መርድ ክፍሉ
የብሔራዊ መግባባት ጉዳይን ስናነሳ፣ በሀገሪቱ እስከ ዛሬ በርካታ መግባባት ላይ ያልደረስንባቸውን ጉዳዮች በማሰብ ነው። የመሬት ጥያቄ፣ የቋንቋ፣ የማንነት፣ የሰንደቅ አላማ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳይ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ።
ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት የማድረግ ጉዳይ፣ የምርጫ ጉዳይ፣ በዘር ወይም በጎሳ ሀገሪቱ በመደራጀቷ የዜጎች እንቅስቃሴና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር ዋስትና ማጣት የመሳሰሉትም እንደ ሀገር አንድ መግባባት ላይ ልንደርስባቸው የሚገቡ ናቸው ።
ዶክተር አብዱልቃድር አደም ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ላይ ስለ ብሔራዊ መግባባት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ አንድነት እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በሚል ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ብሔራዊ መግባባት በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ተዋናዮች እና ባለድርሻ አካላት መካከል ጥልቅ የፖለቲካ ቀውስን ለማስወገድ፣ ጦርነትን ለማስቆም ወይም የተሳካ የፖለቲካ ሽግግር ለማካሄድ በአንድ ሀገር ባለቤትነት የሚካሄድ የፖለቲካ ሂደት ነው ።
ብሔራዊ መግባባት ዋና ዓላማው ቀውስ መከላከል እና ማስተዳደር፣ ስርነቀል ለውጥ ማምጣት፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ መፍጠር፣ የባህል ግጭቶችን ማስወገድ፣ የጦርነት ስጋትን ማምከን፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የመንግሥት እና የዜጎችን ግንኙነት ማደስ/መልሶ መገንባት እንዲሁም ታሪካዊ ቁርሾዎችን ማከም ናቸው፡፡
የብሔራዊ መግባባት እንዴት እና በማን ይጀመራል? ከሚለው በፊት ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ በየጊዜው የሚሰፋ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የፖለቲካ ማሻሻያ ወይም የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ፣ የፍትህ መጓደል፣ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣት እና ተስፋ መቁረጥ፣ ግቡን የሳተ የለውጥ ሂደት፣ በፖለቲካ ልሂቃን መካከል እምነት መጥፋት፣ በቡድኖች መካከል ግጭት፣ የዜጎች ሕይወትና ንብረት መጥፋት መፈናቀል፣ በጎረቤት/በሌሎች ሀገሮች የሚደረግ ፖለቲካዊ የለውጥ እንቅስቃሴ፣ በመንግሥት በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሲቪክ ማህበራት በልሂቃን ድርድር በውጭ ኃይሎች ጥያቄ እና ግፊት ወደ ብሔራዊ መግባባት እንዲገባ ገፊ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።የብሔራዊ መግባባት ሂደት መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ሊጀመር ይችላል፡፡
መንግሥት የተመናመነ የቅቡልነት ጥያቄን መልሶ ለማግኘት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች የመንግሥትን አወቃቀር ለመቀየር፣ አዲስ የኃይል ሚዛን ለመፍጠር፤ እንዲሁም ሲቪክ ማህበራት፣ ልሂቃን ልዩ ልዩ ፍላጎት ያለውን ሥርዓት ለመቀየር የሚደረገውን ሂደት ለማፋጠን ወይም ለማዘግየት፤ የውጭ ኃይላት የየሀገራቱን ጥቅም ማስጠበቅ እንዲሁም የጋራ ፍላጎት ብጥብጥን፣ ደም መፋሰስን፣ የዜጎችን ሰቆቃ፣ የጦርነት ስጋትን ለማስቆም ብሔራዊ መግባባት ለማድረግ ከስምምነት ሊያደርሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው ።
የብሔራዊ መግባባት ምዕራፎች እርስ በርሳቸው በእጅጉ የተቆራኙ እና በተግባር አንዱን ከሌላው ለመለየት የማይቻል፣ ለሁሉም ቦታ/ሀገር እና ጊዜ የሚሰራ ቀመር የለም ።ሁሉም ምዕራፎች እንደ ሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ሊዘጋጁ ይገባል ። ሆኖም የሌሎች ሀገሮች የብሔራዊ መግባባት ተሞክሮ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡
የዝግጅት ምዕራፍ የሚባለው የዋናው ውይይት አካል ሲሆን በራሱ የፖለቲካ ድርድር ነው ።ብሔራዊ መግባባት ቅቡልነት ይወስናል፣ በቂ የዝግጅት ጊዜ ያስፈልገዋል ። የዝግጅት ምዕራፉ ከዋናው ምዕራፍ ሊረዝም ይችላል። በዝግጅት ምዕራፍ ወሳኝ ተግዳሮቶች መለየት እና የመፍትሄ ሀሳብ ማስቀመጥና ሂደቱን የሚያስተባብር ተቋም እና ሎጂስቲክስ ማግኘት ሌሎቹን ሁለት ምዕራፎች ዕጣ ፈንታ ይወስናል ።
በዝግጅት ምዕራፍ መተማመን መፍጠር/ማጎልበት መተማመን እና አቅም የሚገነባበት ምዕራፍ እንደመሆኑ ውጥረት እና አነስተኛ መተማመን የሚታይበት፣ ተቃዋሚዎች የመንግሥትን፣ መንግሠት የተቃዋሚዎችን ቁርጠኝነትና እውነተኛነት ሊጠራጠሩ ይችላሉ ።የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ከሂደቱ የመገፋት ስጋት ስሚኖር በዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ የሚመለከታቸው አካላት በበቂ ሁኔታ መወከላቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ የዝግጅት ምዕራፍ አስተባባሪዎች እና ሰብሳቢ ወሳኝ ነው ። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ መሪዎች ይቅርታ ማድረግ (በጊዜያዊነትም ቢሆን)፣ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ (ታጣቂ ኃይሎች)፣ በቂ መረጃ ማቅረብ እና የሚዲያ ነፃነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ምዕራፍ ሁለት የሚሆነው የብሔራዊ መግባባት የዝግጅት ምዕራፍ በተሳካ/በተሟላ ሁኔታ ሲጠናቀቅ የሚጀመር፣ ዋናው ምዕራፍ ነው ።ቀደም ሲል በተቀመጠው መመዘኛ መሠረት ተሳታፊዎች ይመረጣሉ፣ ታማኝ አመቻች ይመረጣል፣ አጀንዳ ይቀረጻል/ይጸድቃል፣ ዝርዝር የአሠራር ደንቦች እና የሥራ ሂደት ይወሰናል፣ አጋዥ መዋቅሮች ይቋቋማሉ፣ ኅብረተሰቡ በሂደቱ በተለያየ ደረጃ በንቃት ይሳተፋል፣ የችግር መፍቻ ሥርዓቶች መቀየስና በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ በሁሉም እርከኖች ውይይት የሚካሄድበት ነው፡፡
ብሔራዊ መግባባት የሚካሄድባቸው እርከኖች ያሉ ሲሆን በከፍተኛ እርከን ከፍተኛ ተሰሚነት እና እውቅና ያላቸው አካላት የሚሳተፉበት፣ ከፍተኛ የመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች፣ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎችና ሀገር አቀፍ እውቅና ያላቸው ግለሰቦችን ያካትታል።
በመካከለኛ እርከን ደግሞ የሚወክሉት በማህበረሰብ እውቅና እና ተቀባይነት ያላቸው አካላት ወይም የብሔር፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች ይኖራሉ ።በታችኛው እርከን የአካባቢ መሪዎች፣ ብዙኃን ድርጅቶች ተወካዮችና ማህበራት ይካተቱበታል፡፡
ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ሪቫይቫል አገልግሎት በተዘጋጀው ‹‹የወጣቶች ሰላማዊ ተሳትፎ ለብሔራዊ መግባባትና ለመጪው ምርጫ›› መድረክ ሰሞኑን ተዘጋጅቶ ነበር ።በዚሁ መድረክ ታዋቂ አነቃቂ ንግግር አድራጊዎች የተሳተፉ ሲሆን ወጣቱ ክፍል ለብሔራዊ መግባባት መወጣት ስላለበት ድርሻ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የወጣቶች ተሳትፎ ለብሔራዊ መግባባት
በመድረኩ የዓለም አቀፍ ሪቫይቫል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሪቨረንድ ዳንኤል ጣሰው በብሔራዊ መግባባት ወጣቶች እንዴት ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሰጡትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሰላም ያስፈልጋታል ።ብሔራዊ መግባባትና ሰላም ለሁሉም በአገሪቱ ለሚገኙ ክልሎች ያስፈልጋል። በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ብሔራዊ መግባባትን በግንባር ቀደምትነት መምራት አለባቸው ።በእውቀት ላይ በተመሰረተ ለየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ሳያዳሉና ምንም ዓይነት ድብቅ አጀንዳ ሳይኖራቸው የሰላም እንቅስቃሴን መምራት አለባቸው ።እንደ አንድ ትውልድ የድርሻውን ለመወጣት ሁሉም ሊንቀሳቀስ የሚገባ ሲሆን ሁሉም አካል እውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እንዲያደርግም መሰራት አለበት ።በተለይ ወጣቶች ምክንያታዊ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ሁሉም ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ መንታ የለውጥ ጊዜ ላይ ስትሆን መገዳደሎች፣ መፈናቀሎች፣ ጭፍጨፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሴቶች መደፈር አለ ።እነዚህን ለማስቆም እርስበርስ መነጋገር ያስፈልጋል ።ሁሉም ነገር የሚፈታው በውይይት መሆን አለበት ።አራት አንገብጋቢ ጉዳዮች በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ነው ።የመጀመሪያው በአገሪቱ አንገብጋቢ የሆነው የአንድነት ጉዳይ ነው ።
ሌሎች ደግሞ መቅደም ያለበት ብለው ይሞግታሉ ።የተወሰኑ ቡድኖች ፍትህና ዴሞክራሲ ነው መቅደም ያለበት ብለው ያምናሉ።ሌሎች ደግሞ መቅደም ያለበት ልማትና ብልፅግና ነው ብለው ይናገራሉ ።የተቀሩት ደግሞ አንገብጋቢው ጉዳይ ሰላምና እርቅ ነው መቅደም ያለበት ሲሉ ይሞግታሉ ።ከአራቱ የትኛው ነው መቅደም ያለበት የሚለው በውይይት ሊወሰን ይገባል ።
ወጣቱ ብሔራዊ መግባባት ላይ በሰከነ መንገድ ውይይት እንዲያደርግ መከባበር ያስፈልጋል። ይህ ሲባል የሚነገሩ የብሔሮችን ትርክት ማክበር ያስፈልጋል ። መናናቅና ማንቋሸሽ መቆም ይገባል ።በትርክቶች ላይ መስማማት ያስፈልጋል ።አንዳንድ አክቲቪስቶች የነሱን ትርክት ሕዝቡ ሁሉ እንዲቀበል ይፈልጋሉ ።ይህ አካሄድ ወደ አለመግባባት የሚያመራ በመሆኑ ሊቆም ይገባል ። መደማመጥ ከተቻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ።ሌላው አለመፈራረጅ ያስፈልጋል ።በተለያዩ ጊዜያት እንደታየው እነ እከሌ እንደዛ ናቸው የሚሉ መፈራረጆች ሊቆሙ ይገባል ።መፈራረጅ ካለ መግባባትና ውይይት ሊኖር አይችልም ።
ሦስተኛው በኃይልና በሰብዓዊ ጥሰት መብትን ማስከበር ሊቆም ይገባል ።በየቦታው የሚታዩ ግድያዎችና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት የሚጠቅሙ አይደሉም ።አራተኛው መደራደር አስፈላጊ ሲሆን በሁሉም ነገር ላይ መስማማት ስለማይቻል መደራደር ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ጠቃሚ ነው።ይህ ሲባል በመስጠትና በመቀበል በድርድር ችግሮችን መፍታት ይቻላል ።ፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድር ሊያምኑ ይገባል ።የመጨረሻው ደግሞ በድርድር የማይሆንን ነገር ምርጫ በማካሄድ መፍታት ይቻላል። ምርጫ ሲካሄድ ያሸነፈው ሲገዛ የሌላውን መብት ባከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል ።
በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ወጣት ለብሔራዊ መግባባት
ሌላው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ናቸው ።በመድረኩ የሰጡትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።የተዘጋጀው መድረክ ሀሳብ ወጣቶች ላይ እንደ ማተኮሩ እንደ አጠቃላይ በአገሪቱ ላሉት ነገሮች ባለቤት ሊሆን የሚችለው ወጣቱ ክፍል ነው ።ወጣቱ ክፍል ወጣትነቱን ቢረዳው አገሪቱ አሁን የደረሰችበት ደረጃ አትደርስም ነበር ።ይህ ማለት አካላቸው ወጣት ሆኖ ውስጣቸው (አስተሳሰባቸው) ያረጀ ወጣቶች እየበዙ ይገኛሉ ።
ከመስራትና የተሻለ ነገር ከማሰብ መቀመጥና ማውራትን የመረጡ እንዲሁም ከአገር እድገት ይልቅ ስቃይን የመረጡ አሉ ።ወጣትነት የሚለካው በብዙ ነገር ነው ።በአገር ውስጥ ታዳጊ ንቃት ያለው ሕፃን ይኖራል፣ በመሀከል ዕድሜያቸው የገፋ አዛውንቶች ይኖራሉ ።እነዚህ ሰዎች ጥንካሬ፣ ጥበብና የዕድሜ ተሞክሮ ቢኖራቸውም እንደወጣቱ ብቃት ላይኖራቸው ይችላል ።ነገር ግን ሁለቱን ነገሮች የያዘ ነገር ያለው ወጣቱ ክፍል ብቻ ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ በሁሉም ነገር የሚታየው ወጣት ነው።ረብሻም የሚፈጥረውና ለውጥ የሚፈልገውም ኃይል ወጣቱን ነው የሚፈልገው ።የወጣቱ ኃይል አቅም ያለውና ለለውጥ ዝግጁ በመሆኑ በሁሉም ደረጃ ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል ።ይህን የተሰጠ ትልቅ ኃይል ወይም አቅም በትክክለኛ ቦታ ላይ ማዋል ካልቻለ ጥፋት ያመጣል። በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ማሰብ የሚችል ወጣት ካለ ከስሜት መነጋገር ወይም የተሻለ ነገር ይዞ ለመውጣት የራስን ነገር ይዞ ለመጓዝ ያስችላል ።
ወጣቱ ጨማሪ እንጂ ተጨማሪ የማይሆንበት፣ በመኖሩ ዋጋ የሚጨምርና ዋጋውን ሊያሳይ የሚችል አካል መሆን አለበት ።እየኖርንበት ባለው ተጨባጭ ዓለም ውስጥ ምንድነው የምንጨምረው ነገር የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል ።እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሃይማኖተኛ ማህበረሰብ አሁን እየሆነ ያለው ነገር ከባድ ነው ።
አማኝ ከሚባል ማህበረሰብ አይደለም ዛሬ እምነት የላቸውም ተብሎ ከሚታሰበው አብዛኛው ምዕራብ አገር ያለበት ሁኔታ ይታወቃል ።ለሰው ልጅ የሚሰጡት ክብር ከፍ ያለ ነው ።ኢትዮጵያውያን ፈጣሪን እናውቃለን ብለው የሚያምኑ የማህበረሰብ ችግሮች ሲመጡ ከራስ ውጪ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ አለ፡፡
ችግሮች ሲፈጠሩ ከራስ ውጪ ማየት አዝማሚዎች በመብዛታቸው ጥፋት ከመፈጠሩ በፊት ማገድ ባለመቻሉ ሁኔታዎች እንዲባባሱ አድርጓል ።ነገር ግን ችግሮች እንዳይባባሱ መፍትሄ የሚፈልግ ወጣት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያስፈልጋታል ።በአካላቸው ወጣት የሆኑ ሳይሆን በአዕምሯቸው ወጣት የሆኑ ሰዎች ነው የሚያስፈልጉት። አካላቸው ወጣት ሆኖ ውስጣቸው ያረጁ ወጣቶች ለአገሪቱ አያስፈልጉም ።ወጣቱ እኔ ማነኝ ብሎ መጠየቅ ከቻለ ወደተፈለገው ደረጃ ለመድረስ መንገድ ይጠርጋል ።
ሰው እራሱን ለመለወጥ ከሚረዱት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው በዙሪያቸው የተሻለ ጓደኛ ያስፈልጋቸዋል።ሁለተኛው ሞዴል የሚሆኗቸው መሪዎች ያስፈልጓቸዋል ።በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የጠላቶቻቸው አስተያየት ያስፈልጓቸዋል ።
የጠላት አስተያየት ብዙ ጊዜ የሌለን ብቻ ሳይሆን ጨምረው ሊያወሩ ስለሚችሉ እራስን ለማየት ያግዛል ።አገሪቱ የተሻለች ናት ተብሎ ሲታሰብ ሌላ አካል መጥቶ እንዲቀይራት አይደለም ማሰብ የሚገባው ሁሉም የራሱን አበርክቶ ማድረግ አለበት ።በዚህ ሂደት ውስጥ የሁሉም ድርሻ እንዳለ ሆኖ አገር የሚመሩት ብቻ ሁሉንም ነገር ያስተካክላሉ ይለውጣሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው ። ሁሉም ነገር በእጃቸው ባለመሆኑ የሕዝብ ድርሻ የግድ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013