አንተነህ ቸሬ
ሰውየው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የቆዳ ስፔሻሊስቶች (Dermatologists) መካከል ግንባር ቀደሙ ናቸው። የቆዳ፣ የስጋ ደዌ፣ የአባላዘር፣ የትራኮማና ሌሎች ትሮፒካል በሽታዎችን በመቆጣጠር ረገድ ያከናወኑት ተግባርና ያስመዘገቡት ውጤት በዋጋ የሚተመን፤ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ።
ከሐኪምነታቸው በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌ፣ እርዳታ አስተባባሪ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል፣ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል … ሆነው ሀገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል ።ታላቁን የሎሬትነት ማዕረግንም የደረቡ የሐገር ዋርካ፤ የወገን አለኝታ ነበሩ ።ሰውን መርዳት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲከውኑት የኖሩት መገለጫቸው ነው ።
የመኖሪያ ቤታቸው አሰራር ታይቶ አይጠገብም ። ‹‹ቪላ ብርሃን›› የተሰኘው ቤታቸው ኢትዮጵያን በሚገልፁ ስዕሎች፣ ቅርፃ ቅርፆችና የመገልገያ እቃዎች ያሸበረቀ ነው። የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባሕልና ታሪክ የሚገልፁትና አስደማሚ ዕይታን የሚፈጥሩት ስዕሎቹና እቃዎቹ ላያቸው ሰው ስሜትን ያሞቃሉ፤ ትዝታን ይቀሰቅሳሉ። አለባበሳቸው፣ አነጋገራቸው፣ አኗኗራቸው ኢትዮጵያዊ ነው! እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን!
ጥበበ የተወለደው በ1941 ዓ.ም በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ ሐረር ከተማ ውስጥ ነው ።ገና በሕፃንነቱ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ጥበበ፤ ያደገውና የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ ነው። የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ከተማረ በኋላ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ተሸጋገረ ።የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ነው። ከአማርኛ ትምህርት አስተማሪ በስተቀር ሌሎቹ የኪነጥበበ መምህራን ከውጭ አገራት የመጡ ነበሩ። በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩት ተማሪዎች ቁጥርም ጥቂት ነበር ።
አባቱ ሻለቃ የማነብርሃን ወልደ ሥላሴ የጦር ሰራዊት አባል (በምህንድስናው ዘርፍ መኮንን) ስለነበሩና በጦር ሰራዊት ውስጥ የሚታየው ዲስፕሊንና አለባበስ ከስካውት (Scout) ዲስፕሊንና አለባበስ ጋር የሚቀራረብ ነገር ስለነበረው ጥበበ በዚያ ተማርኮ የስካውት ክበብ አባል ሆነ።
ጥበበ ስምንተኛ ክፍልን ለማጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት ሲቀረው አንዳንድ የተቸገሩን ልጆች በትምህርት ቤቱ አካባቢ በመመልከቱ ልጆቹን መርዳት ስለሚቻልበት መንገድ ከጓደኞቹ ጋር ተማከረ ።ከሚሰጣቸው የኪስ ገንዘባቸው ቀንሰው በማጠራቀም ለመርዳት ቢሞክሩም ችግሩ ሰፊ ስለነበር በእነርሱ አቅም የሚሞከር አልሆነም።ስለሆነም ‹‹የ10 ወንድማማቾች ማኅበር›› የተባለ ማኅበር መሰረቱ።
የጦር ሰራዊት እና የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድኖችን ጋብዘው ስራዎቻቸውን ለተማሪዎች እንዲያሳዩ በማድረግ ከዚያ የሚገኘውን ገንዘብ ለችግረኛ ተማሪዎቹ እንዲሰጥ መላ ዘየዱ ።ከዝግጅቶቹ ያገኙት ገንዘብ የተማሪዎቹን የምግብና የደንብ ልብስ ወጪ ለመሸፈን አስቻላቸው።
ይህ እንቅስቃሴያቸው ተጠናክሮ ቀጥሎ አንዳንዶቹ ተማሪዎች እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ተምረውና ትልቅ ደረጃ ደርሰው በአሁኑ ወቅት በውጭ አገራት ይኖራሉ። የጥበበ ሰውን የመርዳት ፍላጎቱ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረ ባሕርይውና ተግባሩ ነበር ።
ጥበበ በልጅነቱ ዲፕሎማት የመሆን ምኞት ነበረው። የዚህ ምኞቱ ምንጭ ደግሞ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን በዲፕሎማሲው ዘርፍ የነበራቸው አበርክቶ ነው። ታዳጊው ጥበበ የጠቅላይ ሚኒስትር ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ልጅ፤ የኦክስፎርዱ ምሩቅ ልጅ እንዳልካቸው፣ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በተሾሙበት ወቅት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ሲያቀርቡ የሚያሳይ ቪዲዮ መኮንኖች ክበብ ውስጥ ሲመለከት ‹‹ዲፕሎማት መሆን አለብኝ›› ብሎ ተመኘ።
እናቱ ታመው ሆስፒታል የገቡበት አጋጣሚ ግን የጥበበን ፍላጎትና የሕይወት መንገድ የቀየረ ሆነ። እናቱ ታመው ልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል (የአሁኑ ‹‹ጦር ኃይሎች ሆስፒታል››) ገቡ። የእናቱን ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ያከናወኑትን ኢትዮጵያውያን ዶክተሮችን (ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን፣ ፕሮፌሰር ታዬ መኩሪያንና ሌሎች ሐኪሞችን) ሲመለከት ‹‹ሐኪም መሆን አለብኝ›› ብሎ ሃሳቡን ቀየረ ።
ከዚያም የሩስያ ወዳጅነት ማኅበር የትምህርት እድል ሲሰጥ ጥበበ እድሉን አግኝቶ ወደ ሩስያ ሄደ ።ወደ ሩስያ ሄዶ ለስድስት ዓመታት ያህል የሩስያ ቋንቋና የሕክምና ትምህርት ተምሮ በከፍተኛ ማእረግ አጠናቀቀ ።ጥበበ የሩስያ ትምህርቱን በከፍተኛ ማዕረግ ስላጠናቀቀ በቆዳና አባላዘር ጥናት የድህረ ምረቃ ትምህርቱን እንዲቀጥሉ እድል አገኘ።
‹‹ይህን እድል የምጠቀመው እጮኛዬ አብራ መጥታ ከተማረች ነው›› የሚል መደራደሪያ አቀረበ። ጥያቄውም ተቀባይነት አግኝቶ እጮኛው ወደ ሩስያ ሄዳ ተማረች። ጥበበ በ1968 ዓ.ም ደግሞ በቆዳ ሕክምና የሁለተኛ ዲግሪውን አገኘ፤ ሁለተኛ ዲግሪውን የተመረቀውም በማዕረግ ነበር ።በ1970 ዓ.ም የሦስተኛ ዲግሪውን አጠናቆ ተመረቀ ።የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪ ሳለ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርትም ተምሯል ።
ዶክተር ጥበበ ከ1972 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በሎቮቭ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በአማካሪ ስፔሻሊስትነትና ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ካገለገሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመላው አፍሪካ የሥጋ ደዌ ማገገሚያና ስልጠና ማዕከል (All Africa Leprosy Rehabilitation and Training Center/አለርት) ዋና የቆዳ ሐኪምና የሕክምና ክፍሉ የበላይ ኃላፊ ሆነው መስራት ጀመሩ ።
ዶክተር ጥበበ በ‹‹አለርት›› ማዕከል ስራቸውን እያከናወኑ ሳለ ከጎኑ ካለው አርማወር ሐንሰን የጥናትና ምርምር ተቋም (Armauer Hansen Research Institute – AHRI) ባለሙያዎች ጋር ተጨማሪ የጥናትና ምርምር ተግባራትን ያከናውኑ ነበር። የ‹‹አለርት›› ሕክምና ከአርማወር ሐንሰን የጥናትና ምርምር ተቋም የምርምር ስራ ጋር ተደምሮ ለህሙማን የተሻለ ሕክምና ለመስጠት አስችሏል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ያከናወኗቸው ምርምሮች ለዓለም አዲስ የሆኑ የጥናት ውጤቶችንም አስተዋውቀዋል። የጥናት ውጤቶቹም በታላላቅ ዓለም አቀፍ የጥናት መጽሔቶች ላይ ለመታተም በቅተዋል ።
ዶክተር ጥበበ በ‹‹አለርት›› የሕክምና ክፍል ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ማዕከሉ ስልጠናዎችን ይሰጥ ነበር። በማዕከሉ በተዘጋጁ የስልጠና መመሪያዎች ዝግጅት ላይ የዶክተር ጥበበ አሻራ ደማቅ ነው። የስልጠና ማዕከሎቹ ከአፍሪካ አልፈው በእስያ አገራትም ጥቅም ላይ የዋሉ ነበሩ። ዶክተር ጥበበ በዚህ አገልግሎታቸው በስጋ ደዌ፣ አባላዘርና ቆዳ በሽታዎች ቁጥጥር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ።
እርሳቸው ‹‹አለርት›› ሆስፒታል መስራት በጀመሩበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታና የኅብረተሰቡን አመለካት ለመቀየር ስለተሰራው ስራ እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር …
‹‹ … እኔ አለርት ሆስፒታል መስራት ስጀምር ሰዎች እንኳን ሆስፒታሉ ውስጥ ገብቶ መታከም ይቅርና በሆስፒታሉ አካባቢ ሲያልፉ ዝንብ ካረፈባቸው ምናልባትም ለሦስት ቀናት ይሆናል ሲታጠቡ የሚሰነብቱት።
ግን ይህን ለመቀየር ያላሰለሰ የሚዲያ ቅስቀሳ/ዘመቻ አደረግን። ምስጋና ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ይሁንና ጣቢያው የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፤ በኋላ ቴሌቪዥኑም ተጨምሮበት በሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ነገሮች ሁሉ ተቀየሩ። ሰዎቹ ወረፋቸውን እየጠበቁ ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ መታከም ጀመሩ … ››
ዶክተር ጥበበ ‹‹አለርት››ን ሲቀላቀሉ በኢትዮጵያ የነበረው የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቁጥር በሽታው በዓለም የጤና ስርዓት መስፈርት መሰረት የሕብረተሰብ የጤና ችግር/አደጋ ተብሎ እንዲፈረጅ የሚያስገድድ ነበር። ከ12 ዓመታት በኋላ ከተቋሙ ሲለቁ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ የሕብረተሰብ የጤና ችግር/አደጋ ተብለው ከተለዩ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ ወጥቷል ።
ዶክተር ጥበበ ጉልህ ተሳትፎ ካደረጉባቸው በርካታ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ የላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን (Lions Clubs International) ነው።በዚህ ክለብ ተሳትፏቸው በተለይ የዓይን ሞራ ግርዶሽና የትራኮማ በሽታዎችን በመቀነስ ረገድ እጅግ አስደናቂ ተግባራትን አከናውነዋል። የጊኒ ወርም በሽታ ማጥፊያ ፕሮግራም የበጎ ፈቃድ አምባሳደርም ሆነው አገልግለዋል። ዶክተር ጥበበ ከ60 በላይ የሚሆኑ የጥናት ውጤቶቻቸውን በታዋቂ ዓለም አቀፍ የጥናት መጽሔቶች ላይ ስራዎቻቸውን አሳትመዋል ።
ሎሬት ዶክተር ጥበበ የሎሬትነት ማዕረግን ያገኙት ከአሜሪካ ነው። አስገራሚው ነገር ሎሬት ዶክተር ጥበበ የሎሬትነት ማዕረግን ያገኙት ከሌላኛው የሎሬትነትን ክብር ካገኙት እጀ-ወርቁ ሰዓሊ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጋር በተመሳሳይ ቀን መሆኑ ነው። ይህም ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር ሁለት ልጆቿ የሎሬትነት ማዕረግ ያገኙላት አገር እንድትሆን አስችሏታል። ራቅ ያለ ቢሆንም ሁለቱ ሎሬቶች የሥጋ ዝምድና አላቸው ።
የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ‹‹… ማንም ሰው የትም አገር ሄዶ ሽልማት ሊሸለም ይችላል። ግን በአገሩ የተሸለመው ሽልማት ትልቁ ሽልማቱ ነው ብዬ አምናለሁ።ለእኔ ትልቁ ሽልማቴ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀበልኩት የክብር ዶክትሬት ነው።
ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ ለእኔ ነው የሰጠኝ … ›› በማለት በ2002 ዓ.ም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ሽልማታቸው ከሁሉም ሽልማቶቻቸው እንደሚልቅባቸው ተናግረዋል ።
በዓለም የጤና ድርጅት፣ በዓለም ባንክ፣ በብሪታኒያ የቆዳ ሐኪሞች ማኅበር፣ በአሜሪካ የቆዳ ሕክምና አካዳሚ፣ በዓለም አቀፍ የቆዳ ሕክምና ማኅበር፣ በአፍሪካ የኤድስ (AIDS) መከላከል መርሃ ግብር፣ በዊልያም ዱ ቦይስ የአፍሮ-አሜሪካ የጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአፍሪካ የቆዳ ሕክምና ማኅበር፣ በአፍሪካ ፆታዊ ሕክምና ማኅበር እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል፤ንቁ ተሳትፎም አድርገዋል ።
ከበርካታ የዓለም አገራት መሪዎችና የተቋማት ስራ አስፈፀሚዎች ጋር የሚተዋወቁት ሎሬት ዶክተር ጥበበ፤ ከመሪዎቹ ጋር መልካም የስራና የወዳጅነት ትብብርን ያፈሩ አንጋፋ ሰው ነበሩ። ከሩስያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ለሩስያም ሆነ ለቀሪው ዓለም መልካም ተግባር ላከናወኑ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ ሽልማት ተቀብለዋል። ከ39ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ጋር በካርተር ማዕከል (Carter Center) እና ዶክተር ጥበበ አባል በነበሩበት የላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን በኩል በጥምረት ብዙ ጤና ተኮር ስራዎችን ሰርተዋል ።
ከቀድሞው የኩባ ፕሬዝደንት ፊደል ካስትሮ እና ከፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (PLO) መሪ ያሲር አረፋት ጋርም ይተዋወቃሉ ።በአንድ ወቅት ከስዊድን ንጉሥ የመልካም ልደት መግለጫ መልዕክት ተላልፎላቸዋል ።
የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ እጅግ ታላቅ ተግባር ስለመሆኑ ደጋግመው ተናግረዋል ።‹‹ብዙ መሪ ወዳጆች አሉዎት፤ በአንድ ጊዜ ከሶሻሊስትም ከካፒታሊስት አገራት መሪዎች ጋር ወዳጅ መሆን አይከብድም? ከመሪዎች ሁሉ ማንን ያደንቃሉ?›› ተብለው ተጠይቀው ‹‹ … ጎበዝ መሪ የሚባለው የሀገሩን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሪ ነው፤ ወዳጆችና ጠላቶች ይቀያየራሉ፤ የሀገር ጥቅም ግን አይቀየርም … ›› በማለት እርሳቸውም ለአገራቸው ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ለሕዝባቸው የነበራቸው ፍቅርና አክብሮት ልዩ ነው።‹‹… በጤናው ዘርፍ ገና ብዙ ስራ ይቀረናል፤ የገጠሩ ሕዝብ ገና በበቂ ሁኔታ ንፁህ ውሃ እያገኘ አይደለም። ብዙ ሕዝብ አሁንም በትሮፒካል በሽታዎች (Tropical Diseases) እየተጠቃ ነው። ህብረተሰቡ ጠንክሮ እየሰራ ሀገሩን እንዲገነባ ጤናው መጠበቅ አለበት … ተምረን ትልቅ ደረጃ እንድንደርስ ያበቃን ሕዝቡ ስለሆነ ለገጠሩ ማኅበረሰብ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ።እኛ የተማርነው ሕዝቡ በከፈለው ግብር ነው።
ገና ያልከፈልነውና መክፈል ያለብን ብዙ እዳ አለብን ። ይህ ሕዝብ ከመሩት የሚመራ፣ ካስተማሩት የሚማር፣ ካከበሩት የሚያከብር ታላቅ ሕዝብ ነው። ይህን ህዝብ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ አለብን ። ለእያንዳንዱ ለደረስኩበት ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሚና አለው … ›› ብለው ነበር።
በ1983 ዓ.ም የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሰራዊት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ተዋጊዎች ሕክምና እንዲያገኙ ከማድረጋቸው በተጨማሪ የቀድሞ ወታደሮች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሸኙ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ።
ከሕክምና ሙያቸው ባሻገር የሀገር ሽማግሌ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል፣ እርዳታ አስተባባሪ፣ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል … ሆነው ሀገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል። ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ከዶክተር ያለም አምባዬ ጋር ትዳር መስርተው ድንበሯ እና ኒያት የተባሉ ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፤ ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል። ዶክተር ያለም የድንበሯ የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል ዳይሬክተር ናቸው ።
ለበርካቶች ፈውስ ሆነው የኖሩትና ‹‹ገና ማሳካት የምፈልጋቸውና የሚቀሩኝ ብዙ ነገሮች አሉ›› ብለው የነበሩት ሎሬት ዶክተር ጥበበ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የክልል መስተዳድሮች በሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀው፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተርና ባለቤታቸው ሮዛሊን ካርተርም በሎሬት ሕልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀዋል ።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013