በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አድዋን ስናስብ የምናስበው ቶሎ ድላችንን ነው።ድላችን ያስከፈለውን ዋጋ እና የፈጠረልንን ድንቅ ብሔራዊ ጥምረት ግን አለዝበን ነው የምናየው።ግን ከቶውንም ቸል የማንለው በአንድ ቋንቋ (ልብ) በአንድ ሐሳብና በአንድ ኃይል ተጣምረን ለአውሮፖውያን ራስ ምታት የሆነውንና ለተገዢ ሐገራት ሁሉ ግን አንቂ የሆነውን ደወል ከደቡብ እስከ ሰሜን ከምስራቅ እስከ ምእራብ ላቲን አሜሪካውያንና ካሪቢያን ደሴቶች ድረስ ደወል የደወልነው እኛ ነን።
እኛ ነን፤ ሲገፉን መገፋት እምን ድረስ ብለን የነጮቹን ቅኝ ገዢዎች ፍላጎት ያመከንን።እኛ ነን፤ ነጮች ልክ ናቸው፤ ብለው ያስቡ የነበሩ ጥቁርና ብጫ (እስያውያን) ህዝቦችን የአስተሳሰብ ለውጥ ያጫርነው።እኛ ነን ቻይናውያን በጃፓን ቅኝ ገዢዎች ፊት ለመገዳደር እንዲቆሙ በር የከፈትነው።ቻይናዊው የታሪክ ፀሐፊ “የምስራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያውያን፣ ጣሊያኖችን በመሳሪያ ሃይላቸው እንዳይመኩና እንዳይጫኗቸው እድል ነስተዋቸዋል፤ እኛስ?” ሲል ነው፤ ህዝቡን የጠየቀውና ያነሳሳው።እኛ ለሌሎች የተቋቋሚነትና የአይበገሬነት ምሳሌዎች ነው፤ ሆነን የተገኘነው።
አድዋ ያለመንበርከክ፤ ለመገዛት ያለመረታትና ያለመገ ፋት ምልክት የሆነው፤ በህብረታችን ነው። በመተባበራችን ነው።በሁለተኛው የኢትዮ-ኢጣሊያ ጦርነት፣ ጣሊያኖች የተገነዘቡት እውነት ካለፈው የተለየ ነበረ።ይህንን ህዝብ ያስተባበረውን የሸዋውን አካባቢ ህዝብ ጥምረት፤ ባህሉንና ቋንቋውን መሰረት አድርጎ መነጣጠል፣ ቀላሉ መንገድ አድርገው ነበረ፤ የተገነዘቡትና ያዘጋጁት።
በዚያ ላይ ትናንሾቹን ልማዶቻችንን ጠንቅቀው በማስጠናት ጭምር ተጫውተውብናል።በአማራው መካከል ጨዋና ቡዳ፣ በወላይታው መካከል ነጻ ሰውና ፉጋ፣ በሲዳማውም፣ በትግራዩም ፣ በኦሮሞውም፣ ሁሉ ያለውን የዘውግና የአካባቢ ሁሉ መገፋፋት በሚገባ ተጠቅመውበታል።
የማይጨው ውጊያ በአየር የበላይነትና በዓለም የውጊያ ህግ ያልተፈቀደውን የመርዝ ጋዝ በመጠቀም የድሉ ሚዛን ወደ እርሱ እንዲያጋድል ምክንያት መሆኑ የማይካድ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን በሃይማኖት ስብከት ስም፣ በወፍጮ ቤት ባለቤትነትና በዳቦ ጋጋሪነት በሐገሪቱ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች በመግባት የህዝቡን ባህል ስነልቦናና የአኗኗር ዘይቤ በማጤን ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሲዘረጋ ሐረርጌን ወይ ኦጋዴንን ከዋናዋ ሶማሊያ በመቀላቀል፤ ሶማሊያ ፕሮቪንስ፣ ትግራይን ከኤርትራ በመደመር፣ ኤርትራ ፕሮቪንስ፣ ጎንደር ጎጃምን ወሎንና ሸዋን በአንድ አድሚኒስትራሲዮን ስር በማድረግ አማራ ፕሮቪንስ፣ ወለጋን፣ ከፋንና ከፊል ሸዋን አርሲንና ባሌን ሲዳማን በአንድ ስር በመጠቅለል ኦሮሞ ሲዳማ ፕሮቪንስ፣ በማድረግ በባህል የሚቀራረቡትን ወዳንድ በመሪ ቋንቋነት ደግሞ በየራስ አድርጎ ለመግዛት ሙከራ አድርጎ ነበረ።
ይህን ዘዴ ሰው በቅርብ ባህሉ እና ቋንቋው የመለየት ዘዴ፣ ለአገዛዙ ምቹ ይሆንልኛል በሚል ዘዴ ነበረ፤ በጠላትነት የጠነሰሰው።ይሁንናም አይደማመጡም ብሎ ሲያስብ ያለሶሻል ሚዲያ፣ ያለ ኢሜይልና ያለቴሌግራም፣ ወይም ትዊተርና ሬዲዮ ጋዜጣ ተደማምጦ፣ በእረኛና አዝማሪ እየተቀባበለ ጠላቱን መድረሻ አሳጣው።በነገራችን ላይ ለወቅቱ አዝማሪዎች ምስጋና ይግባቸው።ጠላትም ይህንን አውቆ፣ ብዙ ስመጥር አዝማሪዎችን በወቅቱ ፈጅቷል።
በዚህ ጊዜ አብያተ-ክርስቲያናት እና ገዳማት ከፀሎታቸው ሌላ በደማቸው የከፈሉትም ዋጋ በቀላሉ የሚገመት አይደለም ።የሸዋው አቡነ ጴጥሮስና የኢሉባቦሩ አቡነ ሚካኤል ተጠቃሽ ሰማእታትና የመነቃቃት ሃይልም ናቸው። ነገር የተና የሰከነና ዝም ያለ ሲመስልም ገጣሚያን በብዕራቸው ብዙ ይቀሰቅ ነበረ።እንደ እነ፣ ዮፍታሔ ንጉሴና ሐሰን አሚኖ ያሉ ገጣሚያን ድርሻም የሚናቅ አልነበረም ።
በአብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም እርምጃ ሳቢያ፣ ሌሎች የጣሊያን ሹሞችና ማርሻል ግራዚያኒ ቆስለው የአየር ሃይሉ አዛዥ ሲሞት፣ በሰጠው የእብሪት ትዕዛዝ በአዲስ አበባ ብቻ በሶስት ቀን ከሰላሳ ሺህ በላይ ሰው በጥይት፣ በእሳት በአካፋና ዶማ እየተፈለጠ ሲገደል፤ ከሁለት ሺህ በላይ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትም ሽፍታ ደብቃችኋል፤ ተብለው ተፈጅተዋል፤ በሐገሪቱም ሌሎች ከተሞች እንዲሁ ለከት የለሽ ኢሰብዓዊ ግፎችና ግድያዎች በመቀጣጫነት ስም ተፈጽመዋል።
ዮፍታኼ ባለቅኔው ሐገሩ ስታዝን እያዘነ፣ ስትነሳ እያበረታታ ብዙ ቀስቅሷል ።
ድንግል ሐገሬ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ፣
ህጻናቱ ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ፤
አስጨነቀኝ ጭንቀትሽ፣
እመቤቴ ተመለሺ።(1929 ዓ.ም) ሲል ለነጻነት መመለስ ክፉኛ የሃዘን እንጉርጉሮውን ማንቂያ ደወል አሰምቷል።
ጣሊያን ከ1929 ዓ.ም በኋላ ባሉት ዓመታት የተረጋጋ ሲመስልና የዓለም መንግስታትን ይሁንታ ለማግኘት ብዙ ሲጥር ብዥታው የጥፋታችን መንስዔ ሊሆን እንደሚችል አሳስቦት ፡-
ተስቦ ገብቷል እቤታችን ፤
መቼ ይወጣል በሽታችን። ሲል አበክሮ አርበ ኛው እንዲነቃቃና ጣሊያንን መግ ቢያ መውጫ እንዲነሳ ሲያሳስብ ነበረ።ያለው አልቀረም ፤ በየስፍራው በጎበዝ አለቃው እየተመራ በየስፍራው ጣሊያንን ማስጨነቅ ተያያዘ።ሲታገሉ መውደቅ፣ ሲመቱ መንፏቀቅ እንጂ ወድቆ ላለመቅረት ወስኖ በዱር በገደሉ ተጋድሎውን አፋፋመው።
ያኔም ነው፤
አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተተግሬ፤
ስመኝ አድሪያለሁ ትናንትና ዛሬ።…. እያለ የአድዋን ጀግኖች ገድል በመተረክ መንፈሳቸው በአርበኞች ልብ እንዲያንሰራራ መቀስቀስ የጀመረው።ይህም ተሳክቶልን ጸረ-ፋስሽት ትግሉ ተፋፍሞ ቀጠለ።ይህ ግን ያለዋጋ አልተገኘም።አንዱ ሲወድቅ ሌላው እየተተካ በየስፍራው ያጋጠመውን የጠላት ፍላጻ በደረቱ በመመከት ነው፤ ወደድል የመራው።ትግሉ ማይጨው ላይ የተቋጨ ሲመስል እየተቀጣጠለ፣ እየቀጠለ ነው፤ የሄደው።
በሲዳማ ጀግናው አሊቶ ሔዋኖ እንደ ባላባትነታቸው፣ ህዝቡን አረጋጋልን ግዛትህን አንነካብህም፤ ሲሏቸው እንዲህ ያላችሁት እንዴት ደግ ብታስቡልን ነው፤ ሲሉ ጠየቋቸው።ከላያችሁ ላይ አማራን አንስተንላችኋልና ደስ ሊላችሁ ይገባልና፤ በሰላም ህዝቡ አርፎ እንዲቀመጥ ንገሩልን፤ ይሏቸዋል።አማራን ማንሳታችሁ ጥሩ ነው፤ ግን ጥያቄ አለኝ።እናንተስ አማራን አባርራችሁ፣ ልትሄዱ ነው ፤ ወይስ እዚሁ ልትቀሩ ነው፤ ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ።
የአካባቢው ገዢ የነበረው ጣሊያንም አሁን ታላቂቱ ጣሊያን ኢትዮጵያን በሙሉ የያዘችው ልትለቅ አይደለም።እኛ እናሰለጥናችኋለን፤ እኛ እናስተምራችኋለን፤ እኛ ስልጣኔ በሙሉ ሲዳማ እናዳርሳለን ሲሏቸው፤ ከት ብለው ስቀው ፤ በቀደም እለት የፈጃችኋቸው የሲዳማ ልጆችስ ብለው ደግመው ሲጠይቁ እነርሱ እናንተ በሰላም እንዳትኖሩ የሚበጠብጡ ሽፍቶች ስለሆኑ ነው፤ እርምጃ የወሰድንባቸው፤ አሏቸው።
በሲዳማ አንድ ተረት ከሰማኸኝ እነግርሃለሁ አሉት።
ምን የሚል ሲል በንቀት ይጠይቃል።
“ዓይናውጣ እንግዳ፣ ስጋውን ወደራሱ አድርጎ ባለቤቱን ከጎመኑ ብላ ብሎ ይገፋል” አሉና፤ ቡርሳሜውን ያዘጋጀችው ሚስቴ፣ ወርሜው (መቀረጫው) የኔ፣ ሻናው (ጎመኑ)የኔ ፣ ማላው (ሥጋው) የኔ፣ አንተን አካፋይ ማን አደረገህ? ሲሉ ይጠይቃል።እና ሐገሩ የእኛ፣ ህዝቡ የእኛ፣ ሰላሙም የእኛ የምታስጠብቀው አንተ እንዴት ትሆናለህ ፤ አሉት።
ይህንን ሲሰማ በቁጣ የጦፈው ጣሊያን፣ “አንተ ሰው መቀጣጫ ነው የማደርግህ!” ሲል ይዝትባቸዋል።ብቀበልህም ልትገድለኝ፣ ባልቀበልህም ልትገድለኝ ማቀድህን መቼ አጣሁት ሲሉ ነው፤ መልስ የሰጡት።እንዳሉትም አልተዋቸውም እንደ ሽፍት ገድሏቸዋል።የዚህ ታሪክ ባለቤት ሐውልት ሀዋሳ ላይ ቆሞላቸዋል።
በየስፍራው ያሉ የሀገሪቱ ልጆች ባሳዩት ቆራጥነትና ህብረት ነው፤ የጣሊያን ዕድሜ ያጠረው።በኢትዮጵያ ምድር መጥቶ ተመችቶት ዘመን ያስቆጠረው የራሳችን ሥቃይና የአለመደማመጥ በትር እንጂ የትኛውም ባእድ ዕድሜ አላገኘም።በ16ኛው ክፍለ ዘመን ፖርቱጋሎች ሞክረውናል አልቻሉም፤ በኋላ ግብጾች ፈትሸውናል፤ አልሆነላቸውም ፤ ቱርኮች በሐረር በኩል ጎብኝተውናል አልቻሉም፤ እንግሊዞች በመስፋፋት ጥበብና በምጽዋ በኩል ጎንትለውናል፤ አልተሳካላቸውም።
አድዋ ለማይጨው በጣሊያኖች በኩል የ40 አመት ቁጭትና የበቀል በትርና የመንገብገብ ውጤት ሲሆን፤ ለእኛ ሁለተኛው ህጋዊ የመከላከል ጦርነት እምብርት የአንድነታችን ማሳያ የአርበኝነታችን መቀስቀሻ መግነጢስ ነው።አድዋን ስናስብ በማይጨው የተሰበረው ቅስማችን ቀና ይላል፤ አድዋን ስናስብ የየካቲት 12/1929 ዓ.ም እልቂት መዓት ምክኑ ይታወቀናል፤ አድዋን ስናስብ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ቀንዲላችን የማይጠፋ እሳት ብርሃን ወገግታ ይታሰበናል፤ አድዋን ስናስብ መላው የጥቁር ህዝብ ኩራት በመሆናችን በወረራው ወቅት የተሰማንን ስብራት ይጠግናል፤ አንገት እንዳንደፋ ያደርገናል።
አድዋ ለማይጨው ታላቅ ወንድም ብቻ አይደለም፤ ለጥቃት ያበቃንን ምክንያት አውቀን በድህረ ወረራው ማግስት እኛ የአየር ሃይል እንድናደራጅ፣ እኛ የምድር ጦራችን በሜካናይዝድ ብርጌድ እንዲታጠቅ፣ እኛ የጦር ሃይላችን ዘመናዊ የእዝ ሰንሰለት እንዲኖረው ምክንያት ሆኖልናል።
በማይጨው ውጊያ ጣሊያን በድንገታዊ የማጥቃትና የማሳሳት ስልት (Surprise and deception) የዋሁን ህዝብ ክፉኛ ጎድቶታል።በርሜል በርሜል የሚያህለው ቦንብ ከሰማይ ሲወድቅ፣ እቃ የተጣለለት የሚመስለው ተዋጊ ቆሞ አጠገቡ ሲፈነዳ ነው፤ የመርዝ ጋዝ ጉዳቱን ውሎ አድሮ ያወቀው።
የኢትዮጵያ ልጆች መሳሪያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ቆመህ ጠብቀኝ፣ አልቤንና ምንሽር ሳይወጣ ጣሊያኖች መትረየስና ታንክ ይዘው ነው፤ የመጡበት።ሌላ ሌላው የመሳሪያ ብልጫ እንዳለ ሆኖ በተጨማሪም የወቅቱ የዓለም መንግስታት “ሊግ ኦቭ ኔሽንስ” የመሳሪያ ፋብሪካ ባለቤቲቱንና ወራሪዋን ሐገር ከተወራሪዋ እኩል የመሳሪያ ማዕቀብ መጣሉ አስቂኝ ነገር ነበረ።
እና ይህን ሁሉ በማጤን አድዋን ስናስብ ኩራት ቢሆነንና የማይጨውን ድካም የማስረሻ መነሻ እንዲሆነን ምክንያት ስለሆነ እናወድሰዋለን።እኩል ከቆምን የማንሸነፍ ነንና፤ እኩል ከቆምን የማንወድቅ መሆናችንን እንድናጤን አድርጎናልና፤ ድክመታችንን ፈትሸን ለመክላትና ጥንካሬን ለማዳበር ኃይል ሆኖናልና።
አድዋ ለማይጨው የኩራትና የአልበገር ባይነት ራስ የሆነው ያክል፣ ማይጨውም ለአድዋ ወድቆ የመነሳት ተገፍቶ የመነቃቃት ምልክት ሆኖ ታይቷል።እንደተገፋን አልቀረንማ እንደተወረርን አልተረሳንማ።
ተነስተናል፤ ቆመናል።ማናቸውን ድላችንን እና ሽንፈታችንን እንደ አድዋ ሁሉ ማይጨውም የቁስልና የወረራ ምልክታችን ነውና እንደ የካቲት አስራ ሁለት ሁሉ፣ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ እንዳሉት ከአበባ ማስቀመጥ ዝክር ባለፈ በትምህርት ገበታችን ላይ በዝርዝር ተቀምጦ ትውልድ እንዲማርበት ማድረግ ዳግመኛ ስህተት እንዳይፈፀም ያግዘናል።ትውልዱ ሲማር ምን ለምን ሆነ ፣ ብቻ ሳይሆን የሆነብንን ደግመን እንዳንኖረው እንዴትነቱ ከማስጠንቀቂያ ታሪክ ጋር ማስቀመጥ ይገባናል።
አሁን በቅርቡም እርስ በእርሳችን ያደረግነውን ማድረግና፣ የሆነብንን መሆን ለትውልድ በተዘክሮ ማስቀመጥና እንዳንደግመው ማስተማሪያ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ።ዕብሪት፣ ንቀትና ትዕቢት ፍጻሜው መራራ መሆኑን ተረቺው ወገን ብቻ ሳይሆን ረቺውም (አሸናፊና ተሸናፊው ላለማለት ነው) ሁሉም በሚገባ መረዳት እና ተከባብሮ በእኩልነት መኖር ለዘላቂ ሰላማችን ጉልበት እንደሚሆን መረዳት አርቆ አስተዋይነት ነው።
ጀግና ዘር አለ ካልን፣ ፈሪ ዘር አለ፤ ማለታችን ነው፤ ብልህ ዘርአለ ካልን ሰነፍ ዘር አለ ማለት እንዳይሆንብን በንግግራችንም ሆነ በጽሑፋችን ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ስራችንን ማከናወን አለብን።የተረታው እብሪት፣ የተሸነፈው ማንአህሎኝነት፣ የተዘረረው ግፈኛነት ነው።ስለዚህ በመጪው ግዜያችን ውስጥ የመጣንበትን መንገድ አስበን፤ የምንሄድበትን በላቀ ጥበብ መለካት የትውልዱ ፋንታ ነው።
መልካም የአድዋ ድል መታሰቢያ ይሁንልን !!
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013