የሀገር ብሄራዊ ጥቅም እንዲከበር ሰላምና ደህንነቷ እንዲጠበቅ፣ ጸረ ሰላምና ጸረ ሀገር የሆኑ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እግር በእግር ተከታትሎ ማጋለጥ፣ መንግስትና ሕዝብን ማንቃትና ማሳወቅ፣ ራሳቸውን የሚያዩበት መስታወት ሆኖ መስራት የመገናኛ ብዙሃን ተቀዳሚ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡
መገናኛ ብዙሃን በተለምዶ አራተኛው መንግስት ተብሎ የሚጠራ ግዙፍ ኃይል ነው፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ስራ ውስጥ ረጅም ዘመን የካበተ ልምድ የነበራቸው ዛሬ በመስኩ የተመናመኑ ቢሆንም በሌሎች ታላላቅ ሀገራት በእድሜያቸው አንቱ የተባሉ አዛውንት ጋዜጠኞች አዲሱን ተተኪ ትውልድ በስራው ላይ እየኮተኮቱ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ሀገራዊ ፍቅርና ክብር ያለው ሙያውን የሚወድድ እንዲሆን አድርገው ያሳድጉታል፡፡
ምክንያቱም ጋዜጠኛው በመጀመሪያ መቆም ያለበት ለሀገሩ ሰላም ብሔራዊ ጥቅምና ለሕዝቡ ሰላም ነው፡፡ከሁሉም በፊት ለሁሉም መነሻና መሰረት የሆነችው ሀገር ሰላሟ ተጠብቆ ሲኖር ነው ጋዜጠኝነትም ሆነ ሌላው የሙያ መስክ መስራት የሚችለው፡፡ ጋዜጠኝነት ሰፊ የስራ ልምድን፣ እውቀትንና ማገናዘብን የሚጠይቅ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት የሙያ መስክ እንጂ በስሜትና ጀብደኝነትና በጥላቻ ስሜት ተዘፍቆ የሚያከናውኑት ስራ አይደለም፡፡ ጋዜጠኝነት ሙያዊ ኃላፊነትን ከሕግ ተጠያቂነትና ግዴታ ጋር ያቆራኘም ነው፡፡
በሕትመት ሆነ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሚዛናዊነት ሳይኖራቸው በጥላቻ ተሞልተው የሚያሰራጯቸው መረጃዎች በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ አደጋን ያስከትላሉ፤ሰላም ያናጋሉ፡፡የአብሮነት መቻቻልን ያዛባሉ፡፡ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ታላቅ ጥፋትን ያስከትላሉ፡፡
መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልን በማስተማር ችግሮች ቢከሰቱ እንኳ በሰላም ብቻ እንዲፈቱ ማድረግ ሲኖርበት የጦር መሳሪያ ሆኖ ጎራ ለይቶ ድብደባ ማድረግ የለበትም፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛው ተልእኮ ተገቢነት ያላቸውን በማስረጃ የተደገፉ ሚዛናዊ መረጃዎችን ገለልተኛ ሆኖ ለሕዝብ ማቅረብ ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃን የችግሮች ማባባሻ መሳሪያ ሳይሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ መፍትሄ የማስገኘት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡
በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጭ መረጃ ትክክለኛና ተጨባጭነት ያለው፤ግዜና ቦታን፣ ድርጊቱን፣ የሰው ምስክሮችን፣ የአሀዝ ጥንቅርን ያካተተ ካልሆነ የሚሰሯቸው ስራዎች ተአማኒነት አላቸው ለማለት አይቻልም፡፡ መገናኛ ብዙሃን ምንም ይሁን ምን የሕዝብን ቀልብ ስቤና ነግጄ አተርፋለሁ ብለው ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የገንዘብ ትርፍን እያሰሉ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ሀገራዊ አደጋን ያስከትላሉ፡፡ በስተመጨረሻም ተጠያቂነት ይከተላል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጨው ዘገባ ጥላቻን የማዛመት፣ የስም ማጥፋትና በቀልን የተንተራሰ ከሆነ ውሎ አድሮ ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ከትናንት ስህተት ተምሮ ወደፊት የተሻለች ሀገርና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር መስራት ይኖርበታል፡፡ መገናኛ ብዙሃንን በአግባቡና በስርአቱ ከተጠቀምንባቸው ለሀገር ሰላምና ግንባታ ሕዝብንም ለማስተማርና ለማሳወቅ በእጅጉ ይጠቅማሉ፡፡
መገናኛ ብዙሃን በእጃቸው ይዘው የማያባራ ተራ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የተጠመዱት ደግሞ በህዝብ መሀል ጥላቻን በመንዛት፣ ግጭትን በመዝራት ሀገርን ለቀውስ ይዳርጋሉ፡፡ይህ እንዳይሆን በየትኛውም መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ከሁሉም በላይ የመጀመሪያው ቀዳሚ ስራና ኃላፊነታቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሰላምና ደህንነት በሙሉ አቅማቸው መቆም ግዴታቸው መሆኑን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡የመገናኛ ብዙሃን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ በብሔራዊም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ግልጽ ሕጎች አሉት፡፡ልቅ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት የሚባል ነገር በምድራችን የትም ሀገር ላይ የለም፡፡
የመገናኛ ብዙሃን መብት በግልጽ የተሰመሩ የማይታለፉ መስመሮች ያሉት ሲሆን፤ ከመስመሩ ሲታለፍ የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም፤ የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮና ሕይወት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማንኛውንም አይነት እንቅስቀሴ( ከቦታ ቦታ ዝውውር፤ መሳሪያ አይነት፣ ብዛት፣ አሰፋፈርና አቅም) ሌሎችንም በክልከላ ሕጉ ውስጥ የተዘረዘሩ ከሀገራዊ ደህንነት ጋር በቀጥታ የተያዙ ምስጢሮችን መዘገብ አይቻልም፡፡ይህን ማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት መብት ሳይሆን ሀገራዊ ምስጢሮችን ለሌላ ወገን በአደባባይ አሳልፎ የመሸጥ ወንጀል ነው የሚሆነው፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ሕጉ ስላለ እስከምን ድረስ ነው የሚለው ነገር በሙያተኛው ዘንድ በውል ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡ሕጉን አንቀበልም እንዳሻን መሆን እንችላለን የሚል ስርአተ አልበኝነት በየትኛውም ሀገር ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህን አካሄድ የሚከተሉት ፖለቲካዊ አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ሕዝብን በተሳሳተ መረጃ ከጎናችን እናሰልፋለን ብለው የሚያስቡት ብቻ ናቸው፡፡በሀገር መከላከያ ላይ መዝመትና ሰራዊቱን ለመከፋፈል መጣር ፤በመሪዎቹ ላይ እምነት እንዲያጣ ማድረግ፤ የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈት፤ የመሪዎቹን ስለልቦና ለመጉዳት በፈጠራ ወሬ ማዛመትና ማሰራጨት የፕሬስ ነጻነትና መብት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡
የመረጃ ነጻነት ሕጉ በግልጽና በማያሻማ መልኩ የደነገጋቸው በቀጥታ ከበለጸጉ ሀገራት የተቀዱ (የተወሰዱ) ክልከላ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ምስጢሮችን እያነፈነፉ መረጃዎችን መልቀቅ ለሌሎች ሀገራት መረጃን አሳልፎ የመስጠት ተግባር ስለሆነ በከፍተኛ ወንጀልነት ያስጠይቃል፡፡በሌላውም አለም ይኸው ተፈፃሚ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ሕግ ውስጥ መታረምና መሻሻል ያለበት የቅጣት ሕጉን የመሳሰሉ ቢኖሩም እንኳ የሀገርን ምስጢር፣ በአመራሩ ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን፣ የፓርላማ ሰነዶችን፣ የተፈጥሮ ማእድናት ምስጢርንና ሌሎችንም በተገኙበት ሁኔታ እያወጣን እንጽፋለን፤ እንሸጣለን፤ መብታችን ነው፡፡ ማለት የሀገርን ምስጢር አሳልፎ የመሸጥ ያህል አደጋ አለው፡፡ሀገራት ሁሉ የሚጠብቁት የራሳቸው ብቻ የሆነ ብሄራዊ ምስጢሮች አሏቸው፡፡ልቅና የሕግ ጥበቃ የሌለበት ሀገርም ሆነ ሕዝብ የለም፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ ገና ዳዴ እያልን ስለሆንን በሙያውም ላይ ያለው ሰራተኛ በቂና የተጣራ ግንዛቤ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በዘመናችን ሀገራት ታላቅ አደጋ እየተደቀነባቸው ያሉት በተቃራኒያቸው ጎራ በተሰለፉ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን፣ በሶሻል ሚዲያውና በፌስ ቡክ አማካኝነት በሚሰሯቸው መረን የለቀቀ በሀሰት የተሞላ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡
ዛሬ ለአሜሪካ ታላቅ ፈተና ሆኖ የቀረበውና ተአማኒነት እያጣ በመሄድ ላይ የሚገኘው መገናኛ ብዙሃኑ ናቸው ፡፡ በቅርብ አመታት ተከስቶ ላየነው የአረቡ አለም አብዮት ሕዝቡን እያነሳሳ ከመንገድ ያወጣው፤ ግጭቱን ያስተባበሩት፣ ያስፋፉት፣ የጦር አዋጊ እቅድ አውጪ ሆነው ዘመቻውን በበላይነት የመሩት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡እነርሱ የየሀገራቸውን ተልእኮ ለማሳካት ስለሚሰሩ በእነርሱ መንገድ ትክክል ናቸው፡፡ትክክል ያልሆነው ሀገሩን መጠበቅ የተሳነው፤ በእነሱ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ እየተመራ የገዛ ሀገሩን፣ ቤቱን፣ ንብረቱንና ታሪኩን ያወደመው በስሜታዊነትና በጀብደኝነት እየተመራ እልቂትን ያመጣው ጥፋት ነው፡፡ ይህን መሰሉን ድርጊት እንዲስፋፋ ያደረጉት መገናኛ ብዙሃኑ ናቸው፡፡ሚዲያ በሰከኑና አርቀው ማሰብ በሚችሉ ሰዎች ካልተመራ በጥላቻ በተመረዙ ግለሰቦች እጅ ከወደቀ ታላቅ ሀገራዊ አደጋን ይጋብዛል፡፡ሀገርን ሰው ወደሌለባት ባዶ አውድማነት ይለውጣል፡፡ አይተንና ሰምተን የምንመሰክረው እውነትም ይህ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ ካለቀና ሀገር ከወደመ በኋላ ቢቆጩት የማይመልሱትና ይቅር የማይባል ታላቅ ስህተት ስለሆነ ጸጸትን ያስከትላል፡፡ የመን፣ሶርያ፣ጎረቤት ሶማሊያ፣ ዩጎዝላቢያና ሌሎችም የወደሙት በዋነኛነት ተልእኮ ባላቸው መገናኛ ብዙሃን አጋፋሪነት ነው፡፡ ከኋላ ሰራዊትና መሳሪያ ይሰማራሉ፡፡ ዳሩ እነርሱ ምንቸገራቸው ? የእነርሱ ሀገር ሰላም ውሎ ይደር፡፡ግጭት የለበት ጦርነት፤ ጥይት አይጮህበት፡፡እንደተመኙት የሌላውን ሀገር ሕዝብ አባልተው እንዲጨራረስ አደረጉ፡፡ ሀገራቱን አፈራረሱ፡፡ሕዝቡም አለቀ፡፡የተሰደደውም ተሰደደ፡፡ዛሬ ሚሊዮኖች ሀገርና ነጻነት አልባ ሆነው በሰው ሀገር በስደት ይኖራሉ፡፡
የግሉ ፕሬስ መኖር ለሃሳቦች በነጻነት መንሸራሸር መሰረታዊ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ሚዛናዊ በማስረጃ የተደገፉ ለችግሮችም መፍትሄ የሚያስገኙ ከሁሉም በላይ የሀገራቸውን ሰላምና ደህንነት ብሔራዊ ጥቅም ዘብ ቆመው መጠበቅና ማስጠበቅ ይገባቸዋል፡፡የግሉ ፕሬስ ካለበት ሰፊ ከፋይናንስ ችግር አንጻር የተለያየ የፖለቲካ አላማና ፍላጎት ባላቸው የሚረዳና የሚታገዝ ከሆነ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ሀገራዊ ጉዳዮችን ሊፈትሽ አይችልም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋዜጠኝነት ( ሚሊታንት ጆርናሊዝም) ፍጹም ወገናዊ በመሆኑ ለሁሉም ሕዝብ እኩልና ሚዛናዊ ሆኖ ሊሰራ ወይም አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡ኢዲቶሪያል ፖሊሲው የሚመራው በፓርቲው ድርጅታዊ መስመር በሚፈስለት አቅጣጫ ብቻ ነው፡፡በስራው ላይ ያሉት ሰዎች የትኛውንም ያህል ስለሀገርና ሕዝብ ቢያወሩም ግባቸው የራሳቸውን ድርጅት አላማ ማሳካትና ሌላውን ማጣጣል፣ መኮነን፣ የእነርሱን ተመራችጭነትና ብቃት ማሳየት ነው፡፡
እነርሱ የሚያራምዱት የፓርቲያቸውን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተልዕኮ ነው፡፡ ሁሉንም አመለካከትና የሕዝብን የተለያየ ፍላጎት በሚዛናዊነት አያስተናግዱም፡፡ ብዙዎቹ በተጨባጭ እንደታየው አክቲቪስቶችና የድርጅታቸው ካድሬዎች እንጂ ሚዛናዊ ሆነው የሚሰሩ ጋዜጠኞች አይደሉም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ሚዛናዊና ኃላፊነት የተሞላበት ጋዜጠኝነት ነው፡፡ቅጥ ያጣውን ልዩነት የሚያጠብብ፤ ዘረኝነትን የሚያጋልጥ፤ ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ በቂ መሆኑን የሚያሳይ፤ጎራ ለይቶ በጎሳና በዘር ጉዳይ የማይዳክር፤ ትልቁን የሀገር ሰላም ረስቶና ዘንግቶ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የማይጥር፤ ይልቁንም በግለሰቦች መንስኤነት ችግሮች ቢፈጠሩም ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ የህዝቦች አብሮነት ፍቅርና ወንድማማችነት ተከብሮ መኖር እንዲቀጥል የሚሰራ ሊሆን ይገባል፡፡
ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ከተራ ስም ማጥፋት ከጥላቻ ፕሮፓጋንዳና ከበሮ ድለቃ የተላቀቀ ሚዛናዊ ሚዲያ ነው፡፡ ከትልቋ ሀገር ኢትዮጵያ ይልቅ ወደጎጥና መንደር ተንከባልሎ፤እይታውም በክልል ብቻ ታጥሮ በጠብ አጫሪነት ተሞልቶ አንዱን በሌላው ላይ ሲያነሳሳ የሚውል፤ የራሱን ትልቅነት በጭፍን የሚሰብክ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ አይመጥንም፡፡ ለሀገር ውድቀት እየቆፈረ ያለ መገናኛ ብዙሃን ከመሆን አይዘልም፡፡
ይህች ታላቅ ሀገር ከዘረኝነትና ከጎጠኝነት በላይ ስሟና ታሪኳ የገዘፈ ነው፡፡ነጻነቷና ክብሯ ከሁሉም የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ቆመው ጠላትን እየመከቱ በየትውልድ ፈረቃ የደም መስዋእትነት ከፍለው ያቆዩአት ሀገር ነች፡፡ይህ ትወልድ የአባቶቹን ታላቅ ተጋድሎ ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅ በታል፡፡ ኢትዮጵያ በወሬ በሽብር በአሉባልታ የምትፈርስ ሀገር አይደለችም፡፡አትበታተንም፡፡ አትወድቅም፡፡፡ የጠላቶቿ ሕልም አይሳካም፡፡ሕዝብን በመከፋፈል እርስ በእርሱ እንዲጋጭ በማድረግ ሀገርን ከማጥፋት ውጭ የሚገኝ አንዳችም ትርፍ የለም፡፡ መገናኛ ብዙሃን በስነምግባር የሚመሩ የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቁ ለልማት ሕዝብን የሚያተጉ ችግሮች ሲከሰቱ በሰላም ብቻ እንዲፈቱ የሚያደርጉ ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን ይተካል፡፡መሪዎች ያልፉሉ፡፡ ዘመን የፈጠራቸው መሪዎች ይተካሉ፡፡ ፓርቲዎች ይፈጠራሉ፤ ፓርቲዎችም ይቀየራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን አታልፍም፡፡ የሚተካው አዲስ ትውልድ እያዘመናት ታሪካዊና ታላቅ ሀገርነቷን ጠብቆ ያስቀጥላታል፡፡ መገናኛ ብዙሃን ከውዥንብርና ከጊዜያዊ የፖለቲከኞች የተዛባ አመለካከት ነጻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ፖለቲከኞችን ስራ ጠንቅቆ መረዳት ይገባል፡፡ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ መሆን ካልቻሉ ሀገራዊ ውድቀትና ትርምስን ያመጣሉ፡፡ ይሄ ደግሞ አይበጀንም፡፡ ከፖለቲካ ድርጅት ጋዜጠኝነትና ከአክቲቪስትነት ወደ ሀገራዊና አለምአቀፋዊ ጋዜጠኝነት መሸጋገሩ ይበጃል፡፡ መንደርተኝነትን ይዞ ክልልን ለይቶ በመቆም ሀገራዊ ራእይ ማራመድ አይቻልም፡፡ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደረጋት መልከ ብዙ፣ ባህለ ብዙ፣ እምነተ ብዙ፣ መሆኗ ነው፡፡ «ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን፤ ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለውጥም» እንዲሉ ይህችን ባለታሪክ ታላቅ ሀገር መጠበቅ መንከባከብ፤ልዩነትን አስወግዶ ሕዝቧን በፍቅር ማስተሳሰር እንጂ፤ የብሔርና ጎሳ ልዩነትን በመስበክ ቅራኔን በማስፋት ጥፋትን መጋበዝ ተገቢ ባለመሆኑ መገናኛ ብዙሃኑ ታላቅ ሀገራዊና ሕዝባዊ አደራቸውን በፍጹም የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ስሜት ሊወጡ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
መሐመድ አማን