የትግራይ ሕዝብ በተለያዩ ዘመናት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበርና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ ኃይል በመታደግ ረገድ የማይተካ ሚና ሲጫወት የቆየ ሕዝብ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ቢሆን የፊውዳልና የደርግን አምባገነን አገዛዝ በመታገልና ነፃነትና ፍትህ በሀገሪቱ እንዲሰፍን በርካታ መስዋዕትነቶችን የከፈለ ለአገሩና ለነፃነቱ ቀናኢ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡
ይህ ኩሩ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ከመሆኑም ባሻገር እንግዳ ተቀባይና ያለውን አካፍሎ ኀዘንና ደስታን በጋራ የሚያሳልፍ ድንቅ ባህል ያለውም ሕዝብ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋራ ለዘመናት ክፉና ደግ ያሳለፈና የሀገሩን ዳር ድንበር ላለማስደፈር በዱር በገደሉ የተጋደለ እውነተኛ ኢትዮጵያዊም ነው፡፡ ሆኖም ግን ከጉያው ወጣን የሚሉት እኩይ ፍጡሮች ከትናንት እስከዛሬ የዚህን መልካም ሕዝብ መከራ ሲያበዙበት ኖረዋል፡፡
በክፋት ተጠንስሶ በክፋት ያደገው የጁንታው ሴረኛ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት የመጨረሻ ግብዓተ መሬቱ ቢፈጸምም አሁንም የቀሩ ርዝራዦች የትግራይ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን መንገዶች፣ ስልክ፣ መብራት፣ የትምህርት ተቋማትና የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች በማውደም ሞተውም ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ጠንቅ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ብሂል የትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳያገኝ በማወክ ጭምር ጠላትነታቸውን በገሃድ እያሳዩ ነው፡፡
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጁንታው በቀሰቀሰው ጦርነት የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ ለመደገፍ በሚንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት የጁንታው ርዛራዦች በትግራይ ሕዝብ ችግር ለመቆመርና ለማትረፍ በመዋተት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀደም ሲል ጁንታው በአገዛዝ ላይ በነበረበት ወቅት ጭምር ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በተለየ መልኩ እስከ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚደገፍ ሕዝብ ያለበት መሆኑን በመካድ ችግሩ አሁን ከሕግ ማስከበር ሂደቱ በኋላ የተከሰተ በማስመሰልና አንዳንዴም ከትግራይ ሕዝብ በላይ የሆነ ቁጥርን በማደናገሪያነት በማቅረብ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር እየሞከሩ ነው፡፡
የጁንታው ርዝራዦችና የእነሱን የጥፋት መስመር የሚከተሉ የውጭ ሀገር ተከፋዮችና ሚዲያዎች ኢትዮጵያንለማመስ ቆርጠው የተነሱበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በማያባራ ሀሰተኛ መረጃና ውንጀላ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የለውጥ መንገድ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይሄን ያህል ሰው ተገደለ፤ ይሄን ያህል ሰው ተደፈረ፤ ይሄን ያህል ሰው በሞት አፋፍ ላይ ይገኛል የሚሉ ሀሰተኛ መርዶ ዜናዎችን በማሰራጨት የከሰረ ፖለቲካቸውን እየነዙ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አሜሪካና አውሮፓ ተቀምጠው ሀሰተኛ ወሬዎችን ከመፈብረክ ባለፈ ለትግራይ ሕዝብ ጠብ ያለ ነገር ሲሰሩ አይታዩም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጠውን የሰብዓዊ ድጋፍ አትቀበል የሚል ክፉ መልዕክት በማስተላለፍ በተራበ ሆድ ላይ በመሳለቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ግን የአነዚህን የጥፋት መልዕክተኞች ችላ በማለት ለትግራይ ሕዝብ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ መንግሥት ይፋ እንዳደረገውም ከየካቲት 17/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከሌሎች ዘርፎች በማዘዋወር ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ከ3.8 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡
በጁንታው አማካኝነት ጉዳት የደረሰባቸውን ውሃ መስመሮች ለመጠገንና አገልግሎቱ የተስተጓጎለባቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ውሃ በቦቴ እያቀረበም ይገኛል፡፡ የወደሙ የመንገድ መሠረት ልማቶችን ለመጠገንም ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ሥራዎችን እከናወነ ይገኛል፤ የመማር ማስተማር ሂደቱንም ለማስቀጠል በጁንታው የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በ96 ሚሊዮን ብር እየተጠገኑ ነው፡፡
በአጠቃላይም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በጁንታው ጠብ አጫሪነት የወደመውን የትግራይ አካባቢ መልሶ ለማቋቋም ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ እናቀርባለን የሚሉ ከ75 በላይ የረድኤት ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ ቢገቡም ድጋፋቸው ከ30 በመቶ የዘለለ አልሆነም፡፡ ይሁንና ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ለኢትዮጵያውያን ደራሽ የለምና የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከ70 በመቶ በላይ ድጋፍ በማድረግ አለኝታነታቸውን እያሳዩ ነው፡፡
ይህም ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ለኢትዮጵያውያን ደራሽ እንደሌለ በገሃድ ያሳየ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማጥፋት የሚደረጉ ማንኛውንም ዓይነት ጣልቃ ገብነትና ሉዓላዊነትን የሚዳፈሩ ተግባሮችን በፍጹም አይቀበሉም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት የቆየ ልምድና አቅም አላቸውና!
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013