ሎላትና ፊላ

ማለዳ ንጋት ሲበሰር ሎላት በመንደሩ ሎላትን የሚቀድም የለም። ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አቅንተው በጋርዱላ ዞን በደራሼዎች መንደር ውስጥ ድንገት የተገኘ በዓይኖቹ አግራሞትን በጆሮው ደስታን መሸመቱ አይቀርም። በፊላ ጨዋታ፣ ከፊላው ጥበብ ስር፣ ሎላትና ፊላን እየሰማ ከእነዚህ ውብና ማራኪ ስሜቶች ለመራቅ የሚፈቅድ አይኖርም።

ከአንደኛው እጅ ላይ እንደ ንጉሥ ፈረስ ቀጥ ብሎ፣ ሽቅብ ተደላድሎ፣ ከትንፋሽ ጋር ተዋዶ፣ ድምጹን ሲያሰማ…እንደ ባሕር ዳርቻ አየር ከድባቴ ያነቃል። ከድምጹ ጋር በስሜት ይንጣል። ጠዋት ማልዶ ወፍ ሲንጫጫ ደራሼዎች የሎላትን ድምጽ ለመስማት ይናፍቃሉ። ይጠባበቃሉ። ይህን ድምጽ ሰምተው የነቁ ዕለት ቀናቸው ብራ ነው። ፈሪውን ጀግና ፊታውራሪ ያደርገዋል። ተቃቅረው ማዶ ለማዶ የቆሙትን ከፊላው ስር አገናኝቶ ያፋቅራል። ያለግነት ሎላትና ፊላ ከደራሼዎች በባሕል ብቻ ሳይሆን በነብስም የተጋመዱ ናቸው።

ደራሼዎች ባሕልን ከጥበብ አስተሳስረው “ፊላ” እና “ሎላት” የተሰኙ ሁለት የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎችን አበጁ። ሙዚቃዊ ስልትና ዜማዊ ቀመርን አዋህደው፣ ሎላትና ፊላን እንደ አንድ አደረጓቸው። በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነው ተገለጡ። አንድ ሆነው ጆሮ ገብ፣ ሱና ልብ እንዲሆኑ ልዩነታቸውን ውበት አደረጉ። ታዲያ በአንዱ ሙዚቃዊ ሕብረ ዝማሬ ውስጥ የሁለቱም ድምጽ የየራሳቸው የሆነ አገልግሎት አላቸው። ለደራሼዎች ይህ ዓይነቱ ሙዚቃዊ ቀመር ግልጥ ያለ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ነው።

“ፊላ” በደራሼ ማሕበረሰብ ዘንድ በአንድ ልዩ ሁኔታ ውስጥ የሚዘወተር ባሕላዊ የትንፋሽ ሙዚቃቸው ነው። በሠርግ፣ በበዓላት፣ በሁነቶች እና በደቦ ሥራዎቻቸው ውስጥ ያለ ፊላ እግራቸውን አያነሱም። ቢሠሩ ድካም፣ ቢበሉና ቢጠጡ ሆድ መሙላት ብቻ ይሆንባቸዋል። እናም በእነዚህና በሌሎችም መስተጋብሮቻቸው ውስጥ ሙዚቃዊ ጨዋታውን የግብራቸው አንድ አካል ያደረጉታል። ጨዋታው በፊላና ሎላት ብቻ የተገደበ አይደለም። በጦርና ጋሻ የታጀበ ዝላይና ፉከራ መሰል የጋራ ጨዋታም አላቸው። ታሪክ፣ ፍቅር፣ ጀግንነትና አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና የሚያሳዩበት ልዩ ትርዒት ያለው ነው። እዚህ ጋር ከፊላ ቀድሞ የሚደመጠው ድምጽ የሎላት ነው። ምክንያቱም ሎላትን የሚጠቀሙት አንድም ተዘጋጁ ለማለት ፊሽካውን የሚነፉበት ነው። ድምጹን በሰሙበት ቅጽበት እያንዳንዱ እርምጃውን ይጀምራል። ሙዚቃዊ ጨዋታውን ለመጀመር ፊላውን የያዘ ሁሉ ከአፉ ይደግነዋል።

ፊላ አንድ ራሱን የቻለ ባንድ ማለት ነው። በየመጠናቸው ተለክተው የተሠሩና በቁጥር በዛ ያሉ ፊላዎች አንድ ላይ ይሰለፋሉ። ትልቁና ወፍራሙ ቶንቶሊያ (ካሳንታ) የተሰኘው ፊላ ከፊት የሚሰለፍ ፊታውራሪው ነው። ካሳንታን ተከትለው ሌሎችም እንደመጠናቸው እየተደረደሩ እስከመጨረሻዋ ፊትን ፊታያ ድረስ እንደ ብርቱ ጦረኛ ሠራዊት ከሚጫወታቸው እጅ ላይ በረድፍ ይቆማሉ። ከአፍ ተደግነው፣ አፋቸውን ቁልቁል አድርገው የየራሳቸውን መሳጭ ዜማ እየለቀቁ፣ ሕብረ ዝማሬውን ይሠሩታል። እያንዳንዱ የፊላ ተጫዋች የሚያወጣው ሙዚቃዊ ትንፋሽ የድምጾቹን መድረሻና መገናኛ እየቀየሰ፣ በጋራ አንድ ዓይነት ሙዚቃዊ ምትን ይፈጥራል። ምቱን ተከትለው የሚጨፍሩ ወደ ጭፈራው ይገባሉ። ሎላት እዚህም ጋር ይሰማል። ጨዋታው ደብዘዝ የማለትና ነገር ከታየበት ሎላት ይነፋል። እንደማንቂያና ማነቃቂያ ደወል ነው። ይሄኔ ብንን ብለው ስሜታቸውን የሚነቁ ብዙ ናቸው። የሎላትን ድምጽ ሰምቶ ባለበት እንደነበረው ሆኖ ለመቀጠል የሚቻለው የለም። ታዳሚው እንኳን በጭብጨባና በፉጨት ያቀልጠዋል።

በዚህ ጊዜ ላይ ሎላትን እንድናነሳ፣ በፊላ ቅኝት አብረን እንድንቃኝ የሚያደርገን ምክንያት አለ። በጋው ወደኋላ እየሸሸ፣ ክረምቱም ከፊት እየገሰገሰ ነው። ገበሬውም የሰቀለውን ሞፈርና ቀንበር የሚያወርድበት ነው። መጋልና ቡሬም ኃይላቸውን አጠናክረው ቀንበሩን ለሁለት፣ ሞፈሩንም እየገፉ አፈሩን ለመጉድፈር አንድ ሁለት በማለት ላይ ናቸው። የዝናቡን ጠብታ ተከትሎ በግልና በደቦ ከአፈሩ ጋር የሚማስነው ገበሬ፤ በየአካባቢው፣ እንደየባሕልና ቋንቋው ለዚህ የሚሆን የጥበብ መብርቻ አለው። ከመላው ተፈጥሮ ጋር የሚግባባበት ልዩ የባሕልና ጥበብ ቋንቋ አለው። እርፉን ከማረሻው፣ ማረሻውን ከቀንበሩ፣ ቀንበሩን ከበሬው አድርጎ መሬቱን የሚያለማው ገበሬ፣ ባሕሉን ከሥራ፣ ሥራውን ከጥበብ ጋር አቆራኝቶ ድንቁን ኪነት ያለመልማል። የሰማይና የምድሩን እየተመለከተ፣ ደመናና ብራውን፣ ፀሐይና ዝናቡን እያጤነ ከጊዜው ጋር እንደጊዜው ይኳትናል።

ይሄኔ ሎላትና ፊላም በዚያ አካባቢ የገበሬው ቀኝ እጅ ሆነው አብረው ደፋ ቀና ይላሉ። ደራሼዎች በልዩነት፤ ለየብቻ በግል ከመሥራት ይልቅ በቡድን ተጣምረው በጋራ የመሥራት ልማድ አላቸው። ለምሳሌ ከ2-7 አባላትን የሚይዘው “ዳኤታ” ይሉታል። “ኦርቶማ” የሚሰኘው እንዲሁም ከ20 አባላት በላይ የሚያሳትፈውን “ካላ” ጨምሮ ሌሎችም ዓይነት አንድነታዊ የደቦ ሥራ ክፍሎች አሏቸው። በሥራ ብቻ ሳይሆን፣ ለስድስት ሆነው አንዱን “ማይራ” የተሰኘውን የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያንም ይጫወታሉ። ከፊላና ሎላት በስተጀርባም ያላቸው ብዙ ነው። በተለይ ከጥር መጀመሪያ እስከ የካቲት መጨረሻ፣ በእህል አጨዳና መሰብሰቢያ፣ ከዚያም ድል ባለው የጥጋብና የእረፍት ጊዜ ላይ ሁለቱም ወገባቸውን አስረው የሚነሱበት ነው።

ጊዜና ባሕል፣ ጥበብና ዘመን በበጋና በክረምቱ አብረው እያወጉ የሚሄዱት አንድም በደራሼዎች መንደር ውስጥ ነው። በጥበብ እዋዛ ከአንዱ ተዋዶ ከሌላው ተጋምዶ የፊቱን ለመያዝ ይገሰግሳል። ታዲያ በደራሼዎች መንደር ሲደርስ ሁሉም ነገር ከሎላት ጋር ነው። ሽርብትን የሚለው በፊላ ነው። ክረምትና በጋ ፊት ለፊት ተገናኝተው ሲተላለፉ፣ ደራሼዎቹም አንዱን ሸኝተው ሌላኛውን ሲቀበሉ በሎላት አጅበውና በፊላ ጭፈራ ሞቅ ደመቅ አድርገው ነው።

ከአየሩ ለውጥ ጋር ጊዜ ጠብቀው ለሚያከውኗቸው ግብሮች ብቻ ሳይሆን፣ ለሚመጣና ለሚሄደው የሰው እንግዳም በፊላውም ቢሆን በሌላው ከሎላት ድምጽ ጋር ነው። ከፍቅራቸው ትንፋሽ የሚወጣው ሙዚቃዊ መዓዛው ማስታወሻና መታወሻ የሚሆን የልብ ስጦታ ነው። የበጋው መሄድ የክረምቱን መምጣት እያበሰረ፣ ወደ መስኩ እንዲረባረቡ ሌሊት ማልዶ ይቀሰቅሳቸዋል። ቀኑን ሲያበረታና ጉልበታቸውን ሲያድስ ውሎ፣ ማታም ከድካም ስሜት ይገላግላቸዋል። የደራሼ ሕጻናት ልጆች፣ ወጣት ወንዶችና ኮረዳ ሴቶች፣ አባወራና እማወራው ሁሉ በሚስረቀረቀው የሎላት ድምጽ ሀሴት ያደርጋሉ።

በደራሼዎች ባሕል ውስጥ በመጀመሪያ ጥበብ ነበር፤ ጥበብም ሎላትን አበጀ። ሎላትን ለማበጀት የአጋም እንጨት ወይንም የሳላ ቀንድ ወሳኝ ነው። ቀንዱን አሊያም እንጨቱን በመጠንና ቅርጹ ያስተካክሉታል። የትንፋሽ መግቢያና ድምጽ መውጫ ሙዚቃዊ ስሌቱንም እየለኩ ነድለው፣ ቆርጠውና ገጣጥመው ከሠሩት በኋላም፤ ቅቤ እየለወሱ እስኪጠግብ ያጠጡታል። ከዚያም ከቤታቸው የእሳት መደብ በላይ ከሚገኘውና “ቅሻይት” እያሉ ከሚጠሩት ቆጥ ላይ ይሰቅሉታል። ይህን የሚያደርጉት የጠጣው ቅቤ በጭስ ተንፏሎ በደንብ እንዲወዛ ነው። እንደ ሁኔታው ለቀናት አሊያም ለሳምንታት ከጭሱ ካሰነበቱት በኋላ አውርደው ደግሞ በስነ ውበት ይጠበቡበታል። በፍየል ሪዝና በላመ ቆዳ እየለበጡ ሌላ አዲስ መልክ ያሲዙታል። በመጨረሻም ሎላትን እንደ ልዕልት በልዩ ልዩ ጌጣጌጦች ያንቆጠቁጡታል። በኪነ ጥበብ፣ በስነ ጥበብ እንዲሁም በስነ ውበት እየተራቀቁ ለሙዘቃ ያበቁታል። ሎላት፤ ፊላ በሌለባቸው ጊዜና ቦታዎች እንኳ አይታጣም። ከብዙ መሞዘቂያ መሳሪያዎቻቸው በላይ አብልጠው የሚወዱትና የሚያዘወትሩት ሎላትን ነው።

ሎላት፤ ከባሕላቸው የተቀበሉት፣ ለባሕላቸው የሚኖሩበትና መልሰውም ለባሕላቸው የሚሰጡት የጥበብ ልሳናቸው ይሆናል። ሎላት ቃላትን ባያወጣ ድምጹ በሰሙ ቁጥር ሁሉ ዜማው ያግባባቸዋል። በጠዋቱ እንደየሁኔታቸው ሆነው ከየቤታቸው ታዛ ስር ያሉ ደራሼዎች፤ ድንገት የሎላትን ደምጽ የሰሙ እንደሆን ቀጥሎ አንድ ነገር አለ ማለት ነው። ሁሉም ልብና ጆሮውን ለመልዕክቱ ይሰጣል። ለአንድ ነገር ተዘጋጁ ይላቸዋል። ማልደው ለእርሻ አሊያም ለአደን የተቃጠሩ አባዎራዎች፣ የሎላትን ድምጽ የሰሙ እንደሆን፤ ለቀጠሮው ነግቷልና ኑ! ውጡ የሚል ልዩ መልዕክት ይደርሳቸዋል። በዚያው ቅጽበት ሁለትና ሦስት ዓይነት የሎላት ድምጽ ቢሰማ እንኳ፤ እነርሱን የሚመለከተውን ከድምጹ አወጣጥ ለይተው ያውቁታል። ልክ እንደ ቃላት የድምጽ አወጣጡ የራሱ የሆነ የመግባቢያ ኮድ አለው። ጠዋት ተጠራርተውና ተያይዘው የወጡ ሰዎች፣ ከእርሻም ይሁን ከአደን አመሻሹን ተመልሰው ከቤታቸው አቅራቢያ ሲደርሱ ሎላት ያንጧርሩታል። “ከውሏችን በሰላም ተመልሰናልና በቶሎ የሚበላና የሚጠጣ ይዘጋጅልን” የሚል መልዕክት አለው። ከቤት ያሉ እማወራና ልጆችም በፍጥነት ጉድ ጉድ በማለት አንዱ የሚበላ፣ ሌላውም መታጠቢያ ውሀ፣ ቡናው..ሲኒው…ረከቦቱ…ከያሉበት ብድግ ነሳ ተደርገው ወደፊት ይቀርባሉ።

ፊላ በግዝፈትና ቁመቱ ሎላትን ያጥፋል። ድምጹን ሲሰሙት ብቻ ሳይሆን ገና ሲያዩት ግርማ ሞገሱ ለዓይን ይከብዳል። በእጅ ያምራል። ድምጹም እንዲሁ የሚያስገመግም ነው። ማስገምገም ብቻም አይደለም፤ ከወደ አፍ ጠበብ ብሎ ከአፋ ጋር የተጋጠመው ጫፉ፣ ቁልቁል ተመዘግዝጎ ከታች ሰፋ ካለው ክብ ቅርጹ ውስጥ የሚወጣው ድምጽ ውበት ያለው የቋንቋ ሕብረ ዝማሬ ነው። እንደ አብዛኛዎቹ የትንፋሽ መሣሪያዎች ቀጭን ወይም አጭር አይደለም። ፊላ በዓይነት፣ በቁመት፣ በመልክና በግዝፈት፤ በተለያየ መጠን ይሠራል። ነገር ግን ሁሉም የፊላ መጫወቻዎች የሚዘጋጁት ከተመሳሳይ ግብአት ነው።

በአሠራር ሂደቱ ውስጥ ሸንበቆና ቀርክሃ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። በድምሩ ከ24 እስከ 32 የሚደርሱ ቁርጥራጮች ይዘጋጃሉ። እኚህም እንደ አስፈላጊነታቸው ከ5 ሴ.ሜትር እስከ 1 ሜትር ባለው ይቆራረጣሉ። የሚዘጋጁበት ቅርጽም በአንደኛው ክፍል ክፍት በሌላኛው ጫፍም ድፍን እንዲሆኑ በማድረግ ነው። አንዱን ከአንደኛው እየገጣጠሙና እየቀጣጠሉ እንደዋዛ ቆንጆ አድርገው በልዩ ጥበብ ይሠሩታል። በፊላ አሠራር ውስጥ የምንገረምበት አንድ ነገር፤ ሦስት ዓይነት የድምጽ ልኬቶች (ቤዝ) እንዲኖራቸው መደረጉ ነው። ወፍራም፣ መካከለኛ እና ቀጭን ድምጾችን በአንድ ላይ እንዲያወጣ የሚያስችለውን ቀመር ቀምረው ያስቀምጡበታል። የድምጽ ፍሰቱን ጠብቆ ከላይ ወደታች እየተንፎለፎለ ሲወርድ በቅንብር የተዘጋጀ ረቂቅ ሙዚቃ ይመስላል።

ፊላ እንደሎላት በሁሉም ጊዜና ቦታ ላይ አይገኝም። አንዳች ወሳኝ የሆነ ሁኔታና አጋጣሚን ይጠብቃል። አንድ ጊዜ ሲነሳ ግን ማብረጃ የለውም። ትልቁ አገልግሎቱ ሙዚቃዊ በሆኑ ጨዋታና ትርዒቶች ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያ ሆኖ ማገልገል ነው። ደራሼዎች ሰብሰብ ብለው በተገናኙባቸው ክብረ በዓላትና መሰል ዝግጅቶች ውስጥ በክብርና በግርማ ሞገስ ይገኛል። እንደ ሠርግ ያሉ ድምቀት ናፋቂ ሥነ ሥርዓቶች ያለ ፊላ አይደረግም። ከሎላት ጋር አብረው ሲገማሸሩ፣ ሁለቱም ሌላ አንድ ጥንድ ይመስላሉ። ፊላ ባለው ሙዚቃዊ ባሕሪ ለብቻው ያለ ሰዎች ድምጽ ሊደመጥ የሚችል ነው። የተለያዩ ዓይነት ድምጾችን ማውጣት የሚችል በመሆኑ፣ በድምጻዊው ድምጽ ሲታጀብ በቀላሉ ለማጣጣምና ለማዋሃድ አይቸግርም። በሦስተኛ ደረጃ የተወዛዋዡን የጭፈራ ስልት ይሰጣል። ይጠብቃል። ልክ ጎንደርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ጉራጊኛ…የምንላቸው ሙዚቃዎች የየራሳቸው ሙዚቃዊ ምትና ሪይትም እንዳላቸው ሁሉ፤ ፊላም በአጨዋወቱ የራሱ የሆነ ምትና ሪይትም አለው። እኚያ ከ24-32 የሚደርሱ ቀርክሃና ሸንበቆዎች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ድምጸት የሚሰጡ ናቸው። ይህ በዘመናዊው የሙዚቃ መሳሪያ ውስጥ እንኳን ለማድረግ የማይቻል ምትሀታዊ ጥበብ ነው።

በሎላትና በፊላ ውስጥ የሚገኝ ድንቅ ባሕል፣ ድንቅ ጥበብ፣ ግሩም ጨዋታ ብለን አድንቀን ብቻ እንድናልፋቸው አይገባም። እኚህን መሰል ቱባ ጥበባትን ስናነሳ እንዴት አሳድገን ዘመናዊው የጥበብ ኢንዱስትሪ ልናመጣቸው እንችላለን የሚለውንም እንድናስብበት ነው። እያንዳንዱ ማሕበረሰባችን እንዲህ ባሉ ጥበባት ውስጥ የታደለ ነው። ያለን የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን፤ በተፈጥሮ ማንነት ውስጥ የበቀለ ጥበብም ጭምር ነው። የእኛ አባቶችን ፈልስፈው ከሰጡን፣ እኛ ደግሞ እኚህን የማዘመን ኃላፊነት አለብን። መፍራት ያለብን ማዘመኑን ሳይሆን ማፍረሱን ነው። የነበረውን አጥፍተን በሌላ መተካቱን ነው እንቢ ማለት የሚኖርብን። የኢትዮጵያን የባሕል ጥበባት ወደዘመናዊነት እንቀይራቸው ማለት፤ በብዙዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ እንዳለው፣ ከባዕዱ ጋር ቀላቅለን ወደ ባዕዳን ዓለም እንሂድ ማለት አይደለም። ከባሕላዊነት ወደ ዘመናዊነት መሻገር ማለት ቀሚስ አስቀድዶ ሱሪ እንደማስፋት ወይንም ሱሪው ቆርጦ ቁምጣ እንደማድረግ ያለ ለውጥ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የነበረውን እንደነበረው አድርጎ “ማደስ” የሚለው ይገጥማል።

ስለዚህ ሁሉንም እንደ ፊላና ሎላት ተመለከትን፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዴት አድርገን ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ማሰብ፤ አንድም በዘመናዊው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ፈንታ ነው። ሁል ጊዜ ጊታርና ኪቦርድ ላይ ብቻ ከማተኮር፣ ወረድ ብለን ምን አለ የሚለውን ከራሳችን ብንፈልግ የሚሆነንን አናጣም። የባሕል ሙዚቃ መሳሪያዎቹን ወደ ከዘመናዊው ጋር ማዋሃድ ብቻ ሳይሆን፤ አንድ የባሕል ሙዚቃ መሳሪያ የተሰራበትን ቀመር ወደ ኢንዱስትሪው ማምጣትና ይዘትና መልኩን ሳይቀር እድሳት ማድረግ ይቻላል። በዚያ ቀመር መሠረት ከየትኛውም ዓለም ዘመናዊው የሙዚቃ መሳሪያ ጋር ሊገዳደር የሚችል፣ አዲስ ኢትዮጵያዊ ግኝት አናጣበትም።

ሎላትና ፊላ ግን አሁንም ከደራሼዎች መንደር ውስጥ ድምቀትና ውበትን አያጎድሉም። ሎላት በመረዋ ድምጹ ጡርር! ባላበት ቅጽበት፣ ከየቤቱ ተያይዘው ሲከንፉ ከትውፊታዊው አደባባይ ላይ ይገናኛሉ። ግዙፉ ፊላ ቶንቶሊያ እንደ ዳልጋ በሬ ሻኛ፣ እንደ ዝሆን ኩንቢ እየተንጎማለለ፣ ትንሽዬዋን ፊትንፊታያን አስከትሎ ይደርሳል። ጦርና ጋሻ ተያይዘው ሲወነጨፉ ይከሰታሉ። ሎላት ግን አሁንም ሳይታክትና መንጧረሩን ሳያቋርጥ፣ ከዚም ከዚያም ቱር! ቱር! እያለ በማካለል ቅስቀሳውን አጧጡፎ ደራሼዎቹን ከአንድ ያሰባስባቸዋል። ድምጻዊያኑ ድምጻቸውን ሞርደው፣ ተወዛዋዦቹ መላ አካላቸውን እያፍታቱ ለጭፈራው አዘጋጅተው ቦታ ቦታቸው ላይ ይሰየማሉ። ካሳንታ ፈርጠም ብሎ ከፊት እንደቆመ፣ እርሱን ተከትለው በሦስት መሪዎች የሚመራ 3 ረድፍ ይፈጥራሉ። የግራ ቀኝ ጠቋሚው ሎላት አሁንም ሁሉንም እየቃኘ ምልክት ይሰጣቸዋል።

ሎላት ያለውን ውስጣዊ ሀይሉን በመጠቀም በተቻለው ተስረቅርቆ ደወሉን ሲደውል፣ የሁሉም ጨዋታ ጅማሬ ይሆናል። የፊላዎች ውህድ ሕብረ ዝማሬ፣ የጨፋሪዎች የእግር ኮቴና ስልታዊ ውዝዋዜ፣ ከፊት የታዳሚው የእጅ ጭብጨባና ፉጨት…በመሃል ሎላት ተገልብጦ በቀጭኑ በኩል ድምጹን ሲያሰማ፣ የነበረው ጨዋታ አክትሞ፣ በሌላ አዲስ ስልት ይቀየራል። ሎላት እንደ ፊሽካ ጡርር! ይላል፤ ዲታ! ዲታ! …በእግር ድም! ድም! ጭፈራው ከእጅና ወገብ ወደ እግር ይወርዳል። ሙዚቃና ጨዋታ፣ ባሕልና ጥበብ ተያይዘው ተቃቅፈው እንደደሩ፣ ሎላት ለመጨረሻ ጊዜ ከመንጧረሩ በፊት ሁሉም ነገር ከደራሼዎቹ መሃል ይቀጥላል…

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You