በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አንዳንድ መጽሐፍት ገና ሽፋናቸውን እንዳየን፤ የመጀመሪያውን ቅጠል እንደገለጥን ይፈፀማሉ። ሌሎች ደግሞ የመጨረሻ ገፃቸው ላይ ስንደርስ “ሀ” ብለው ይጀምራሉ :: የቤት ሥራ ይሆናሉ። እንድናሰላስልና እንድንቀጥላቸው ዕድል ይሰጡናል:: እንደ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ሬይሞንድ ጆናስ” አፄ ምኒልክና የዓድዋ ድል “ አይነት ያሉ መጽሐፍት የዚህ አንዱ ማሳያ ናቸወ ።
አፄ ምኒልክና የዓድዋ ድል ወደ አማርኛ ከተመለሱ መጽሐፍት የሚስተካከለው የለም ። ሙሉቀን ታሪኩ ጥሩ አርጎ ተርጉሞታል ። የሥነ ታሪክን ዳና እና የታሪክ አጻጻፍ ፍልስፍናን የተከተለ ማለፊያ መጽሐፍ ነው ።
በዚህ መጽሐፍ እንደ መደምደሚያ የቀረበው ሃሳብ ጥልቅና ዓይን ከፋች ሆኖ ስለአገኘሁት እንዲሁም ላለፉት 30 ዓመታት የተሄደበት የጥላቻና የልዩነት ትርክት ምን ያህል ስህተት እንደነበር የሚያስታውስ ከመሆኑ ባሻገር እግረ መንገድም የዓድዋ ድልን አንድምታም ከአሸናፊነትና አልበገርባይነት ስነ ልቦና አሻግሮ በመመልከት የልቦና ዓይንን ይከፍታል በሚል ዕምነት ትምህርቱን ላጋራችሁ ወደድሁ ።
“…የሕዝቦች ጥብቅ ትስሰር የሚፈጠረው በእያንዳንዳቸው የኃይማኖት ፣ የብሔር ፣ የቀለም ማንነት ላይ ተመስርቶ አይደለም :: ሁሉንም የሚያስተሳስረው የጋራ ነፃነትን ለማግኘት በሚከፈል መስዋዕትነት ነው :: ይህ አይነቱ መተሳሰር ነው የኢትዮጵያ የነፃነት ከፍታ መገለጫ ፤ …” ይለናል ሪሞንድ ፤ ከ125 ዓመታት በፊት አያት ቅድመ አያቶቻችን አንድ ህይወታቸውን ከፍለው ፤ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያወረሱን አኩሪ ገድልና ትምህርት ።
ሁሉንም የሚያጋምድ የወል ነፃነት ለመቀዳጀት የሄዱበት ርቀትና የከፈሉት መስዋዕትነት ነው የዓድዋ ትምህርት ። አዎ ! የወል ነፃነት ፣ 85ቱ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች እኩል የሚያጣጥሙት የጋራ ነፃነት። የዓድዋ ድል የትግራዩ ፣ የአማራው ፣ የኦሮሞው፣ የሱማሌው፣ የአፋሩ ፣ የአሶሳው ፣ የጋምቤላዊ፣ የደቡቡ፣ የሲዳማው ፣ የሐረሪው ፣ ወዘተረፈ ነፃነት ነው። የዓድዋው ድል የትግራዊው ብቻ እንዳልሆነው የካራማራው ድልም የሱማሌው ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ነው ።
የዓድዋ አያት ቅደመ አያቶቻችን ሆኑ የካራማራ አያት አባቶቻችን መስዋዕት የሆኑት ለአንድ ማንነት ወይም ማህበረሰብ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑ እየታወቀ በተሳሳተ ፖለቲካዊ ትርክት ጀግኖችም ሆኑ ታሪኩ ከአንድ ማህበረሰብና አገዛዝ ጋር ለማያያዝ ሲሞከር ያሳዝናል ። በእነሱ መስዋዕትነት የተገኘውን ነፃነት እያጣጣሙ ታሪካቸውንና ጀግንነታቸውን መካድ ወለፈንዲነት ነው ።
እፉኝቱና ከሀዲው ትህነግ ስሟን ለመጥራት እየተጠየፈ “ሀገሪቱ” የሚላትን ኢትዮጵያ ታሪክና ብሔራዊ ጀግኖቾ ሰድቦና አዋርዶ ለሰዳቢና አዋራጅ እየሰጠ አያት ቅድመ አያቶቻችን ተሰውተው ያቆዩትን የነፃነት ትሩፋት አካል የሆነውን ማንነት ግን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው እና ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ዓይኑን በጥሬ ጨው ታጥቦ ለፖለቲካዊ አላማው ተጠቅሞበታል ።
ከትህነግ ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ልሂቃን ፤ በዚህ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ባቆዩት ማንነት እየተደራጁ፤ ለተረኝነት እየቋመጡና ምራቃቸውን እየዋጡ በዚያ የዓድዋን ድል ከአንድ ማንነት ጋራ ሊያያይዙና ሊያናንቁ ሲከጅሉ ያበግናል ። ያማልም ።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተለይ በዘንድሮው የ125ኛ የዓድዋ ድል በዓሉ አከባበር ቅርጽም ሆነ ይዘት ላይ ይሄን የተዛባ ትርክት ለማረም አበረታችና ተስፋ ሰጭ ጅምሮች ተመልክተናልና ይበል የሚያሰኝ ነው ።
ሁለተኛው የዓድዋ ድል ትምህርት ይላል ሬይሞንድ ጆናስ ፤ “…አፄ ምኒልክ ፣ እተጌ ጣይቱ ወደ ሰሜን የዘመቱት ወራሪውን ፋሽስት ጣሊያንን ድል ለመንሳት ብቻ አልነበረም :: የሀገሪቱን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ አገር ለመገንባት እንጅ ዙፋናቸውን ለማጽናት አይደለም ።…” የታላቁ የዓድዋ ድል ዘላለማዊ አሻራ በደም የተሳሰረ ውስጣዊ አንድነትና ቅኝ ያልተገዛች አኩሪ ሀገር አያት ቅድመ አያቶቻችን ለእኛ ማቆየታቸው ነው ።
ከአባቶቻችን የተረከብናት ሀገራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ፣ ለፍርፋሪ ካደሩ ባንዳ ተላላኪዎቻቸውና በአቋራጭ ሥልጣን ለመጨበጥ ያሰፈሰፉ ኃይላት አደጋ ተደቅኖባታል ። ከጣሊያን ሁለቱ ወረራም ሆነ በዛይድባሬ ይመራ የነበረው “ የታላቋ ሶማሊያ “ አክራሪ ብሔርተኛ ደቅነውት ከነበረው አደጋ የበረታ ነው ::
ከሃዲውና እፉኝቱ ትህነግ ሀገራችንንም ሆነ ቀጣናውን ወደ ማያበራ ግጭትና ቀውስ የመዳረግ ቅዠቱ በጀግናው የመከላከያ ፣ የአማራና የአፋር ኃይሎች ቢመክንም በምዕራቡ ዓለም በሚገኙ ጭፍራዎቹ ሀገራችንና የለውጥ ኃይሉን በማጠልሸት ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥይት እያቀበለ ከመሆኑ ባሻገር ግንባር ፈጥሮ ሌት ተቀን እየሰራ ነው።
የውሸትና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ በመንዛት የሀገራችንን ገጽታ ክፉኛ ከማጠልሸት አልፎ ምዕራባውያንና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ማደናገሩ ሳያንስ የተሳሳተ አቋም እስከማሲያዝ መድረሱን ከአውሮፓ ሕብረትና ከአሜሪካ እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎችና የሚዲያዎቻቸው የተዛባ ዘገባ ለዚህ ዋቢ ነው ።
ለአንድ ቀን ተኝታልን የማታውቀው ግብፅ ሱዳንን ተጠቅማ የውክልና ጦርነት ከፍታብናለች። ከሚወድቅላቸው ፍርፋሪና ከስልጣን ጥም ውጭ የማይታያቸውን ከሀዲ ኢትዮጵያውያንን ስምሪት በመስጠትና ስፖንሰር በማድረግ ማባሪያ ወደ ሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ለመዝፈቅ እንደ ቆሰለ አውሬ በደመነፍስ እየዛከረች ነው ። ከከሃዲው የትህነግ የፈጠራ ፕሮፖጋንዳ ሰላቂ ጭፍራ ጋርም በማበር እየተንቀሳቀሰች ነው ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከድህነት ፣ ኋላቀርነት እንዳትላቀቀ እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖራት ከምንጊዜውም በላይ የዲፕሎማሲዋና የወታደራዊ አስኳሏ አድርጋ ሌት ተቀን እየጣረች ነው ።
ሀገራችን ከበለፀገችና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ካላት የተፈጥሮ ሀብቷን በተለይ ዓባይንና ገባሮቹን ማልማቷ ስለማይቀር ይሄን ብሔራዊ ጥቅሟን ለመከላከልና ለማስከበር ደግሞ አስተማማኝ የጦር ኃይልና በጫና የማይንበረከክ ጠንካራ መንግሥት እንደሚኖራት አበክራ ስለምታውቅና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ደግሞ ማርሽ ቀያሪ የባንዲራ ፕሮጀክት መሆኑን ግብፅ ስለምትረዳ ለማጨናገፍ የሞት ሽረት ትንቅንቅ እያደረገች ነው።
ለዚህ ነው ሀገራችን ፣ ሕዝባችንና መንግሥታችን በታሪካቸው እንዲህ ያለ ውስብስበ ፈተና ገጥሟቸው አያውቁም የምለው ። አባት ፣ አያትና ቅድመ አያቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩን ነፃነትና ሀገር ህልውና ከምንጊዜውም በላይ ቋፍ ላይ ነው ። አቅልለን የምናየው ከሆነ የዋሆች ነን። የማንከላከለው ሀገር ፣ የማንጠብቀው ነፃነት አይደለምና አባቶቻችን የሰጡን ፤ ነቅተን ልንጠብቀውና ልንከላከለው ታሪካዊ ግዴታ አለብን።
ሦስተኛው የዓድዋ ትምህርትም ይሄው ነው ። ሬይሞንድ ጆናስ “…ልንታደለው የሚገባን ነፃነት ልንከላከለው የሚገባ አይነት መሆን እንዳለበት ዓድዋ ያስታውሰናል :: …” ያለው ለዚህ ነው ። ለአባቶቻችን፣ ለአያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ክብርና ምስጋና ይግባቸውና ያጎናፀፉን ነፃነትና ሀገር መከላከልና መጠበቅ ያቅተናል !? ኧረ በፍጹም ። በከሃዲው የትህነግ ጁንታ ላይ በዘጠኝ ቀናት የተቀዳጀነው አንፀባራቂ ድል ህያው ምስክር ነው ።
የሰላማችን ፣ የአንድነታችን ፣ የሉዓላዊነታችንና የተስፋችን ስጋት የሆኑ ኃይሎችን ልናስቆማቸው የምንችለው አያት ቅድመ አያቶቻችን የዓድዋ ድል ለመቀዳጀት በአንድነት እንደቆሙት ሁሉ እኛም ልዩነቶቻችንን አቆይተን ይሄን ክፉ ቀን ለማለፍ ዳር እስከ ዳር እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት መቆም ስንችል ነው ::
በታላቅ መስዋዕትነት እጃችን የገባ የጋራ ነፃነትን ለመከላከልና ለመጠበቅ ሌት ተቀን በንቃት መቆም አለብን :: የዓድዋ አንፀባራቂ ድል የተመዘገበው ሰው ተከፍሎለት ፤ አጥንት ተከስክሶለት፣ ደም እንደጎርፍ ፈሶለት እንጂ ዳር ቆሞ አይዞህ በማለት አይደለም :: በሀገራችን ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአለት ላይ እንዲመሰረት መተኪያ የሌላት የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ጣት መጠቋቆሙን ፣ መጠላለፉን፣ ልዩነትን ፣ ወንዜነትን ፣ አቃቂር ማውጣቱን ፣ አቅላይነትን ፣ አሉባልታውን ፣ ወዘተ. ትተን የመፍትሔው አካል በመሆን የዜግነት ግዴታን መወጣት ይጠይቃል :: የዓድዋ ትምህርት ሀ ሁ …. ይህ ነው ::
ለአለፉት 125 ዓመታት ብንቆጥረው ብንቆጥረው አልገባ ያለን እንደ እስፔስ ሳይንስ የከበደን የታሪክ ፊደል :: ለእነ ማዲባ ፣ ኦሊቨር ፣ ንኩሩማህ ፣ ማርከስ ፣ ስቲቭ ቢኮ ፣ ጆሞ፣ ሙጋቤ ፣ ቦብ ፣ ለመላው አፍሪካ ፣ ለዩናይትድ ስቴትስ መብት ተሟጋቾች ለእነ ማርቲን ፣ ሮዛ ፣ ጄሲ ጃክሰን ፣ ማልኮም ኤክስ ፣ ሉዊስ ፋራካህ ፣ ኤሊጃህ ሞሀመድ፣ ኦባማ የተቆጠረው የፊደል ገበታ እኛ በአጥንት ፣ በማንነት ፖለቲካ ፣ በታሪክ ምርኮኝነት፣ በታሪክ ሽሚያ ተጋርዶብን ፣ ዛሬም ቅኔ፣ ሚስጥር እንደሆነ አለ ::
በዚህ የተነሳ የጋራ ህልም ፣ ርዕይ ፣ የታሪክ ብያኔ ፣ የጋራ ጀግና ፣ የጋራ ድል ፣ የጋራ ሀገር፣ የጋራ መሪ ፣ የጋራ መነሻና መዳረሻ …፤ እንዳይኖረን አድርጓል :: ግርዶሹን ለማንሳትና ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን ማንነቶችን መመልከት እንድንችል በአያት ቅድመ አያቶቻችን ሰው የመሆን ኢትዮጵያዊ ንስር ዓይን እንመልከት።
እንደ እልባት
በአፄ ቴዎድሮስ መሰረቱ የተጣለው የሀገረ መንግሥት ፣ የአንድነት ግንባታ ህልም ፤ በአፄ ዮሐንስ እውን ሊሆን ሲል ሞትና የእርስ በእርስ የሥልጣን ሽኩቻ መንገድ ላይ አስቀርቶታል :: በመጨረሻ በአፄ ምኒልክ እና በእቴጌ ጣይቱ ዋልታና ማገርነት በዓድዋ የማዕዘን ራስነት ፤ በመላው ኢትዮጵያውያን ክዳንነት እውን ሊሆን ችሏል ::
ለ19ኛው መ/ክ/ዘ ታላቁ ዘመቻ ጀግኖች አባቶቻችንን ፣ እናቶቻችንን በጥበብ ፣ በማስተዋል በፊታውራሪነት መርተው አኩሪ ድልንና ነፃነትን ላቀዳጁን ፤ በጊዜው ዓለም ከእነ ናፖሊዎን ሳልሳዊ እኩል ክብር ፣ ሞገስ የሰጣቸውን ፤ የጣሊያኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒን ከስልጣን ያወረዱትን፤ የሰው ልጆች የነፃነት ምልክት የሆኑትን አፄ ምኒልክንም ሆነ እቴጌ ጣይቱን ያለልዩነት ዕውቅና ለመስጠትና ብሔራዊ ጀግና ለማድረግ በማንነት ፖለቲካ የተቀየደው እግራችን ወደኋላ ሲጎተት ስመለከት እንደዜጋ ሃፍረት ይሰማኛል ::
ባለፉት 50 ዓመታት በአንድ ሕዝብ ላይ አነጣጥሮ የተሰራ የጥላቻና የፈጠራ ታሪክ ሀገራችንን የብሔራዊ ጀግኖች ሾተላይ አርጎት ቆይቷል :: ወደፊት ለምንገነባት ዴሞክራሲያዊ ፣ ፍትሐዊ ሀገር ይሄ አሚካላ ፣ ኩርንችት በጥንቃቄ መለቀም አለበት:: ትርክቶቻችን በሀቀኛ ፣ ተጨባጭ ፣ ተጠየቃዊ፣ አመክኖአዊ እና ዘመነ ጓዴነትን contemporary በተከተለ ገለልተኛና ሳይንሳዊ ሥነ ዘዴ ላይ ሊመሰረቱ ይገባል ::
እንኳን የታላቁ የሰው ልጆች ሁሉ የነፃነት የድል በዓል የሆነው ዓድዋ 125ኛ አኩሪ የድል በዓል ደረሰባችሁ ::
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013