ለዱር እንስሳት ጥበቃ ተልዕኮ የተሰማሩ አነፍናፊ ውሾች

ትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች:: ካላት የሥነምህዳር ውበት እና የተፈጥሮ ሀብት አንፃር ዘርፉን የሚመጥኑ እንቅስቃሴዎች ለማሳለጥ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከውጪ ሀገር አነፍናፊ ውሻዎችን ማምጣቱ ታውቋል:: ይህንን እና መሰል ሃሳቦችን እንዲያጋሩን በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት እና ውጤቶቻቸው ዝውውር ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ጳውሎስ ጋር ቆይታ አድርገናል::

ሀገሪቱ የተለያዩ የዱር እንስሳት እና እጽዋቶች መገኛ ሀገር ናት:: እነዚህ የዱር እንስሳት እና እጽዋቶች በተለያየ መልኩ ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ:: እንደሀገር ለቱሪዝምም ሆነ ለብዝሃ ሕይወት ያላቸው ድርሻ ትልቅ ነው:: ይሁንና በትልቅ ችግር ውስጥ የሚገኙ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል::

እንደሳቸው ገለፃ፤ ከችግሮቹ መካከል ሕገ ወጥ አደን፤ ሕገ ወጥ ግጦሽ፤ ሕገ ወጥ የእርሻ ቦታ መስፋፋት ተጠቃሽ ናቸው:: እነዚህ ችግሮች በአካባቢ ጥበቃ ላይ ተጽዕኖ እያደረሱ ሲሆን፤ ለአብነት በሕገ ወጥ መንገድ የዱር እንስሳት የሚታደኑበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል:: ከታደኑ በኋላ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ:: ከሀገር የሚወጡትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: የሀገር ሀብቶች ከሀገር እንዳይወጡ በኤርፖርት በኩል ያለውን ቁጥጥር ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ፤ በዚህ ዓመት መጨረሻ ለተልዕኮ የሰለጠኑ አራት አነፍናፊ ውሻዎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ተደርጓል::

እነዚህ አራት የሰለጠኑ ውሾች እንደ ሕገወጥ አደን ያሉ በዘርፉ ላይ እንደ ችግር የተነሱትን በመከታተል ለመቆጣጠር እንዲሁም ለአካባቢው ሰላም አስፈላጊ እንደሆኑ ባለሙያው ጠቁመዋል:: ውሾቹን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቢያመጣቸውም፤ የሥራ ክንውኑ ከተለያዩ አካላት ጋር የሚሠራ እንደሆነ አስታውሰዋል:: ውሾቹ የመጡበትን ዓላማ ከማስተዋወቅ፣ ከማስረዳት አኳያ ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል:: በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 6/2017 የቆየው ስልጠና ዓላማቸውን በሚደግፉ እንደ ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አኒማል ዌልፌር እና ሌላ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ እንደሆነ አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል::

ውሾቹ በዘርፉ ላይ እየተሠራ ላለው ነባር የጥበቃ እና ሕጋዊ ማሕቀፍ ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል:: ላለው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጨማሪ ጉልበት እና የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ የመጡ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ለዚህ አገልግሎት እንዲውሉ ካደረጋቸው መሀል ቀዳሚው ተፈጥሮአዊ የማሽተት አቅማቸው መሆኑን አንስተዋል:: እኚህ ውሾች በሥነ ሕይወት እንደተረጋገጠው የሰው ልጅ ማሽተት ከሚችለው መቶ ሺህ እጥፍ የማሽተት ችሎታ እንዳላቸው የተናገሩት ባለሙያው፤ ይሄ ተፈጥሯዊ ችሎታቸው ለአደን እንዲመረጡ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል::

የአነፍናፊ ውሾች አገልግሎት በዱር እንስሳ ጥበቃ ባለስልጣን ውስጥ አዲስ ይሁን እንጂ፤ በሀገሪቱ በፖሊስ ማዕከል ውስጥ ወንጀለኛን አነፍንፈው እንዲይዙ፣ እንዲሁም በመከላከያ ውስጥ ፈንጂ የመለየት ተልኮ ተሰጥቷቸው እየሠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል:: ከዚህ አኳያ በዱር እንስሳት ላይ ላለው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዲውሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሊጠቀምባቸው እንዳመጣቸው አንስተዋል::

የውሾች አገልግሎት በዘርፉ ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው ያሉት ሃላፊው፤ በተለይ ሕገወጥነትን ከመከላከል፣ ከማጋለጥ፣ ከመቆጣጠር አኳያ የላቀ ሚና ያላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል:: የተለዩ ዝርያዎች መሆናቸው፣ በአገልግሎታቸውም ዓለም አቀፍ ግልጋሎት እየሰጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል:: አልፎ ተርፎም አውሮፓ እንደመገኘታቸው ለይቶና መርጦ ገዝቶ ለማምጣት እንዲሁም ለማሰልጠን ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል:: አያይዘውም እንደሀገርም ሆነ እንደተቋም ይሄን ለማድረግ አቅም ስለሌለ የአጋሮች ድጋፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን የተባለ ድርጅት አጠቃላይ ፕሮግራሙን ለመደገፍ ፍቃደኛ ከእነሱ ጋር መጠናቀቁን አመላክተዋል::

ውሾቹ ከአውሮፓ ተገዝተው ታንዛንያ ውስጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት አነፍናፊ ውሻዎችን የያዙ ለሕግ ማስከበር ሥራ የሚሆኑ ባለሙያዎች ወደታንዛኒያ ሄደው ለሁለት ወራት ስልጠና እንደተከታተሉ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል:: በአሁኑ ሰአት ውሾቹም ሆኑ ግለሰቦቹ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደኢትዮጵያ በመመለስ ወደሥራ ከገቡ አስራ አንድ ወራት መቆጠራቸውን አንስተዋል::

የማነፍነፍ አቅማቸው ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውሾች ለተለያየ ዓላማ ይውላሉ ያሉት ባለሙያው፤ ነገር ግን እንደዱር እንስሳት ጥበቃ መሥሪያ ቤት ግን ሊያነፈንፉ የሚችሉት የዱር እንስሳ ውጤትን እንደሆነ ገልጸዋል:: ውሾች ከሰለጠኑበት ሙያ ሌላ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸው፤ በመስሪያ ቤታቸው የሰለጠኑት ውሾች የዱር እንስሳት ውጤትን ካልሆነ ፈንጂም ሆነ አደንዛዥ እጽን እንደማያነፈንፉ ተናግረዋል:: በዚህም መሠረት አገልግሎታቸው ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከሕገ ወጥ አደን እና ከመሳሰለው ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ገልጸዋል::

በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ከፍተኛ የዱር እንስሳት ውጤት ዝውውር አለ የሚል ሪፖርት በየጊዜው እንደሚወጣ፤ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅትም ይሄኑኑ እንደሚያምን አስታውሰዋል:: እንደተቋምም ሆነ እንደአየር መንገድ ሀብትን ከመጠበቅ አኳያ መልካም ባለመሆኑ የውሾቹ እዚህ ሥራ ላይ መሳተፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል::

እንደአቶ ዳንኤል ገለፃ፤ አየር መንገድ ላይ ቁጥጥር አለ:: የተለያዩ የቁጥጥር ሥራዎች ይሠራሉ:: ስካነር፣ ሴኩሪቲ ማሽን፣ ፖሊስ፣ ጉምሩክ እነኚህ ሁሉ ደህንነትን ለመጠበቅ የሚሠሩ ናቸው:: ይሁንና በአንዳንድ ሁኔታዎች ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ:: ሲስተሙን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ፣ ካሉት የደህንነት ሥርዓቶች ጋር የተናበበ የደህንነት ሥርዓት መገንባት ስላለበት የውሾቹ መኖር ወሳኝ ሆኖ ተገኝቷል::

በተለይ ብዙ ጥያቄ እየተነሳበት ላለው ለሕገ ወጥ የዝሆን ጥርስ፣ ለአውራሪስ ቀንድ፣ ለፓንጎሊን ስኬል ዝውውር መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ በአየር መንገዱ በኩል ለሚፈጠር ለየትኛውም ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ውጤት ምላሽ የሚሰጡ እንደሆኑ ገልጸዋል:: በአሁኑ ሰአት አየር መንገድ ጊቢ ውስጥ በተሰራላቸው መኖሪያ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል::

ውሾቹ የሥራ ውሾች በመሆናቸው እንደቤት ውሾች የቤት ምግብ እንደማይመገቡ ገልጸው ፤ምግባቸው ከውጪ ሀገር እንደሚመጣ አመላክተዋል:: በስልጠና ወቅት በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ከነበረው ወጪ አሁን ላይ ለምግብ ፍጆታ እስከሚወጣው ድረስ ያለውን የሚሸፍነው ዋና አጋራቸው አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን እንደሆነ አቶ ዳንኤል አመላክተዋል::

በዱር እንስሳት መስክ ላይ የሰው ሠራሽ ችግሮች ብዙ ናቸው:: ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በሀገሪቱም በተለያዩ ቦታዎች ባሉት ሃያ አምስት በላይ ጥብቅ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ ከዋነኞቹ ተግዳሮቶች መሀል አብዛኛው ሰው ሠራሽ ችግር እንደሆነ አንስተዋል:: ወደጥብቅ ፓርኩ ከብቶችን ለግጦሽ ማሰማራት፣ እርሻ ማረስ፣ ፓርኮቹ ውስጥ ዛፍ መቁረጥ፣ የዱር እንስሳትን ማደን፣ ቁፋሮ ማድረግ በሕግ የተከለከሉ ድርጊቶች ናቸው ብለዋል::

‹‹ሰው ሕግና ሥርዓትን በመተላለፍ አጥፊ እየሆነ ነው:: ሁሉም ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ እነዚህ ችግሮች አሉ::›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ዳንኤል፤ የራስን ንብረት በራስ እጅ ማበላሸት ተገቢነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ለፓርኩ የህልውና ስጋትን የሚፈጥር ድርጊት እንደሆነ ጭምር ገልጸዋል:: ፓርኮች በሕዝብ የሚጠበቁ፣ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው መታወቅ እንዳለበት አስታውሰው፤ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ችግሩን ለመቅረፍ ከነባር ሥራዎቹ ጎን ለጎን አነፍናፊ ውሾችን ወደሥራ ያስገባው ከዚህ አኳያ ነው ሲሉ ጠቁመዋል::

እንስሳዎቹ በሕገ ወጥ ሰዎች እየተገደሉ፣ እየተሰደዱ ናቸው:: ለምሳሌ ጨቅላ አቦ ሸማኔዎችን ከነሕይወታቸው በመውሰድ ድንበር ላይ ባሉ አስተላላፊ ደላላዎች ከሀገር ውጪ ይሸጧቸዋል:: በዚህም የእንስሳዎች ቁጥር ከመቀነሱም በላይ የሀገር ሀብቶች ላይ ከፍተኛ ስጋትን እየደቀኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል:: እንደምሳሌ አቦ ሸማኔ ቢነሳም በሌሎችም እንስሳዎች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚፈጸም ነው የገለጹት::

ቦሌ ላይ ትኩረት የተደረገው ሕገ ወጥ ዝውውሩ የአየር ትራንስፖርትን የሚጠቀም በመሆኑ እንዲሁም አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው እንዲሁም ብዙ ሰዎች የሚጠቀሙበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አንስተዋል:: አንድ ሰው ሕጋዊ ፍቃድ ከሌለው ከሌላ ሀገር የዝሆን ጥርስ ይዞ በቦሌ አየር መንገድ ወደ ጀርመን፣ ወደ አሜሪካ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር አይችልም ብለዋል::

‹‹የእኛ ካልሆነ ኤርፖርት ላይ የምንከለክለው ለምንድ ነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም::›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተባብራ የዱር እንስሳት ሀብትን ለመጠበቅ የፈረመችው የሳይተስ ስምምነት አለ:: ይሄ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ መቶ ሰማንያ አምስት ሀገራት ፈርመውታል:: እነዚህ ሀገራት በሀገራቸው በኩል የትኛውንም ሕጋዊ ዶክመንት የሌለውን ሕገወጥ ድርጊት የመከላከለ፣ የመቆጣጠር ሃላፊነት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል::

ቦሌ ኤርፖርት የብዙሃን መተላለፊያ ነው:: ከኢትዮጵያም ይወጣል፤ ከሌላ ሀገርም በኢትዮጵያ በኩል ያልፋል:: የውሾቹ እዛ ቦታ መገኘት ይሄን መሰሉን ሕገወጥ ድርጊት ከማጋለጥ፣ ከመከላከል ብሎም ከመቆጣጠር አኳያ ሚናው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል:: እንደዚሁ የባለፈው ሳምንት ስልጠና አጋር ተቋማቱ ውሾቹ የመጡበትን ዓላማ ተረድተው በትብብር እና በቅንጅት ከጎናችን በመሆን አየር መንገዱ ላይ የሚፈጠርን የሕገ ወጥ ዝውውር ለመቆጣጠር ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ አንስተዋል::

የስልጠናው ውጤታማነት በሂደት እንደሚታይ ገልጸው፤ ስልጠናውን ባካሄዱ በሳምንቱ ከኤርፖርት ካርጎ ክፍል ከቦቶስዋና ከመጡ የእንስሳት ውጤቶች ጋር በተያያዘ መረጃ እንደደረሳቸው አንስተዋል:: ቀደም ሲል ዝም ብለው ያልፉ ነበር:: አሁን ላይ በተሠራው ሥራ ዝም ብሎ ማለፍ ስለሌለ ከስልጠናው በኋላ ነገሮች መስተካከል እንደጀመሩ ገልጸዋል:: በተለይ በዓለም አቀፉ ሕግ የተመዘገበ ዱር እንስሳ ከሆነ ሕጋዊ ሰነድ ከሌለ ያዙት የሚል ሕግ እንደተቀመጠ አንስተው፤ ስታንዳርድ ሰርተፍኬት በዶክመንቱ ውስጥ ካለ የዱር እንስሳት ውጤቱ ሳይያዝ እንደሚያልፍ አመላክተዋል::

የጋራ ትብብር ለሁለንተናዊ ጥቅም ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ እንደምሳሌ ሕገወጦች ከኢትዮጵያ ዝሆን ገለው ጥርሱን ወደሌላ ሀገር ይዘውት ቢሄዱ በጋራ ስምምነቱ መሠረት ወንጀለኞቹ ባሉበት ሀገር እንደሚያዙ አንስተዋል:: ሕግን ከማስከበር ረገድ እንደፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊሶች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት፣ ኢምግሬሽን፣ ኢንተርፖል ያሉ አካላት አብረዋቸው እንደሚሠሩ አመላክተዋል:: ከሕግ ማስከበር ሌላ እንደ ግብርና ሚኒስቴር፣ ብዝሃ ሕይወት ያሉ ተቋማትም አብረዋቸው እንደሚሠሩ ባለሙያው ገልጸዋል::

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እንደሃላፊነት የተሰጠውን የሀገሪቱን የዱር እንስሳት ሀብት በጥናት ላይ ተመርኩዞ፤ ህብረተሰቡን አሳትፎ፣ ሌሎች አጋር ድርጅቶችን አስተባብሮ የመጠበቅ፣ የማልማት እና ጥቅም እንዲሰጡ የማድረግ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየተጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: አያይዘውም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ብቻውን የሚሠራው ምንም እንደሌለ አንስተው፤ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ከመሆኑም በላይ እየተደረጉ ላሉ የሕግ ማስከበር ሥራዎች አቅም በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል::

አብረውት የሚሠሩ የተለያዩ አጋር አካላትን ያቀፈው መሥሪያ ቤቱ ከምንም በላይ የማህበረሰቡ ተሳትፎ ለሥራው አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል:: አክለውም ሕዝብ ያልተሳተፈበት የትኛውም ነገር ውጤት እንደማያመጣ ገልጸው፤ ህብረተሰቡ በዱር እንስሳት ጥበቃ እንቅስቃሴ ላይ በተሳትፎው ሚናውን እንዲወጣ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል::

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You