ለምለም መንግሥቱ
ለሥራ ጉዳይ አሜሪካን ሀገር በሄዱበት ወቅት ነው። በአየር ማረፊያ ውስጥ ሆነው ከጎናቸው የቆመ አንድ ረጅም ጥቁር ሰው ዞር ብሎ ይመለከታቸዋል። ሊያናግራቸው እንደፈለገ ከሁኔታው ተረድተዋል። እርሣቸውም ገፍቶ እስኪያናግራቸው ጠበቁት። ሰውየውም ጠጋ ብሎ ‹‹ኢትዮጵያዊ ነህ?›› ብሎ ይጠይቃቸዋል።
ለማረጋገጥ እንጂ ደማቸው ኢትዮጵያዊ መሆኑ እንደሚመሠክር አላጣውም። እንዲህ ያለ ጥያቄ ሲያስተናግዱ የመጀመሪያቸው ባለመሆኑ ጥያቄውን ላቀረበላቸው ሰው በአዎንታ አንገታቸውን በመነቅነቅ አረጋገጡለት።
ሰውየው ለመግባቢያ ጥያቄውን ካቀረበ በኋላ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታላቅ ሀገር ነች›› ብሎ ያስከትላል። እርሣቸውም ልባቸው በደስታ ተሞልቶ በአፋቸው ‹‹አዎ›› ብለው መለሱለት። ‹‹ከኢትዮጵያ ብዙ ይጠበቃል፤ ጣሊያኖች ወርረውን ነበር አይደል?›› በማለት አከታትሎ ጠየቃቸው።
እርሣቸውም ያ ሰው ጣሊያኖች ወረሩዋችሁ ሣይሆን፣ ወርረውን ነበር ማለቱ እያስገረማቸው ሥሜቱን ለመረዳት ሞከሩ። መወረርን የራሱ አድርጎና እንደ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ‹‹አሸነፍናቸው አይደል?›› በማለት የእርሣቸውን መልስ ሣይጠብቅ አስረግጦ ይነግራቸዋል። እርሣቸውም በሰውየው የበለጠ ሐሴት አደረጉ።
ያ ሰው ጥቁር አሜሪካዊ ነው። ሚስተር ጃክሰን ብሎም ተዋውቋቸዋል። ግን የዓድዋ ድልን እንደራሱ አድርጎ እንዲያ ረገጥ ባለ ቃል ‹‹አሸናፍናቸው አይደል?›› ብሎ ለኢትዮጵያዊው የሕክምናና ሥነመለኮት ተመራማሪ ዶክተር ወዳጄነህ መሐሪነ ሐሣቡን ያጋራው። በዚህም ሣያበቃ ቀጠለ በነጭ የበላይነት ጥቁሮች ላይ ይደርስ የነበረው ጭቆና እና ግፍ ብሎም በ19ኛው ክፍለዘመን አውሮጳውያን ከአፍሪካ 12 ሚሊዬን አፍሪካውያንን በመርከብ ጭነው እንደ ዕቃ ላቲንና ኖርዝ አሜሪካን፣ ካሬቢያን ተወሥደው እንደተሸጡና በጥቁሮች ላይ ብዙ አንገት የሚያስደፉና ልብ የሚሠብር ድርጊቶች እንደተፈፀሙባቸው ይገልጻል።
አውሮጳውያኑ ይኼ አልበቃ ብሏቸው እኤአ በ1884 በርሊን ላይ ተሰብስበው አፍሪካውያንን ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ሥሜታቸውንና ሥነልቦናቸውን ባላገናዘበ አፍሪካን እንዴት ሊቀራመቷት እንደሚችሉ በወቅቱም መሥመር በማስመር ጭምር ድርሻቸውን እንደተከፋፈሉና እንደተነጋገሩ ሣይቀር የሚያውቁትን ታሪክ በማስታወስ ነበር በቁጭት ሲያጫውታቸው የነበረው።
ሰውየው በአፍሪካውያን ላይ የተፈፀመውን መጥፎ ታሪክ እንዲህ እያስታወሰ፤ ግን ደግሞ በሌላ በኩል ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን በኃይል ሊወር የመጣውን የነጭ ኃይል እንደአመጣጡ አሣፍረውና ድል አድርገው ልቡን ስላራሱለት ቁጭቱ በደሥታ መቀየሩን ነበር ዶክተር መሐሪነ በአጋጣሚ ያገኙት ሰው ያጫወታቸውን ያካፈሉን።
እርሣቸውም ከጨዋታው የተረዱት በእርሱ አዕምሮ ውስጥ ነጩ አሸንፎ ጥቁሩ ሰው ተንበርክኮ ነው። እርሣቸው እንዳሉት ይህ ሰው አስተሳሰቡ የሚቀየረው አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሀገር፣ ሀገሩ ኢትዮጵያ፣ ሕዝቡ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ሲያስታውስ ነው። የዚያ ሰው የጋለ ሥሜት የእርሳቸውንም አስተሳሰብ ቀይሮታል።
ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በአጋጣሚ ካገኙት ጥቁር አሜሪካዊ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ለዓድዋ ድል ያላቸው ክብር ጨመረ። ከዚያ በፊት ግን ብዙም ትኩረት የማይሰጡት፣ በዓመት አንዴ ሲከበር እንደማንኛውም በዓል አድርገው የሚያዩት እንደነበር ያስታውሣሉ። ቆይቶ ሲገባቸው ግን ‹‹የዓድዋ የድል በዓል ሁሌም ሲዘከር መኖር አለበት›› አሉ ለራሣቸው።
በአጋጣሚ ያገኙት ሰው ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ሀገር ነች። ከእናንተ እኮ ብዙ ይጠበቃል።›› ያላቸውንም በልባቸው እንዲይዙ ስላደረጋቸው የበለጠ ትኩረት ሰጡት። ‹‹ፓን አፍሪካኒዝም የሚጠበቀው ከኢትዮጵያ ነው። ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት ምሣሌ ሆኖ የተቀመጠው የዓድዋ ድል ነው። በመሆኑም አፍሪካውያን ኢትዮጵያ እንድትመራቸው ይጠብቃሉ›› ሲሉ ዶክተር ወዳጄነህ ይናገራሉ። እንዲህ ለአፍሪካ ኩራት የሆነ ድል እያለ ዛሬ እዚህም እዚያም በሚታየው የዘረኝነት ፖለቲካ መታመስ አግባብ አይደለም ይላሉ።
ስለ ዓድዋ ድል ያጫወታቸውና ልባቸውን በኩራት የሞላውን ሰው ዛሬ ላይ ቢያገኙትና አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተፈጠረው የዘረኝነት ጉዳይ ለመናገር እንደሚያፍሩ ነው የገለጹት። ‹‹ዓለም በጀግንነት የሚያውቃት ሀገር ዛሬ እርስ በርስ በዘር ፖለቲካ እየታመሠች እንደሆነች ከሌላ ጋር ለመጫወት ቀርቶ ለራስም መሥማት ያሣፍራል። ድላችንን መሠረት አድርጎ ዓለም እንደሚጠብቀን ሆነን መገኘት አለብን›› ሲሉም መክረዋል።
የዓድዋ የድል በዓል በመላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝቦች በሚኖሩበት ጭምር መከበር አለበት ብለው ያምናሉ ዶክተር ወዳጄነህ። የዘንድሮው ከአምናው በተሻለ ያውም ከየካቲት ወር መግቢያ ጀምሮ ወሩን ሙሉ የዓድዋ ድል በዓል እንዲዘከር መደረጉ አሥደስቷቸዋል።
ጥቁር አሜሪካውያን ከቁጭትም ባለፈ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል ወርሮ በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ተባርሮ ከወጣ በኋላ ቁጭቱን ለመወጣት 40 ዓመት በሠራዊት ኃይልና በዘመናዊ መሣሪያ ተደራጅቶ ዳግም ወረራ ባካሄደበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው ወራሪውን ለመመከት ጥያቄ አቅርበው፣ አንዳንዶችም ተመዝግበው እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
የታሪክ ተመራማሪና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሠር አበባው አያሌው፤ ታሪኩን እንዲህ አስታውሰውናል። እርሣቸው እንዳስረዱት ኢትዮጵያና አሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል ከመውረሩ በፊት ነው። በወቅቱም የአሜሪካን ቆንስላ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋቁሟል። አንድ ሁለቴም ወደ አሜሪካን ሀገር ልዑክ ተልኳል። መላኩ በያን የተባሉ ሰው ደግሞ አሜሪካን ሀገር ለትምህርት ተልከው ተምረዋል። በአሜሪካን ሀገር የሚታተሙ ጋዜጦችም ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯን በሥፋት ዘግበዋል። ይህ ሁሉ ከዲፕሎማሲ ሥራው ጋር ተደምሮ ጥቁሮች ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ወይንም ለመዝመት ዝግጁነት እንዲኖራቸው ምክንያት ሆኗል።
በጥቁሮቹ በኩል ፍላጎቱ ቢኖርም ከአንድ የአውሮፕላን አብራሪና ጥቂቶች በሥተቀር እንደፈለጉት ብዙዎቹ መጥተው አልተሣተፉም። ምክንያቱ ደግሞ የመጓጓዣ ወጭ ችሎ ከአሜሪካን ሀገር ኢትዮጵያ መምጣት የገንዘብ አቅሙ ለጥቁሮች የሚቻል አልነበረም። ጥቁሮቹ የጥይት ፋብሪካ እስከ መክፈት ወይንም እስከማቋቋም ድረስ ፍላጎት አሣይተው ነበር።
ኢትዮጵያ በዚያን ዘመን እስከመታወቅ ደርሣ ጥቁር አሜሪካውያንን እስከ ማነሣሣት ድረስ ስለደረሰው የዲፕሎማሲ ሥራ ረዳት ፕሮፌሠር አበባው ለቀረበላቸው ጥያቄ በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ ንጉሠ ነገሥት የአፃ ኃይለሥላሴ ንግሥና በዓለም የታወቀ እንደነበር ነው ምላሽ የሰጡት። የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴም ከዚያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስታውሠዋል።
መድረክ ላይ ወጥተው በሚሰጡት ሐሣብ ታዳሚን በመያዝና የያዙትን ሐሣብ እያዋዙ በማስተላለፍ በብዙዎች ዘንድ የሚወደዱት የሥነመለኮት መምህር መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ‹‹ዓይነቱና መጠኑ እንዲሁም የመዋጊያው መሣሪያ ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ጦርነት የሰው ልጅ ከገነት ከተባረረ ጀምሮ የነበረ ነው። ጦርነትን ማቆም አይቻልም። ነገር ግን ፍትሐዊ ወይንም ምክንያታዊ ማድረግ ይቻላል። ይህንንም ስል ዓድዋ ላይ የተደረገው ጦርነት ለኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ ነው። በጣሊያኖቹ በኩል ተገልብጦ ሊነገር ይችል ይሆናል እንጂ በኃይል ለመውረር የመጣችው ጣሊያን ናት። ኢትዮጵያ ሣትፈልግ ተገዳ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ አድርጋታለች›› በማለት ኢትዮጵያውያኑ በኃይል ሊወርራቸው የመጣውንም ኃይል መክተው በመመለስ ድል የተቀዳጁት ተገደው ሣይሆን ተደፈርን በሚል የአንድነት ሥሜት በመነሣሣታቸው ድሉ የጋራ ሊሆን እንደቻለም አመልክተዋል።
እንደ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ገለጻ፤ በዘፈን ወይንም በሽለላ ‹‹ኧረ ገዳይ›› እየተባለ የሚፎከረው በሽፍትነት ወይንም በአልባሌ ነገር ሰውን ለገደለ ሣይሆን፣ በግፍ ሀገርን ሊወር የመጣን የጠላት ኃይል አሣፍሮ በጀግንነት ግዴታውን ለተወጣ ነው። የሽለላ መልዕክቱም ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል። ዓድዋ ላይ ድል አድርጎ የሀገሩን ዳርድንበር ያስረከበው ጀግናም ‹‹ሀገርህ ተወርሯል። ብትችል በጉልበትህ፣ ባትችል በፀሎትህ ተብሎ ጥሪ የቀረበለት እንጂ ተገዶ የገባ ሠራዊት አይደለም›› ሲሉም የነበረውን የኢትዮጵያውያንን አንድነትና የሀገር ፍቅር አስታውሰዋል።
ከዓድዋው ጦርነት ወዲህ በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያን የገጠማት ጦርነት ላይ ወዶ ዘማች እንደማያስታውሱም ገልፀዋል። ድንቅ ታሪክ የተሠራበት የዓድዋ ድል እያለ በዚያ አለመኩራትና ኩራትንም አለመግለጽ ትልቅ የታሪክ ውድቀት እንደሆነ የተናገሩት መጋቢ ሐዲስ ታሪኩ ተሠንዶ ለሕዝብ የሚቀርብበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ለታሪክ ምሁራን መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ የዓድዋ ድልን ጨምሮ ሦስት የድል በዓላትን ታከብራለች። ሁለተኛው ከዓድዋ ያልተናነሰው የአርበኞች የድል በዓል ነው። ጣሊያን ዓድዋ ላይ ድል ተደርጎ ወደመጣበት ከተመለሰ በኋላ ለ40 ዓመታት በዘመናዊ መሣሪያና በሠለጠነ የጦር ሠራዊት ራሱን አደራጅቶ ዳግም ተመልሶ ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየበትም ጊዜ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ተጋድሎ ከሀገር እንዲወጣ በማድረግ ድል ተቀዳጅተዋል። ሦስተኛው የካቲት 12 የሠማዕታት መታሠቢያ ቀን ሲሆን፤ ዓድዋ ላይ ድል የተመታው ፋሽስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ከተማ 30 ሺህ የሚሆኑ ንፁሀን ኢትዮጵያውያንን በአደባባይ ላይ በግፍ የጨፈጨፈበት ነው። ይህ አረመኔያዊ ድርጊት ሁሌም ከኢትዮጵያውያን ልብ የማይጠፋ በመሆኑ በየዓመቱ ይታሠባል።
እነዚህ ድሎች ሲታወሱ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ይጠቀሣል። ማህበሩ ከተመሠረተ 85 ዓመት አሥቆጥሯል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ድሉን ከማክበር ባለፈ ማህበሩ መሪ ሆነው ማገልገላቸው ኩራት እንደሚሠማቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በቁጭት የሚናገሩት ነገር ቢኖር እነዚህን ትላልቅና የሀገር ኩራት የሆኑ የድል በዓላትን በማክበርና ጀግኖችንም በመንከባከብ ማህበሩ ከስምንት አሥርት ዓመታት በላይ ሲጓዝ ከመንግሥትም ሆነ ከሀገር ወዳዶች ማህበሩን የሚያጠናክር ተግባር በሚፈለገው ያህል አለመሆኑ ነው። የትኩረት ማነሱ እጅግ አሳስቧቸዋል።
ሁለተኛው ድል ወይንም የአርበኞች ድል ባይኖር ኖሮ ዛሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኮራበት የዓድዋ የድል በዓል አይከበርም ነበር ሲሉም አንስተዋል። ትውልዱ ከሀገሩ አኩሪ ታሪክ በላይ ስብዕናውን በማይገነባውና ማንነቱን በማይገልፀው መጤ ባህል ተጠምዶና የአውሮጳውያኑን ታሪክ ለማወቅ ጥረት ሲያደርግ እንደሚስተዋል ያስረዳሉ። ስለድሉ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ብቻ ሣይሆን የራሱ አድርጎ እንዲይዘውም በየሙያው የሚመለከተው ሁሉ ኃላፊነት እንደሆነ በማሳሰብ ነበር ሐሳባቸውን ያካፈሉት።
ስለዓድዋ ድል ያነበቡና የሰሙ ሁሉ የድል በዓል ቀኑ ሲደርስ ብቻ መታሰቡ አግባብ እንዳልሆነ ይሞግታሉ። የዛሬ 125 ዓመት ጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች ዓድዋ ላይ በኃይል ለመውረር የመጣን የጣሊያንን ጠላት በሰዓታት ውጊያ ያውም በኋቀር የጦር መሣሪያ ተዋግተው አሣፍረው ሲመልሱት በዓለም አቀፍ ሠበር ዜና ሆኖ ሲነገር ኢትዮጵያውያን እንኳን ቀድመው እንዳልሠሙ ታሪክ ያነበቡ ሲናገሩ ይሠማል። የዚህ ታሪክ ፈጻሚ የሆነች ሀገር በዓለም ሥሟ ከፍ ብሎ መነገሩና ሕዝቦቿም የዚያ ባለቤት መሆናቸው የሚያሣድረው ኩራትና ክብር በቀላሉ መታየት እንደሌለበት ሁሉም ሊገነዘበው፣ የዓድዋ ድል እንደወይን እየበሠለና እየጣፈጠ የሚሄድ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013