
ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ አይባ ኒባ መንደር አባቷን ቄስ ደገፋው ከበደንና እናቷን ወይዘሮ እንዳሻሽ አለነን በ1978 ዓ.ም በወርሃ የካቲት ከበቡሽ ደገፋውን አገላገለቻቸው። ስምንት ዓመት ሲሆናት “ልጃችሁን ለልጃችን” ተባሉና በማደጎ ሊሰጧት ፈቅደው ወላጆቿ ሽር ጉዱን ሲጀምሩት ከበቡሽ እንዳትሰማ ጥንቃቄው የበዛ ነበር። ይሁንና የታሰበው ፍጥርጥሩ የተፈራው ድንግርግሩ ዝናር ተሸልመው በፈረስና በቅሎ ተጭነው ሚዜና ሰርገኛው ሙሽራውን አጅቦ ሲገባ የደከሙበት ስውር ዝግጅት አይኑን ገለጠና ድንጋጤያቸውን አቃጠረባቸው። ምን እንደሆነ ስትጠይቃቸው አባቷ አርፈው ስለነበር “ተስካሩ ነው” ይሏታል። እሷ ግን “ያባቴ ተስካር በሆታና በልልታ የሚወጣው ከሞት የተነሳ መሰላችሁ እንዴ?” አለች ሃሳቧ ተሰቅሎ ሆዷ ነገር አዝሎ። እንደነገር ፒኪያታ እየተንሳፈፉ የባጥ የቆጡን ሲዘላብዱ ቆዩና ቁርጥ ሲሆን ልታገባ እንደሆነ አረዷት። ይህን ጊዜ ሊቀይዳት ካሰፈሰፈው አጉል ባሕል ትብታብ ያመልጥ ዘንድ አቦሸማኔ እግሯ ተፈተለከ። ወንድሟ አዛናው በበነጋታው እንደሚመልሳት ቃሉን ሰጥቶ
“አፋፉ ላይ ቆሜ ፉጨቴን ብለቀው፣
ከነሊጧ መጣች ሳትለቃለቀው።”
ይሉትን አይነት የሙሽራ ወግ ሳታደርስ እንሶስላ ሳትሞቅ፣ በጆሮ ጉትቻው፣ ባንገት ድሪና እርባኑ፣ በጅ ዱኮቱ [አንባሩ]፣ በጣት ፈርጡና በግር አልቦው ሳታጌጥ እንዲሁም አታሞው በቅጡ ጮሆ ሽነት ሳትባል ምወድስ ሳትሸለም እንደነገሩ ተነስታ ሄደች። እንቅልፍ ሳይኩልባት ያደረችው ከበቡሽ ወንድሟን ይመጣል ብላ ደጅ ደጁን ብታይ ዝር የሚል የቤተሰብ አባል ጠፋና አንጀቷ ሲደብን በግብር ውሃ ሰበብ ማምለጫ ብልሃት ዘየደች። በማኅበረሰቡ ወግና ልማድ ባገባች በሶስተኛው ቀን መልስ የምትጠራ ቢሆንም ከበቡሽ ግን ትግስቷ ተሟጦ የመጥፋቱን ነገር አምናበት ሁኔታዎችን አውጥታ አውርዳ ለሃሳቧ መቋጫ አገኘችለትና “ግብር ውሃ መውጣት እፈልጋለሁ” ስትል ፈቃድ ጠየቀች። በባሕሉ ግብር ውሃ ስትወጣ ሚዜው ነውና አዝሎ የሚያደርሳት አንገቱን ቀብሮ ጉልበቱን ሰብሮ ሊያዝላት ሲሰናዳ “እረዱኝ” አለችና ከሴቶች ጋር እንድትሄድ ሆነ። ከአካባቢው ሳትርቅ እንዳይናገሩ ሴቶቹን አስጠንቅቃ የደረበችው ወተት የመሰለ ቀጭን ኩታ ከጨረቃዋ ጋር ተሰባጥሮ እንዳያጋልጣት ሰግታ ጥላው ብን አለች። ትንሽ ቆይቶ “ሌባ ያዙልን” የሚል ተማጽኖና ምድርን የሚንጥ ተኩስ ከኋላ እየተከተለ ሲያባርራት ከመንገድ አገለለችና አንድ መናኛ ግቢ ውስጥ ዘላ በመግባት ያገኘችውን የጭድ ክምር ሰርስራ ተኛች። የአይጦቹና የዕባቡ ሲርሲርታ ከምትሸሸው ያለዕድሜ ጋብቻ አይበልጥምና ሞራልን የሚያበረታ፣ ሽንፈትን የሚረታ ቅዱስ ቃል ለልቧ ነገረችው።
“መስከረም አህዱ የሚባለው፣
ጳጉሜ ጎዶሎው ታልፎ ነው።”
ምድር የተከናነበችውን ጨለማ በብርሃን ቡልኮ ስትለውጥ ከበቡሽ እንቅልፍ ያልጠገቡ አይኖቿን ባይበሉባዋ እንደዕንጭጭ በቆሎ እያርመጠመጠች ከእናቷ ቤት ስትደርስ “አንድ ቀን መታገስ አቅቶሽ ለውርደት አበቃሽን?” አላት ቤተዘመዱ በሞላ እየተቀባበለ። “በነጋታው እመልስሻለሁ” ያላት ወንድሟ ሲደበድባት እግሯን ከመስበር አልፎ የልቧን ጠባሳ አከፋው፤ እሷ ግን ስጋዋን ለአሞራ ቢሰጡት እንኳን በጄ የምትል አልነበረችም።
ታዲያ ይሄ ሁሉ ግብግብ ሳይበግራት
“የኛ ልጅ ኩሪባቸው፣
በእንግሊዘኛ አናግሪያቸው።”
ሲባል እየሰማች አድጋለችና 1991 ዓ.ም ደንጎልስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች። ሀገሬው ግን “ሚስትህ ተምራ ዶክተር ልትሆንልህ ነው፤ ይልቅስ ጠልፈሃት ትዳርህን አትይዝም?” ሲሉት የተወችው ባሏ እልህ ተጋባና በየመንገዱ እየጠበቀ ሰላም ይነሳት ጀመረ። ምንም እንኳን ከዓላማዋ ሊያስቀራት ባይችልም። ከበቡሽ ቀለም አቀባበሏ ጥሩ የሚባል ሲሆን የምትሳተፍባቸው የሙዚቃና ቲያትር ክበባት ዛሬ ላይ በሙዚቃው ዘርፍ ለገዛችው ስሟና ላተረፈችው ዝና እርሾ ሆነዋታል። ክበባቱንም በመጠቀም ያለእድሜ ጋብቻን አስከፊነትና የሴቶች ጥቃት ይቆም ዘንድ ብሎም ተምረው ከራሳቸው አልፈው ሀገርና ትውልድን አሻጋሪ ሃሳብ ማዋጣት እንዲችሉ እንዲሁም ለማኅበረሰብ ግንባታ የበኩላቸውን ኃላፊነት በመሸከም አስተዋጿቸው እንዲጎለብት የትምህርትና ሥራ ምቹ ከባቢ እንዲፈጠርላቸው አጥብቃ በማስተማር የተሳሳተ አመለካከቷን ተሟግታለች። ይህም ለከፍተኛ ሽልማት አብቅቷታል።
ድምጻዊቷ የነበራት የደንጎልስ ቆይታ የቀዬዋ ትዝታ ወደስድስተኛ ክፍል መሻገሪያው ላይ ተቋጨ። አብሮ አደጓ ሙሉ ከአንድም ሁለቴ አዲስ አበባን አይታለችና በጨዋታቸው ሁሉ ስለከተማው እድገትና ስልጣኔ ስታወጋት ቀልቧ ሸፍቶ መሸኛ አውጥታ ጉዞ ጀመሩ።
ማደጎ ከወሰዷት አሚን ባሏ ቄስጌ ጊዮርጊስ ጎጥ ሌላ ሩቅ መንገድ ሄዳ የማታውቀው ከበቡሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳፈረችበት መኪና አቧራውን እያቦነነ ሲከንፍ ቶሎ የምትደርስ መስሏት ነበር፤ በወሬ ከምታውቀው ከአባይ በረሃ ደርሳ ያየችው ጠመዝማዛ ጎዳና ልቧን አርዶት እንጉርጉሮ አስከተለች።
“አባይ ዙሪያው ገደል መጠምጠሚያው ዘንዶ፣
ማን ይመጣልኛል አባይን ተራምዶ።”
“እግሬን በሰበረው፤ እናቴ ጥሪኝ” አሰኛት። “ወይ ድንግርግር ተጓዝ ያለው እግር” ብላ በራሷ ብትተርትም መድረስ አይቀርምና የአዲስ አበባን መሬት ጫማዋ ስሞ ለአጎቷ ጋሻው ተስፋው ቤት በቃች። በፊት አውራሪ ትምህርት ቤት ስድስተኛን፣ ሰባትና ስምንትን ደግሞ በመድሀኒዓለም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተለችው ከበቡሽ ለሚኒስትሪ በመዘጋጀት ላይ እንዳለች ከእናቷ ጉያ ያራቃት የሙዚቃ ፍላጎቷ እንዳይደበዝዝና ተዳፍኖ እንዳይቀር ሃሳብ እንዲሰጣት አጎቷን አዋየቻቸው። እሳቸው ግን “የቄስ ልጅ መሆንሽን ዘንግተሽው ነው? ብለሽ ብለሽ አዝማሪነትን ተመኘሽ? ለአንበሳ ያሳደኩት ውሻ ለዝንጀሮም ሳይሆነኝ ቀረ አሉ፤ በትምህርትሽ ገፍተሽ ትልቅ ደረጃ ደርሰሽ ታኮሪናለሽ አልን እንጂ ይሄንንማ መቼ አስበን?” አሉ እጅጉን ተቆጥተው። ባፈገፈገች ቁጥር ከሕልሟ እየሸሸች በመሰላት ጊዜ በንቢታዋ ጸንታ አጎቷን ተጫነቻቸውና “ሚኒስትሪ ካለፍሽ በትምህርትሽ ትቀጥያለሽ፤ ከወደቅሽ ግን የምትፈልጊውን ሙዚቃ ማስኬድ ትችያለሽ” ሲሉ ምርጫ ለመስጠት ተገደዱና ገርበብ አድርገው የተውትን የሃሳብ በር ወለል አድርጋ በመክፈት ዳግም ላትወጣ ናኘችበት። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን መቋጫ ቀን ደርሶ ለሚኒስትሪ ፈተና ስትቀመጥ “ኤ እንዳይጎልባት፣ ቢ እንዳይከፋት፣ ሲ እንዳይቀርባት” እያለች ግምታዊ መልሷን በዝግዛግ አቀለመች። ውጤት መጥቶ የፈተና ወረቀቷ ቢታይ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መሻገር አለመቻሏን ሲናገር የቤተሰቦቿ መሻት መክኖ የሷ ምኞት እውን ሆኖ ሃዘንና ደስታን ሁለት ጎራ አስያዛቸው።
በዚህ ምክንያት ዓላማና ግቧን ያቆራኘችው ከበቡሽ ካጎቷ ቤት ትይዩ ወደሚገኘው ኤምቲ ሙዚቃ ቤት በማቅናት ሙዚቃ እድሉን እንዲሰጧት ደጅ ጠንታ እሽታቸውን በማግኘቷ ለሙከራ ቀረበች፤ ይሁን እንጂ ፈታኙ ጸጉሩን ድሬድ የተሠራ ራስታ ነበርና እሷ ደግሞ እንዲህ ያለ ሰው አይታ አታውቅምና በሸበባት ፍርሃት ሰበብ ችሎታዋ ከቀልቧ ጋር አብሮ ተገፎ ኖሯል ብታባብለው ብታቀማጥለው እንደለዘብተኛ ሰይጣን ድምጿ ተደብቆ አልወጣም አለ። የፈጠረባት ድንጋጤ ተስፋ አስቆርጦ ወደኋላ ሳያንደረድራት ከፊቷ የተዘረጋውን የምኞት ሃረግ አጥብቃ በመያዟ በቀበሌ ወጣት ማእከል ሰልጥና ከስድስት ወራት በኋላ ዳግመኛ ለኤምቲ ሙዚቃ ቤት የሙከራ ጊዜ በቅታ ተሳካላት። ከሙሉጌታ አፈወርቅና መልካሙ ሙላት ጋር በመሆን በ1999 ዓ.ም አድባሩ አቡዬ ጋር በመቀናጀት “ሁለቱ ሰገነቶች” የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሟን ላድማጭ ጆሮ ማድረስ ቻለች። በካሴቱ ያካተተቻቸው አምስት ዘፈኖቿ ጆሮ ገብነትን አግኝተው ከሕዝቡ ልብ ሰርጸው ተደማጭነትን ቢያተርፉም “ሸጋው ቦረና” በሚል ርዕስ የሚጠራው ሙዚቃዋ ግን ከሁሉም በበለጠ ድፍን ኢትዮጵያን አዳረሰ። “ሸጋው ቦረናን” በተመለከተ አንድ ጊዜ እናቷ የልጃቸው ከበቡሽ ፖስተር ድፍን ድብረታቦርን አጥለቅልቆ ሳለ ሃገሬው “የሆነችውን እንጃ የልጅሽ ፎቶ በየሱቁ ደጃፍ ተሰቅሏል” ሲሏቸው እየሮጡ ሄደው መገንጠል ያዙ። “ዘፈን አውጥታ ነው፤ ሞታ አይደለም” ቢሏቸው ላፍታም እንባቸው ጋብ አላለም።
“የሸጋው ቦረና” እውቅና ወፍራም እንጀራ አጎናጸፋትና ከአውቶብስ ተራ ፊት ለፊት በሚገኘው የንጉሴ ባሕል ምሽት ቤት ለመቀጠር በቃች። ሥራ በጀመረችበት እለት ታዳሚው አዲስ ፊት ናፍቆ ኖሯል “እሷ ትዝፈን፤ ከበቡሽ ትዝፈን” እያለ በከፍተኛ ሞራል ወደመድረክ ጋበዛት። የታዳሚውን ፈቃድ ለመሙላት ሌሎች እየዘፈኑ በውዝዋዜ ብትሳተፍም መሰንቆ ተጫዋቹ አስችላልና አርቲስት አለቤ ጫንያለው በባሕል ምሽት ቤቶች ለሚዘወተሩ ቅኝቶች እንግዳ በመሆኗ በትርፍ ግዚያቸው አለማመዷትና የትም ቦታ የምትጠራ ብርቅዬ የሞያ አጋራቸው ሆነች። በዚህ መሃል ቁንጅናዋን ያዩ ገላዋን የተመኙ ሁሉ ቁንጥጫቸው በዛና የብረት አጥር ይሆናት ዘንድ መሰንቆ ተጫዋቹ ይትባረክ ጌታቸው ጋር ሞሰብወርቅ ሰፉ።
የሚሊኒዬሙ ጊዜ “ሸጋው ቦረና” በወጣ ባመቱ ካሙዙ ካሳና ፒስ በላቸው በቅንብር የተሳተፉበት “በርሬ እንዳሞራ” የተሰኘ ሁለተኛ አልበሟን ስታወጣ ካሳንቺስ በሚገኘው የማለፊያ ተካ ይወዳል ባሕል ምሽት ቤት ትሠራ ነበር፤ ዝናዋ ተንሰራፍቶ እሷን ለመውሰድ የባሕል ምሽት ቤቶች ሲራኮቱ ዳትሰን ሰፈር የሚገኘው የሻረግ ባር ቀልቧን ገዛውና ተቀላቀለች። ይህም የመጀመሪያ ልጅ ያገኘችበት ገዷ ሆነ። ከወሊድ ስትመለስ የሻረግ ሞልቶ ጠበቃትና ወደሳምሪ ባር ተዛወረች፤ ከሁለት ዓመት በኋላም ከጊሽ አባይ ሙዚቃ ቤት ጋር ሄኖክ ነጋሽ ያቀናበረው “ልቤ ወዶታል” የተሰኘ ሶስተኛ አልበሟን ብትሠራም በጥቅም ጉዳይ ተጋጭተው የሙዚቃ ሕይወቷን የሃምሌ ጉም አለበሰው። በፍርድ ቤት ቢገላገሉም ልቧ እንዳኮረፈ ነበር፤ በዚህ መሃል ከባለቤቷ ጋር ተለያዩና የመከራ ቁልቁለቱን አከፋባት።
የደረጀ አቅሟ የረጠበ እጇ ሳይነጥፍ በግሩም ሃይሌ ግጥምና ዜማ ለጋስነት በጥበበ ወርቅዬ ሙዚቃ ቤት አስተባባሪነት አንዷለም ዳኛቸው፣ ዙማም አያሌውና ወርቁ አንዷለም ጋር “የቆላ ጥንቅሾች” የተሰኘ ኮሌክሽን በመሥራት ያገኘችውን ገቢ በመጨመር የራሷን የባሕል ምሽት ቤት ከፈተችና ለገጣፎን አደመቀችው፤ ይሁን እንጂ በገጠማት የጤና እክል የምሽት ቤቱ ሥራ ከአራት ወር አልዘለለም። ቤቷ ሲዘጋ ጤናዋ ሲናጋ የሰው ፊት ጠቁሮባትና ችግር የማያውቃት ከበቡሽ ያጀባት ሰው ሁሉ በሕመሟ ጊዜ ከጎኗ ሸሸ ። ሰማይ የታከከው ሃብቷ ጠፍቶ በሰው ልብ ጽላት የከተበው ስሟ ተፍቆ “ማነሽ? የት ነበርሽ?” ለመባል በቃች። በየጸበሉ ስትንከራተት ኖራ የልጇን ነፍስ ለማቆየት በሰው ቤት እንጀራ መጋገር፣ ልብስ ማጠብ፣ መሸታ ቤት… ሁሉ ዳበሰች። ከሰራችው ይልቅ ያልሰራችውን ማንሳት ይቀላል።
ኑሮ ተንጋዶ ሕይወት ከብዶ መላ ሲጠፋት ኮማ ሳሙና ፋብሪካ በገባችበት አጋጣሚ ከወሬ ወሬ ሙዚቀኛ እንደነበረች ያወቁት የሥራ ኃላፊዎች ወደነፍሷ ጥሪ ሊመልሷት ነበር፤ በስፖንሰር እጦት አልቻሉም እንጂ። ሕመሟ ከፍቶ ከቤት ሲያውላት “ፈረስ ግዙ ጨው ላያግዙ” እንዲሉ እፍኝ ጥሬ ባይሰፍሩላትም “ምን አለበት? ትንፋሽም መድሃኒት ነው” ብላ የሰውን ምክር በመስማት አያሌው አበጀ ጋር ወዝ ተናሳችና ሁለተኛ ልጇን ወለደች፤ ትዳሩ ግን አልሰመረም። በጤናዋ መታወክ የቤት እመቤት በመሆኗ ገቢያቸው ሲከሳ “ሥራ የለሽ፤ በዚያ ላይ የዳር ልጅ ማሳደጉ” አለና ሁለተኛ ባሏም ትቷት ወጣ።
በአሁኑ ሰዓት የተገናኘነው አቶ የሽዋስ ሚሊዮን በሻማ ማምረቻ ፋብሪካቸው አስጠግተዋት ነው። መልካሙ ሙላት በግጥምና ዜማ የተሳተፈበትና በቅርብ ቀን የሚወጣ “የልጅነት ፍቅር” የተሰኘ ነጠላ ዜማ እንድታዘጋጅ የገንዘብ ድጋፍም አድርገውላታል። “ሰው ለሷ አልኖረም እንጂ እሷስ ለሰው የምትኖር ነበረች” አለ መልካሙ ሙላት እንባው እየወረደ፤ እኔው ወርቁም “የተጎዳ ሰው ስታገኝ ችግሩን እንዲረሳ ያለፈውን እንዳይረሳ የምታግዝ ደግ ነበረች” ይላል። አርቲስት ከበቡሽ ደገፋው ቃለመጠይቁን ስናደርግ እንባዋ እንደጅረት ይፈስ ነበር፤ ያም ሆነ ይህ “እህል ያለመንጋጋ አይደቅ ሰው ያለሰው አይደምቅ” ነውና በቻልነው ልክ እናግዛት መልክቴ ነው።
ሃብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም