ኢያሱ መሰለ
ዕድሜው ከ40ዎቹ መጀመሪያ ያለ አንድ ጎልማሳ ሰው ትልቅ የማዳበሪያ ከረጢት በጀርባው ላይ አዝሎ ከአምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ለውስጥ ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ በሚወስደው መንገድ ቁልቁል ይንደረደራል።
የለበሰው የሥራ ልብስና የዓይኖቹ መባዘን የሰውዬውን ሥራ ይጠቁማሉ። ጥቅም ሰጥተው የተጣሉ እቃዎችን በተለይም ፕላስቲኮችንና ካርቶኖችን ከየመንገዱና ከየአጥሩ ስር እየሰበሰበ ለተፈለጉበት ዓላማ እንዲውሉ የሚሸጥ ታታሪ ሰው ነው።
አብዛኛው ሰው አራት ኪሎ አካባቢን ለመዝናኛነት ይመርጠዋል። ለባብሶ ይወጣል። ይህን ሰው በአራት ኪሎ ጎዳናዎች ላይ ተሽቀርቅረው ከሚጓዙ ሰዎች የሚለየው ኑሮውን ለማሸነፍ የሰበሰባቸውን ውድቅዳቂ እቃዎች በጀርባው ላይ ተሸክሞ የሚኳትን መሆኑ ነው።
ቆራጥነቱ ያኮራል፤ ስራ ወዳድነቱ ያስደስታል። ብዙዎች ከገቡበት ችግር ለመውጣት ዋጋ መክፈል እንደሚገባቸው ቢያውቁም ዝቅ ብሎ ከመስራት ይልቅ ሲለምኑ ይታያሉ።
ይህ ሰው ግን ልመናን ይጠየፋል። የኑሮውን ጎዶሎ ለመሙላት ዝቅ ብሎ መስራትን መርጧል። በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርቷል። አንዱም ስኬታማ አላደረገውም፤ ነገን ተስፋ ሳይቆርጥ መፍጨርጨሩን ቀጥሏል።
የእንዲህ ዓይነት ሰዎች ተሞክሮ ለሌሎች ትምህርት ስለሚሰጥ እኛም የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርገው ወደድን።
ቶማስ ሳሙኤል ይባላል። ተወልዶ ያደገበትን አካባቢ መናገር አይፈልግም። ምክንያቱ ደግሞ አሁን እየኖረ ካለው ጎስቋላ ህይወት አንጻር በቤተሰቦቹ ላይ የሥነልቦና ጫና እንዳይፈጠር በማሰብ እንደሆነ ይናገራል። እርሱ እንዲህ ይበል እንጂ ማንኛውም ሥራ ህጋዊ እስከሆነ ድረስ ክብር አለው፤ በዚህ አጋጣሚ የስራ ትንሽ እንደሌለው ጠቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል።
ቶማስ ከትውልድ መንደሩ ኮብልሎ አዲስ አበባ የመጣበትን ሁኔታ እንዲህ ያስታውሳል። ስድስት ልጆችን ያለ አባት የሚያስተዳድሩት እናቱ የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት፣ የምግብና የልብስ ወጪ የሚሸፍኑት ያለቻቸውን ትንሽ መሬት በማሳረስ ነው። የመሬቷ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ፣ የቤተሰቡ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ቤተሰቡ ይቸገራል።
በጠባብ መሬት መኖር ያልቻሉትንና ሁልጊዜም በችግር ውስጥ የሚኖሩትን ቤተሰቦቹ ሁኔታ እንቅልፍ የነሳው ወጣት እራሱን በራሱ ለመርዳትና እናቱንም ለመደገፍ በማሰብ 9ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጣ።
ይዞት የመጣው መኪና ከአንድ ቀን ጉዞ በኋላ የድሮው ለገሃር አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢ ይጥለዋል። ቶማስ የያዛት ገንዘብ ከአንድ ቀን የአልጋና የምግብ ወጪ በኋላ ታልቅበታለች። በዚህም ላይ በፌስታል ቋጥሮ የያዘው ልብስና የትምህርት ማስረጃ በሌባ ይወሰድበታል።
ቶማስን የአዲስ አበባ ከተማ ሁኔታ በምናቡ ካስቀመጠው ስዕል ውጭ ሆኖ አስፈራው። በየጎዳናው ላይ ያለ ስራ የሚቀመጡ፣ የሚለምኑ፣ የሚተኙ፣ የሚነግዱ፣ የሚቀሙ ሰዎችን ማየት እንግዳ ነገር ይሆንበታል።
ሁኔታው ባይመቸውም ወደኋላ መመለስ አልፈለገም። ሰርቶ የሚኖርበትን ሁኔታ መቃኘት ይጀምራል። ከትንሿ የገጠር ቀበሌ የመጣው ወጣት የሰዎች ትርምስ በሚበዛበት መርካቶ አካባቢ በመሄድ የስራ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጀምራል። ነገሮች እንዳሰባቸው አልሆኑለትም፤ በማያውቀው አካባቢ የማያውቀውን የከተሜነት ህይወት መጋፈጥ ይጀምራል።
ቶማስ ቀን ቀን ተባራሪ የጉልበት ስራ እየሰራ የምግብና የማረፊያ ቦታውን ወጪ ለመሸፈን ይጣጣራል። በቀን ከ30 እስከ 50 ብር ያገኝ እንደነበርም ያስታውሳል። ይህችኑ ለምግቡና ለቀን ማረፊው እያዋለ ከአዲስ አበባ ኑሮ ጋር ይለማመዳል።
ተመላሽ ምግቦችን ከ10 ብር ባልበለጠ ዋጋ ገዝቶ ይበላል። በአንድ ቤት ውስጥ ከ30 እስከ 40 ሰዎች በሚያደሩበት ቤት ውስጥ ለዕለት ማረፊያው ከስምንት እስከ አስር ብር እየከፈለ ያድራል። በቤት ውስጥ የሚያድሩት አብዛኛዎቹ እንደእርሱ ከክፍለ ሀገር የመጡና የተለያየ ባህሪ ያሏቸው እንደነበር ያስታውሳል።
አንዳንዶቹ ሰክረው እየገቡ ሲሳደቡ ያድራሉ፤ ሌሎችም እዚያው ከሚያድሩ ሰዎች ኪስ ለማውለቅ ይሞክራሉ። ቶማስ ይህን ሁሉ እንግዳ ነገር እየተቋቋመ የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት ይጥራል።
ቶማስ ቤት ተከራይቶ ለመኖር ቢመኝም አቅሙ አልፈቅድለት ይላል። ይሁን እንጂ ጎዳና ላይ ማደር አይፈልግም። ቀን በቀን የመኝታ ቤቱን ወይም የማረፊያውን እየከፈለ ይኖራል። አዲስ አበባ ከገባ ጀምሮ በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል። ግን ለልመና እጁን ሰጥቶ አያውቅም።
ቤተሰቦቹን ለመርዳት ባይችልም ተጣጥሮ እራሱን ያኖራል። እርሱ ገቢውን አሳድጎ ቤት ለመከራየት ሲያስብ ኑሮ እየተወደደ ወጪውም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፤ የቤት ኪራይም ይወደዳል። በዚህ ምክንያት ቶማስ ዛሬም ከ10 ዓመት በፊት የሚኖረውን ኑሮ ለመኖር ተገዷል።
ቀደም ሲል ከስምንት ብር እስከ አስር ብር የሚከፍልበት የጋራ ማደሪያ ቤት እንኳን ዛሬ ከሃያ ወደ 30 ብር ከፍ ብሎበታል። ባለው መልካም ባህሪና ታማኝነት ቤቱን በበላይነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢሰጠውም ዛሬም የሚጠበቅበትን እየከፈለ አዳሩን እዚያው ቤት አድርጓል።
ቶማስ አብዛኛውን ጊዜውን አትክልት ተራ በጫኝና አውራጅነት ስራ ያሳልፋል። ዘወትር ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከማረፊያ ቤቱ እየወጣ አትክልት ተራ ይሄዳል። ግብይቱ በአጭር ሰዓት የሚጠናቀቅ በመሆኑ ልክ ሲነጋ ያገኛትን ይዞ ወደ መርካቶ ይሄዳል። እዚያም ያገኛቸውን የጉልበት ስራ ሲሰራ ውሎ ወደ ማደሪያው ይገባል።
የገቢውን መጠን ለማሳደግ በአንድ በኩልም ሙያ ለመቅሰም ቀን ቀን በኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ ረዳት ግንበኛ ሆኖ መስራት ይጀምራል። ቀስ በቀስ ረዳት ግንበኝነቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መስራት ይጀምራል።
ቶማስ በዚህ ስራ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ህይወቱን መምራት ይጀምራል። ነገር ግን በሲሚንቶ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ስራዎች ሲስተጓጎሉ ብዙ ጊዜ ያለ ስራ ይቀመጣል። ያም ባቻ ሳይሆን የእለት ገቢ ያጣል። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደገና ሌሎች ስራዎችን እንዲሞክር ያስገድደዋል።
አሁን ቶማስ የወዳደቁ ፕላስቲኮችን፣ ካርቶኖችን እና ብረታ ብረት እየሰበሰበ በመሸጥ በሚያገኛት የቀን ገቢ ይኖራል። የተለያዩ ስራዎችን ቢቀያይርም አኗኗሩ ግን አልተለወጠም። ቤት እንኳን ተከራይቶ መኖር አልቻለም። ዛሬም ህይወቱ ከ10 ዓመት በፊት እንደሚኖረው ዓይነት ነው።
ስራውን ሰርቶ እዚያቸው የሚያውቃት ቤት ለአዳር ይሄዳል። እንደሌሎች ጓደኞቹ ጫት አይቅምም፤ ሲጋራ አያጨስም፤ አይጠጣም፤ ሁልጊዜ እራሱን ለማኖር ይታትራል፤ ግን ጠብ ያለለት ነገር እንደሌለ ይናገራል።
ቶማስ አዲሱን ስራውን ለማከናወን ማለዳ ተነስቶ እግሩ ወዳመራው ይጓዛል። ማለዳ ከመርካቶ ተነስቶ ሽቅብ ወደ አዲሱ ገበያ ይወጣል፣ ቀጨኔ፣ ሽሮ ሜዳ፣አቧሬ መገናኛ፣ ላምበረት ወዘተ ደርሶ እንደገና በሌላ ሰፈር አቆራርጦ የሰበሰባቸውን እቃዎች ተሸክሞ ወደ መርካቶ ይመለሳል።
ከሰዓት በፊት የሰበሰበውን እቃ አስረክቦ ምሳውን ከበላ በኋላ ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ይባዝናል። ቶማስ በቀን በቀን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እየተዟዟረ ለምግቡና ለመኝታው የሚሆነውን ገንዘብ ለማግኘት ይጥራል።
በአማካይ በቀን ከመቶ እስከ 120 ብር ያገኛል። የገቢውን መጠን ባሳደገ ቁጥር የኑሮ ውድነቱ እየከፋ የወጪው መጠንም እያደገ ይሄዳል። በዚህ የተነሳ ህይወቱን መቀየር አልቻለም። ግን እጁን ለልመና ላለመስጠት ይጥራል።
አንዳንድ ጊዜ ቶማስ ሲንከራተት ውሎ የረባ ነገር ይዞ አይመለስም። በተለይም በክረምት ወቅት ዝናብ እንቅስቃሴውን ስለሚገድብበት ስራውን በሚገባ ለመስራት አያስችለውም። ያም ብቻ ሳይሆን በዝናብ ወቅት ሰዎች ውሃ የመጠጣት ፍላጎታቸው ስለሚቀንስ የውሃ ጠርሙሶችን እንደልቡ እንደማያገኝ ይናገራል።
ቶማስ በቀን በቀን በትንሹ 30 ኪሎ ሜትር በእግሩ እንደሚኳትን ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ በየመንደሩ ሲደርስ የተለያዩ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙት ይገልጻል። የሚሰራውን ስራ የሚያበረታቱት እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች እንደሌባ እየተመለከቱት ይሰድቡታል፤ ያመናጭቁታል፤ ውሻ የሚለቁበት፣ ድንጋይ የሚወረውሩበት መኖራቸው ንም ይናገራል።
ቶማስ ከሚያስገርመው ነገር አንዱ በደረሰበት ቦታ ሁሉ ሌሎች ሰዎች ላይ የማይጮሁ ውሾች እርሱን ሲያዩ እየተከተሉት የሚጮሁ መሆኑ ነው። በዚህ ስራው ላይ እንደውሻ ተቀናቃኝ እንዳላገጠመው ይናገራል። አንዳንዴ ደግሞ ቆሻሻ የሚሰበስቡ ሰዎች የጥቅም ተቀናቃኝ እያደረጉት እንደሚጋጩትም ይናገራል።
ቶማስን ሌላው ፈተና የሆነበት ጉዳይ የሰበሰበውን ዕቃ ተሸክሞ በመንገድ ላይ ሲሄድ በመንገድ መጣበብ ምክንያት ከእግረኞች ጋር እየተላተመ የሚደርስበት ስድብና ቁጣ ነው። አንዳንድ እግረኞች ተሸክሞ ሲሄድ እያዩት ቦታ መልቀቅ ሲገባቸው ቆመው ይመለከቱና የተሸከመው ማዳበሪያ ሲነካቸው ቆሻሻ አስነካኸን በሚል የስድብ ናዳ እንደሚወርዱበት ይናገራል።
ሰዎችን ላለመንካት ሲል በመኪና መንገድ ውስጥ እየገባ ሲሄድ ተገጭቶ ወድቋል። ጭንቅላቱ ተጎድቶ ለወራት ህክምና ካደረገ በኋላ ተሰፍቶለት ወደ ስራ መመለሱን ቶማስ ይገልጻል። እንደቶማስ አባባል መንገድ ላይ ዕቃ ዘርግተው እየነገዱ መተላለፊያውን የሚያጣብቡ ሰዎች በስራው ላይ እንቅፋት ፈጥረውበታል።
እግረኞች እነርሱን ህጋዊ አድርገው እንደቶማስ ዓይነቶቹን እንደ ህገወጥ ተመልክተው መናገራቸው ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራል። ሰዎች አዳፋ ልብስ ለብሶ መናኛ ስራ ለሚሰራ ሰውም ክብር መስጠት እንደሚገባቸው ቶማስ ይናገራል።
የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የቶማስ ገቢ ከአምና ጀምሮ እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራል። የቀን ገቢው ለተከታታይ ወራት አሽቆልቁሎበት ነበር። ለዚህም ዋናው ምክንያት የሚሰበስቧቸውን ውድቅዳቂ እቃዎች ወደ ሌላ ምርት የሚቀይሩ ፋብሪካዎች ስራ ማቆማቸው ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወደ ነበሩበት እየተመለሱ በመሆኑ የቶማስ ገቢ በማንሰራራት ላይ ይገኛል። በዚህም መሰረት አንድ ኪሎ የውሃ ጠርሙስ የሚያስረክብብት ዋጋ ወደ አራት ብር ከፍ ብሎለታል። ያም ቢሆን በየጊዜው እየጨመረ ከሚሄደው የኑሮ ውድነት አኳያ አሁንም ቢሆን የቶማስ ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይናገራል።
ቶማስ መስራት የሚችል አቅም፣ ጥሩ የስራ ተነሳሽ ነትና መልካም ስነምግባር ይዞ እራሱን ለመቀየር የሚታትር ሰው ነው። ዛሬም ህይወቱን ለመቀየር ይጥ ራል። ቤት ተከራይቶ ፤ ትዳር መስርቶ የመኖር ህልም አለው። የተሻለ የስራ ዕድል የሚፈጥሩለትን ሰዎች ቢያገኝ ሰርቶ መለወጥ እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም አቅም ያላቸው ሰዎች ሰርቶ የመኖር ዕድል እንዲፈጥሩለት ይማፀናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013