ራስወርቅ ሙሉጌታ
ሦስት ጉልቻ አቁሞ ትዳር በመመስረት ቤተሰብ ማፍራት የሚያስደስተውን ያህል በርካታ መሰናክሎችና ውጣ ውረዶችም ያሉበት የህይወት ጉዞም ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ሊሳካ የማይችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ከዚህ በተቃራኒ ብዙዎች በተለያዩ ምክንያቶች የልጅ እናት ለመሆን ቢበቁም እንኳን ሦስት ጉልቻ ለመመስረት ይቅርና በትንሹ ለመኖር እንኳን አቅም አንሷቸው ለበርካታ ችግሮች ሲዳረጉ ማየት አዲስ አይደለም።
ከእነዚህም መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የጎዳና ህይወትን ተቀላቅለው አንዳንዶቹ በየመንገዱ ዳርቻ የበረቱት ደግሞ በላስቲክ ቤት የሚመሰርቱት ኑሮ እንኳን እነሱን ተመልካችንና ሰሚን የሚያሳዝንና የሚያሳቅቅ ነው።
በቅርቡም መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት አርባ እናቶችን ከወደቁበት የጎዳና ላይ ህይወት በማንሳት ስልጠና በመስጠትና በሰለጠኑበት የሞያ መስክ የሚሰሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት ቤት ተከራይቶ የአዲስ ህይወት ባለቤት እንዲሆኑ አብቅቷል።
አቢግያ አሸናፊ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ነው። ጣፋጭ የልጅነት ጊዜዋንም ያሳለፈችው ከቤተሰቦቿ ጋር በመሆን ነበር። በመሃከሉ ግን ሳታስበው በልጅነት አዕምሮዋ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ በመግባቷ ከቤተሰብ ወጥታ እስጢፋኖስ አካባቢ ለዓመታት የጎዳና ህይወት ስትመራ ቆይታለች።
የጎዳና ህይወት በርካታ መሰናክሎች እንዳሉት የምትናገረው ወጣት አቢግያ በተለይ እዛው ሆና ከተዋወቀችውና አሁን ያለበትን በውል ከማታውቀው ጓደኛ የልጅ እናት ለመሆን ከበቃች በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ ይበልጥ እየተወሳሰቡ ይመጡባታል።
በዚህ ወቅት ነበር ከመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር ለመገናኘት የበቃችው። ወደ ተቋሙ ስትመጣ አሁን የደረሰችበት ሁኔታ ይፈጠራል ብላ ያልገመተችው አቢግያ ለራሷ አንድ ቀን ካለችበት አስከፊ ህይወት ለመላቀቅ እያውጠነጠነች አጋጣሚውንም ስትጠባበቅ ኖራ ነበር። እናም በመሰረት በጎ አድርጎት ድርጅት ጥሪው ሲደረግላት የሁለት ዓመት ከስድስት ወር ልጇን ይዛ ለመከተም ትበቃለች።
አቢግያ ተቋሙን ከተቀላቀለች በኋላ የገጠማት ነገር ግን የበለጠ ተስፋ የሚያሰንቅ ነበር። በግቢው በርካታ የእሷ አይነት ተመሳሳይ ችግር የደረሰባቸውን እህቶቿን ስታገኝ የበለጠ ተስፋ ሰንቃ ህይወቷን ለማሻሻል መንቀሳቀሱን ትቀጥላለች።
በተቋሙም ለሁለት ወራት ያህል በርካታ ስልጠናዎችን ማግኘት የቻለች ሲሆን ከዋናው የልብስ ስፌት ስልጠና በተጨማሪ የተለያዩ የእጅ ሥራ ሞያ ስልጠናዎችን ለመውሰድ በቅታለች፤ ከሁሉ በላይ የተሰጣት የህይወት ክህሎት ስልጠና ለወደፊት ህይወቷ ከማህበረሰቡ ጋር በምን መልኩ መኖር እንደሚገባት በቂ እውቀት መቅሰም መቻሏን ትገልፃለች።
ወጣት አቢግያ ለቀጣይ ህይወቷ ከተቋሙ የተደረገላትን የመነሻ ጥሪትና ድጋፍ እንዲሁም የወደፊት ዕቅዷን እንዲህ ትገልፃለች ከዚህ ስንወጣ የሦስት ወር የቤት ኪራይ፣ አስቤዛ፣ ጤፍ፣ ፍራሽ የመሳሰሉት በድርጅቱ ተሟልቶልኛል። የራሴን ሥራ እየሰራሁም ራሴን እስከምችል ድረስ በተመሳሳይ ሙሉ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግልኝም ቃል ተገብቶልኛል።
በተጨማሪ ሥራ ስሰራ ልጆቼ እንዳይቸገሩ በተቋሙ ማቆያ ተዘጋጅቶላቸዋል የምትለው አቢግያ በቀጣይም የራሷን የልብስ ስፌት የመክፈት ዕቅድ እንዳላትና ለዚያም እራሷን እያዘጋጀች መሆኑን እንዲሁም እራሷን ብቁ አድርጋ በጎዳና ህይወት የሚገኙ ሌሎች ጓደኞቿን ከአስከፊው የጎዳና ህይወት እንዲወጡ የበኩሏን እገዛ ለማድረግ እንደምትፈልግም ጠቁማለች።» “ጎዳና ለመንገድ እንጂ ለኑሮ አይሆንም”፤ በመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ስም መሰረትን እና ዶክተር ስርጉት ሀደርን አመሰግናለሁ ስትል መልዕክት አስተላልፋለች።
በተመሳሳይ ሰላሌ አካባቢ የተወለደችውና ለሥራ ብላ ከጓደኛዋ ጋር ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ሳታስበው ለጎዳና ህይወት የተዳረገችው ወጣት መሰረት ቶላም ለጎዳና የዳረጋት አሳዛኝ አጋጣሚና ዛሬ የደረሰችበት ሁኔታ የተፈጠረው እንዲህ ነበር። አዲስ አበባ የመጣችው ለሥራ ቢሆንም በአጋጣሚ ከአንድ ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ትጀምራለች ጓደኝነታቸው እየተጠናከረ ይመጣና የልጆች እናት ለመሆን ትበቃለች። ነገር ግን ባልታሰበ ሁኔታ ባለቤቷ ይታመምና ሥራ መሥራት የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ እናም ቤተሰቦቹ ለማሳከም ብለው ከእሷና ከልጆቹ ነጥለው ይወስዱታል።
በዚህ ወቅት ነበር ለትንሽ ጊዜ አቅሟ የቻለውን እየሰራች የልጆቿን ጉሮሮ ለመድፈን ከተውተረተረችና አልሳካ ካላት በኋላ ሦስት ልጆቿን ይዛ ለጎዳና ህይወት ለመዳረግ የበቃችው።
መሰረት በዚህ አይነት ሁኔታ የጎዳና ህይወትን ከተቀላቀለችና ሦስት ዓመታት አስቸጋሪም አሳዛኝም የጎዳና ላይ ህይወትን ካሳለፈች በኋላ ነበር የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅትን ለመቀላቀል የበቃችው።
መሰረት በመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት በነበራት ቆይታ በወሰደችው መሰረታዊ ስልጠናዎች፣ እራሷን ችላ ልጆቿንም ለማሳደግ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን በመግለጽ ከሁሉም በላይ ለእሷና አብረዋት ላሉ አህቶቿ ምንም ችግር ቢፈጠር ዳግም ወደ ጎዳና እንደማይቀላቀሉ በድርጅቱ የተገባላቸው ቃል ውስጧ ትልቅ ስም እንደፈጠረላትና ተስፋ እንዳሰነቃትም ትናገራለች።
በተክለሃይማኖት አራት ኪሎና ሳሪስ አካባቢዎች በጎዳና ህይወት ለአራት ዓመት ያህል መኖሯን ያጫወተችን ሌላኛዋ የአዲስ ህይወት መሥራች ደግሞ ሚሚ ሱልጣን ትባላለች። ሚሚ ወደ መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ልትመጣ ስትል የነበረውንና አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንዲህ ታስታውሳለች «ሳሪስ አካባቢ ሸራ ወጥሬ ከሁለት ልጆቼ ጋር አምስት ወር እንደኖርኩ እነዚህን ልጆች ይዘሽ እዚህ መኖር አይቻልም በሚል ቀበሌዎች አስነስተው ከመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር እንድገናኝ አደረጉኝ።
በወቅቱ ምን ሊገጥመኝ ምን ላገኝ እንደምችል የማውቀው ነገር አልነበረም ነገር ግን ያሉኝን ተቀብየ የሦስት ዓመት ወንድ ልጄንና የአምስት ዓመት ሴት ልጄን በመያዝ ወደ መሰረት የበጎ አድራጎት ደርጅት መጣሁ። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ሙሉ የጤና ምርመራ ተደርጎልኝ ከሌሎች እህቶቼ ጋር መኖር መሰልጠንም ጀመርኩ።
አሁን ደግሞ ስልጠናው በማለቁ የቤት ዕቃ ተሟልቶልኝ ቀለብ ተሰፍሮልኝ ሥራም ተዘጋጅቶልኝ ቤት ተከራይቼ የራሴን ህይወት ለመጀመር በቅቻለሁ፤ የነገን ለፈጣሪ ትቼ አሁን ያገኘሁትን ዕድል እንደገና የተወለድኩ ያህል አስደስቶኛል ትላለች።»
ሲስተር ሰርጉት ሀደረ በመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የህከምና ባለሙያና የእናት ምትክ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች። ሲስተር ስርጉት ከጎዳና የሚነሱት ወጣት እናቶች ወደ ተቋሙ ሲመጡ እንዴት አቀባበል እንደሚደረግላቸውና በቆይታቸው የሚደረግላቸውን እንክብካቤ እንደሚከተለው ታብራራለች።
ወጣቶቹ ከጎዳና እንደተነሱ ወደ ተቋሙ ከመግባታቸው በፊት ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲያውቅ ተደርጎ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ የገቡት ቃሊቲ አካባቢ ከሚገኝ አረጋውያን ግቢ ከሚባል ማቆያ ነበር። ከዛ በኋላ የመጡትም በክፍለ ከተሞችና በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በኩል ነው።
በዚህ ሁኔታ ወደ ተቋሙ ከመጡ በኋላ አብዛኞቹ የክትባት ወረቀት የሌላቸውና የጤና ምርመራም ያላደረጉ በመሆኑ መጀመሪያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀውና በማዕከሉ ባለው ማቆያ ለሰባት ቀን እንዲቆዩና ምርመራ እንዲያደርጉ ይደረጋል። በዚህም የተለያዩ በሽታዎች እንዳይተላለፉ አስፈላጊው የንጽህና ጥበቃም ይደረግላቸዋል። ከዚህ ቀጥሎ ለእናቶች በቀን ሦስት ጊዜ ለህፃናቱ ደግሞ መክሰስን ጨምሮ አራት ጊዜ ምግብ እንዲያገኙ ይደረጋል።
በዚህ ሁኔታ በመቆያው አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ከተደረገ በኋላ በየክፍለ ከተማው በመዞርም የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ የነበሩትንም ሆነ ሌሎች በህክምና ሥር የነበሩትን ፋይላቸው ወደ ቃሊቲ ጤና ጣቢያ እንዲዛወርና በዛ ክትትል እንዲያደርጉ ይደረጋል። በዚህም የኤች አይ.ቪና የአዕምሮ ህመም መድሃኒቶችን ጨምሮ ያቋረጧቸው መድሃኒቶች አልያም ህክምናዎች ካሉ እንዲቀጥሉ አዲስ መጀመር ያለባቸው ካሉም እንዲጀምሩ ይደረጋል።
እርጉዞቹም ሙሉ የእርግዝና ክትትል የሚደረግላቸው ይሆናል። በዚህ ወቅት አብሯቸው በጤና ጣቢያ የሚቆይ ሰው የሚመደብላቸው ሲሆን በሰላም ተገላግለው ሲመጡም እንደየሃይማኖታቸው አስፈላጊው አቀባበል ይደረግላቸዋል።
አብዛኛዎቹ ከቤተሰብ ተለይተው የቆዩ በመሆናቸው ባይተዋርነት እንዳይሰማቸውና ከቤተሰባቸው ጋር እንዳሉ እንዲሰማቸው የገንፎ ፕሮግራም ደግሞ ለሁሉም የሚከናወን ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ አብዛኞቹ የሱስ ተጠቂ እንደነበሩ የምታስታውሰው ሲስተር ስርጉት «የበጎ ፈቃድ አገልግገሎት የሚሰጡ የስነልቦና የአዕምሮ ህመም ህክምና ባለሙያዎች አሉን፤ በሳምንት አንድም ሁለትም ቀን እየመጡ ህክምና ይሰጡልናል። ከዚህ በተጨማሪም በድርጅቱ ሱሰኛ ለነበሩት በርካታ ማስቲካ፣ ቆሎ፣ ሎሊፖፕና ከረሜላ እየቀረበ ከሱሳቸው እንዲላቀቁ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
በሱስ የተያዙትን ልጆች መንከባከብ በጣም አስቸጋሪ የምትለው ሲስተር ስርጉት አብዛኞቹ መድሃኒት ለመውሰድ ፈቃደኛ ካለመሆናቸው ባሻገር ሁሌም ካላስታወስናቸው በፈቃዳቸው ለመውሰድ የሚነሳሱት ጥቂቶች ናቸው ትላለች። የህፃናቱን ህይወት መንከባከብ ዋነኛ የተቋሙ አላማ እንደሆነ በመግለጽም በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሰባት አስተዳደርም ለትምህርት የደረሱትን ልጆች በሙሉ ተቀብሎ እያስተማረላቸውም እንደሆነ ትናግራለች።
አሁን ሰልጥነው የተመረቁት አርባዎቹ እናቶች ግቢውን ከመልቀቃቸው በፊት የተደረገላቸውንም ድጋፍ ሲስተር ስርጉት እንደሚከተለው ገልፃለች። በመጀመሪያ በሚፈልጉት አካባቢ አንድ ሺህ ብር ድረስ የሚያወጣ ቤት ኪራይ ለሦስት ወር ክፍያ ተፈጽሞ ይዘጋጅላቸዋል።
ነገር ግን ተቋሙ የልጆች ማቆያ ስላለው እነሱ ሥራ ሲሰሩ እንዳይቸገሩ በነፃ ልጆቻቸው በማቆያው እንዲቆዩ ቃሊቲ አካባቢ ቢከራዩ የሚመረጥ መሆኑን በሀሳብ ይነገራቸዋል።
ነገር ግን የሚኖሩበት ቦታና የሚሰሩት ሥራ የሚወሰነው በእነሱ ፈቃድ ብቻ ነው። ቀጥሎም መሰረታዊ የሚባሉ ለአንድ ቤት የሚያስፈልጉ እቃዎች የምገብ ፍጆታ እንደ ጤፍ፣ ፓስታ፣ ዘይት፣ ሽሮን ጨምሮ ይሟላላቸዋል።
ከወጡ በኋላ ደግሞ አጠቃላይ ክትትል በሥራም በልጅ አስተዳደግ ረገድም የሚደረግላቸው ሲሆን በተለይ ወደነበሩበት የሱስ ዓለም እንዳይመለሱ በባለሙያዎች በቅርበት ድጋፍና ምክር ይሰጣቸዋል። ከዚህ ባለፈም በአጋር ድርጅቶች በኩልም የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ዕቅድ መኖሩንም ሲስተር ስርጉት ጠቁመዋል።
ሲስተር ስርጉት በተቋሙ ባሰለፈቻቸው ጊዜያት አገኘሁት የምትለውንም ተሞክሮ እንደሚከተለው አካፍላናለች «ድሮ በጎዳና ላይ ለነበሩ ሳንቲም ወርውሮ ከማለፍ የዘለለ ስለእነሱ ግንዛቤ አልነበረኝም። አሁን ግን ሃያ አራት ሰዓት ከእነሱ ጋር ማሳለፍ በመቻሌ በርካታ ነገሮችን ለመማር በቅቻለሁ። ሌላ የህክምና ቦታ በምሰራበት ወቅት ታካሚዎች እኛን የሚያናግሩን እየተለማመጡ እየለመኑ ነበር።
እዚህ ግን መድሃኒት እንዲውጡ እንኳን ራሳችን ማስታወስ፣ ከእንቅልፋቸው መቀስቀስ፣ ሲቆጡ ለምነን፣ እየተሰደብን መስጠት ይጠበቅብናል። ሲጀመር ይህን አካሄድ መቋቋም ተስኖኝ በተደጋጋሚ ለመልቀቅ አስቤም ወስኜም ነበር፤ ይህን ሀሳቤን ሰርዤ በመቀጠሌ ዛሬን ለማየት በቅቻለሁ። እስካሁን በእኔ ግፊት አርባዎቹም ተመራቂዎች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።
አስራ አንድ ወንድ ልጆች የግርዛት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስደረግ ችያለሁ። ከሁሉም በላይ አንዲት የፌስቱላ ታማሚ ጤናዋ ወደነበረበት እንዲመለስ ያደረኩት ክትትል ትልቅ ተስፋ አሰንቆኛል አስደስቶኛልም ትላለች ሲስተር ሰርጉት»
ለአዲስ ህይወት መስራቾቹ የጎዳና ላይ ተነሺ እናቶች በተደረገው የሽኝት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ አበባ እሸቴ በበኩላቸው የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል። «መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጀት ከቢሯችን ጋር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ይህ ሥራ በዋናነት መሰራት ያለበት በመንግሥት ቢሆንም እየተሰራ ያለው ከምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ነው።
በመሆኑም እንደዚህ ከመንግሥት ጎን በመቆም ህዝብን በተለይ ሴቶችን የሚታደጉትን ማበረታታት ይጠበቅብናል። ሴቶች ድርብ ድርብርብ ሃላፊነት ያለባቸው ናቸው፤ ከሁሉም በላይ ቤተሰብ ማስተዳደርና ልጆችን በማሳደግ ረገድ የሴቶች ሃላፊነት ከፍተኛ ነው። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ሴቶች ይህንን ሊያደርጉ በሚያስችላቸው ሁኔታ ውስጥ አይደሉም። በመሆኑም ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል ያሻቸዋል ብለዋል» ሃላፊዋ።
በተጨማሪም ለአዲስ ህይወት መስራቾች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎች ያገኙትን እድል በመጠቀም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም ለመብቃት እንዲሰሩ በማሳሰብ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ቃል ገብተውላቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013