እንደ አረም እያደገ ያለው ሱሰኝነት

ሱስ በኢትዮጵያ የብዙ ወጣቶች አሳሳቢ ችግር እየሆነ ነው። በከተማ እና በመንደር፣ በትምህርት ቤቶች እና በጎዳናዎች ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወጣቶች በሱስ ወጥመድ ውስጥ እየገቡ ናቸው። በእርግጥ ይህ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም የሚስተዋለው። በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶች ተመሳሳይ ችግር እየተጋፈጡ ነው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ሱሰኝነት በፍጥነት እያደገ ነው። በውጤቱም ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች እና የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታን ፈተና ውስጥ ሊከት እንደሚችል ይታመናል።

በዛሬው የ«መጋቢ አዕምሮ» ዓምድ ላይ በሱስ ላይ ትኩረት ለማድረግ ያስገደደን ምክንያትም የአደጋው መጠን መስፋት ነው። ብዙ ወጣቶች ሱስ በተለያየ ምክንያት ይጀምራሉ። በተለይ በሕይወታቸው ውስጥ በሚያጋጥማቸው ጭንቀት፣ በእኩዮች ግፊት፣ በትምህርት ገበታቸውም ይሁን በሌሎች የሕይወት መንገዶች ላይ እራሳቸውን በሚገባ መምራት የሚያስችል እድል በማጣት ምክንያት ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም ይጀምራሉ።

አንዳንድ ወጣቶች በሱስ ለመጠመዳቸው ምክንያት በሕይወት አሰልቺ አጋጣሚዎች ሲጋፈጡ እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሲገቡ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተመሳሳይ ወጣቶች በቤት ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች (የአባትና እናት አለመስማማት፣ የኢኮኖሚ ችግር) ምክንያት የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፤ ይህንን ለመሸሽ የሚያስረሳቸውን ነገር ይፈልጋሉ። የመጀመሪያም ምርጫቸው የሚሆነው ታዲያ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገር መጠቀም ነው። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርላቸዋል፤ ነፃነት እንዲሰማቸው እና ከችግሩ የተላቀቁ እንዲመስላቸው ያደርጋል። ከጊዜ በኋላ ግን እራሱ ሱስ አስያዡ ንጥረ ነገር ሕይወታቸውን ወጥመድ ውስጥ ይከትተዋል። ማቆም ቢፈልጉ እንኳን በቀላሉ አይችሉም። በዚህ ጊዜ የሱስ ሕይወትን አንድ ብለው ይጀምራሉ። ከትንሽ የጀመሩት ሱስ ከዚያ በኋላ ሕይወታቸውን ይቆጣጠራል። ከማይወጡበት ማቅና ችግር ውስጥ ይዘፈቃሉ።

ሱስ እያደገ ሲሄድ ጤናን ማወክ ይጀምራል። ሰውነትን ደካማ ያደርጋል። አእምሮ ተቆጣጥሮ ደካማ ያደርጋል። የንጽህና መጎዳል ያስከትላል። በራስ መተማመንን ያሳጣል፤ ሌላም…ሌላም…። ለምሳሌ አንዳንድ ወጣቶች ሲጋራ በብዛት በሚያጨሱበት ወቅት ለሳንባ ሕመም እና ለሌሎች ተያያዥ በሽታዎች ይጋለጣሉ። ሌሎች ደግሞ አልኮል ጠጥተው ጉበታቸውን ክፉኛ ይጎዱታል። ከዚህም ከፍ ያሉ አደንዛዥ እፅና ሌሎች አንጎልን የሚጎዱ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ አሉ። ከጊዜ በኋላ የበለጠ ሕመም፣ የበለጠ ድካም እና የበለጠ ሀዘን ውስጥ ይጥላቸዋል። ሱስ ያለባቸው ወጣቶች ጥሩ እንቅልፍ መተኛት አይችሉም፣ ክብደታቸው ይቀንሳል፣ በቀላሉ ይታመማሉ።

ሱስ ይህንን ብቻ አያመጣም፤ አንዳንድ ሱሰኛ ወጣቶች በሕይወት ዘመናቸው አብረዋቸው የሚቆዩ በሽታዎች ተጠቂ ይሆናሉ። ወጣቶች ቶሎ ቶሎ ከሚሞቱበት አንዱ ምክንያት ሱስ እንደሆነ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሱስ ልማድ ብቻ አይደለም፤ ከባድ የጤና ጠንቅ ጭምር ነው። ሱስ ሰውነትን የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥም ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር እኩይ ተግባር ነው። በሱስ የተጠመዱ ብዙ ወጣቶች ትምህርት ቤት መሄድ ያቆማሉ። ከቤተሰባቸው እንዳይስማሙ ያደርጋቸዋል። ወላጆቻቸውን ሊዋሹ ወይም ሱሳቸውን ለማርካት ሲሉ ስርቆት ውስጥ እስከመግባት ይደርሳሉ። ከቤተሰብ ጋር ብቻ ሳይሆን ሱስ ያለባቸው ወጣቶች የጓደኞቻቸውን አመኔታ ያጣሉ፤ ይገለላሉ። ከዚህም በከፋ ሁኔታም ወደ ከፍተኛ ወንጀል ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እንደ ቀልድ በተጀመረ ሱስ ምክንያት በአንድ ወቅት ተስፋ የነበረው ወጣት ወደ ውስብስብ ችግር ውስጥ ይገባል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገራችን ኢትዮጵያን የሚሆነውን ነገር በጥልቀት ስንመለከት ሱስ በብዙ ቦታዎች እንዴት እየተስፋፋ እንደሆነ እናያለን። በአንዳንድ አካባቢዎች ጫት መቃም በጣም የተለመደ ሆኗል፤ እንደ ባሕል የሚቆጠርበትም ቦታ እንዳለ ልብ ይሏል። በተለይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የአልኮል መጠጥ መጠጣት እየጨመረ ነው። አንዳንድ ወጣቶች ትንቧሆ (ሲጋራ) ወይም ጠንካራ እጾች ይጠቀማሉ። የኢንተርኔት እና የቪዲዮ ጌም ሱሰኝነትም እያደገ የመጣ ችግር መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ወጣቶች ቀኑን ሙሉ በስልካቸው ላይ ያሳልፋሉ፣ ትምህርት ቤትን፣ ሥራን እና ግንኙነታቸውን የሚጎዳ ከባድ ሱስ ነው። እነዚህ ልማዶች መጀመሪያ ላይ ምንም ጉዳት የሌላቸው ይመስላሉ። ነገር ግን ቀስ በቀስ አእምሮን በመቆጣጠር ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ። ይህ ዓይነቱ ሱስ ደግሞ በወጣቶች ዘንድ ብቸኝነትን እና ሀዘንን ያመጣል።

የሱስ አስከፊው ጎን አንድን ሰው ብቻ የሚጎዳ አለመሆኑ ነው። ሱሰኛ በሆኑ ወጣቶችና በዙሪያቸው ያሉ ብዙ ሰዎችም የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፤ ወላጆች ልባቸው ይሰበራል። ልጆቻቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸው ብቻ ሳይሆን ከዚያ የሚወጡበትን መንገድ ለመፈለግ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። ተማሪዎች በሱስ ምክንያት መማር ሲያቆሙ መምህራን በሥራቸው እና በጥረታቸው አለመሳካት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገባሉ። በሱስ ምክንያት ማኅበረሰብ፣ ሀገር ጥንካሬውን ማጣት ይጀምራል። ወጣቱ ሲጠፋ የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታም አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው። ለዚህ ነው ይህ ችግር የሁሉም ዜጎች የሆነው። ጥናቶች አንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መካከል ወጣቱ ድርሻውን ይወስዳል።

ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሱስ ቀውሱ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ችግር የሆነው። የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ፅህፈት ቤት ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በዓለም ዙሪያ ከ 35 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአደንዛዥ ዕፅ ይሰቃያሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከ35 ዓመት እድሜ በታች ናቸው። ይህ ቁጥር በአፍሪካም እየጨመረ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያመለክተው ደግሞ፤ በአሁኑ ጊዜ ሱስ ለወጣቶች ጤና መጓደል ዋነኛ መንስኤ ነው። እነዚህ እውነታዎች ይህ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ እንዳልሆነ ያሳዩናል። ዓለም አቀፍ አንድምታው በምድራችን ላይ ከባድ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል ያመላክታል። ሆኖም ይህንን አስከፊ ችግር ለመቆጣጠር የሚያስችል ተስፋ አለ። በችግሩ ላይ ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ግንዛቤ መስጠት ከሁሉ የተሻለው መፍትሔ እንደሆነ ይስማማሉ። ወጣቶች ቀድመው ስለ ሱስ አስከፊነትና ሰለሚያስከትለው ጣጣ ሲማሩ ከመጀመራቸው በፊት እራሳቸውን እንዲጠብቁ ዕድል ይከፍታል።

ይህንን ቀውስ ለማስቆም ወጣቶች ራሳቸውን አስቀድመው እንዲከላከሉ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰጣቸው ይገባል። በዚህ ዙሪያ ዋናውና አስፈላጊው መሣሪያ እውቀት ነው። ወጣቶች ሱስ እንዴት በሰውነት እና በአእምሮ ላይ እንደሚሠራ ሲረዱ አስከፊነቱን ይረዱታል። ራሳቸውን የመጠበቅ ዕድላቸው ሰፊ ነው። ሌላው በዚህ ዙሪያ ማድረግ የሚገባው ጉዳይ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ድጋፍ ማድረግ ነው። በሱስ ውስጥ ያሉም ሆነ ወደዚህ ችግር ውስጥ ያልገቡ ወጣቶች የሚያናግሩት፣ የሚያማክሩት ሰው ይፈልጋሉ። ለዚህ ነው ፍቅር መስጠት፣ አክብሮት አለመንፈግ እና በብልሀት ወደ መልካሙ መንገድ እንዲሄዱ መምራት የሚገባው። ወጣቶች ብቸኝነት ሲሰማቸው ሱስ ውስጥ የመውደቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ክትትል ካደረግንላቸውና ድጋፋችንን ካሳየናቸው ራሳቸውን የመጠበቅ፤ በራስ መተማመናቸውን የማዳበር አቅማቸው እያደገ ይመጣል።

ወጣቶች በመልካም ነገሮች መጠመዳቸው ጠቃሚ ነው። ስፖርት፣ ሙዚቃ፣ ማንበብ እና አዳዲስ ክህሎቶችን መማር አእምሮንና አካልን ንቁ እንዲሆን ያደርጋል። የተሻለ ሕይወት ለመገንባት የሚያልም ወጣት በሱስ ጊዜውን የማባከን እድሉ አነስተኛ ነው። ለዚህ ነው ወጣቶች ዓላማ እንዲኖራቸው ማገዝና አብሮ መሥራት የሚያስፈልገው። ተስፋ የሱስ ተቃራኒ ነው። ተስፋ ለሕይወት ትርጉም ይሰጣል። በመሆኑም ሁሌም ልጆቻችን እና የማኅበረሰቡ ክፍል የሆኑ ወጣቶች ከሱስ ይልቅ በውስጣቸው ተስፋና ጥንካሬ እንዲኖራቸው መሥራት ይኖርብናል።

የኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር እሴቶች ወጣቶችን ከሱሰኝነት ይታደጋሉ። ወጣቶች በታማኝነት፣ በአክብሮት እና በትጋት ሲያምኑ ትክክለኛውን መንገድ የመምረጥ ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል። ፍላጎታቸውን ለመቆጣጠር እና ለዓላማቸው ስኬት ጠንካራ መሆንን ይማራሉ። ለምሳሌ ቤተሰብ በፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አንፆ ልጁን ሲያሳድግ በአቻ ግፊት አንድ ሰው አደንዛዥ ዕፅ ወይም አልኮል ሊሰጣቸው ቢሞክር እንኳን በቀላሉ ጥያቄውን ውድቅ ለማድረግ አይቸገሩም። ጥያቄውን ከመቀበላቸውና ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት ስለወደፊታቸው እጣ ፈንታ ያስባሉ። እነዚህ እሴቶች ከቤት፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሃይማኖት እና ከማኅበረሰብ የሚመነጩ ናቸው። በመሆኑም ልጅን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ማሳደግ እና ከአደንዛዥ እፅ ሱሰኝነት ራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ የቤተሰብና የማኅበረሰብ ኃላፊነት ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ቤተሰብ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ፣ መነጋገር አለባቸው። የልጆቻቸውን ሀሳብ ጫና ሳይፈጥሩ፣ ሳይጮኹ ማዳመጥ ይኖርባቸዋል። የልጆቻቸውን ስሜት መረዳት ይገባቸዋል። ልጆች ሲሳሳቱ እንኳን ፍቅር መስጠት ማቆም አይገባም። ወላጆች ለልጆቻቸው ቅርብ ሲሆኑ፣ እርስ በርስ መተማመን ሲፈጥሩ ችግር ሲያጋጥማቸው ወደ እነርሱ ይመጣሉ። ነገር ግን ቤተሰባቸው የማያቀርባቸው እና ስሜቶቻቸውን ለመረዳት የማይችል ቤተሰብ ልጆቹን ለአደጋ የተጋለጡ እንዲሆኑ ያደርጋል።

መምህራንና ትምህርት ቤቶችም ኃላፊነት አለባቸው። ለተማሪዎቻቸው ሒሳብና ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር በቂ አይደለም። የሕይወት ክህሎት ትምህርትም መስጠት አለባቸው። አስተማሪዎች ስለ ሱስ አስከፊነት፣ ስለ አቻ ግፊት፣ ጫና ተማሪዎቻቸውን በማስተማር የችግሩ ተጋላጭ አንዳይሆኑ መሥራት ይኖርባቸዋል። በሱስ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ የእውነተኛ ሰዎች ታሪኮችን ማጋራት በራሱ ወጣቶችን ያስተምራል። እነዚህ ታሪኮች ተማሪዎች አደጋውን እና የችግሩን መጠን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።

መንግሥትም በዚህ ዙሪያ የራሱ ሚና አለው። በተከታታይ በሱስ አስከፊነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ማድረግ ይጠበቅበታል። የወጣቶች ማዕከላት በብዛት (አሁን ካሉትም በተሻለ ብዛትና ጥራት) መገንባት ይኖርበታል። የአእምሮ ጤና አገልግሎት (ሕክምና ተቋማት) መሻሻል አለባቸው። ወጣቶች ለእርዳታ የሚሄዱባቸው አስተማማኝ የሕክምናና ማገገሚያ ቦታዎች መኖር አለባቸው። በተለይ ወጣቶቸ አልባሌ ቦታዎች እንዳይውሉ የሚያግዝ የሥራ እድሎች መፈጠር አለባቸው። ሰርቶ ገንዘብ ማግኘት የሚችል ወጣት ወደ ሱስ የመቀየር እድሉ አነስተኛ ነው። የኢኮኖሚ ድጋፍ የመፍትሄው አካል ነው። ሥራ ከሌለ ሱስ እንደ አረም ያድጋል። ማኅበረሰቡ እና የሃይማኖት መሪዎች በዚህ ዙሪያ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ። አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች እሴቶችን ማስተማር እና ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ።

በመጨረሻም ወጣቶችን ከሱስ ለማውጣት እርምጃ የምንወስድበት ጊዜው አሁን ነው እንላለን። ከላይ በዝርዝር ለማየት አንደሞከርነው መፍትሄው ሊደረስበት የሚችል ነው። እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት፣ እያንዳንዱ መሪ እና እያንዳንዱ ወጣት አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ አለበት። የበለጠ በመማር፣ የበለጠ በመተሳሰብ እና ብዙ በመሥራት ሱስ በወጣትነታችን ላይ ጥላ የማይሆንበትን ጊዜ መገንባት አለብን። ሰላም !!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You