ከደረቴ የቀረው የዩኒቨርሲቲ ዳቦ

ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ በምግብ ሳይንስ ተመርቃ ሥራ ለማግኘት የደከመችባቸውን ሁለት ዓመታትን ስታወጋኝ ቆየት ሲል የሰማሁትን አንድ ቀልድ አስታወሰኝ። ሴትዮዋ በመንደሩ ስም የገዛውን ጎበዝ ወጥ ቀማሽ ልጃቸውን ይዘው ምግብ ቤት ይከፍቱና በድፍን ሀገሩ ኪሳቸውንም እግራቸውንም ተከሉ።

ታዲያ አንድ ቀን እንደዛሬዋ እንግዳዬ ሰርካለም በምግብ ሳይንስ የተመረቀ አንድ ወጣት የሴትየዋን የምግብ ቤት ዝና ሰምቶ ኖሮ በኮንግራ ጁሌሽኑ ማግስት መመረቂያ ጋውኑን እንኳን በቅጡ ሳያወልቅ ቴንፖውን አንጠልጥሎ አንካሳ ወፍም ብትሆን ሳትቀድመው እየበረረ ይሄድና “ከታዋቂ ዩኒቨርሲቲ በምግብ ዝግጅት ጥሩ ውጤት ይዤ ተመርቂያለሁና ምግብ ቤታችሁ ከልማዳዊ አሠራር እንዲወጣ ብሎም ከዚህ በበለጠ እንዲያድግ የምትፈልጉ ከሆነ ቅጠሩኝ” ይላቸዋል የጫነውን የማዕረግ ቆብ ጭራ እየነሰነሰ።

ወጥ ቀማሹ ልጃቸው ታዲያ በኩራት እጁን አቆላልፎ “አየህልኝ የዚህን የመኪና ሰልፍ? ሕዝቡ ሲራኮት ልብ አልክ? ምን ለመቀበል ይመስልሃል? ስኳር ወይስ ዘይት? አይደለም የኔን እናት ሽሮ ለመብላት ነው ይሄ ሁሉ ትርምስ፤ እናኮ ግን እንዳንተ ትምህርት ቤት ገብታ በምግብ ዝግጅት አልተመረቀችም” የሚል መልስ ሰጠው ትክሻው እስኪርገፈገፍ እየሳቀ።

ከአባቷ አቶ ጸጋዬ ሃይሌና ከእናቷ ከወይዘሮ መንግሥቴ ተካልኝ በመሃል አዲስ አበባ የተወለደችው ሰርካለም ጸጋዬ “እኔን የመታኝ እንቅፋት ሌሎች ወጣቶችን መምታት የለበትም” ስትል የወጠነችው የሥራ ፈጠራ ብርታት ከሃሳብነት አልፎ ዛሬ ላይ በተግባር ተገልጦ ለብዙዎች እንጀራ ሆኗል። ገና ከጅምሩ ለአስራ ሰባት ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።

ሰርካለም በአሁኑ ሰዓት እውቅናን ያተረፈችበትና ለብዙዎች ምሳሌ የሆነችበት የምግብ ዝግጅት መሰረቱን የጣለው ከእናቷ በቀሰመችው ልምድ ነው፤ እናም በዚህ ወቅት የሼቪ ሄራንን “ዩ ካን ዊን” መጽሃፍን ከማንበብ ተሻግራ በሕይወት እንድትተረጉመው ማለፊያ እርሾ ሆኗታል። ለመሆኑ ራስን መሸከም የሚያስችል አንገት እንዲኖርሽ ማገር የሆነሽ ምን እንደሆነ ማወቅ ብንችል? አልኳት የጽናቷ ጥግ ከመደነቅ በቀር የምለው ነገር አሳጥቶኝ።

ጎርባጣውን መንገድ ያለዘበችበትን ፈገግታ እየለገሰችኝ “ከመጥፎ ነገሮችም ትምህርት እንዳለ ልብ ካልን ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል” በማለት ጸሃይ እንዳጠወለገው ጎመን ኩምሽሽ ያለውን ተስፋ የሚያለመልም ምክረ/ሃሳብ ሹክ አለችኝ።

ሰርካለም “ከመጥፎ ነገሮች መማር” ስትል አጽኖት ሰጥታ የገለጸችው አንኳር ነጥብ ከጆሮዬ ሲያንቃጭል የተሸመኑ የሃሳብ ሰበዞች ከሕሊናዬ ሰሌዳ ተሰደሩና በሰላላ ጣቶቼ የብዕሬን ወገብ ሰንጌ ሳልበው የተፋው የቀለመ ምራቅ የወረቀቱን ደረት አረጠበው። ቅዱስ ያሬድ በመምህሩ ወቀሳ ከትምህርት ዓለም ቢሸሽም ከትሏ ጽናትን ተምሮ የዜማ አባታችን ለመሆን በቅቷል፤ ምዕራባውያኑ ኢምንት ቅንነታቸውን በግዙፍ የተንኮል መርዝ በርዘው ሲግቱን የኋሊት ያሽቀነጠርነውን ማንነታችንን ፍለጋ ኮቲያችን እስኪነቃ ዳከርን፤ “ምቀኛ ራስን ያስችላል” ብለን እንደተረትነው ያለ ማለት ነው።

በኖህ ዘመን ጥፋት የነበረው ውሃ በክርስቶስ መወለድ ተባርኮ ቅዱስ ጸበል ሆኗል፤ ሰዶምና ገሞራን የበላው የቁጣ እሳት መዓቱን በምህረት መልሶ የመንፈስ ቅዱስን እሳትነት በመለኮቱ ገልጦልናል።

ነብዩ መሃመድ ሁልጊዜ በመንገዳቸው እሾህ የሚነሰንስ አንድ ጎረቤት ነበራቸው፤ ታዲያ አንድ ቀን ከቤታቸው ሲወጡ የተዘራ እሾህ አላዩም፤ ይህን ጊዜ ክፉኛ ደንግጠው ወደባልንጀራቸው ጎጆ በጥድፊያ በማቅናት ሲጎበኙት ታሞ አገኙትና ከልባቸው መሪር ሃዘን አነቡ፤ “እኔ ላንቱ ደመኛ እንጂ ወዳጅ ልሆን አልችልም” ብሎ የጎደፈ ሰብዕናውን ከሥራቸው ሲያርቅ “ባንተ የሾህ ችንካር የአላህን ፍቅር ተምሬበታለሁ” አሉና ምህረት አድርገውለት በፈጣሪ ጎዳና እንዲመላለስ አገዙት።

እኛስ ጎበዝ? ከጥሞና ልምምዳችን ምን አትርፈን ይሆን? መልከ/ስብሃትን ስንገልጥ መጠጥ ቤት ሳይቀር ያነብ ነበር፤ ምንኛ የምናብ ምጥቀት፣ የእይታ ርቀት፣ የጥሞና ልህቀት ቢታደል ነው? ለዚህ ሳይሆን አይቀርም በዓሉ ግርማ “ጋዜጠኛ ስትሆን የግድ ደራሲ ትሆናለህ” ማለቱ፤ ይህ ውስጠ/ወይራ አባባሉም “በካድማስ ባሻገር” መጽሃፉ ውስጥ በሳላቸው ዓብይ ገጸ/ባህሪያት ማለትም በአበራ ወርቁና ሃይለ/ማርያም ካሳ በኩል ቁልጭ ተደርጎ ሰፍሯል።

አበራ ወርቁ ሉሊት የግል ይዞታው እንድትሆን ከነበረው መሻት የተነሳ ባደረበት ቅናት ሳቢያ የሰው ነፍስ አጥፍቶ እስር ቤት ቢገባም የስዕል ችሎታውን እንዲያገኝ ምክንያት ሆኖታል፤ ሮጦ ባልጠገበበት ሰርቶ ባልደከመበት ወራት አካላዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቹ ሳይስማሙለት ቀርተው ያባከናቸው ግዚያት ሕሊናውን በጸጸት በትር ይሸነትሩታል፤ የኔ ትውልድም መፈናፈኛ ያሳጣው ሕመም ይህ መሆኑን ቢያውቅ ምን ይል ይሆን?

መጥፎ የታሪክ እጥፋቶችን አርቀው ሀገርን ከማነጽ ትውልድን ከመቅረጽ ይልቅ ነጣጣይ ትርክቶችን ያነገቡ አያሌ የጥበብ ሥራዎችን የሚያግተለትሉ ስንት የዘመን ደንቃራዎች አሉ? መቼቱን በፋሲካ በዓል ዙሪያ ያደረገውን “ካድማስ ባሻገርን” መበርበሬን ቀጥያለሁ። እንቅልፍ እያንጠራወዘውም ቢሆን ከመጽሃፍ ጋር የሚታገለውን ሃይለማርያም ካሳን አበራ ወርቁ “ለሞተ ትውልድ ንባብ ምን ይሰራለታል ብለህ ነው የምትደክመው? ይልቁንስ በትንሳዔው ዋዜማ እዚህ ከምንተኛ ገነት ግሮሰሪ እንሂድና አንድ ሁለት እያልን የክርስቶስን መነሳት እንቀበል” አለው፤ ሃይለማርያምም በሰላ አንደበቱ “አሟሟትንም ለማወቅ ንባብ ጥቅም አለው፤ የትናንትን ስህተት ማምለጫ የነገን ሕላዌ ማረጋገጫ ሂደታዊ ትንሳዔው ንባብ ነው” ሲል መለሰለት።

እውነት ብሏል። የዘቀጠው ንባባችንና “ሲስተሙ አይፈቅድም፤ መመሪያው ያግዳል” በሚል ውትፍትፍ መጋረጃ የተከለለው የሥራ ባሕላችን እንዲሁም ተፈጥሮ እንደከዳው ምድረበዳ እርቃኑን የቀረው እሳቢያችን ትንሳዔ ያስፈልገዋል፤ ለዚህም ነው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ለሚዋኘው ወጣት ተሞክሮዋ ትንሳዔ ይሆነው ዘንድ ሰርካለም ጸጋዬን እንግዳ አድርጌ ማቅረቤ፤ “ከቀደሙት ተማሩ” እንዲል መጽሃፉ።

ሕብረት ፍሬና ኮከበጽባህን ተራምዳ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የደረሰችው ሰርካለም አጥር ከሚጋራቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በክፍላቸው መስኮት ትይዩ ከሚገኘው አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ከወንዶች ዶርም ባሻጋር የሚወረወረው ዳቦ ቀልቧን ገዝቶት “መውደድ እሹሩሩ፣ ፍቅር እሹሩሩ” አስባላት። በየቀኑ በዓይን ፍቅር ከተለከፈው ቁራኛዋ የሚወረወርላት ዳቦ የሕይወቷ አንድ አካል ሆነ።

ያልሰከነ ወጣትነት ላይ ፍቅር ሲጨመርበት ዓላማ ያስታል ይባላል፤ አንቺ ስሜት ላይ ምን ፈጥሮ ይሆን? የዘረጋሁላት ጥያቄ ነበር። “ሴቶች ተፈጥሯዊ ባህሪ ያላበሰን ማንጋጠጥ ዛሬ ለደረስኩበት ስኬት አቅም ሆኖኛል፤ ወንዶቹ ከምሳ ሰዓታቸው መልስ በረንዳ ላይ ተቀምጠው ማዶ ማዶ እያዩ በነገር ሲለክፉን ፊት ብንነሳቸው ጊዜ በንዴት እንደጥምቀት ሎሚ የወረወሩት የዩኒቨርሲቲው ዳቦ ደረታችንን ያፈርሰዋል፤ እኛም ተሻምተን ስንበላው ወዛቸው ነካንና ጥንዶች ሆንን፤ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ይባል የለ? ልክ እንደዚያ ነው፤ እናልህ! እንደሱ ዩኒቨርሲቲ መግባት፣ ባራዳ ቋንቋ ምላስን ማጮህ፣ የሂሳብ ተማሪ መሆን እያማረኝ ሳንጋጥጥ ፍቅሩ መሰላል ሆነኝና ባጭር ቁመት ረጅም ልብ ታድዬ አሁን ላይ በተባረከ ትዳር ተቃኝቼ የሶስት ልጆች እናት ለመሆን በቅቻለሁ” ስትል በተገደበ ጊዜ ያልተወሰነ ስኬቷን አስነበበችኝ።

አንዳንዶቹ ስኬትን በቁስ ይመዝኑታል፤ ያንቺን ሃሳብ ልስማ አልኳት በማስከተል። በኛ ሀገር ልማድ ጊዜን እንደሃብት ያለመቁጠር ችግር እንዳለ ገልጻ ወጣቶች ግን የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ ነገር ጊዜ መሆኑን ተገንዝበው በውድድር ዓለም ውስጥ ወደኋላ ቀርተው ኢትዮጵያንም እንዳይጎትቷት አደራ አለች፤ ቀጠለችና እሷ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ስትወጣ አሰፍስፎ የጠበቃት ሥራ አጥነት እንጂ እንደ ሕልም እንጀራ አጣፍጠው ያጎረሷት ተስፋ አበባው ጎምርቶ የሚቆረጥ የፍሬ ዘለላ ይዞ እንዳልሆነ አንስታ ገጠመኟን በዝርዝር አጫወተችኝ።

በሥራ አጥነት መንፈስ የሰለቀጧት እነዚያ ሁለት ዓመታት ጸባይ ነስተው ከሰው ባህሪ ጋር አላገጣጥም ብለዋት ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ነገሩን ያከፋባት የወላጆቿ የተሳሳተ አመለካከት ነው። በጥቁር ወንበር ተቀምጣ እንዲያይዋት የጠበቋት ልጃቸው ቪዲዮ ቤት ስትከፍት “ክብራችን ከሚጎድፍ ሥራ – ሥራ አጥነትሽ በስንት ጣዕሙ? ለምን ሳይበላ አይቀርም” አሉና ውርጅብኙን አዘነቡባት።

ተስፋ ያልቆረጠችው ሰርኬ ግን ባልትና በመጀመር ራሷን ከማኖር አልፋ ተጨማሪ ትምህርት በመማር ምሳሌ መሆንን አሰበች፤ በዙሪያዋ የሚናፈሰው ወሬ ካቴና ቢሆንባትም። በዚህ ወጀብ ወዲያ ወዲህ ስትላጋ በመሃል ማስታወቂያ ወጣና በመንግሥት መሥሪያ ቤት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ በወጣቶች አደራጅነት ተቀጠረች። ይህ ጥረቷ አድጎ ምስራቅ ቴክኒክና ሞያ ኮሌጅን እንድትቀላቀል በር ከፈተላት፤ ባሁኑ ሰዓትም በተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በምግብ ዝግጅት ስመጥር አሰልጣኝ ናት። በተጨማሪም ከማደራጀት ተደራጅቶ መሥራት ይሻል ብላ የራሷን ሥራ ጀመረች።

እኔም አጋጣሚውን በመጠቀም ከማደራጀት ወደመደራጀት ሽግግሩ እንዴት ቀላል ሆነልሽ? ስል ጥያቄ ሰነዘርኩላት። ያሰልጣኞችና የሰልጣኞች ውድድር መኖሩን ሰምታ እድሏን ለመሞከር ያቀረበችው የምግብ ዝግጅት [ኩልነሪ አርት] ፕሮጀክት ጉድ ትንግርት አስብሎ ሰመር ካንፕ ገብታ የበለጠ እውቀት በማዳበር መንግሥት የሰጣትን አራት ነጥብ አምስት ሚሊዬን ገንዘብ በመጠቀም አስራ ሰባት ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችላለች።

ወጣቶች በሥራ ፈጠራ ዙሪያ በቂ መረጃ የሚያገኙበትና አዳዲስ ፈጠራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ቲቪ ሾው በመቅረጽ መድረክ አጥተው እምቅ ችሎታቸውን ለራቁትም ሁነኛ መፍትሄ አሰናድታለች። በተሳተፈችባቸው የሥራ ፈጠራ ውድድሮች ላይ ለሶስት ጊዜ አንደኛ በመውጣት የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት ከማግኘቷም በላይ ከሀገራቸው ለመሰደድ የሚያኮበኩቡ ሴቶችን በመገሰጽ በቀያቸው ሰርተው እንዲለወጡ ሞራል ሆናቸዋለች።

በፍርሃት ጥላ ተሸብበን እንደሀገር አዲስ ሃሳብን ቶሎ የመቀበል ችግር አለብን፤ በተለይ ወጣቶች፤ እንዲህ አይነቱ ፈተና አንቺነትሽ ላይ ምን ፈጥሮ ይሆን? አልኳት የማብቂያ ጥያቄዬን መሆኑን በመግለጽ።

“የተማረ ሁሉ ይቸገር የማይመስለው ማኅበረሰባችን የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም፤ የተማረ ይግደለኝ፤ ብሎ በመተረት አጀገነንና ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ ድረስ ተማርን፤ ምንም እንኳን ውጤቱ ፍየል ወዲያ ቢሆንም።

በኔ እምነት ማኅበረሰቡ ያልተጨበጠ ተስፋ ግቶን ሲያበቃ ከሥፍራው ደርሰን ሞራላችን ሲንኮታኮት እየተጠቋቋመ ከመሳለቅ ይልቅ ወደፊት የሚጠብቀንን ፈተና በማሳየት በቂ የሥነ/ልቦና ዝግጅት በማድረግ ፈተናውን በብልሃትና በጥበብ እንድንሻገረው የሚያስችል ተረክ መለማመድ ይኖርበታል፤ አለበለዚያ ግን በሕልም ዓለም የተወጠነ ስኬት ውጤቱ ተስፋ በመቁረጥ ከሰውነት ተራ የወጣ ትውልድ እናፈራና ሀገርን ተተኪ፤ ተረካቢ ዜጋ እናሳጣታለን። ለውጥና ስኬት ከንቃተ ሕሊና ይጀምራልና ወጣቶች ሆይ ልባችንን ልብ እንበል” አለች ቁምጭጭ ብላ።

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You