ሰላማዊት ውቤ
እንደ ሀገር የ60 ሚሊዮን እንስሳት ሀብት አለን። ከግብርናው ምርት 47 በመቶው የሚገኘው ከነዚሁ እንስሳት ተዋጽኦ መሆኑን ደግሞ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ መረጃው ከሆነ የሀብቱ ባለቤት የሆነውና በተለይ በቆላማው የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው 10 ሚሊዮን አርሶና አርብቶ አደር በአብዛኛው እንስሳቱን የሚጠቀምባቸው የእርሻ ሥራውን ለመደገፍ ነው።
ይህ የኅብረተሰብ ክፍል የእንስሳት አያያዝም ሆነ አረባብ ሥርዓቱ የዘመነ አይደለም። በባህላዊ ልማድ አዙሪት የተተበተበ ነው። የልምድ ማነስ ጎልቶ ይታይበታል። መኖ ሊለማበት የሚገባውን መሬት ለእርሻ ሥራ ነው የሚያውለው። ለምሳሌ፦ ኢንስቲትዩቱ በተለያየ ጊዜ ከስድሳ በላይ የእንስሳት ሀብቱንና የወተት ልማቱን ማሳደግ የሚችሉ የመኖ ዝርያዎች የለቀቀበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም መሬቱን ለእርሻ ሥራ ብቻ እንጂ እነዚህን የመኖ ዝርያዎች ለማልማት እንደማይጠቀምበት በተጨባጭ እየታየ ያለበት ሁኔታ አለ።
በዚሁ ምክንያት በተለይ ወተት ማምረት የሚያስችል ሰፊ ዕድሉን አጥቷል፤ ከወተት ሊያገኝ የሚገባውንና ሕይወቱን በተሻለ መንገድ መምራት የሚያስችለውን ገቢም እንዲሁ። ይሄ አልበቃ ብሎም አርሶና አርብቶ አደሩ የወተት ልማቱ ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመሥራቱ የሕፃናት ሕይወትና መፃኢ ተስፋም አደጋ ላይ የወደቁበት ሁኔታ እስከ መፈጠር የተደረሰበት አጋጣሚም ተከስቷል። በዙሪያው የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በሀገራችን ከሚገኙት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 15 ሚሊዮን ሕፃናት መካከል 40 በመቶው ወይም ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት በወተት እጥረት የመቀጨጭ (መቀንጨር) ክስተት ሰለባ ለመሆን ተገድደዋል። የሚያሳዝነውና የሚያሳስበው እነዚህ ሕፃናት የሚቀጭጩት በአካል ብቻ አለመሆኑ ነው። በአእምሮም ጭምር የሚቀጭጩበት ሁኔታ አለ። ሕፃናቱ ለዚህ በሽታ የተጋለጡት ደግሞ ከወሊድ በኋላ ባለው አንድ ሺህ ቀን ሊያገኙ የሚገባቸውን የወተት ፍጆታ ማግኘት ባለመቻላቸው ነው።
የወተት ፍጆታው እንደልብ አለመገኘቱ እንደ ሀገር ባለው ወተት የመጠጣት ልምድም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። ይሄ የዜጎቻችን ወተት የመጠጣት ልምድ ዓመታዊ ስሌት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፤ ከ20 በመቶ አይዘልም። የኅብረተሰቡ ወተት የመጠጣት ልምድ ምጣኔ ያዘቀዘቀው እንደ ልብ የወተት ምርት ባለመገኘቱ ምክንያት ከጊዜ ጊዜ እየዳበረ መምጣት ባለመቻሉ መሆኑም በምክንያትነት ይቀርባል።
እነዚህ ችግሮች የራስ ምታት በመሆን በብርቱ ያሳሰቧት ሀገራችን ኢትዮጵያ በበኩሏ ወተት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባች ትገኛለች። በርግጥ ችግሩ ሀገር ውስጥ መኖሩን የሚጠቅሱት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ፈቀደ ፈይሳ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ከምርምር አንፃር ወተት ለሰው ልጆች ያለውን ፋይዳ በማስቀደም ነበር።
እንደ ተመራማሪው ወተት ሰውነትን ይገነባል፤ ያጠነክራል፡፡ አጥቢ እንስሳት በጡት በኩል ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚያመነጩት ፈሳሽ በውስጡ ቅባት፣ ገንቢ ንጥረ ነገሮች ወይም ፕሮቲን ማዕድናት፣ ቫይታሚንና ሌሎች ለሰውነት ጠቃሚ ነገሮችን ይይዛል። በአጠቃላይ ወተት በየትኞቹ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ያሉና ይገኛሉ የሚባሉ 118 ንጥረ ነገሮችን በሙሉ የያዘ ለአጥንትና ለአእምሮ ጥንካሬ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ምግብ ነው። ካልሺየምና ፎስ ፈረስም ከዚሁ ከወተት የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ናቸው።
ነገር ግን የዚህ የጎላ ጥቅም ያለው የወተት ምርት እንደ ሀገር ሲቃኝ ምርቱ በአርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ጭምር የሚካሄደው ጥቅሙን ታሳቢ አድርጎ ሳይሆን በዘፈቀደ ነው። ይሄ ሥርዓት በእንስሳት መኖ አለማሙም ሆነ አጠቃቀሙም የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። ሌላው ቀርቶ ወተት በመጠጣት ባህልና ምርታማ ዜጋ በማፍራት ሂደት ላይም ሳንካ እየሆነ ይገኛል። እንደ ሀገር እያስከተላቸው ያሉ ብዙ ፈርጀ ብዙ ችግሮች አሉ።
ወተት ከውጭ እየገባ የሚገኘው ሀገር ውስጥ ያለው የወተት ሀብት የዜጎችን ፍላጎት ባለመሸፈኑ እንደሆነም ይጠቁማሉ። እንደ ሀገር የወተት ልማቱን የሚያሰፉና የሚያሳድጉ አማራጮች መኖራቸውንም ይመክራሉ። አሁን ላይ በሀገር ደረጃ ካሉት 60 ሚሊዮን እንስሳት ሁለት ሚሊዮን ታላቢ ላም ብቻ ቢኖረን የወተት ምርቱን መጨመር እንደሚቻልም በእርግጠኝነት ይናገራሉ። ይሄን ለመተግበር አርሶና አርብቶ አደሩ ከብቱን አስሮ የመቀለብ ልምድ ከማዳበር ጀምሮ የእንስሳት አረባብ ሥርዓቱን ሳይንሳዊ መንገድ የተከተለ ማድረግ አለበት። ከነዚህ መንገዶች አንዱ በኢንስቲትዩቱ በየጊዜው የሚለቀቁ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን በማልማት መጠቀም ነው። ኢንስቲትዩቱ ይሄን ታሳቢ አድርጎ የወተት ሀብቱን ማስፋት የሚችሉ ከስድሳ በላይ የተለያዩ የመኖ ዝርያዎችን የለቀቀበት ሁኔታ አለ። ይሄን መኖ መጠቀም በበቂ ወተት መስጠት የምትችል ላም ያስገኛል። ሌላው ቀርቶ አርሶ አደሩ ሰርክ ለእርሻው የሚጠቀመውንና እንዳይለየው የሚሻውን በሬ እንድትወልድለትም ማድረግ ያስችላል።
ተመራማሪው እንደሚያክሉት ኢንስቲትዩቱ ከውጭም የተሻሻሉ እንስሳት ዝርያዎችን የሚያመጣበት አሠራር አለ። የተለያዩ ዝርያዎች ያላቸውን የሀገር ውስጥ የወተት ላሞችም በመረጣ እያሻሻለም ያቀርባል። ሁለተኛው መንገድ አርሶና አርብቶ አደሩ ይሄን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ያለበት መሆኑ ነው። ሌላው ቀርቶ ሀገር ውስጥ ያለውን እንስሳት በአግባቡ መጠቀም ልምድ ቢኖር በወተት ምርቱም ሆነ በአወሳሰድ ሥርዓቱ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
እንደ ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ ሀሳብ አርሶና አርብቶ አደሩ ኢንስቲትዩቱ በየጊዜው በዚህ መልኩ የሚያደርግለትን እገዛ ተጠቅሞ የእንስሳት አረባብ ሥርዓቱን ቢያዘምን በአጭር ጊዜ በወተት ምርቱ ላይ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በዘመናዊ መልኩ እንደ ሀገር ካሉት 60 ሚሊዮን እንስሳት ሁለት ሚሊዮኑን የተሻሻሉ ላሞች ብቻ እንኳን መያዝ ቢችል የወተት ምርቱ በእጅጉ የሚጨምርበት ሰፊ ዕድል ይኖራል። ምክንያቱም በዚህ መልኩ የተያዘች አንዲት ላም በቀን ከ10 እስከ 15 ሊትር ወተት ትሰጣለችና ነው። ከነዚህ ሁለት ሚሊዮን ታላቢ ላሞች የሚገኝ ወተት ደግሞ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በበቂ መጠን ተደራሽ ይሆናል።
እንደ ሀገር ያለውን ከ20 በመቶ የማይበልጥ ወተት የመጠጣት ዝቅተኛ ምጣኔ የማጎልበት አቅም ይኖረዋል። በዘመናዊ መልኩ መያዝ ብንችል ይሄን ቁጥር በስምንት እጥፍ አሳድገን እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፍስ ወከፍ 100 ሊትር ወተት እንዲጠጣ ማድረግ እንችላለን። ይሄን ማድረግ የሚቻለው በመንግሥት እገዛና ድጋፍ አቅም በመፍጠር ነው።
ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ስንዴ ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ብዙ ወጪ ለማስቀረት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ ነው። ይሄ በትንሹ የቆላ ስንዴ ላይ እየተሰራ ያለው ቢሳካ መንግሥት ወተት ሀብቱ ላይ ደግሞ ማልማት የሚያስችለው አቅም እየተፈጠረ ይመጣል የሚል ዕምነት አላቸው። ኬንያን እንደ አብነት የሚያነሱት ተመራማሪው አክለውም እነ ኬንያ የእንስሳት ሀብታቸው ዝቅተኛ እንደሆነም ይጠቅሳሉ። የወተት ልማት የሚያካሂዱትም ውሱን ቦታ ላይ ነው። ነገር ግን ዜጎቻቸው በነፍስ ወከፍ የሚጠጡት ወተት በእጅጉ ከእኛ ሀገር የተሻለ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ምርቱ የሚመረተው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ነው። ምርምር፣ ብድር አቅርቦትና ቴክኖሎጂን ጨምሮ ብዙ ተያያዥነት ያላቸው አቅርቦቶች ይደረግለታል።
ወጣት ኢኮኖሚስት የሆነችው ልዕልትወርቅ ታፈሰወርቅ ልማቱን ማስፋፋት የሚያስችል ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመሆኑንና የውጭ ተሞክሮም ይሄንኑ ዕውነታ የማረጋገጡን የተመራማሪውን ሀሳብ ትጋራለች። ስለ ወተት ልማቱ ችግር ስትገልፅ አስረግጣ «ትልቁ ችግር እንስሳት እርባታውን ማዘመን አለመቻሉ ነው» ትላለች። አርሶና አርብቶ አደሩ እንስሳ ማርባት፣ አረባቡንም ማዘመንና የኑሮ መሰረቱ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበትም ትመክራለች። በተለይ የተሻሻሉ የወተት ከብቶችን የሚያረባ አርሶ አደር ቶሎ መለወጥ ይችላል። ገቢውን በቀላሉ ለማሳደግም የተሻለ ዕድል ይኖረዋል ባይ ነች።
እንዳከለችው ይሄን ስኬት በሀገር ውስጥ ለማግኘት የውጭ ተሞክሮ ማየት ተገቢ ነው። የውጭ ተሞክሮ እንደሚያሳየው የወተት ሀብት ከፍተኛ እገዛና ድጋፍ ይፈልጋል። በዓለም እንደ ሕንድ ያሉ ሀገራት በወተት ሀብት ማደግ የቻሉት መንግሥት የተለያየ ድጋፍና እገዛ ስላደረገላቸው ነው። የሕንድ ተሞክሮ ቢታይ ሕንዶች በወተት ሀብት ማደጋቸውን የሚያረጋግጡ ብዙ ቁም ነገሮች መጨበጥ ይቻላል። በሕንድ መንግሥት ለአራት አስርት ዓመታት ያህል ልማቱን ወስዶ ሲያለማው የቆየበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ በኋላ ነው ባለሀብቶች ገብተውበት ዕድገት ማምጣት የቻለው።
በመሆኑም እኛ ሀገርም የወተት ምርት ልማቱን ለማሳደግ እንዲህ ዓይነቱን ዕድል መስጠትና መጠቀም ያስፈልጋል። መንግሥት እጁን እያስገባ ዘርፉን ማጠናከር አለበት። ይሄኔ ደግሞ ባለሀብቱ አቅም እየፈጠረ ይመጣል። ከዚህ በኋላም ባለሀብቱ በመስኩ ሙሉ ለሙሉ ስለሚገባበት እጁን ሰብስቦ የሚወጣበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
ከኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከወተት 87 በመቶ የሚሆነው ክፍል ውሃ ነው። ቢሆንም 13 በመቶው ጠጣር ነው ጠጣር በመሆኑ የሚሰጠው አገልግሎት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ትንሽ ከሚመስለው 13 በመቶው ውስጥ ብቻ ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ዕድገትና ጤንነት ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ይመረታል። አይብ፣ ቅቤ፣ እርጎ፣ አይስክሬም፣ አሬራ፣ አጓትና ሌሎች ምርቶች ከሚመረቱት ይጠቀሳሉ።
በእርግጥ አነሰም በዛም በልማቱ እየተሳተፈ የሚገኘው አርብቶና አርሶ አደር ይሄን ይረዳል። ነገር ግን ኅብረተሰቡ ወተትንና ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎችን አብዝቶ እንዲጠቀም የሚያስችል ሰፊ ምርት በማምረት በኩል ሰፊ ክፍተት አለበት። ሥራውን ራሱን እንደገቢ ማግኛ ቆጥሮ የማያስኬድበት ተግዳሮቶች ይስተዋሉበታል። ይሄ ሁኔታ እንደ አጠቃላይ በሀገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ ወተት የመጠጣት ባህልም የሸረሸረው የሚመስሉ አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ።
በእኛ ሀገር ያለው ወተትን የመጠጣትና በተለይ ሕፃናትን የማጠጣት ባህል ከሌሎች ያደጉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ አይባልም። ጥናቶችን መሠረት ያደረጉ መረጃዎች ይሄንኑ ዕውነታ ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ፦ እንደ ጥናቶቹ በዓለም ላይ የአደጉና ሰለጠኑ የሚባሉ አገሮች በዓመት እስከ 366 ሊትር ወተት ይጠጣሉ፡፡
እንዲሁም 280 ሊትር ወተት የሚጠጡ አሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አንድ ሰው በአማካኝ በዓመት ይጠጣል ተብሎ የተቀመጠው ወተት 19 ሊትር ብቻ ነው። ትኩረት መስጠቱ ይሄን ሁሉ ይቀይራል። እኛም ሀገርንና ወገንን ለማሳደግና በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ወተት ዓይነተኛ መፍትሄ ነውና በአርብቶና አርሶ አደሩ እንዲሁም በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ትኩረት ይሰጠው እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013