የበለስ በረከቶች

“እናቶች እንጀራ ለመጋገር ሰምቶ እሺ ያለውን ምጣድ ያሰሱበትን ጨርቅ ከገላው የቀረውን እሳት ለማጥፋት በእግራቸው ከመሬቱ ጋር ያሹታል፤ እኔንም ሕይወት በኑሮ ሽክርክሪት እንደዚህ ነው ያሸችኝ” አለ የሽዋስ ሚሊዮን ያለፉት አርባ ሶስት ዓመታትን በምናቡ የትዝታ ፈረስ የኋሊት አስግሮ በምልሰት እየፈተሸ። ይህን ሲል በደቡብ ሕንድ ግዛት ቼና መንደር ነዋሪ የሆነውንና የጽናት ምሳሌ ተደርጎ የሚዘመርለትን የአፓ ራዎን የሕይወት ውጣ ውረድን አስታወሰኝ።

ታሪኩ እንዲህ ነው። የሽርሽር ፕሮግራም አዘጋጅቶ ሚስትና ልጆቹን ይዞ ከቼና ወደታሚል ናዱ ባቡር ተሳፍሮ ጉዞውን ጀምሯል። የተጫጫነውን እንቅልፍ ለማባረር ሲል ሻይ ሊቀምስ በወረደበት አጋጣሚ ባቡሩ የጉዟቸው መሃል ወገብ ላይ በበረሃማው ክፍል ትቶት ይሄዳል፤ በዚህም ከቤተሰቡ ጋር ለመቆራረጥ በቃ። ድንጋጤና ሃዘኑ ተዳምሮ መንፈሱን ያወከው አፓ ራዎ የባቡሩን መቆም እየጠበቁ ሻይና ቡና በፔርሙዝ ይዘው የሚሸጡ ትንንሽ ልጆችን ማረፊያ እንዳለ ቢጠይቃቸው ወደሼንፕዳራዝ መሩት። ፍርሃት አዝሎት የተብረከረከ ጉልበቱ እያዘገመ ሼንፕዳራዝ ደርሶ በግዜር እንግድነት አንገት ማስገቢያ ጎጆ ፍለጋ ሲያሥስ ከአንድ ገበሬ ጋር ተገጣጠመና በዕረኝነት ቀጥሮ አስጠጋው። የበቀለባት ደቡብ ሕንድ ግዛት በቼና ከበሬታን በሼንፕዳራዝ ነቀፌታን ብታቀርብለትም ሕይወት ንጽጽር ናትና የክርስቶስን መወለድ ቀድመው ብስራቱን የሰሙት እረኞች መሆናቸውን አምኖ በመጽናናት ለሃያ ዓመታት ያህል አገለገለ። ይህ ጽናቱም በሰዎች ልብ ውስጥ መልካም ስም አትርፎለት የታሚል ናዱና የሼንፕዳራዝ ሀገረ ገዢዎች በመተባበር ለቤቱ አበቁት። የለያያቸው ቀን ፈቅዶ መልሶ ሲያገናኛቸው ጉልቻ የመሰረቱባት ቼና መንደርም ቃል ኪዳኗ ሳይላላ የጠበቀችውን ባለቤቱን ለማመስገንና ለጠፋ ልጇ አፓ ራዎ አቀባበል ለማድረግ ዳግም አሰረገች። “ሴት ጥበብ ናት፤ ጥበብ ደግሞ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር የሚሉ መንፈሳዊ ሃብቶችን ያጎናጽፋል፤ ይህም ትዳርን ያቆማል፤ ትዳር ደግሞ የሀገር ካስማ የትውልድ ዓርማ የሆኑ ልጆች ይፈራበታል” በማለት ተናገረ በእንባ ተውጦ።

የሽዋስ የወግ እንዝርቱን እያሾረ “እኔም ብሆን ከሕሊናዬ ተስማምቼ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ተሞልቼ ባልበረታ ኖሮ ሕይወት የፈተለችልኝ የመከራ ትብታብ ጠፍንጎ ይዞ መቀመቅ ያወርደኝ ነበር” ሲል አጫወተኝ። “አዳምና ሔዋን የተሰመረላቸውን ገደብ አልፈው የፈጣሪያቸውን ሕግ ሽረው የቀጠፏት በለስ ምንም እንኳን የዘላለም ሞት ብታመጣባቸውም ጥራችሁ ግራችሁ ብሉ የሚለውን አምላካዊ በጎ ፍቃድን አግኝተዋል፤ እኔም በመንገዴ ሁሉ እንደበለሷ ክፉ ሰዎች የጋረጡብኝ ፈተና ድካሜን ቢያበዛውም የሥራ ሞራሌን አልሰለበውምና ከእዮብ ትግስትን ከሙሴ ጽናትን ተምሬ ዛሬ ላለሁበት ደረጃ በቅቻለሁ” አለ በድጋሚ ከድቦ ኪዳነ ምህረት መርጦለማርያም እስከሚዛን ቴፒ ገሌቻ፣ ከጎንደር መተማ እስከ አዲስ አበባ ያለውን መንከራተትና እሱነቱን ገልጦ የሚያሳየውን የሕይወቱን ማሕደር ወገግ አድርጎ እያስነበበኝ።

በጎጃም ክፍለሀገር እነፍሴ ሳር ምድር አውራጃ መርጦለማርያም ከተማ ድቦ ኪዳነምህረት ቀበሌ ከአባቱ አቶ ሚሊዮን ይግረመውና ከእናቱ ከወይዘሮ አበባአየሁ ተመስገን በወርሃ ግንቦት 1974 ዓ.ም የሽዋስ ሚሊዮን ተወለደ። ገና ማለዳ ጡት እንኳን በቅጡ ሳይጥል እናትና አባቱ በመለያየታቸው የተነሳ የእንጀራ እናት እጅ ለማየት ተገደደ። ይህም ለጋ እድሜውን በመከራ ሸብቦ የሕይወት ፈተናው አየለና ኑሮውን ዳገት ስላደረገበት ያልጠነከረ አካሉን ለጉልበት ሥራ አዘጋጀ። የተጣሉ ሰዎችን ለመገላገል መሃል ሲገቡ በተተኮሰ ጥይት አባቱን የተነጠቀው የሽዋስ ከአያቱ ይግረመው በላቸው እግር ስር ተተክቶ መሳሪያ መፍታትና መገጣጠም በመማሩ ለእጅ ሙያ ልዩ ፍቅር እንዲያድርበት ምክንያት ሆኖታል። ሆኖም የመሳሪያ ሥራው ለረዥም ጊዜ መዝለቅ አልቻለም። የአያቱ ቤት በመንግሥት ፍተሻ ሲካሄድበት 23 መሳሪያና የመለዋወጫ እቃዎች ስለተወሰደበት እንዲሁም እንጀራ እናቱ መሸታ ቤት ከፍታ ትኩረት ስለነፈገችው ቀምሶ ለማደር የቀን ሥራ ሲያማርጥ ከጫማ ማሳመር ጋር ተዋወቀ። “የገሌ ልጅ እንዳልባል” ብሎ ሲፈራ ሲቸር የጀመረው ሥራ በአክስቱ ስድብና ጥላቻ ደረሰበት። “ ዘር አሰዳቢ፤ ጥንብ ጠራጊ” የሚለው የአክስቱ ስድብ ስደትን እስከወዲኛው አማራጭ እንዲያደርገው ምክንያት ሆነው። ውሎ ሳያድርም ያደገበትን ቀዬ ለቆ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ጉዞ ወደ ሸዋ አደረገ። ደጀን እንደደረሱ አንደኛው ጓደኛቸው ወደኋላ ሲመለስ ሁለቱ ግን እኩሉን መንገድ በእግራቸው ቀሪውን በጭነት መኪና ተሳፍረው

“ጉለሌም አበደ አራዳም አይድን፣

እሷ ታውቀዋለች የምትወደውን።”

ተብሎ የተዘፈነላትን የአዲስ አበባን ምድር ረገጡ።

ሆኖም መንገዳቸው አልቆመም፤ ኪሳቸው ርጋፊ ሳንቲም አልነበረውምና የእግር ጉዞውን ተያያዙት። ለወልቂጤ አፈር እንደበቁ የሽዋስ አካሉ የበሰለ ባለመሆኑ በወር አስራአምስት ብር እየተከፈለው በእረኝነት ሲቀጠር ጓደኛው የጫኝና አውራጅ ሥራ ጀመረ። ከአንድ ወር የወልቂጤ ቆይታ በኋላ ለተሻለ ሥራ ወደሚዛን ቴፒ አቀኑ፤ እዚያም እንደደረሱ ከጠዋቷ ጮራ ድምቀት ጋር ተስፋቸውን አፍክተው ሥራ ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ የኩራ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ሲሳይ ታከለ ጥቁር ሰሌዳና ወንበሮችን የትራንስፖርት አገልግሎት እስካለበት አካባቢ ድረስ እንዲያጓጉዙ የሸክም ሥራ ሰጧቸው። የሽዋስ ፍጥነቱ ከዐይን ይቀድማልና “ጋሼ እዚህ ሀገር የዝንጅብልና እርድ ቁፋሮ አለ ሲባል ሰምተን ነውና የመጣነው የሚያሠራ ሰው ካለ ቢያገናኙን?” ሲል ጠየቃቸውና መምህሩ ከራሳቸው አባት ዘንድ አደረሷቸው። በስምምነታቸው መሰረት በመጀመሪያ ዙር ስምንት ኩንታል ዝንጅብል አገኙና እኩል ተካፈሉ፤ የደረሳቸውንም አራት ኩንታል ሸጡና የሌሊት ብርድ ልብስ መግዛት ቻሉ። የለበሱትን ቁምጣ በዘመን አመጣሽ ፋሽን አልባሳት ቀየሩ። ማተበኛነታቸው የባለቤቶቹን ልብ ገዝቶ እንደልጆቻቸው ቆጥረዋቸው አብረው መኖር ቢችሉም ወባ ጣለቻቸውና ጓደኛው ወደጎጃም ሲመለስ የሽዋስ ግን “ምን ይዤ እመለሳለሁ?” አለና ጥርሱን ነክሶ ሊሠራ ወደደ።

የሽዋስ እንደወላጅ አምኖ የተጠጋቸው አቶ ታከለ “ትህትና የሞራል ስንቅ ነው” ብሎ ተንበርክኮ እግር ማጠቡ ሳያንስ አንዴ በእረኝነቱ አንዴ በንግድ ሥራቸው እየተተካ ሲያገለግላቸው የኔ የሚለው ጥሪት እንዲያፈራ ከማገዝ ይልቅ ልጆቻቸው ባጠፉ ቁጥር እሱ ቢኖርበትም ባይኖርበትም አለንጋ ያስታጥቁት ጀመር። “ቀን ጥሎኝ ነው? ወይስ ሰው ከድቶኝ አቅሜ ሳይጠና ለመከራ የበቃሁት?” አለና እንባውን እያዘራ የደከመበትን የሁለት ዓመት የላቡን ፍሬ ሰባራ ሳንቲም ሳይጠይቅ ፍርዱን ለእግዜር ትቶ ቤቱን ለቆ ወጣ።

ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ብለው የጨለማ ካባ ቢያከናንቡትም የሽዋስ ግን ባይነስጋቸው የገፉት በሕሊናቸው እንደሚያቀርቡት፣ ባፋቸው ያቀለሉት በልባቸው እንደሚያነግሱትና ያንንም ቀን በጥረቱ እንደሚወልደው አምኖ ጎዳናውን እየታዘበ በመጓዝ ላይ እንዳለ ተሰማ ከሚባል ያካባቢው ነዋሪ ጋር ተገናኘና እህቱ መሸታ ቤት ስላላት በውሃ ቀጂነት እንዲያግዛት ዋጋ ተነጋግረው ወሰደው። የሽዋስ ሥራ ሳይንቅና ለትንሹም ለትልቁም በትህትና እጅ እየነሳ ዝቅ ብሎ በመታዘዙ ተወዳጅነትን አተረፈና የተሰማን እህት ቤቷ ውስጥ ሳንቡሳ እየሠራ እንዲሸጥ ያቀረበላትን ሃሳብ ፈቅዳ ይሁንታን ሰጠችው፤ የልቡ መሻት ደርሶ ገበያ ሲቀናው ምንም እንኳን አቶ ታከለ ገንዘቡን አይስጡት እንጂ አብሯቸው ሲኖር የምግብ አዘገጃጀትን በጨረፍታም ቢሆን ተምሯልና ከልቡ ይቅር አላቸው። ሥራው ጦፎ አቅሙ ሲደረጅ ጌለቻ መንደር ሮጠው ያልጠገቡ ሰርተው ያልደከሙ ወጣት ነዋሪዎቿ ከጥንካሬው ይማሩ ዘንድ ስለ የሽዋስ ምሳሌነት ልትመሰክር ልሳኗን ፈታች፤ ይሁን እንጂ ሙገሳዋንም ደስታዋንም ምላስ አድጥ የሚያስመስልባት እክል ገጠመው። አንድ ቀን ለማገዶነት የቆረጠው የዘንባባ ዛፍ አቅጣጫውን ስቶ ሲወድቅ የታፋውን አጥንት ሰበረውና ለሃያ ስምንት ቀናት ለአልጋ ዳረገው፤ ቢሆንም ግን ለሕመሙ እጅ አልሰጠም። ባለባላ እንጨቶችን ቆርጦ እንደክራንች በመጠቀም እየተንቀሳቀሰ ወዳጁን ተሰማን “ስሠራ ገንዘብ አገኛለሁ፤ ገንዘብ ሳገኝ እበላለሁ፤ ስበላ እድናለሁ” በማለት አሳመነውና በጋራ የሻይ ቤቱን ሥራ ቀጠለ።

“ለሰው ልጅ ትልቁ በሽታ አእምሮው ሥራ ሲፈታ ነው” የሚለው የሽዋስ መንፈሱን በብሩህ ተስፋ ኮትኩቶ ጉልበቱን በሞራል አበርትቶ በመሥራቱ አካላዊ ድጋፉን ጥሎ በራሱ መቆም ቻለና እጅን በአፍ አስጫነ። ገበያው ደርቶ መናኛ ጥሪት ሲያበጅ ከከተማ ወደገጠር ሸቀጥ ለሚያመላልሱ ነጋዴዎች ለማጓጓዣነት አህያ ገዝቶ ትርፉን ሎሚ ለሁለት ሊሉ አከራያቸው። ሃብቱ ስር ሰደደና እንደዋርካ ሰፍቶ ሲደላደል ከኪራይ ቤት ወጣና ወዙን አንጠፍጥፎ በገዛው ቤት ማለፊያ ሆቴል ከፈተ። ይሁን እንጂ ሕይወት በቀደደላት ቦይ አልፈሰሰችለትም። “ሃይ ሃይ” ብለው ያስወጠኑት ጎጆ በልጅ እሳቤ ደፈረሰና የደከመበትን ሃብት ሜዳ በላው። ያገባት ሴት ምራቅ የዋጠች አለመሆኗ ጋር ተዳምሮ ወዳጄ ያላቸው ሁሉ ገንዘቡን እየከዱት ባዶ እጁን ቀረና አጎቱ ዘንድ ደርሶ ለመምጣት ወደ ጎንደር አቀና።

የተሻለ ሥራ እንዲያገኝለት አሊያም መንቀሳቀሻ ገንዘብ እንዲሰጠው አስቦ ችግሩን ያዋየው አጎቱ ግን አራት መቶ ብር ከመስጠት የዘለለ ጆሮ ሰጥቶ በቅጡ ሊያዳምጠው እንኳን አልፈቀደም። ወድቆ መነሳትን ጠንቅቆ የሚያውቀው የሽዋስም ወደሁመራ ሄደና ቁርስ ቤት በመቀጠር ሕይወት የወረወረችበትን ቅዝምዝም ጎንበስ ብሎ አሳለፈው። በሥራ ትጋቱ አብዝተው የሚደነቁበት የቤቱ ባለቤቶች ፍላጎቱን ገድቦ ነገን አስቦ ያጠራቀማትን ደሞዙን ከምርቃት ጋር ሰጥተው ሸኙትና በመተማ ምድር የራሱን ቁርስ ቤት ከፈተ። ከቁርስ ቤቱ ጎን ለጎንም የጀመረው የመስኖ እርሻ ያግዘው በነበረው በወንድሙ ሞት ሰበብ አመርቂ ውጤት ባያገኝበትም ተስፋ ሳይቆርጥ ፊቱን ወደ ከተማ ግብርና መለሰ። የወተት አቅርቦት እጥረት መኖሩን ልብ ያለው የሽዋስ ከባሕርዳር ስድስት የወተት ላሞችንና አንድ ኮርማ ገዝቶ ማርባት ጀመረ። ይህ ሥራውም አድጎ የወተት ላሞቹን ቁጥር ሰላሳ ማድረስ ቻለ። ይሁን እንጂ በገጠመው ቢሮክራሲ ሥራው ተደናቅፎ ጓዙን ጠቀለለና አዲስ አበባ ገባ።

አንድ ቀን ጦር ኃይሎች አክስቱ ጋር አድሮ ሱሉልታ የምትኖረውን እህቱን ለመጠየቅ ሊሄድ የታክሲ ሰልፍ ይዞ በቆመበት ዙሪያውን ሲያማትር “የሻማ ሥራ እናሰለጥናለን” የሚል ማስታወቂያ ተሰቅሎ ተመለከተ። ከመቅጽበት ሃሳቡ ወደ ቻግኒ ሽምጥ ጋለበ። ቻግኒ ከሚያስተምር አጎቱ ዘንድ በሄደበት አጋጣሚ የማርያም ማህበር ሲጠጡ የለኮሱትን የሻማ ቅላጩን ሰብስቦ በማቅለጥ የዛሃ ክር በዣንጥላ ሽቦ እየሳበ ሻማ መሥራቱን አስታወሰና ፈገግ አለ።

ጊዜ ሳያጠፋ አንድ ማምረቻ ማሽን ገዝቶ የጀመረው የሻማ ሥራ በአዲስ ካፒታል አጋዥነት አድጎ ዛሬ ከሃያ በላይ ማሽኖችን ታጥቆ ለአርባ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ባሁኑ ሰዓትም ሰላሳ ሠራተኞችን ለመጨመር በዝግጅት ላይ ይገኛል። በሻማ ሥራው ውጤትም ሶስት ተሳቢ መግዛቱን አጫወተኝ።

ከአፉ የማይነጥላት እህቱ ሰላማዊት ብርታት ሆነችው እንጂ በኮሮና አማካኝነት የገበያ መቀዝቀዝና ምርቱን የተረከቡ ነጋዴዎች ገንዘቡን መክዳታቸው በሥራው ሂደት እንቅፋት እንደነበሩበት አልሸሸገኝም። አርቲስት ከበቡሽ ደገፋውና ሌሎችም ሠራተኞች በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በቀዳሚነት እንደሚሰለፍ ምስክርነታቸውን ሰጥተውኛል።

ባሁኑ ወቅትም ከሻማ ሥራው ጎን ለጎን በከተማ ግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ዝግጅት መጨረሱን አጫውቶናል። የልቡ መሻት ይሰምር ዘንድ በመመኘት ጽሁፌን ቋጨሁ።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You