ተገኝ ብሩ
በህብረ ቀለማት ያጌጠች፣ በውብ ባህል የደመቀች፣የነፃነት አርማ የጥቁር ህዝቦች የድል ችቦ የለኮሰ ጀግና ህዝብ መገኛ ኢትዮጵያ። አይነተ ብዙ ቀለም፣ ዘርፈ ብዙ ኪን ከገፅታዋ ላይ የሚነበብባት ድንቅ የባህልና ጥበብ መድረክ ናት። ይህ ድንቅ ውበት ለዓለም መታየት ይችል ዘንድ መስራት ግድ ይላል።
አባቶች ለዚህች ምድር ታላቅ መስዋእትነት ከፍለው አድዋን የመሰለ ታላቅ ድል አበርክተዋል። በዚህች በአብሮነት የፍቅር ጎጆ የተፈፀመ ታላቅ ገድል፣የሚገባውን ያህል አልተነገረለትም።ገድሉ የታላቅነቱን ያህል አልተዘመረለትም።
ይህን ድል አለም ይበልጥ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል።ይህቺ በመሰዋዕትነት የተጠበቀች በፍቅር ዘመናትን የተሻገረች አገር የተዋበ ታሪክ፣ በጥበብ ሊቃኝ ይገባል።
ኪነ ጥበብ አገራዊ ገፅታን በመገንባት፣ ባህልን በማጎልበትና የማህበረሰቡን ትስስር በማጠንከር በኩል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህንን ዘርፍ በወጉ ከተገለገሉበት በቀላሉ ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣትና ታሪክን ለማውረስ ያስችላል፤ለብዙ ልማታዊና አገራዊ ጉዳዮች ማጎልበቻነትም ይጠቅማል።
ከኪነ ጥበብ ዘርፎች አንዱ የሆነው ፊልም የማህበረሰቡን ልዩ ልዩ መልኮች አጉልቶ ለማሳየት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሀገሮች የአንድን አገር ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በፊልሞች ለሌላው አለም ከማሳየትና ከማስተዋወቅ ባለፈ ሀገራዊ ፍቅርን በማሳደግና የህዝባቸውን የእርስ በርስ ትብብር ያጎለብቱበታል።
የማይገናኝና የተራራቀ ነገርን ሳይቀር ወደ አንድ ማቅረብ የሚቻልበት መንገድ ነው። የሀሳብ ልዕልናን ማስረፅ ሰብዓዊነትን ማነፅ የሚያስችለው ፊልም እኛ አገር ላይ የሚጠበቅበትን ያህል ለውጥ መፍጠር እንዳልቻለ ይነገራል።
ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ታሪክ አላቸው፤የእርስ በእርስ ትስስራቸው የጠነከረ፣ አብሮነታቸው እንዳይበጠስ ሆኖ የተገመደ ነው፤ ከሚለያዩበት ይልቅ የሚጋሩት ይበዛል፤ይሁንና ይህ በደንብ ተገልጦ እንዲታይ አልተደረገም።
ታላላቅ ታሪኮቻችን በፊልሞቻችን አለመዳሰሳቸውና ፊልሙ የራሱን ተፅዕኖ መፍጠር ያልቻለበት ምክንያት ምን ይሆን? ለምን የፊልም ሰሪዎቻችን ታሪካችንን ለራሳችን ብሎም ለዓለም ማሳየትና አንድነታችንን ለማጠንከር የእርስ በርስ ትስስራችንን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ አያዘጋጁም? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን ባለሙያዎችን አናገርን።
ፊልሞች ታሪክን ለሌላ ለማሳወቅ፣ ማህበራዊ ትስስርን በማጠንከርና አብሮነትን በማጎልበት ለሁለንተናዊ ለውጥ ታላቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው የማይካድ ሀቅ መሆኑን የሚናገረው የፊልም ደራሲና አዘጋጅ ግዛቸው ገብሬ፣ ከ6 በላይ ፊልሞችን ፅፎ አዘጋጅቷል። የፊልሞቹን ትኩረት ታሪክ ላይ ተመስርቶ ላለመስራቱ ስሶት ምክንያቶችን ይጠቅሳል።
የሚሰራበት መንገድ ከባድ መሆንና ለፊልም ሰሪዎች የሚያስፈልገው የገንዘብ አቅም ማነስ፣ የመንግስት በዘርፉ ላይ የሚያደርገው ድጋፍ አነስተኛ መሆንና የፊልም ተመልካቹ ለታሪክ ያለው የተዛባ ምልከታ በዋናነት የምጠቅሳቸው ምክንያች ናቸው ሲል ያብራራል።
ኢትዮጵያ በእጅዋ ያለን ወርቅ መጠቀም ያቃታት አገር ናት የሚለው የፊልም ባለሙያው ግዛቸው ፤እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ ታሪክ ያላቸው አገራት ታሪካቸውን ኪነ ጥበባቸው ላይ እንደ ግብዓት ተጠቅመው ቢሰሩ ታላቅ ጠቀሜታን ማግኘት ይችላሉ ይላል።
ረዲ በረካ (የሴት ልጅ) የፊልም ስራ ባለሙያ ነው። 10 በሚሆኑ ፊልሞች ላይ በድርሰትና በአዘጋጅነት እንዲሁም “እጅ ወደ ላይ” የተሰኘ ቲያትር በድርሰትና በአዘጋጅነት ተሳትፎ አድርጓል። 50 ሎሚ፣ ሱማሌው ቫንዳም፣ የህዝብ ነኝ፣ሰማያዊ ፈገግታ፣ ወራጅ አለ፣ የትነበርሽ፣ በ17 መርፌ ከፊልሞቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ታላላቅ አገራዊ ታሪኮችን አውቆ ለሌላው ለማሳወቅ፣ አገራዊ አንድነትን ለመገንባትና የእርስ በርስ ትስስርን ለማጠንከር ፊልሞች የጎላ ሚና እንዳላቸው ያምናል። በመሆኑም በዘርፉ በቂ የሆነ ስራ ቢሰራ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ይገልፃል። በተለይ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ወደተሻለ ገፅታ ለመቀየርና መግባባትን ለመፍጠር ፊልሞችን ትልቅ መሳሪያ ማድረግም ይቻላል ነው የሚለው።
በአይነትና ይዘታቸው ሀገራዊ የሆኑ ፊልሞች የሚጠበቀውን ያህል ባይሆኑም የሉም በሚባል ደረጃ ላይ አይደሉም ይላል። በጥቂቱም ቢሆን ተሞክረዋል የሚለው ደራሲና አዘጋጅ ረዲ በረካ፤ ባለሙያዎች እጅግ በጣም ትልልቅ ተፅዕኖን የፈጠሩ በርካታ ሀገራዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞች መስራታቸውን በማሳያነት ያነሳል። ነገር ግን በአገራዊ ታሪኮች፣ ማህበራዊ ጥምረትና አብሮነት ላይ የተሰሩ የፊልም ስራዎች ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑን ያምናል።
እንደ ረዲ ገለጻ፤ባለሙያው ማለትም ፊልም ሰሪው አገራዊ ታሪኮች፣ የማህበረሰቡን የአብሮ የመኖር መልካም እሴት የሚያጎለብቱ ሀገራዊ ፍቅርን ከፍ የሚያደርጉ ሀገራዊ ፊልሞችን መስራት እንዲያስችለው ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
ፊልም ሰሪው የፈለገውን ይዘት በተለይም ታሪካዊና አገራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ፊልሞች መስራት እንዳይችል ያደረገው የመጀመሪያ ምክንያት የፊልም ባለሙያው ክህሎትና እውቀት ችግር መሆኑን ያመለክታል።ስለ አገሩና ታሪኩ ያለው እውቀት በቂ አለመሆን፣ የፊልም መስሪያ በጀት ግብዓት እጥረትና ከዚህ በፊት የነበሩት የፊልም ግምገማዎችን በዋናነት ይጠቅሳል።የፊልም ሰሪው በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ በትብብር ያለመስራት ውስንነት እንዳለም ይጠቁማል።
አገራዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞችን አብዛኛው ፊልም ሰሪና ማህበረሰቡ በተሳሳተ መንገድ እንደሚወስድ የሚገልፀው ደራሲና አዘጋጅ ረዲ በረካ፣ ታሪካዊና ሀገራዊ ፊልም ማለት የተለያዩ አካባቢዎችን ዘዬ አላብሶ መስራትና ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ወጣ ብሎ መስራት የሚመስለው ብዙ የተሳሳተ እሳቤ እንዳለ ያስረዳል።
የተለያዩ ታሪኮችና መቼቶች ማሳየትም አገራዊ የሆነ ገፅታን መግለፅ ነው የሚለው ባለሙያው፣ ከዚህ ለየት ባለ መልኩ መታሰብ እንዳለበት ያስገነዝባል። ታሪክና አገራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ፊልሞች አገራዊ ጉዳይ አንስተው የማህበረሰቡን የእርስ በርስ ትስስር የሚያጠነክሩና አገራዊ ፍቅርን የሚያሳድጉ መሆን እንደሚገባቸውም ይመክራል።
ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ በአማርኛ ፊልሞች በሚያሳየው የትወና ብቃት አድናቆትን ያተረፈ ተወዳጅ አርቲስት ነው። ፊልሞች የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠንከርና ሀገር በመገንባት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳል። በተለይ ከአገር አልፎ በውጭ አገራት ጭምር አገርን በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ሚና እንዳላቸው ያስረዳል።
በባለሙያዎቹ በመፍትሄነት የቀረቡት ሀሳቦች በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው። የፊልም ባለሙያው በፊልም ሙያ ያለውን እውቀት ማጎልበት ይኖርበታል፤ መንግስት ለዘርፉ የሚሰጠውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት።
ከፊልም የሚገኘውን ታላቅ አስተዋጽኦ በመረዳት ትኩረት መስጠት ለታሪካዊ ሁነትና ለአገራዊ ፊልሞች መበራከት ዋነኛ መፍትሄ ነው። በተለይም አገርን በአንድነት ለማስተሳሰርና የአገር ታላቅነትን ለማሳየት አዝናኝ በሆነ መልኩ የሚሰሩና የአገር ፍቅር ስሜትን የሚያሳድጉ ፊልሞችን በብዛት መስራት ያስፈልጋል።አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013