ሁሉ ዴሞክራሲ ፤ዴሞክራሲ ሲል የሚደመጠው። ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል ሳይጠራ የመንግስትን ስልጣን የተቆናጠጠ ፓርቲ ወይም ተመራጭ ያለ አይመስለኝም።አምባገነኑም ዴሞክራሲያዊውም ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ይላል።ሁሉም ቃሉን ለመጥራት ችግር የለበትም።
ለዚህ ደግሞ ከእኛው ሀገር ውጪ ሌላ ምሳሌ መጥቀስ አያስፈልግም።የንጉሳዊውን አገዛዝ አሻፈረኝ ያሉ ወገኖች ሁሉ ፍላጎታቸው አንድም የዴሞክራሲ ስርአት መሻት ነው።ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ፣ምርጫን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማካሄድ ነው ፍላጎታቸው የነበረው።ይሁንና በተማሪዎች የአመታት እንቅስቃሴ በወታደሩ ተቃውሞ የ1966ቱ አብዮት መጣ ።ወታደሩ ስልጣን ያዘ።
ሰዎች እንደልብ ሀሳባቸውን መግለጽ ያዙ።በርካታ የፓለቲካ ፓርቲዎችም ተፈጠሩ።እያደር የአመለካከት ልዩነት እየሰፋ ሲመጣ በሀሳብ ላይ በሚደረግ ክርክር ለመብለጥ ከመስራት ይልቅ መሳሪያ ማንሳት ተጀመረ፤አንዱ አንዱን መብላቱን ተያያዘው።መጀመሪያ ማን ተኮሰ የሚለውን እንተወውና በዚህ የፓርቲዎች ግብግብ ሀገር ውድ ልጆቿን አጣች።
ኢህአፓ ደርግን በአደባባይ ሲገድል፣ደርግ የጭቃ ጅራፉን አመጣና ይጨፈጭፈው ጀመር።የዴሞክራሲያዊ ስርአት ነገር አበቃለት።ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለው የደርግ መፈክር ከሰረ፤ ሀገር በደም ጎርፍ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ተፈጠረና አረፈው።
ሌሎች ፓርቲዎችም በደርግ ህልውናቸውን እያጡ ደርግ ለ17 አመታት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ቆየ።ደሞክራሲ ውሃ በላት።እንዲያም ሆኖ ታዲያ ቃሉ መጠራቱ አልቀረም።
የህዝብ ብሶት የወለደኝ ያለው ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ስልጣን ተቆናጠጠ።ኢህአዴግ በጦርነት አሸንፌ ብመጣም ስልጣን ማካፈል አለብኝ አለና /ውስጥ ውስጡን ለቄስ ቢሆንም/ የተለያዩ የፓለቲካ አስተሳሰቦችን ወክለናል ያሉ ወገኖች በሽግግር መንግስቱ እንዲሳተፉ ተደረገ።
ኢህአዴግም ዴሞክራሲያዊ ነኝ እያለ/ስያሜውም ዴሞክራሲ አለበት አይደል/ ጸረ ዲሞክራሲ በመሆን ሀገር ማስተዳደር ሳይሆን መግዛቱን ቀጠለበት።ኢትዮጵያውያን በመንግስታቶቻቸው ላይ አኩርፈውና አምጸው ያመጡትን ለውጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተበሉ።ኢህአዴግ ፓርቲዎችን ሁሉ አንዳንድ እያለ ከጨዋታ አስወጣቸው።አንዳንዶቹ ከሀገር ወጡ፤አንዳንዶቹ ህልውናቸውን አጡ።ዴሞክራሲ አሁንም የውሃ ሽታ ሆነች።
በምርጫ 97 የዴሞክራሲ ነገር ትንሽ ብልጭ ያለ መሰለ።የፓርቲዎች ተሳትፎ ፣የምርጫ ቅስቀሳው፣የድምጽ አሰጣጡ ፣በአንዳንድ አካባቢዎች በርካታ ድምጾች በተፎካካሪ ፓርቲዎች ተይዞ የነበረበት ሁኔታ፣ ወዘተ የዴሞክራሲ ጭላጭል የታየበት ነበር። ይሁንና በምርጫው ውጤት ስጋት ያደረበት ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት አምባገነንቱ አገርሽቶበት ሁሉኑም የተስፋ ጭላንጭል አዳፈነው።ዴሞክራሲ ወሬ ብቻ ሆኖ ቀረ።
ኢህአዴግ ጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዙን ቀጠለ፤አሁንም ተቃውሞ ገጠመው።ኢህአዴግ እየገደለም፣ እያሰረም፣ እየገረፈም ትግሉ ቀጠለ።ትግሉ በኢህአዴግ በራሱም ውስጥ ጭምር ሆኖ የዛሬ ሶስት አመት አዲስ ለውጥ ከተፍ አለ።ለውጡ እንዳለፉት ስርአቶች ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን እገነባለሁ የሚል ሆነ።ለፓለቲካ ሀይሎች ሁሉ ጥሪ ቀረበ።ይህን ተከትሎም በውጭ ሀገር የነበሩ የፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አክቲቪስቶች ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸው ወደ ሀገር ቤት ገቡ።ጫካ ገብተው መንግስትን ሲፋለሙ የነበሩት ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተመለሱ።በእስር ላይ የነበሩ የፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተፈቱ።
አንዳንድ ችግሮች ቢስተዋሉም ሰላማዊ የፓለቲካ ትግሉ ቀጥሏል።አዳዲስ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል።መንግስት ነጻ ዴሞክራሲያዊ እና እውነተኛ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ፈጥሯል።ምርጫ ቦርድን በአዲስ አዋቅሯል፤የምርጫ ህጉ ተሻሽሏል።ምርጫው ባለፈው አመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ ቆይቶ ዘንድሮ ሊካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በዚህ ውስጥ ሁሉ ግን አሁንም የዴሞክራሲ ጥያቄ ይነሳል። መንግስት ዴሞክራሲያዊ አይደለም የሚሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል።አንደ ፊቱ ነፍጥ አንግቦ ጫካ የገባም አለ።መንግስት ምርጫውን ማራዘም የለበትም በሚል ተቃውሞ የራሴን ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ምርጫ ያካሄደ ክልል የሚያስተዳድር ፓርቲም ተከስቶ ነበር ።
ምርጫውም ፓርቲውም ህገወጥ ነበሩና መንግስት መከረ ዘከረ በመጫረሻም ምርጫውም ፓርቲውም ህገወጥ ተብለው በሀይል ተወገዱ።
እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ስልጣን የተቆናጠጡት ሁሉ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ቢሉም መሬት ምንም ነገር የለም።ስለ ዴሞክራሲ ነጋ ጠባ የሚያነሱት ለምርጫ ውድድር ነው።ሜዳ ሲገቡ እና ስልጣን ለመያዝ ሲሉ ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል እንደ ማጣፈጫ ያልጠቀሱትን ያህል ስልጣን ላይ ሲቆዩ ሲያስቡት ይቀፋቸዋል።ከምርጫው በሁዋላ ስልጣን ይዘው ብቻ ሳይሆን ገና ምርጫው ሊካሄድ ባለበት ወቅት ነገሮች አላምር ሲላቸው ወይም ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ እንዳይባሉ ተብለው ወይም ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ እየሆነ የዴሞክራሲን ነገር ለመድረክ ፍጆታ ካልሆነ በቀር አይጠሩትም።
ያኔ ስለዴሞክራሲ ያላችሁትና እየተገበራችሁ የምትገኙት አይጣጣምም፤አምባገነን ሆናችሁዋል ሲባሉ ዴሞክራሲ በአንድ ጀምበር አይሰርጽም።እነ አሜሪካም ቢሆን 200 አመት ወስዶባቸዋል እያሉ ሊያረጋጉን ሞክረዋል።ዴሞክራሲ በገድብና ያለገደብ የሚል ነገርም ነበር።ያለገደብ ከሆነ ለሀገርም ለህዝብም አይበጅም ያሉም ነበሩ።
የሚያሳዝነው ግን ጧት ኮሶ ሲያጠጡ ዶሮ ማታ እንደሚሉት የባህላዊ ኮሶ መድሀኒት አጠጪዎች ስለዴሞክራሲ አስፈላጊነት እየሰበኩን አምባገነንነት ስር እንዲሰድ ያደረጉ ገዥዎችን አይተናል።በስንቶች የዴሞክራሲ ጥያቄ ላይ እየቆሙ፣ የሬት ፓለቲካቸውን ሊግቱን ሲሞከሩ አይተናል ።እነዚያ ታሪኮች አሁን መደገም የለባቸውም።
የዛሬ ሶስት አመት ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ መንግስት ምርጫ ለማካሄድ እየሰራ ነው።በመጪው ሰኔ ወር ምርጫው ይካሄዳል።ቅስቀሳዎች ተጀምረዋል።ፓርቲዎች እጩዎችን እያስመዘገቡ ነው።ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን ይጠበቃል።ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ጽኑ እምነት ስለመኖሩ የለውጡ መንግስት አስቀድሞ አስታውቋል።
መንግስት ብቻውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ አይችልም፡፤ምርጫ ቦርድ፣ፍርድ ቤቶች፣ፓርቲዎች ፣እጩዎች፣ደጋፊዎች፣መላ ህዝቡ ፣የሲቪክ ማህበራት ፣ወዘተ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ሚናቸው ጉልህ ነው።
ሁሉም ሚናቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው።የሀገሪቱን ህግ የምርጫ ህጉን አክብረው ሊሰሩ ይገባል።ጸረ ዴሞክራሲ እየሆኑ ስለዴሞክራሲ ማለም አይቻልም።በሰላማዊ መንገድ መታገል አለባቸው።በህግ ካልተንቀሳቀሱ መንግስት ህግ አንዲከበር ያደርጋል።ይህን ማድረግ ግን ጸረ ዴሞክራሲ መሆን አይደለም።የፓለቲካ ፓርቲዎችም መንግስት ከህግ አግባብ ውጪ ተንቀሳቅሷል ካሉም በሀግ አግባብ መጠየቅ አለባቸው።
ፓርቲዎች ስለ እውነተኛ ዴሞክራሲ አስቡ።ለእዚህም ፕሮግራማችሁን በሚገባ ቃኙት።በዚህ ወሳኝ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ይህን ፕሮግራም በሚገባ አስተዋውቁ ።
ይህን ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታው መሰረት ለማድረግ ሁሉም አጥብቆ መስራት ይኖርበታል።እንዳለፉት ዘመናት ምርጫዎች ወይም የመንግስት ለውጦች ዴሞክራሲ መሻታችን ሊበላ አይገባም።ሁሉም ነገር በእጃችን ነው።
መንግሰት ሆይ አደራ አለብህ።የዛሬ ሶስት አመት ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለማምጣት እንደምትሰራ አረጋግጠሃልና የመተግበሪያው ወሳኝ ወቅት አሁን ነው።ይህን የሰማ ህዝብ አደራ ጥሎብሃል።ቃልህን ጠብቅ! አደራ ላለመብላት ተጠንቀቅ!
ዴሞክራሲን ፍለጋ ብለን ብዙ ማስነናል።ብዙ መስዋእት ተከፍሏል።ብዙ ተስፋዎች ተሰንቀው መና ቀርተዋል።ሁሉም ፍሬያማ ሳይሆኑ እዚህ ተደርሷል።ይህ ታሪክ በምንም አይነት መልኩ መደገም የለበትም።
ይህን ታሪክ ለመለወጥ በሚያስችለው ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንገኛለን።ዴሞክራሲ ፍለጋው ዴሞክራሲን በማግኘት ማብቃት አለበት!!በቀጣይ ለዘመናት ስለተጠማነው ዴሞክራሲ እውን መሆን ሳይሆን አሁን የምንጨብጠውን ዴሞክራሲ ስለማጎልበት ነው መነጋገር ያለብን።
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም