ሦስቱንም እንደ አንድ

በምናውቃቸው ነገሮች ውስጥ ሌላ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አንድ ብቻ የመሰለን ነገርን ብዙ ሆኖ ይሆናል፡፡ ብዙ ናቸው ብለን የምናስባቸው እልፍ ነገሮች ደግሞ አንድ ሆነው አሊያም እንደ አንድ ቆመው ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡ በዚያን ሰሞን በተመለከትኩት አንድ ነገር፣ በዚያቹ ቅጽበት አንዲት ሃሳብ ድንገት ወደ ውስጤ ዘላ ገባች። ፌስቲቫሉ ስፖርታዊ ነው፡፡ ጨዋታና ውድድሩ ሁሉ ከባሕል የተቀዳ ባሕላዊ ስፖርት እንጂ፤ ጥበብን በስም የሚጠራ የማንም ድምፅ አይሰማም፡፡

በስታዲየሙ ውስጥ ያለው ብዙኃኑም ቢሆን የባሕል ስፖርት ቤተሰብ ነው፡፡ ግን ከመሐከል በዓይኑ በግንባሩ ሲመለከታት የነበረ አይጠፋም፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ንዑስ ከተማ በሆነችው በሆሳዕና ከተማ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫልን ለመታደም ወይም ለመሳተፍ ከፌዴራሉም ከክልሎቹም በዛ ብለው ከስታዲየሙ ውስጥ ተገኝተዋል፡፡

የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ዕለትም የነበረው ድባብ ስፖርት…ባሕል…ኪነ ጥበብ…ብቅ ጥልቅ እያሉ የሚውለበለቡ ብዙ ነገሮች፣ በዓይንና በጆሮ፣ ደግሞም በምናብ ይከሰታሉ፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የማርቺንግ ባንድ ኦርኬስትራ ከመድረኩ ፊት ለፊት መሐሉ ላይ ሆነው የሚያስደምጡት ጥዑም ኅብረ ዜማ ልብን የሚጣራ ነው። በወዲህ ደግሞ በባሕል አልባሳትና ጌጣ ጌጦች፣ በቀለማት ተውበው ክውን እሴቶቻቸውን በትውፊታዊ ጥበባት ያስመለክታሉ፡፡ በስታዲየሙ መም ላይ በአራቱም አቅጣጫ ተደርድረው ሲታዩ፣ ሜዳው መሐል ያለችው ኢትዮጵያ ትመስላለች፡፡ ከዚያም ከዚህም የሚታዩና የሚደመጡ ነገሮች ልክ እንደኔው ስለአንዳች ነገር ማሰብ እንድንጀምር የሚጋብዙ ናቸው፡፡

የባሕል ስፖርት ልዑካኑ ሲያሳዩ ከነበሩት ነገሮች አንዱ የባሕል ውዝዋዜ ነበር፡፡ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ ውዝዋዜ ኪነ ጥበብ እንደሆነ አድርገን ብቻ እንቆጥረዋለን። ውዝዋዜ ግን ስፖርትም ጭምር ነው፡፡ በባሕሎቻችን ውስጥ ኪነ ጥበብና ስፖርት የአንድ እናት ልጆች ብቻ ሳይሆኑ መንትዮች ሆነው የምናገኛቸው ብዙ ቦታ ላይ ነው፡፡ የሁለቱን ጣምራነት የምንመለከተው አንድም በውዝዋዜ ውስጥ ነው፡፡ ውዝዋዜ ያለ ሙዚቃና የአካል እንቅስቃሴ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ውዝዋዜ የማን ልጅ ነው ካሉ፤ የኪነ ጥበብና የስፖርት ልጅ ነው፡፡ ያለ አባትና ያለ እናት፣ በአንደኛቸው ብቻ ልጅ እንደማይወለድ ሁሉ፤ ያለ ጥበብና ያለ ስፖርት ውዝዋዜ ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ ይህ እውነታ በባሕላዊ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊው ክዋኔ ውስጥም ይሠራል፡፡ ብዙ ሆኖ እንደ አንድ በመታየት ባሕሎቻችን ውስጥ ስናስስ ሁሉም ነገር ትርጉም ያለው መሆኑ ይታየናል፡፡

ኢትዮጵያን ከብዙ የዓለም ሀገራት ለየት ከሚያደርጓት አንዱ የባሕል እሴቶቿ ናቸው፡፡ ለየት ማለቷ ብቻ ሳይሆን ሕልውናዋ የተመሠረተውም በዚሁ ነው፡፡ ባሕሎቿ ከውበትነት ያለፉ የቆመችባቸው ምስጢራቶቿ ናቸው፡፡ የእነኚህ ባሕሎቿ ዘለቄታዊ ሕልውና የተመሠረተው ደግሞ ከጎን በበቀሉት ቅርንጫፎች ነው፡፡ ከእነዚህም ቅርንጫፎች ዋነኞች ስፖርትና ኪነ ጥበብ ናቸው፡፡ አንድ ዛፍ ያለ ቅርንጫፎቹ ግንድና ስር ብቻ ነው፡፡ ስሩ ከአፈር ተጣብቆ ውሃና አስፈላጊውን ማዕድን ለቅርንጫፎቹ በመላክ የፀሐይ ብርሃንም ሆነ ምግቡ የሚዘጋጀው በቅርንጫፎቹ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ስፖርትና ኪነ ጥበብ ከባሕል ጋር፤ የአንዱ የመኖር ሕልውና በሌላኛው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የባሕሎቻችንን በር ከፍተን ወደ ውስጣቸው ስንዘልቅ፣ አብዛኛዎቹ ከሁለት በአንዱ ላይ መሠረት ያደረጉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ኢትዮጵያ ብለን ባሕል፣ ባሕል ብለንም ኪነ ጥበባዊ አሊያም ስፖርታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከዚህም የተለየና አንድ እስከመሆን የተቀራረቡ ነገሮችን ደግሞ እናገኛለን፡፡ በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት ተለይተው የታወቁ 294 የባሕል ስፖርቶች አሏት፡፡ እነዚህን 294 የባሕል ስፖርቶችን አንድ በአንድ ስንመረምር፣ አብዛኛዎቹ ትውፊታዊ ውበታቸው የሚገለጠው በውድድር ውስጥ ሳይሆን በጨዋታ ውስጥ ነው፡፡ የባሕል ጨዋታዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ታዲያ ስፖርት ብቻውን አይደለም፡፡

ባሕላዊ ስፖርት ብንል በግልባጩ ፍጥጥ! ብላ የምትታይ ጥበብ ትገኝበታለች፡፡ ለአብነት የገና ጨዋታን እንውሰድ። የገና ጨዋታ አንድ ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ኪነ ጥበባዊም ስፖርታዊም፤ ሁለቱንም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሜዳ ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች በሚያደርጉት ጨዋታ፤ ከአካላዊ እንቅስቃሴ፣ ከቁሳቁስና ከአጨዋወት ስልቱ እስከ አጨዋወት ሕጎቹ ድረስ በብዙ ነገሮች ስፖርታዊነትን የተላበሰ ነው። በሌላኛው ግልባጭ ደግሞ የገና ጨዋታን ኪነ ጥበባዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቱባ የሆነው የገና ጨዋታ በሌጣው ያለ ሙዚቃ፣ ያለ ጭፈራ አይደረግም፡፡ የገና ጨዋታ ያለ እነዚህ ነገሮች መኪና ያለ ጎማ እንደማለት ነው፡፡ ዓመት ዓመት የገና በዓል በደረሰ ቁጥር ሁሉ ስንዘክረው፤ ከስፖርታዊ ማንነቱ ይልቅ ኪነ ጥበባዊ መገለጫዎቹ ጎልተው ይወጣሉ፡፡ የገና ጨዋታን ጥበባዊ ነው ብለን ለኪነ ጥበብ፣ ስፖርታዊ ነው ብለን ለስፖርቱ ልንተወው አንችልም፡፡ በእኛ ባሕሎች ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የተሠራበትን ምስጢራዊ መዋቅር የያዘ ስዕል መስሎ ይታያል፡፡

እዚህ ጋር ማስተዋልና ደግመን ማጤን የሚኖርብን አንድ ነገር አለ፤ በአሁኑ ጊዜ በባሕል ስፖርቶች ውስጥ ተካቶ፣ ጨዋታውን ለማሳደግና ወደ አደባባይ ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ፤ ጥበባዊ ትውፊቱንም አብሮ ስለማስቀጠል ማሰብ ይኖርብናል፤ ለገና ብቻ ሳይሆን ጣምራ ሆነው የሚገኙ ሌሎችንም ቢሆን፡፡ አለበለዚያ ከነሙሉ ክብርና ግርማ ሞገሳቸው ልንጠብቃቸው አንችልም፡፡ የገና ጨዋታ እንደ እግር ኳስ ራሱን ችሎ ብቻውን እናቁመው ካልን ይባስ መለመሉን እናስቀረዋለን፡፡ ጨዋታ ያስባለው ድምቀትና ውበቱ ያለው በኪነ ጥበብ ዘርፍ በመደብናቸው ላይ ነው፡፡ ከ294 የባሕል ስፖርቶቻችን መካከል አንደኛው በሆነውና ስፖርትና ጥበብ የተጣመሩበት በማይመስለው፣ በአፋር ኮኤሶ ጨዋታ ውስጥ እንኳን ሁለቱንም እናገኛለን፡፡ እጅግ በርከት ባሉ የባሕል ስፖርቶች ውስጥ ኪነ ጥበባዊ እሴት የሞላባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በስፖርቶቹ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የእኛ በምንላቸው ቱባ ጥበባት ውስጥም እንዲሁ የባሕል ስፖርቶች ብቅ ሲሉበት እንመለከታለን፡፡ እነኚህ ሁሉ ነገሮችም በሁለቱ ዘርፎች ለሚሠሩ አካላት በተናጠል የየራስ የሆነውን ይዞ ከመሄድ ይልቅ፤ ወደ ቀደመው ከፍታቸው ለመመለስ አብሮ በመሥራት ውስጥ ብቻ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ የባሕል ጨዋታዎቹን ማሳደግ ኢትዮጵያዊ ስፖርትን እና ኢትዮጵያዊ ኪነ ጥበብን ማሳደግ መሆኑን አውቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡

ባሕል የሚል ስም ተነስቶ የባሕል ስፖርትና የባሕል ጥበባት ትስስር የላቸውም ለማለት አንችልም፡፡ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ስንመለከት ስፖርትና ኪነ ጥበብ ለየቅል ናቸው። አንዱ በሌላው መድረክ ላይ በትርፍነት ለማጀብ ይገባ ይሆናል እንጂ፤ ዝምድናው የተራራቀ ነው፡፡ የእኛም እሳቤ በዚህ የተቃኘ በመሆኑ በባሕል ስፖርቶቻችን ውስጥ ያለውን ኪነ ጥበባዊ ማዕድን ልብ አላልነውም፡፡ ሁለቱንም በአንድ ፌስቲቫል ላይ በአንድ መድረክ ብናቆማቸው ያለውን ውበትና ድምቀት ከመመልከታችን ባሻገር፣ ከመሐከላቸው እስከዛሬ ያልተመለከትነው አዲስ ነገር ይወጣል፡፡

ሌላኛው መንታ መንገድ ደግሞ፤ በራሱ “ባሕልና ኪነጥበብ” በምንለው መንገድ ውስጥ አንዳንድ ርምጃዎቻችን መቃኘት ይኖርባቸዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የቆምነው እጅግ በበዛ ልዩነት ውስጥ ነው፡፡ ለሚመለከተን እንኳንስ በአንድ ሀገር ውስጥ በአንድ ዓለም ላይ ለመኖር የማንችል ዓይነት እስክንመስል፣ አራምባና ቆቦ ዓይነት የባሕል እሴቶች ያሉንም ጭምር ነን፡፡ ውስጡ ግን አንዳችን ያለ አንዳችን ምንም ነን፡፡ ልዩነት እንደ ስያሜው ቢሆን ኖሮ ለእኛ መጥፊያችን በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን የእኛ አብሮነት፣ አንድነትና ፍቅራችን መመሳሰላችን ሳይሆን ልዩነታችን ነው፡፡ ውበታችን ጎልቶ የሚወጣው በዚያ ውስጥ ነው፡፡ ሰው ሆነን የተፈጠርንበትን ይህን የተፈጥሮ ሕግ የናድነው ዕለት፣ ፍርስራሹ የሚከመረው በማንም ሳይሆን በራሳችን ላይ ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ…ብንሆን፤ የተፈጠርንበትን ኢትዮጵያዊነት የዘነጋን ጊዜ ሰው መሆን አበቃልን፡፡ ዛሬ ዛሬ ይህን እየዘነጋን ለማፈንገጥ በሞከርን ቁጥር አልሆን እያለን ድንብርብራችን የሚወጣው ምስጢሩ ይሄው ነው፡፡ እዚህ ጋር ታዲያ ባሕልና ኪነ ጥበብን ምን አመጣቸው? እንል ይሆናል፡፡ ግን እኛ ብቻ ሳንሆን የእኛ የሆኑ ነገሮችም አፈጣጠራቸው እንዲሁ ነው፡፡

ባሕልና ኪነ ጥበብ…የሚል ነገር ስንሰማ ሁለት የተለያዩ ነገሮች መስሎ ይሰማናል፡፡ ችግሩ እንዲህ መረዳታችን ሳይሆን ለባሕሎቻችን ሟች ነን የምንባል፤ ስለ ኪነ ጥበብ ምንም ስሜት የማይሰጠን ጥቂቶች አይደለንም፡፡ የእኛ ስለሆኑ የኪነ ጥበብ ሀብቶቻችን ቸል ብለን ባሕላችንን እንጠብቅ ማለት ዘበት ነው።

ምክንያቱም ባሕል የምንላቸው አብዛኛዎቹ ጥበባት ናቸው፡፡ ጥበባት ብለን የምንጠራቸውም እንዲሁ ባሕል ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከላይ በጨረፍታ እየተመለከትናቸው ካልሆነ በስተቀር፣ ጠልቀን ወደ ውስጥ ስንገባ አንዱን ከሌላው ለመለየት ይህ ነው ብለን ስያሜ ልንሰጣቸው እስከማንችል ድረስ አንድ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ብዙ አርቀን ከመመልከታችን የተነሳ፣ ጠጋ ብለን መመርመር ስንጀምር፤ ባሕል ኪነ ጥበብ ሆነ ወይንስ ኪነ ጥበብ ነው ባሕል የሆነው? የሚል ጥያቄ ይወጣዋል። ለአብነት ሽለላን እንውሰድ። እያንዳንዱ ማኅበረሰባችን ውስጥ በየቋንቋው ሽለላን ያውቃል። ይከውናል። ከጥንት ጀምሮ የነበረው ባሕሉ ነው። ከጥበብ ሐረግ ላይ የመዘዘው ጥበባዊ ክዋኔው ነው። እንግዲህ ይህንን ባሕልና ኪነ ጥበብ በሚለው ሐረግ ውስጥ አብዛኛዎቻችን ካለን እሳቤ አንጻር ከባሕል ወይንስ ከኪነጥበብ ወገን እንመድበው? ይህን ጥያቄ መጠየቅም ልክ ከዶሮና ከእንቁላል ማን ነው ቀድሞ የተገኘ? ማንስ ማንን ወደ ሕይወት አመጣ? ብሎ እንደማለት ነው፡፡ ነገር ግን፤ እኛነታችን የሆኑ ነገሮች በሙሉ እንዲህ ካለው ጥያቄ ጋር የማይሄዱ ናቸው፡፡ ማወቅ ያለብን ትልቁ ነገር የትኛውም ቢሆን ያለ አንደኛው ከዛሬ ወደነገ መሄድ የማይችል መሆኑን ነው፡፡

ባሕልና ኪነ ጥበብ ሲባል ሁለቱን ከሁለት ቅርጫት ውስጥ አንፈልግ። በጥንት እናትና አባቶቻችን ውስጥ ባሕልና ኪነጥበብ፣ ሥጋና ደም እንደማለት ናቸው። “ሰው” የተባልነውና የተፈጠርነው በሥጋ አሊያም በደም ብቻ አይደለም። ከሁለት አንዱ ቢጎድል እንዴትስ ነው በሁለት እግር ቆመን ሰው ለመከወን የሚችለውን ግብር ለመፈጸም የሚቻለን? ሁለት ስያሜ የሰጠናቸውን ያህል ሁለት አይደሉም። “ሰውነት” ተብሎ የሚጠራው ሰው ስያሜውን ያገኘው በየትኛው የአካል ክፍሉ ነው? በእጅና እግሮቹ? በሆድና ማጅራቱ? በፊቱ ወይንስ በጭንቅላቱ? ለውስጥ የሰውነት ክፍሎቹ ወይንስ ለውጫዊ አካላቱ….ሁሉም ስሙ የሚገባው ለኔ ነው ቢሉ የሚገባው ለማን ነው? አሊያም እንካፈለው ቢሉስ? እዚህ ውስጥ በተናጠል ለመቆም ተፈጥሮም አይፈቅድም፡፡ አንደኛው የአካል ክፍላችን ቢታመም፤ ሕመሙ የመላው አካላችን ነው፡፡ እግርን እንቅፋት ቢመታ፤ ራስ ቅል ከላይ ነኝ ብሎ እንዴትስ ነው ተርፌያለሁ ለማለት የሚችለው…አንዱን መጠበቅ ሌላውን ማዳን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ባሕል እንዲኖረን የምንፈልግ፣ ኢትዮጵያዊ ኪነ ጥበብ ልንወድ ይገባል፡፡ የእኛ የሆኑ ቱባ ኪነ ጥበባትን ከሻትን የእኛ ስለሆኑት ባሕሎቻችን ልንቆረቆር ያስፈልጋል፡፡

ኪነ ጥበባዊ ባሕሎቻችንን ለመጠበቅና ወደ ሀገርም ሆነ የዓለም አደባባይ ለማውጣት መሥራት ያለብን የመጀመሪያው ቦታ የት ነው? እንዲህ ዓይነቶቹን ኪናዊ ሀብቶቻችን ያሉት በከተሞች አደባባይ ላይ ይመስለን ይሁን ወደዚያው ስናበዛ ይስተዋላል፡፡ ፍለጋችንን የተሳሳተ ባንልም፣ በትክክለኛው ቦታ ላይ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከምንም ከማንም ጋር ያልተበረዘውን ባሕላዊ ኪኖቻችንን ለማሳየት የምናደርጋቸው አብዛኞቹ ፌስቲቫሎች፣ ከአዲስ አበባ ከወጡ ከክልል ከተሞቻችን አልፈው አይሄዱም፡፡ ወደ ማኅበረሰቡ ብለን ወጥተን ከከተሞች ውጪ ንቅንቅ አንልም፡፡ ስለ ባሕል ጥበባት ለመመልከትም ሆነ ለማስመልከት፣ ማኅበረሰቡ ዘንድ ወርደን ከምንጩ ያለምንም ትወና ለመመልከት የምንችላቸውን ብዙ ነገሮች በዓመታዊ ፌስቲቫል ካልሆነ በስተቀር አይዋጡልንም፡፡ የአፋርን ማኅበረሰብ ጥንታዊ የባሕል እሴቶች ፍለጋ የሚታየን የሰመራ ትርዒት ብቻ ከሆነ… ስለ አሸንዳና፣ ሻደይ እንዲሁም አሸንድዬ ትርዒት ለማየትና ለማሳየት ዓመት ጠብቀን መቀሌ፣ ደሴ አሊያም በባሕርዳር አደባባዮች ላይ ብቻ የምንገናኝ ከሆነ…ስለ ጊፋታ አሊያም አዳብና ጥናትና ምርምር ለማካሄድም ቢሆን ለመምከር የምናሰባስበው፣ ምሑራንና ባለሥልጣናትን ብቻ በሚጋብዝ አዳራሽ ውስጥ ከሆነ፤ በእርግጥም ከባሕልና ኪነ ጥበብ ጋር አልተገናኘንም፡፡

ዛሬ ላይ አይታዩም፣ ተረስተዋል፣ ጠፍተዋል የምንላቸው ብዙ ነገሮች በባላገሩ ዘንድ የኑሮ ዘዬው ሆኖ የምንመለከትበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ ብዙውን ጊዜ የምናካሂዳቸው የባሕል ፌስቲቫሎች ደግሞ፤ የባሕሉን ባለቤቶች የዘነጉ ይሆናሉ፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ የባሕል እሴቶች የሚገኙት በባላገሩ ዘንድ ሆኖ ሳለ፣ ጥቂቶችን ብቻ ይዘን ከተሞች ላይ የሙጢኝ ካልን እንዴትስ ነው ልንጠብቃቸው የምንችለው? ብዙ ነገሮች እንዳሉት አውቀን በባሕልና መሰል ጉዳዮች ውስጥ ከገበሬውም ጋር ልንጠጋ ይገባል፡፡ በሚዲያዎቻችን እንኳን ባላገሩ ስለ ስንዴና ማዳበሪያ…ካልሆነ በቀር፤ ስለ ባሕልና ጥበባት ሲያወራ መስማት እንደ ተዓምር ነው፡፡ ትርዒቶች ወሳኝ ነገሮች ሆነው ሳለ፣ በምንጠቀምበት መንገድ የትና ከማን ጋር ቢሆን ነው የተሻለ ለውጥ መፍጠር የምንችለው ማለት ያስፈልገዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ “አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል” እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ባሕል ብለው የባሕል ስፖርት፣ ጥበብ ብለው ባሕልና ኪነ ጥበብ ቢሉ፤ አንዱን ሰው እጅ፣ እግር፣ ጆሮና አፍንጫ…እያሉ እንደመቁጠር ነው፡፡ ነገሩ ሳይንሳዊ ይሁን ጥበባዊ፤ የኢትዮጵያዊነት ቀመር የተጻፈበት ረቂቅ ነው፡፡ “ሦስት ብርጭቆ በግርግዳ ላይ፤ አንዱ ቢሰበር ስንት ይቀራል” የሚለው ጨዋታ ለእነዚህ ኪነ ጥበብ፣ ስፖርት እና ባሕል ለሚሉ ለእነዚህ ብርጭቆዎች አይሠራም። ምክንያቱም ከአንዱ መሰበር በኋላ የሚቀር ምንም የለም።የአንዱ መሰበር ማለት የሁሉም መሰበር ነውና፡፡ አንዲት ሃሳብም ብዙ መንገድ ናትና እንዲህ ታሽከረክራለች፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You