ሰሞኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሲጋራ ማጨሻ ስፍራን የሚገድብና አልኮልን በብሮድካስት ሚዲያ ማስተዋወቅ የሚከለክለውን አዋጅ ማጽደቁ የሚታወቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብን ተመልክቶ ነበር አዋጁን ያጸደቀው፡፡
በፀደቀው አዋጅ ላይም ከመስሪያ ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና የወጣቶች መዝናኛ በሚገኙባቸው አከባቢዎች 100 ሜትር ርቀት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ ክልል መሆኑ ተደንግጓል፡፡ (ይበል ያሰኛል) ማንኛውንም የአልኮል ምርት በብሮድካስት ሚዲያ ማስተዋወቅ የሚቻለውም ከምሽቱ አምስት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ብቻ እንዲሆን አዋጁ ደንግጓል፡፡
መጠጥን አምርሮ ለሚጠላና የመጠጥ ሱስ እንዲፈነገል ለሚደግፍ ይበል ያሰኛል፡፡ ዳሩ ግን የመጠጥ ንግድ ቤቶችና ሚዲያዎች መክሰራቸው አይቀርም፡፡ (ያው እንደተለመደው የዳይፐር ማስታወቂያ ገበያውን ይቆጣጠረው ይሆናል፡፡) ትልቁና የጽሁፌ ዓለማ የሚያነጣጥርበት ጉዳይ ግን ከአልኮል መጠጦች ጋር በተያያዘ ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አልኮል መሸጥ ክልክል ሆኖ መደንገጉ ነው፡፡ (ሀሳቤ በተቃርኖ የተቀመጠ አይደለም)
ላለፉት በርካታ ዓመታት ከአስራ ስምንት ቁጥር ጎን የመደመር ምልክት የተቀመጠበት መፈክር አብዝቶ ሥራ ላይ የዋለ ማለቴ የዋለለ ተግባር እንደነበር ከመጠጥ ቤት በራፍ የማይጠፉ ምስክሮች ናቸው፡፡ በተለይ የቢራ ማስታወቂያዎች ላይ ለደንቡ በሚመስል ሁኔታ ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች ለሆኑ የተከለከሉ ነገሮች ሲጠቀሱ ይሰማሉ፡፡ ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች የተከለከሉ ፊልሞች፣ የአልኮል መጠጦች ሥራ እና ሌሎችም ማንሳት ይቻላል፡፡
ብዙ ሰዎች እንደሚሉት ‹‹ይህ ማስታወቂያ እራስን ከተጠያቂነት ለማዳን ካልሆነ በስተቀር ከሚከበረው ሕግ የሚሻረው ይበዛል፡፡›› ይህ የይስሙላ ህግ ባለመተግበሩ መሸታ ቤቶች ለአቅመ አዳም ወሔዋን ባልደረሱ ታዳጊዎች ሲጥለቀለቁ ማየትም የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ከርሟል፡፡ እንዲያውም አዲስ መጣ የተባለን ኮሜዲም ሆነ ትራጀዲ ፣ ሆረርም ሆነ ሮማንቲክ ሌላም ሌላም ፊልም ቀድመው አይተው ለትልልቆቹ የሚተረጉሙና የሚያብራሩ ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ሕፃናት ስለመሆናቸው በየማህበራዊ ሚዲያው ሲወራ ይሰማል፡፡
እርግጥ ነው በሰለጠኑት አገራት አንድ ሰው አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው እራሱን ማስተዳደር ይችላል፤ እኛ አገር ደግሞ በ18 ዓመታቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚጀምሩም ብዙ ናቸው፡፡ (አሁን ቢሻሻልም) የአንዲት አገር ሕዝብ አካላዊ ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ዕድገቱ ከ18 ዓመት በላይ ሲሆን አገሪቱም ክፉና ደጉን የምትለይ ለምትመርጠው ነገርም ኃላፊት የምትወስድ ትሆናለች ከሚል እሳቤ ይመስለኛል ቁጥሩ ሙጥኝ ተብሎ የቆየው፡፡
አንዳንዶች አሥራ ስምንት ዓመት ስለሞላቸውና ሀብት ስላቸው ብቻ ወደ ትዳር ይገባሉ፡፡ (በእርግጥ 18 ዓመት ሳይሞላቸው የሚዳሩም አሉ) ፤ ወደ ትዳር ከገቡ በኋላ ግን ሁለንተናዊ ዕድገታቸው ያልተመጣጠነ በመሆኑ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እንዴት መወጣት እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም፡፡ (ለዚህ ዓይነት ዓላማ የእድሜ ጣሪያ ከፍ ማለቱ አያስከፋም)
ወደ ጉዳዬ መለስ ልበል ከዚህ በኋላ በሚዲያ ጣቢዎች ይተዋወቁ የነበሩ የቢራ ማስታወቂያዎች ብልጠት የተሞላባቸው ይሆናሉ፡፡ (እኔ ነኝ ያልኩት) ‹‹የተከበራችሁ አድማጮቻችን በፕሮግራማችን ደስተኛ እንደሆናችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ፕሮግራማችንን ስፖንሰር ያደረገውን ቢራ ማታ ከአምስት ሰአት በኋላ እንገልጻለን›› ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እስከዛ ሰአት ቁጭ ብሎ የሚከታተል አይጠፋማ፡፡ (እድሜ ለቃና)
ለመሆኑ 18 ዓመት ያልሞላቸውን ህጻናት የመጠጥ ሱስ ማስተው ያቃተው ህግ 21 ዓመት የሞላቸውንስ እንዴት ሊከላከል ይሆን? በእኔ እምነት የእድሜ ገደቡ ከፍ ማለቱ ችግር አይኖረውም፡፡ ግና ማታ ማታ በየመሸታ ቤቱ ገብተው ያለ እድሜያቸው ከሚገባቸው በላይ አልኮል መጠጥ ሲጋቱ የትኛው ተቆጣጣሪ አካል ይሆን ተገኝቶ ርምጃ የሚወስደው፡፡ ነው ወይስ መጠጥ ቤቶቹ ከ21 ዓመት በታች ክልክል ነው ከሚለው ማስታወቂያ ውጭ አትገቡም ብለው ሊሞግቱ ነው፡፡ (የማይመስል ነገር ነው) አንዳንድ መጠጥ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራቶኞች እንኳን ራሳቸው ከዚህ የእድሜ ጣሪያ በታች ናቸው፡፡
የታችኛው የእድሜ ገደቡ 21 መሆኑ ካልቀረ በላይያኛው የእድሜ ጣሪያ ላይም ማስተካከያ ቢሰጥበት እላለሁ፡፡ ለአቅመ መጠጥ የደረሰ ብቻ ሳይሆን ከአቅመ መጠጥ ያለፉትም ሊመለከታቸው ይገባል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ካልንማ እንዲያውም እድሜያቸው የገፉ ሰዎች አልኮል ሲጠጡ ከተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ወጥተው እናያቸዋለን፡፡ ለዚያውም ስኳርና ጉበት የመሳሰሉ በሽታዎች ተጨምረውላቸው ከጠጡ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሰብ እነርሱን ሆኖ በመጠጣት ማሳያ መስጠት አያስፈልግም፡፡ ዳሩ ግን የታችኛውም ሆነ የላይኛው የእድሜ ክልል ገደብ ቢጣልበት ክትትልና ቁጥጥሩ ከሌለ ህጉ የወረቀት ላይ ጌጥ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
አዲሱ ገረመው