ኢያሱ መሰለ
ሰዎች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ዳገት ይወጣሉ፤ ቁልቁለት ይወርዳሉ፤ አንዳንዶች በህይወት ጉዟቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶች አልፈው ለስኬት ይበቃሉ። አንዳንዶች ሰርቶ የመለወጥ ወኔያቸውን ገድለው ለችግርና ለድህነት እጅ ይሰጣሉ። አንዳንዶችም ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ኑሯቸውን ለማሸንፍ ይፍጨረጨራሉ። አንዳንድ ጊዜ አካል ጉዳተኞች ይሰሩታል ተብሎ የማይታሰብን ስራ እየሰሩ እራሳቸውን ለማኖር ሲጥሩ ይታያል። አይነ ስውር ሆነው ሎተሪ የሚያዞሩ፣ ዊልቸር ላይ ተቀምጠው ሸቀጥ የሚነግዱ አካል ጉዳተኞችን በየጎዳናው ላይ ማየት የተለመደ ነው።
የዛሬው እንግዳችን ለየት ያለ ነው። በልጅነቱ በደረሰበት ድንገተኛ የጤንነት ችግር ምክንያት በቀኝ እግሩና በቀኝ እጁ ላይ ጉዳት ደርሶበታል። አብዛኛውን የልጅነት ዘመኑን ጸበል በመመላለስና በህክምና አሳልፏል። የደረሰበት የጤና ችግር እንደልቡ ሊያንቀሳቅሰው ስላልቻለ ህይወቱን ፈታኝ አድርጎበታል። ያም ሆኖ የአካል እንቅስቃሴና ቅልጥፍና በሚጠይቀው የልብስ ስፌት ሙያ ላይ ተሰማርቶ እራሱን ለማኖር ይጥራል።
ይህ ታታሪ ወጣት ኑሮ ጠብ ባይልለትም ልብስ እየሰፋ ለእለት ጎሮሮው የምትሆን የእለት ገቢ ያገኛል። በየእለቱ የሚጠቀመውን የመድሃኒት ወጪም ለመሸፈን ይታትራል። በአንድ በኩል የሰው ጠባቂ ላለመሆን ይሰራል በሌላ በኩል ያቋረጠውን ትምህርት ይከታተላል። የወጣቱ ተሞክሮ ተስፋ ቆርጠው ለሚኖሩ ሰዎች ትምህርት ሰጪ በመሆኑ የአምዳችን እንግዳ ልናደርገው ወደናል።
አማኑኤል ይርጋ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ልዩ ስሙ ኮንጎ ሰፈር ነው። የኮንጎ ሰፈሩ ብላቴና እድገቱና ኑሮው ከአያቱ ጋር ነው። የስድስትና የሰባት ዓመት እድሜ ላይ እያለ ከአብሯደግ ጓደኞቹ ጋር እየቦረቀ ማደጉን እንደህልም ትውስታ ያስታውሰዋል።
በዚሁ የእድሜ ክልል እያለ የደረሰበት የጤና እክል ዛሬም ድረስ የህይወት ጉዞው እንዳይሰምር ተጽእኖ እንዳሳደረበት ይናገራል። ተጽእኖውን የመቋቋም ጽናቱን አጠንክሮ ኑሮውን ለማሸነፍ ከመታተር ግን አልቦዘነም። አማኑኤል በልጅነቱ ጤንነቱን ያጣበትን ክስተት እንዲህ ያስታውሳል።
አንድ ቀን እንደተለመደው ቀን ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ውሎ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቱ ገብቶ እራቱን በልቶ ይተኛል። ከሌሊቱ አስር ሰዓት አካባቢ በተኛበት ቦታ የንዝረት ስሜት ተሰምቶት ከእንቅልፉ ይነቃል። የቀኝ እግሩ እና የቀኝ እጁን ማንቀሳቀስ ይሳነዋል፤ ተነስቶ ለመቆም ሲሞክር ሰውነቱ ከድቶት ተዝለፍልፎ ይወድቃል፤ በሁኔታው የተደናገጠው ብላቴና የአያቱን እርዳታ በመፈለግ ድምጽ ያሰማል። እርሳቸውም መጥተው ምንም ሊረዱት ስላልቻሉ የሌላ ሰው እርዳታ ፈልገው ጎረቤቶቻቸውን ይጣራሉ። የመንደሩ ሰው ቢሰባሰብም ለአማኑኤል የሚሆን መፍትሄ ማምጣት አልተቻለም። አማኑኤል ራሱን ስቶ ተኛ።
አብዛኛው ሰው አማኑኤል ጸበል ቢሄድ ሊሻለው እንደሚችልና ህመሙ ከልክፍት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሀሳብ ይሰጥ ጀመር። በዚህን ጊዜ ቤተሰቦቹ ይዘውት ወደ ጸበል ይሄዳሉ። ለበርካታ ጊዜ የጠበል ክትትል አደረገ፤ ቀናት አለፉ፤ ወራት ተቆጠሩ፤ አመታት ነጎዱ፤ አማኑኤል የጤና መሻሻል አላሳይ አለ። ትምህርቱም ተቋረጠ። ከዚህ ችግር ሳይላቀቅ እድሜው ገፋ።
አማኑኤል እየተውተረተረም ቢሆን እራሱን ከጥገኝነት ለማላቀቅና ህይወቱን ለመምራት የሚያስችለውን አቅጣጫ ማማተር ጀመረ። ምን ሰርቶ መኖር እንዳለበት ከራሱ ጋር እየመከረ ባለበት ሰዓት አንድ ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያውቀው ጎረቤቱ ሙያ የመቅሰም ፍላጎት እንዳለው አማኑኤልን ይጠይቀዋል። እርሱም አቅሙ የሚፈቅደውን ሙያ ሁሉ ለመማር ፍላጎት እንዳለው ይገልጽለታል።
ይህ ቅን ሰው የስልጠና እድል እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ካመቻቸለት በኋላ አማኑኤል ‹‹በሰርቪስ አሎንግ ዘ ናይል ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ መስራች እደ ጥበብ ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ ማዕከል›› ገብቶ የልብስ ስፌት ቅድና ዲዛይን ስልጠና ወስዶ ይመረቃል። የሁለት ዓመት ስልጠና ሰጥቶት በቂ ሙያ ያስጨበጠው በጎ አድራጎት ድርጅት እንደገና የልብስ ስፌት ማሽን ሰጥቶት ወደ ስራ ያስገባዋል። የሲኦሲ ፈተና ወስዶም ያልፋል። አማኑኤል ማሽን ቢያገኝም የስራ ቦታ ስላላገኝ ለጊዜው እዚያው አያቱ መኖሪያ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ልብስ እየሰፋ መኖር ይጀምራል። ከስራው ጋር በደንብ እየተግባባ፤ የአካባቢው ሰውም እርሱ ጋር ማሰፋትን እየለመደ ይሄዳል። አማኑኤል በልብስ ሰፊነት ሙያው በሰፈሩ ሰው ይታወቃል።
አንድ እጁና አንድ እግሩ የማይታዘዙለት ሰው የእጅና የእግር እንቅስቃሴን በሚጠይቅ ሙያ ላይ መሰማራቱ ያስገረማቸው የሰፈሩ ሰዎች አማኑኤልን ያበረታቱታል። አማኑኤል ጥረቱ መና አልቀረም፤ የተትረፈረፈ ጥቅም ባያገኝም ለእለት ጉሮሮው የምትሆን ገቢ ማግኘት ችሏል።
የመኖሪያ ቤቱ ጥበት ለስራ ስላላመቸው ማሽኑን መንገድ ላይ አውጥቶ መስራት ይጀምራል። መንገድ ላይ መስፋት እንደጀመረ የደንበኞቹ ቁጥር እየጨመረ ይመጣል። ገቢውም መሻሻል ያሳያል። አማኑኤል መንገድ ላይ መስፋት በርካታ ፈተናዎች እንዳሉት ይናገራል፤ የስራ ቦታው ከመኖሪያ ቤቱ ከሰባ እስከ ዘጠና ሜትር ይርቃል፤ ሸራ ወጥሮ፤ መብራት ከቤቱ ጠልፎ ይሰራል። አንዳንዴ ዝናብ፤ አንዳንዴ ጸሀይ ስራውን ያውኩታል።
አብዛኛውን ጊዜ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ እየሰራ ሊያመሽ እንደሚችል ይናገራል። ሁልጊዜ ማታ ማታ ስራውን ሲጨርስ ማሽኑን ወደ ቤት ማስገባት ስለማይችል መኪና ለሚጠብቁ የሰፈሩ ሰዎች አደራ ሰጥቷቸው እዚያው ትቶት ይገባል። አማኑኤል በጤናው ጉዳይ ተስፋ ቆርጦ አያውቅም፤ ለበርካታ ዓመታት ጸበል ሲከታተል ከርሞ ለውጥ ያላመጣው ወጣት ከአራት ዓመት በፊት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ይጀምራል። በየቀኑ የሚያገኛትን ሳንቲም እየቋጠረ የተወሰነች ብር ለአያቱ የአስቤዛ ከሰጠ በኋላ ከዚያ የተረፈችውን ለህክምናው ያውላል።
የጤናው ችግር ደም ወደ ውስጥ በመፍሰሱ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነና ይህም በቀዶ ጥገና እንደሚስተካከል ሀኪሙ ከነገረው በኋላ የመዳን ተስፋ ያሳድራል። የተሰጠውን ተስፋ ይዞ ያጠራቀማትን ሰባት ሺህ ብር ለሲቲ ስካን እና ለኤም አር አይ ምርመራ ካወጣ በኋላ ግን የምርመራው ውጤት ቀዶ ጥገናው አስተማማኝ እንደማይሆን እንደውም ሌላ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ያመላክታል። ለተከታታይ አምስት ዓመታት በሳምንት ሶስት ጊዜ እየተመላለሰ ሲከታተል የነበረው ህክምና ውጤት እንደማይኖው ሲነገረው ማዘኑን አማኑኤል ይናገራል። አሁንም ግን ጥቁር አንበሳ እየተመላለሰ የታዘዘለትን መድሃኒት በመጠቀም ጤናውን ይከታተላል።
አማኑኤል ለመድሃኒት በወር ከሶስት መቶ እስከ አራት መቶ ብር ያወጣል። አንዳንድ ጊዜ መድሃኒቱ ተፈልጎ የሚጠፋበት አጋጣሚ እንዳለም ይናገራል። በዚህን ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ መድሃኒት ቤቶችን ሁሉ እንደሚያዳርስ እና ያልተጠበቀ ገንዘብ እንደሚያወጣ ይገልጻል።
ቃሊቲ አካባቢ በአንድ የግል ልብስ ስፌት ድርጅት ተወዳድሮ ስራ የማግኘት እድል አግኝቶ እንደነበር የሚናገረው ታታሪ ወጣት፣ ቦታው ከሚኖርበት ሰፈር የሚርቅ በመሆኑና ያለበት የጤና ችግር ርቆ ለመሄድ ስለሚያስቸግረው ለመተው መገደዱን ይናገራል።
በጤና ችግር እየተፈተነ ኑሮውን ለማሸነፍ የሚጥረው ታታሪ ወጣት ስራውን ለማስፋፋት አቅዶ እንቅስቃሴ ይጀምራል። የሚኖርበት ቀበሌ የስራ ቦታ እንዲሠጠው ያለበትን የጤና ችግርና የስራ ሁኔታ ያስረዳል። ቀበሌው ከሌሎች ሰዎች ጋር መደራጀት እንዳለበት ይነግረውና ይደራጃል።
ሽሮ ሜዳ ታክሲ መያዣው አካባቢ ጉንድሽ ህንጻ አምስተኛ ፎቅ ላይ የስራ ቦታ ይሰጠዋል። አማኑኤል ሌላ የልብስ ስፌት ማሽን በብድር ገዝቶ ወደ ስራ ይገባል። ነገር ግን እንዳሰበው አልሆነለትም። ካለበት የጤና ችግር አንጻር ፎቁ ላይ በቀን ሶስትና አራት ጊዜ መውጣትና መውረዱ ፈተና ይሆንበታል። ያም ብቻ ሳይሆን እዚያ ድረስ ወጥቶ ልብስ የሚያሰፋ ሰው ይጠፋና የቀን ገቢው ይቀንስበታል።
ወረዳው የጤና ችግሩን ተመልክቶ ምድር ላይ ቦታ እንዲቀይርለት ቢማጸንም የሚሰማው አላገኘም። እስከ ተወሰነ ጊዜ ሞክሮ ለውጥ ባለማየቱ በብድር የወሰደውን ማሽን እዚያው ትቶ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ በለመደው ሁኔታ መንገድ ዳር ለመስራት መገደዱን ይናገራል።
አማኑኤል ዛሬ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ እየሰፋ በሚያገኛት ገንዘብ ህይወቱን እየመራ ነው። የነገ ተስፋውን ብሩህ ለማድረግ ከስራው ጎን ለጎን የማታ ትምህርት ይማራል። በልጅነቱ ያቋረጠውን ትምህርት ቀጥሎ አሁን የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል። አማኑኤል አንድ ትልቅ የወንዶች የልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤት እንዲሆን አልሞ ቢንቀሳቀስም ሁኔታዎች እንቅፋት እየሆኑበት ይገኛሉ።
በተለይም ለወረዳ መስተዳድሮች ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡት ባለመቻላቸው ህልሙን እውን የማድረግ ተስፋው እንደጨለመ ይናገራል። አሁን መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ የሚሰራበት ቦታ እራሱ ፈቃድ የለህም በሚል ደንብ አስከባሪዎች እንደሚያስፈራሩት ይናገራል። የጤናው እክል በስራ ተነሳሽነቱ ላይ ምንም አይነት ችግር እንዳልፈጠረበት የሚናገረው አማኑኤል፤ ከዚያ ይልቅ የወረዳ መስተዳድር አካላት ሰርቶ መለወጥን ለሚፈልግ አካል ጉዳተኛ ተባባሪ አለመሆን ሲያይ ሰርቶ የመኖር ሞራሉን እንደጎዳው ይናገራል።
አማኑኤል እግርና እጁ ብቻ ሳይሆን አንደበቱንም ያዝ ያደርገዋል፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለመኖር የሚታትረው ወጣት ህልሙ ትልቅ ነው። ህልሙን ዳር ለማድረስ ግን የሰዎች ድጋፍ ከሁሉም በላይ የወረዳ መስተዳድሮች ትብብር አስፈልጎታል። የማሽኖቹን ቁጥር በማብዛት ለሌሎችም የስራ አድል ለመፍጠር አስቦ ቢንቀሳቀስም ያለው ሁኔታ እራሱንም ለመርዳት ፈተና እንደሆነበት ይናገራል።
አብዛኛውን ጊዜውን በጸበልና በህክምና ያሳለፈው አማኑኤል አሁን 25 ዓመት ሆኖታል። በዚህ እድሜው በጤና ችግር እየተፈተነ በርካታ የህይወት ውጣ ወረዶችን አሳልፏል። ኑሮውን ለማሸነፍ ብርቱ ጥረት እያደረገ ያለው አካል ጉዳተኛ አንድ ቀን ስኬታማ እንደሚሆን ያምናል፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግን ምቹ የስራ ቦታ እንዲሰጡት ይማጸናል።
አማኑኤልን በቅርበት ከሚያውቁት የሰፈሩ ሰዎች አንዱ አለኽኝ ታምሩን አናግረነዋል። አለኽኝ አማኑኤልን እንዲህ ይገልጸዋል። “አንድ እጅና እግሩ ሳይሰራ በልብስ ስፌት ሙያ ላይ መሰማራቱ ያስደንቀዋል። ብዙ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት የጤና ችግር ሲገጥማቸው ችግራቸውን ተጋፍጠው ኑሯቸውን ለማሸነፍ አይጥሩም፤ እርሱ ግን እራሱን ለማሻሻልና የሰው እጅ ጠባቂ ላለመሆን የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።”
“አማኑኤል የአካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሙሉ አካል ላላቸው ወጣቶችም ጭምር ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። አሁን ሸራ ወጥሮ የሚሰራው በግለሰቦች አጥር ስር ነው። እንዲህ አይነት ሰዎችን መደገፍና ማበረታታት ያስፈልጋል። የሚመለከታቸው አካላት የመስሪያ ቦታ በመስጠትና በማደራጀት አማኑኤልን ሊደግፉት ይገባል” ሲል አለኽኝ በሰጠው አስተያየት ተሰናበትን። ሳምንት ሌላ ባለታሪክ ይዘን እንቀርባለን። እስከዛው ቸር ይግጠመን!!
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013