ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሳቸው በፊት የሰሜንና የትግራይ ገዢ ከነበሩት ከደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም (የዳግማዊ ቴዎድሮስ ባለቤት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ አባት) ጋር የመጨረሻውን የዘመነ መሳፍንት ጦርነት ያደረጉት ከ164 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም) ነበር፡፡
ደጃዝማች ካሣ በኅዳር ወር 1845 ዓ.ም ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴን ጉርአምባ ላይ፣ በሰኔ ወር 1845 ዓ.ም ደግሞ ራስ አሊ አሉላን (ዳግማዊ አሊን) አይሻል ላይ ካሸነፉ በኋላ ከወቅቱ የግዛት ኃያላን መሳፍንት መካከል ለደጃዝማች ካሣ ያልገበሩት የሰሜንና የትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ብቻ ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ካሣም ወደ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ለመዝመት አቀዱ፡፡ ከዘመቻቸው በፊትም ደጃዝማች ውቤ በሰላም እንዲገቡላቸውና እምቢ የሚሉ ከሆነ እምቢታቸው እንደማይበጃቸው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ላኩባቸው፡፡
ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ከፊትም ጀምሮ ደጃዝማች ማሩ እና ራስ ይማም፤ ደጃዝማች ሰባጋዲስ እና ራስ ማርዬ በሚዋጉበት ጊዜ በብልጠትና በዘዴ አንዱን ከሌላው ጋር እያዋጉ፣ ከሚመቻቸው ጋር እየወገኑና በጋብቻ እየተዛመዱ፤ ሲሸነፉም እየገበሩ ራሳቸውን ከአደጋ ጠብቀው ይኖሩ ነበር፡፡ ደረስጌ ማርያምን አሰርተው ለመንግሥት ጊዜ ሲጠባበቁ የደጃዝማች ካሣ ተደጋጋሚ ድል ዓይኑን አፍጥጦ በላያቸው ላይ መጣባቸው፡፡ ይባስ ብሎም ለደጃዝማች ካሣ እንዲገብሩ የሚያሳስብ መልዕክት ደረሳቸው፡፡
ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም የደጃዝማች ካሣ መልዕክት ሲደርሳቸው … ‹‹ምን የጠገበ ነው?! ሳልዋጋ ይገባልኛል ብሎ ነው?!›› በማለት ከተናገሩ በኋላ ‹‹አልገባም!›› የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ጳጳሱ አቡነ ሰላማም ለደጃዝማች ውቤ ‹‹ለካሳ ቢገብሩ ይሻላል›› ቢሏቸውም የሰሜኑ ሰው ሃሳባቸውን ሳይቀይሩ ቀሩ፡፡
ደጃዝማች ካሣም ጦራቸውን አስከትተው ‹‹… ከእኔ የተለየህ ለራስህ እወቅ! በምን ጠፋሁ እንዳትል! አይዞህ ወታደር፤ እኔ ደስ ከሚልህ አገር አገባሃለሁ›› የሚል አዋጅ አስነገሩ፡፡ ሕዝቡም ከራስ አሊ መሸነፍ በኋላ ‹‹ደጃች ካሣ መቼ ይነግሱ ይሆን? ስመ መንግሥታቸውስ ማን ይባል ይሆን?›› እያለ ይጠይቅ ስለነበር ‹‹እኔ በመራሁህ ተጓዝ፤ ስሜን በስሜን እነግርሃለሁ›› ብለው ከአምባጫራ አልፈው በወገራ በኩል አድርገው ስሜን ገቡና ደረስጌ ላይ ‹‹እንጨት ካብ›› በተባለ ቦታ ሰፈሩ፡፡ የደጃዝማች ውቤ ጦርም በአካባቢው (‹‹መከሁ›› በተባለች ቦታ) ሰፍሮ ነበር፡፡
ደጃዝማች ካሣም አብሯቸው የነበረውንና ዮሐንስ ቤል (ጆን ቤል) የተባለውን እንግሊዛዊ የደጃዝማች ውቤን ጦር አሰፋፈር በመነፅር ዓይቶ እንዲነግራቸው ጠይቀውት ነበርና የደጃዝማች ውቤን ጦር አሰፋፈርና ድንኳን አይቶ በነገራቸው ጊዜ ‹‹አያሳድረኝ አላሳድረውም! እንኳን ይህን ቁርጥማታም ሽማግሌ ይቅርና ወሎን መትቼ የሸዋውን ንጉሥ እይዘዋለሁ፤ ወታደር ሆይ ‹የውቤ ነፍጥ የውቤ ነፍጥ› ቢሉህ የተለጎመው ጨርቅና ባሩድ ነው፤ አይነካህም፤እኔ የክርስቶስ ባርያ ሁሉንም አሳይሃለሁ! … ‹ስሜን በስሜን እነግርሃለሁ› ያልኩህ ወታደር ሁሉ ስሜ ቴዎድሮስ ነው›› ብለው ፎክረው ተነሱና ጦርነቱ የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም ‹‹ቧሂት›› በተባለ ቦታ ላይ ተጀመረ፡፡
ጦርነቱ ተፋፍሞ ደጃዝማች ውቤ ቆስለው ተማረኩና ድሉ የደጃዝማች ካሣ ኃይሉ ሆነ፡፡ ደጃዝማች ካሣም ተሸናፊውን ደጃዝማች ውቤን ‹‹እኔ እሳቱ የመይሳው ልጅ! … አንተ ቆፍጣጣ (ጎባጣ) ቁርጥማታም ሽማግሌ አክብሬህ ‹ገብር› ብዬ ብልክብህ ምነው ሰደብከኝ? አሁንም ነፍጤንና ገንዘቤን አግባ!›› አሏቸው፡፡ ደጃዝማች ውቤም ‹‹እግዜር ያሳይዎ፤ የነበረኝ ነፍጥና ገንዘብ ሁሉ አንድም ሳያመልጥ ከእጅዎ ገባ፤ ሌላ ምን አለኝ?›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ደጃዝማች ውቤ ያከማቹት ብዙ ወርቅ፣ ብር፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጥ እንዲሁም ከብት ተገኘ፡፡ በዚህ ጊዜም ደጃዝማች ካሣ የታሰሩትን ደጃዝማች ውቤን አስጠርተው ‹‹ይህን ሁሉ ሀብት የሰበሰብከው ምን ሊሰራልህ ነው?›› ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ደጃዝማች ውቤም ‹‹ለክፉ ቀኔ እንዲሆነኝ ብዬ ነው›› አሏቸው፡፡ ደጃዝማች ካሣም ‹‹ሰው ያለውን ሀብት ከተጠቀመ ምን ክፉ ቀን አለ?›› በማለት መለሱና ወደ እስር ቤቱ እንዲመለሱ አዘዙ፡፡ ደጃዝማች ውቤም ከዓመታት በኋላ እስር ቤት ውስጥ ሞቱ፡፡
በመጨረሻም ‹‹የኮሶ ሻጭ ልጅ›› ተብለው የተናቁት … ‹‹ደግሞ ለቆለኛ አንድ ወርች ስጋ ምን አነሰው?›› ተብለው በአማቶቻቸው የተቀለደባቸው … ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ … ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሊነግሱባት አስጊጠው ባሰሯት ደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም በጳጳሱ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኑ!
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
አንተነህ ቸሬ
機票 價格比較了一下發現HOPEGOO很便宜,這網站也很方便容易用,有中英文介面。之後會推薦我的朋友來這邊訂!
假期带小孩岀行,要提前的行程和車票都儘量安排好,發現这里订票很方便,服務也不錯。HOPEGOO這個訂票的系統很贊!期待下次。