
እውነታውን ማጤን የጀመርኩበትን ጊዜ ሳስብ ብዙ አጋጣሚዎቼን ታዘብኳቸው:: ከዕለታት በአንዱ ቀን ነበር… በመሃል አራዳ ጊዮርጊስ፣ በማዘጋጃ ቤት የቁልቁለት መንገድ ቁልቁል ወደ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ማቆልቆል ጀመርኩኝ:: ድንገት ግን በጠራራው ፀሐይ ሰማዩ አለቀሰ:: እንዲህ ያለውን ክስተት “ጅብ ወለደች” አይደል የምንለው…በመሃል ከተማ የተወለደችውን ጅብ ባልመለከትም፣ እኔም እንደሰው ሁሉ ከዝናቡ ሽሽት መጠለያ ፍለጋ ሮጥኩኝ:: የዛሬን አያድርገውና እዚያች ጋር የነበረው የመጽሐፍ መደብር ከዓይኔ ገባና ዘው አልኩበት::
የመጽሐፍ መደብሩ እንደ አብዛኛዎቹ የአራት ኪሎ ኪዮስኮች አይደለም:: በአራቱም ማዕዘናት ግርግዳውን ታከው የቆሙ መደርደሪያዎች ቢኖሩም፤ ቤቱ ሰፊና “ፈረስ የሚያስጋልብ” የሚባልለት አይነት ነው:: ከውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች በአንድ ሥራ ተጠምደዋል:: ከመሃከል አንዱን መጽሐፍ ብድግ አድርጌ መመልከት ጀመርኩ:: እንደ አንዳንድ ካፍቴሪያና ምግብ ቤቶች ‹ሳያዙ መቀመጥ ክልክል ነው!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ከቤቱ ግርግዳዎች ላይ ባይጻፍም፤ በደመነብስ መጽሐፍ ወደ መግዛት ይሁን ወደመመልከት ገባሁ:: ልክ ድንገት እንደወረደው ዝናብ ሁሉ፣ ደመነብሳዊ በሆነ የድንገቴ ሃሳብ ውስጥ ሳለሁ ነበር የሁለቱን ሁኔታ የተመለከትኩት::
ከሁለቱ አንደኛው የመጽሐፍ መደብሩ ባለቤት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መጻሕፍት ለመግዛት የመጣ፣ ራሱ መጽሐፍ ሻጭ ነው:: የመደብሩ ባለቤት በመጋረጃ ወደ ተከለለው የኋላ ክፍል ሄድ መለስ እያለ ያሉትን መጻሕፍት እያመጣ ከፊቱ ይቆልለዋል:: ገዢውም ብድግ እያደረገ በግራና በቀኝ በሁለት ጎራ ለይቶ ያስቀምጣቸዋል:: በአንደኛው ወገን የለያቸውን፣ ባለቤቱ አንስቶ ወዳመጣበት ሲመልሳቸው ገዢው ያልፈለጋቸው እንደሆኑ ገባኝ:: ባለቤቱ ከውስጥ ሲመለስ አሁንም አምስት ያህል አዳዲስ መጻሕፍትን አምጥቶ፤ “እኚህን እንኳን ብትወስዳቸው…የተሻሉ…” ከማለቱ ገዢው አለመፈለጉን የገለጸበት መንገድ የአዲስ መጽሐፍ ዓይነ ጥላ ያለበት ያህል ተረገፈገፈ:: “አ..አይ..ይ አይ! አዲስ መጽሐፍ ይቅርብኝ:: ምንም አይነት አዳዲስ መጻሕፍት ላለመያዝ ወስኛለሁ” አለ፤ በመረረውና ቁርጥ ባለ አነጋገር መጻሕፍቱን አገላብጦ ለማየት እንኳን ሳይፈቅድ::
ለመግዛት ከያዝኩት መጽሐፍ ቀድሞ ቀልቤን የገዛው ይሄው ሁኔታውና ንግግሩ ነበር:: ዞር ብዬ የመራረጣቸውን መጻሕፍት በዓይኖቼ ቃኘኋቸው:: መርጦ በቆለላቸው ከ30 በላይ በሚሆኑ መጻሕፍት ውስጥ ምንም ዓይነት አዲስ መጽሐፍ ያለበት አይመስልም:: የነጋዴው በአዲስ መጻሕፍት መንገሽገሽ እንቆቅልሽ ሆነብኝ:: ጠጋ አልኩና “እኔ ምልህ…አዳዲስ መጻሕፍት አልፈልግም ስትል ሰማሁ…” ስል ምክንያቱን ጠየቅሁት::
የቅድሙን ምሬት ረስቶ በልዝብ ቸልታ፤ “ምን ታደርገዋለህ፤ የሥራው ባህሪ ነው” ካለኝ በኋላ ብጠብቅም ምንም ሳይለኝ ሥራውን ቀጠለ:: የማላውቀው አንዳች የተለየ ነገር ያለ መስሎ ተሰማኝና መልሼ እንደገና ያንኑ ጥያቄ ደገምኩለት:: “ቆየት ያሉ አሮጌዎቹን ካልሆነ በስተቀር አዳዲስ መጻሕፍትን ለማንበብ የሚፈልግ የለም” ሲለኝ፤ ለምን? ልለው አልኩና ለምን ላድክመው ብዬ ተውኩት::
እንደ ዋዛ የተመለከትኩት ነገር ሃሳብ ጭኖብኝ አረፈው:: ወጥቼ መንገዱን ሳዘግም ይህንኑ በሃሳቤ አመናትለው ገባሁ:: ይሄኔ ከወራት በፊት በአንድ የግል ታክሲ(ራይድ) ውስጥ የገጠመኝ ነገርና ሾፌሩ ያለኝ ትዝ አለኝ:: ከያዛት አዲስ መኪና ከኋላኛው ወንበር ላይ ፈልሰስ ከማለቴ፣ ድንገት ከፊተኛው ወንበር ጀርባ ላይ “ያንብቡ” የምትል ደማቅ ጽሁፍ ተመልከትኩ:: ከጽሁፉ ዝቅ ብሎ ካለው የወንበር ኪስ ውስጥ ጋዜጣና መጽሔቶች ከአንድ መጽሐፍ ጋር ተቀምጠዋል:: በነገሩ መገረሜ አልቀረም:: እንደኛ ሀገር እንዲህ ያለው ባህል ተረስቷል:: ምክንያቱም በፊት በመዝናኛ ሥፍራዎችና በሊስትሮ ወንበሮች ላይ እንኳን ይነበብ ነበር:: ስለገረመኝ ግን ጠየቅሁት፤
“ምን ዋጋ አለው…” አለኝ::
“እንዴት?” አልኩት፤ ተስፋ ያስቆረጠውን ምክንያት ለማወቅ::
“ከዚያ ኪስ ውስጥ የሚወጡትና በእጅ የሚዳሰሱት ምናልባትም መኪናዋን ሳሳጥብ ብቻ ነው:: ደፍሮ ንክች የሚያደርጋቸው የለም…” እያለኝ ድንገት የመኪናዋን ጥሩንባ አደበላለቀው:: ከወኋላ ከወዴት እንደመጣ፤ በአራቱም በኩል ከመጨራመቱ የተነሳ በጎማ ብቻ የሚሄድ የሚመስል ላዳ ለጥቂት ስቶን ወደፊት ቱር አለ:: ሾፌሩ ንዴትና ቁጣው ተደባልቆ ያወረደው እርግማን ላዳውን በአፍጢሙ የሚደፋው ነበር የሚመስለው:: እኔም እስኪበርድለት ጥቂት ጠብቄ፣ መኪናው ውስጥ ለሠራት ሚጢጢዬ ላይብረሪ አድናቆቴን ከገለጽኩለት በኋላ “እንዲህ ዓይነቱን ነገር ስላለመድን ተሳፋሪው እዚህ ቁጭ ብሎ የማንበብ ወኔ አይመጣለትም::
…አሁን አዲስ ሆኖበት ባይለምደው ምናልባት ወደፊት…” ከማለቴ አቋረጠኝና “አይምሰልህ…ስላለመደው ብቻ ሳይሆን አዲስ ነገር ስለማይፈልግም ጭምር ነው:: ብዙሃኑ አሮጌ አፍቃሪ ነው” ካለኝ በኋላ “ሁለትና ሦስት ህንጻ አቁመው፣ በየቀኑ መኪናቸውን ሲያስጎትቱ የሚኖሩ ብዙዎችን አውቃለሁ” ያላትን ንግግር ከመጀመሪያው ሃሳብ ጋር ለምንና በምን እንዳገናኘው ግራ እየገባኝም ዝም ብዬ ለማድመጥ ወሰንኩ::
“የኛ ማህበረሰብ አዲስ ነገር ይፈራል:: አጼ ምኒልክ ከዘመኑ ጋር ለመሄድና ሕይወትን ለማቅለል ስልክ ቢያስገቡ ሀገሬው ምን አለ…ቲያትር ቤት ከፍተው ተዝናኑ፣ ተማሩ ዓለምን እወቁ ቢሉ ሰይጣን ቤት ብሎት አረፈው:: በቃ እንዲህ ነን:: የምናውቀውን እንጂ የማናውቀውን ነገር ማወቅ አንፈልግም” ያለኝን ነገር አስታውሼ ነገር ከነገር፣ አጋጣሚውን ከአጋጣሚው ጋር ሳጋጥመው እውነት የሚመስል ነገር ታየኝ::
“አሮጌ መጽሐፍ እንገዛለን” ይህን ጽሁፍ በየመጽሐፍ መሸጫው ብቻ ሳይሆን በየመብራት ፖሎች ላይ ሳይቀር እናነበዋለን:: ግን ለምን አሮጌ መጽሐፍ ብቻ? “አሮጌ” ማለትስ… የቆሸሸ? ከተጻፈ የቆየ? የአሮጌነት መለኪያውስ ምንድነው? እንደ አንዳንዶቻችን እሳቤ አሮጌ መጻሕፍት መፈለጋቸው፤ ነጋዴው በቅናሽ ገዝቶ በደንብ ለማትረፍ ስለሚያስችለው ነው:: እንደሌሎቻችን ደግሞ በድሮ መጻሕፍት የሚፈለጉ ብዙ ታሪክና ዕውቀት በመኖሩ ነው:: እኚህም ሆኑ ሌላ እውነተኛ ነገሮች ናቸው:: ከዚህ በስተጀርባ ያለው ነገር ግን፤ የአሮጌ መጻሕፍት መፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ የአዳዲስ መጻሕፍት መገፋትም አለበት::
አንባቢ ትውልድ ጠፋ የሚለው ሮሮ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፣ የሚያነብ ሰው መጥፋት ብቻ ሳይሆን፤ አንባቢውም ከሚነበበው የዘመን ጥበብ ጋር በመጠፋፋቱ ነው:: በስምና ዝና የሚያውቀውን የጥንቱን ካልሆነ በስተቀር፣ አዲስ አዲሱን ዓይንህ ላፈር ማለቱን ከአንድ መጻሕፍት ሻጭ ሳረጋግጥ በግሌ አስገርሞኛል:: “አሥር አዳዲስ መጻሕፍትን ከመያዝ፣ ሁለት አሮጌ መጻሕፍት ያዋጣል” አለኝ:: እንደምን ያሉትን ብለው፤ “በተለይ ሽሮ መልክ ገጾች ያሏቸው ቆየት ያሉት” ሲለኝ ግን ግራ ይገባኝም ጀመረ:: አሮጌዎቹ ይህን ያህል ከተፈለጉ፤ ገበያው ላይ ለአዳዲስ መጻሕፍት ቦታ ያሳጣው ምኑ እንደሆን ብጠይቀው ካለመፈለጋቸው ውጪ ሊነግረኝ የሚችለው ነገር አልነበረም:: በእርግጥም ይህ ትልቅ ጥናትም የሚያስፈልገው ነው::
ዛሬ ላይ ሥነ ጽሁፍ በዘመን ጥበብ ውስጥ መቆርፈዱን ለማወቅ፤ ወደ አንደኛው የአራት ኪሎ መጽሐፍ መሸጫ ጎራ ማለት በቂ ነው:: ያነባል የሚባለውም ከዛሬ ጋር ተጣልቷል:: አዲስ የወጣን አንዱን መጽሐፍ ብንጠይቅ፣ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከነጭራሹ “…የሚባል መጽሐፍ አለ እንዴ?” ተብለን መጠየቃችን አይቀርም:: እስቲ ከምትወዱትም ሆነ ከምታውቁት መጽሐፍ ስንባል፤ ሁላችንም አንድ ዓይነት መጻሕፍት፣ ተመሳሳይ ስሞችን የምንጠራው ወደን አይደለም… መጥራታችን ሳይሆን አብዛኛዎቻችን የምንጠራው ሲጠሩ የሰማነውን መሆኑ ነው:: የትናንትናዎቹን የምን ጊዜም ምርጦች አድርገን፣ ለዛሬ ደግሞ የዛሬ ምርጥ ያስፈልገናል:: ከሌሉም እንዲኖሩ ማድረግና መፍጠር እንችላለን:: የአሁኖቹ ምርጦቹና ጀግኖቻችን አብዛኛዎቹ በራሳቸው ዘመን ቦታ ያልነበራቸውና የተገፉ ነበሩ:: ይህን ልማድ አድርገን የእኛን ዘመን ጀግኖችና ምርጦች የሚመርጡልን ቀጣዮቹ ትውልዶች ከሆኑ ታሪካዊ ስህተት ማውረሳችን ነው:: በእኛ ዘመን በእኛው ተጽፎ፤ እኛ ሳናነበው የሚያነብልን ትውልድ እየጠበቅን ከሆነም የሚያስፈራ ነው:: ሁሉንም ነገር “በእጅ ያለ ወርቅ…” አድርገን እንዴትስ ይዘለቃል…ገበያው ለአዳዲሶቹ መጻሕፍት ቦታ ስለሌለው በውድ ታትመው በርካሽ ይቸበቸባሉ::
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የሚሸጡት መጻሕፍቶቹ ሳይሆኑ የጸሀፊዎቹ ስም ነው:: በደራሲው አለመታወቅ ብቻ፣ መጽሐፉ አይፈለግም:: ሳናነበው የአንድን መጽሐፍ ረብ የለሽነት የሚገልጠውን ጥበብ ከወዴት እንደተማርነው ባይታወቅም፤ የዛሬ መጽሐፍ የሚለየው ገና በሽፋኑ ሆኗል:: “መጽሐፉን በሽፋኑ አትገምተው” የሚለውን ሕግ ጥሰነዋል:: የትኛው መጽሐፍ ቀርቶ፣ የማን መጽሐፍ ማለት ብቻ ከሆነ፤ በዝና ቲቮዞ ብቻ የሚመራ ሥነ ጽሁፍ ወደገደሉ መውደቁ ነው:: አሁንም እያልን ያለነው፣ በስም የምናውቃቸውን አናንብ ሳይሆን፤ አዲስ ነገር የማየት ፍላጎታችን አናሳ በመሆኑ፣ ተጨማሪ አዲስ ነገሮችን እንዳንመለከት አድርጎናል ነው:: የአዳዲሶቹንም እያነበብን በማበረታታት ልናጀግናቸው ስንችል ፊት ነስተን ይባስ ፈሪ እያደረግናቸው ነው:: ሳይነበብላቸው በምንስ ሞራል፣ ምን ተመልክተው የተሻሉ ነገሮችን ይፍጠሩ…መጥፎ ወይም ጥሩ ለማለት ቅድሚያ ማንበብ ያስፈልጋል:: ምርጥ ጸሀፊያን የአንባቢው ውጤት ናቸው:: ሰው የወለደውን ሲስሙለት ደስ እንደሚያሰኘው ሁሉ የጻፈውን ሲያነቡለትም እንዲሁ ነው:: ትናንት የነበሩ አንባቢያን የትናንትናዎቹን ብዕረኞች ፈጥረዋል:: እኛም ትናንትን ከማውራት ያለፈ የራሳችን ነገር ያስፈልገናል::
ሰው ሁሉ ዛሬውን ማወቅ አይፈልግም:: አዲስ ነገር አንብቦ፣ አዲስ እውቀት አይሻም:: ሰው እንዴት ዛሬ ላይ ሆኖ ትናንትን የሙጢኝ ይላል? የራሱን ዛሬ ትቶ እንዴት በሰው ትናንትና ላይ እንዳቀረቀረ ደንዝዞ ይቀራል? ትናንትናን ለዛሬ እንድንማርበት እንጂ፤ ትራስ አድርገን የሞት እንቅልፍ እንድናንቀላፋበት አይደለም:: ሎሬት “ፍቅርን ፈራን” እንዳለው ሁሉ እኛም አዲስ ነገር ፈራን…ሰው ጋዜጣና መጽሄት ማንበብ ትቷል፤ ለምን? ሲባል የማንበብ ባህል ስለጠፋ ብቻም አይደለም:: ጋዜጣነቱን ብቻ ሳይሆን የዛሬ ጋዜጣ መሆኑን የሚፈራም አለ:: ዛሬ የወጣውን አንብብ ከምትለው፣ የ1950ዎቹን ቢያገኝ ደስታው ነው:: አሁንም ለምን? ሲባል ምላሹ ትናንትን ወዶ ሳይሆን ከዛሬ ተጣልቶ ነው የሚመስለው::
ከወዲህ የትናትናው ባህላችን እንዳይጠፋ፣ እንዳይሸረሸር እንበል እንጂ፤ የዘመንን ጥበብ ትናንት ላይ ማስቀረት በዛሬ ላይ የሚፈጸም ትልቅ በደል ነው:: ወለፈንዲ በሆነ አስተሳሰብ ውስጥ ዕውቀትና ጥበብ ከትናንት ብቻ ይመስላል:: ስለ ዛሬ፤ ዛሬ ላይ የተጻፈውን ሳናነብ እንዴትስ ነው የዛሬ እኛነታችንን ለመገንባት የሚቻለን…አዲስ ነገር፣ አዲስ ዕውቀት ካልፈለግን አዲስ ነገር መፍጠር አይቻለንም::
ትናንትን በዚህ ልክ መውደዳችን በጣም ጥሩ ነገር ነበር፤ ግን ውጤቱ ጥሩ እንዳይሆን ዛሬን ከነመፈጠሩ ረሳነው:: የዘመን ጥበብ አካሄዷ የሚሰምረው፣ በትናንት ድልድይ ወደ ዛሬ ስንመጣ ነበር፤ እኛ ግን ፊታችንን አዙረን በትናንትና ድልድይ ወደ ትናንት በስቲያ እየሄድን ነው የሚመስለው::
እጅግ አብዝተን የምንወዳቸው የትናንትናዎቹ ነገሮቻችን ለምንድነው ዘምነው ከዛሬ ጋር ለመሄድ ያልቻሉት? ስንል፤ ምክንያቱ ከኋላ ወደፊት መሄድ ሲገባን ከፊት ወደኋላ ስለምንራመድ ነው:: በትናንት መሠረት ላይ ቆመን ዛሬን ከመሥራት ይልቅ ትናንትን ማውራት፣ ከትናንት ወደ ዛሬ ከመምጣት ይልቅ ከትናንት ወደ ትናንት በስቲያ መጓዝ ይቀርበናል:: ስለ ዓድዋ እያወራን ዓድዋን መኖር ከተሳነን እንዴትስ ይሆናል…በትናንትናው የእነርሱ ጽድቅ ብቻ ዛሬን ስለመጽደቅ ማሰብ ሞኝነት ነው:: የእነርሱ ሥራ ለእኛ እንደሆነው ሁሉ፣ እኛም ለነገዎቹ መሥራት ግድ ይለናል::
አሁን ላይ “…ድሮ ቀረ” የማንለው ምን ነገር አለን? ችግሩ፤ ድሮ የቀረው እሱ ሳይሆን እኛው ራሳችን ነን:: የእኛ ሥራ የሆነውን ነገር ለመሸሽ ስንል ሁላችንም በዘመን እያመሃኘን እጥፍ እንላለን:: ይሄው አባዜ ወረርሽኝ ሆነና ጥበብም በዘመን ቁጥር ውስጥ ተቀበረች:: ጥበብ ብለን ድሮ፣ የጥበብ ሰው ብለንም ድሮ…ከዘንድሮ ጋር ለመታረቅ ካልቻልን፤ ወደፊትም የዘንድሮ ነገር እንዳቃረን መቀጠላችን ነው:: በተመሳሳይ መልኩ ትናንትን ጥለን የምንፋተገው ከዛሬው ጋር ብቻ ቢሆን ኖሮም፤ እንዲሁ ካገኛት ንፋስ ጋር ሁሉ የምትነፍስ እፉዬ ገላን መስለናል ማለታችን አይቀርም ነበር:: ምክንያቱም ያለ ትናንት ዛሬን ብቻ ብንኖር፣ ከዛሬ ያለፈ ነገ አይኖረንም::
የድሮዎቹን ዓይነት ፍለጋ የገባነው አንባቢያኑ ብቻ ሳንሆን ጸሀፊያኑም ጭምር ነው:: ትልቁ ችግር ግን ሥነ ጽሁፋችን ከድሮም ከዘንድሮም ተጠፋፍቶ መላቅጡ መጥፋቱ ነው:: የራስን ዘመን የራስ ጥበብ ፈጥሮ ካላስቀጠሉት የዘመን ጥበብ ውድቀቷ ይበዛል:: እየሆነ ያለውም ይሄው ነው:: በሙዚቃ፣ በግጥም፣ በድርሰት በሌላም በሌላውም ሁሉ፤ ብዙዎቹ አንድ ዓይነት ነገር፣ አንዱን እንደዳዊት እየደጋገሙ እኛንም ያሰለቹን ሁላችንም አዲስ ነገር በመፍራታችን ነው:: ድሮን ወደን እንደ ድሮ ሳንሆን፣ ዛሬን ይዘንም የዛሬን ሳንኖር፤ ግራጫ መልክ ለብሰን በመሃል ቤት ተጎልተናል:: በዘመን ውስጥ ቱባ ባህሎቻችን እንዳይሸረሸሩ በስጋት በምንቃትትበት በዚህ ጊዜ፣ ከወዲህ ደግሞ ኪነ ጥበባችን አንድ ዘመን ላይ በአንድ ነገር ፈጧል::
እንደኛ ከሆነማ፤ እንኳንም ሀዲስ ዓለማየሁ በዚህ ዘመን አልተፈጠሩ:: እንኳንም በዓሉ ግርማ በዚህ ዘመን ጽፎ ጉዱን አላየ:: እንኳንም በዛብህ እና ሰብለወንጌል በዚህ ትውልድ ባተሌ መሃል ሆነው ፍቅራቸው ሳይታይ መና አልቀሩ:: ይብላኝላቸው ለአሁኖቹ፤ ጸጋዬና ፊያሜታ ጊላይ እንደሆኑ በደህናው ጊዜ በበዓሉ ግርማ ምናብ ተወልደው አመለጡ:: ይብላኝልን ለእኛ እኛን ለማናውቀው… እኚህ ሁሉ የተጻፉት ዛሬ ላይ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም እንደ አብዛኛዎቹ ሁሉ ሳይታወቁ ይኖሩም ይሆን ነበር:: እነርሱ በራሳቸውን ዘመን የራሳቸውን ሕይወት መስለው ኖረዋል:: ደራሲያኑ የኖሩትን ጽፈው፣ የነበሩትንም ተደራሲያን ደርሰዋል:: ይህ ትውልድም እኮ የራሱ ዘመን፣ የራሱ ታሪክና የራሱ የሆነ ጥበብ ያስፈልገዋል:: የእነርሱን ዘመን ልንጠብቅላቸው፣ ጠብቀንም ከራሳችን ዘመን ጋር ለቀጣዩ ትውልድ ልናስተላልፈው እንጂ፤ አዲስ ነገርን ፈርቶ ጥበብ አለኝ ማለት ከንቱ ነው:: ድሮን መውደድ ከዘንድሮ፣ ዘንድሮን መውደድ ከድሮ ሊያለያየን አይገባም:: አንዱን ብቻ ለመምረጥ የምንገደድበት የፖለቲካ ምርጫም አይደለም:: “መ” ሁሉም መልስ በሆነ ጥያቄ ውስጥ፣ የምናውቀውን “ሀ”ን ወይም “ለ”ን አሊያም ደግሞ “ሐ”ን ብናከብብ፤ ስህተት ተብሎ ነጥብ የማያሰጠን ቀሪዎቹን ባለማካተታችን እንጂ ያከበብነው መልስ ለመሆን ስለማይችል አይደለም:: ባነሳናቸው ንባብና ሥነ ጽሁፍ ውስጥ ተምሳሌት አድርገን ብዙ ነገሮቻችንን እንድናስተያይበት ነውና በገላጣው ከፊት ብቻ እንዳንመለከተው::
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም