
ሀገር በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በልማድ፣ በተስፋ፣ በደስታና በመከራ ተሳስሮ የሚኖር ሕዝብ የሚገኝበት የዓለም ክፍል ነው። ሀገር ማለት አያት ቅድመ አያት የተወለዱበት፤ አድገውም በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው ዕድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻቸውን ተከተው የተቀበሩበት ነው። ስንኖር መኖሪያ ስንሞት መቀበሪያ።
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር፤ ሀብታሙ ግርማ ደምሴ ሀገር ማለት ምን ማለት ነው? ሀገርን መውደድ እንዴት ይገለጣል? በሚል ጽሑፋቸው እንዳስቀመጡት፤ ሀገር የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ሕዝብ የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅና የሚጋጩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ በአንድ መንግሥት ስር ለመተዳደር የሚገቡት ቃል ኪዳን ነው፤ በመሆኑም ሀገር በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ሕዝብ (ዜጎች)፣ መንግሥት፣ የተለያዩ ተፎካካሪ እና/ወይም የሚጋሩት ፍላጎቶች ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እነዚሁ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሆነው በጋራ ለመተዳደር መነሻ ወይም መሠረት የሚሆናቸው የጋራ ጉዳይ፤ ይህን የጋራ ጉዳይ የሆነውን በአንድነት የመኖር አጀንዳ ሊያሳኩበት የሚችሉበት መንገድ (ሂደት)፤ እንዲሁም እነዚህ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በአንድነት ለመኖር እንዲችሉ በጋራ የሚስማሙበት የጥቅም እና ግዴታ የውል ስምምነት ሰነድ ናቸው::
ስለሆነም ሀገር በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ ሀገረ-መንግሥት፣ ሕገ-መንግሥት፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ብሔረ-መንግሥት የሚባሉ ጉዳዮች አሉ:: በመሆኑም ሀገር ስለሚባለው ነገር የሚኖረን ዕውቀት እነዚህን ጉዳዮች ማወቅ ነው::
በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ፖለቲካዊ ልዩነቶቻቸውን በጎን አድርገው፣ ነገር ግን የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን የሚከውን አካል ሀገረ-መንግሥት ይባላል፤ ሀገረ-መንግሥቱ ይህን የሕዝቦች የጋራ ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በዝቅተኛ ደረጃ ሊከውን የሚገባው ተግባር ሲሆን፣ ዋነኛ ተግባሩ ብሔረ መንግሥት ለመመሥረት ለሚደረጉ ሂደቶች መሠረት የሆኑ ተግባራትን ማካሄድ ነው፤ ይህም የተራራቁ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማቀራረብ የሚስችሉ ሕገ-መንግሥታዊ፣ ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ መሠረተ-ልማቶችን (Soft infrastructures) መገንባት ነው፤ በመሆኑም የሀገረ-መንግሥት አስፈላጊነት የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደፊት በጋራ አብረው መኖራቸው ጥቅም እንዳለው ማሳየት፣ የአብሮነታቸው ዋስትና እንዲኖር መሠረት የሚሆነውን የጋራ ኑሮ መመሥረቻ የውል ሂደትን ማስተባበር፤ በጋራ የተስማሙበትን የቃል ኪዳን ሰነድ ውሎች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነው::
ሀገርን መውደድ ሀገርን ለማስቀጠል በሚከፈል መስዋዕትነት ይለካል፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን መውደዱ የሚለካው ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ብዝሀ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ እምነት እና የፖለቲካ እሳቤዎችን አክብሮ ማስከበር የሚያስችል ተክለ ስብዕና በመገንባት ነው፤ ሀገር የሚገነባው በአንድ ወጥ ባሕል፣ ቋንቋ ወይም የፖለቲካ እሳቤ ሳይሆን በስብጥር ህብሮች መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል፤ በዚህም ከእሳቤያችን፣ ባሕላችን፣ ቋንቋችን፣ ሃይማኖታችን የተለየ ወንድሞቻችን/እህቶቻችን/እናቶቻችን/አባቶቻችን ክብር ሊኖረን ይገባል፤ ይህ ለእነርሱ ክብር ብለን ብቻ የምናደርገው ሳይሆን የራሳችንን የስብዕና መሠረቶች ለማስከበር ነው፤ እምነታችንን፣ ባሕላችንን፣ ቋንቋችንን እና ፖለቲካ እሳቤዎቻችን ሌሎች እንዲከብሩልን እኛ ቀድመን እነርሱን ማክበር አለብን፤ እንዲህ ሲሆን አብሮነታችን ይጎለብታል፤ እኔ ብቻ ልድመቅ፣ የእኔ ብቻ ፊት ይቅደም፣ የሌሎቹ አያገባኝም የሚሉ እሳቤዎች በመሠረቱ አብሮ የሚያናኑር ሳይሆን የሚያቃቅር ነው::
ኢትዮጵያውያንም በተሳሰረና በተጋመደ ባሕልና እሴት የተጣመሩ ናቸው። በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ የሚቆሙ ናቸው፤ ሀገር ወዳድ ከሚባሉ ውስጥ ይመደባሉ:: ሀገር መውደድ ከጥንት ጀምሮ ሀገረ መንግሥት ሲመሠረትም የመጀመሪያው መሠረት ተደርጎ የሚቆጠር ነው:: በተለያዩ ጊዜያት ስለኢትዮጵያ ታሪክ የተፃፉትን ስንመለከት በአብዛኛው በሀገር ወዳድነት ላይ የተመሠረቱ ታሪኮች ይበዙታል:: ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ አይደራደሩም የሚባለው::
ከላይ እንደተቀመጠው ሀገር የሚመሠርተው በሕዝቦች ይሁንታ ይሁን እንጂ አንድን ሀገር ሀገር የሚያስብላት በአንድ የተካለለ ቦታ የሚጠብቃት፣ የሚያስተዳድራትና በውስጧ ለሚገኙ ዜጎቿ ጥቅም የሚሠራ መንግሥት ሲኖራት ነው:: መንግሥት ደግሞ የሕዝብን አንድነት በመጠበቅ ለአንድ ሀገር ለውጥ የሚተጋ ሥርዓት ነው::
መንግሥት በአንድ ሀገር ወይም ተቋም ውስጥ ሕጎችን ለማውጣትና ለማስፈጸም ሥልጣን ያለው አካል ነው። መንግሥት አንድ ሀገር ወይም ማኅበረሰብ የሚስተዳደርበት ሥርዓትና ለዚህም ሲባል የተቋቋመ ኃይል ያለው አካል ነው:: ይህም ሕግ አውጪውን፣ ሕግ አስፈጻሚውን እና ሕግ ተርጓሚውን ማለትም የዳኝነት አካላትን የያዘ ነው::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ያሉት ትውልዶች ስለ ሀገራቸው ታሪክና እሴት በቂ እውቀት ስለመኖራቸው ያለው ሁኔታ አጠራጣሪ ሆኖ ይገኛል:: ለምን ቢባል ትውልዱ ስለ ታሪኩ እንዲያወቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው ነው:: በተጨማሪ ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እውቀትን ከማስጨበጥ ይልቅ የተሳሳቱ ትርክቶች እና በአጉል ብሽሽቅ ውስጥ የገባ በመሆኑ ነው:: በእነዚህ ምክንያቶች ሀገርን ከመውደድ ይልቅ ሌላ የባዕድ ሀገራትን መመኘት እንደ ባሕል እየተቆጠረ ይገኛል::
አንድ ሰው ሀገሩን ለመውደድ ምንም ዓይነት ምክንያት አያስፈልገውም:: ምክንያቱም አንድ ሰው ተወልዶ፣ አድጎና ሥራ ይዞ የሚኖረው ሀገር ስላለው ነው:: በአሁን ወቅት በዓለም ላይ ባሉ ጦርነቶች ምክንያት ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ:: እነዚህ ታዲያ በስደት የሚኖርባቸው ሀገራት ላይ በርዳታ የሚኖሩ ሲሆን በሀገራቸው የነበራቸውን ክብርና ሀብት በማጣታቸው በድህነት አረንቋ ውስጥ ይወድቃሉ::
ይህን ሁኔታ በሀገራችን በነበሩ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተመልክተናል:: ጦርነት ከነበረበት አካባቢ የመጡ ሰዎች ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው ስለወጡ በየከተማው ጥጋጥግ ተሰባስበው በልመና ሲተዳደሩ ማየት የተለመደ ሆኗል:: እነዚህ ሰዎች ወደዚህ ሁኔታ እንዲገቡ ያደረጋቸው ሀገራቸውን በሚጠሉ ሴረኞች መሆኑ እሙን ነው::
ታዲያ ሁሉም ዜጋ ሀገሩን መውደዱ እንዴት ይገለጻል? የሚለው ጉዳይ አካራካሪ ቢሆንም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ዜጎች ሀገራቸውን እንዲወዱ እና እንዲያውቁ መደረግ አለበት:: ሀገርን መውደድ ሲባል ውስጣዊ ስሜታዊ ተገናኝነት፣ ተግባራዊ አስተውሎ እና ገላጭ ኅሊና የሚጠይቅ ነው። በሚከተሉት መንገዶች ሀገርን እንዴት መውደድ እንደምንችል እናያለን:: የመጀመሪያው የሀገርን ታሪክ፣ ባሕል እና ቋንቋ በመማርና በማወቅ ነው::
የሀገርን ታሪክ ከመጀመሪያው ጀምሮ ማወቅና መረዳት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው:: ለምሳሌ ሀገራችን አሁን የያዘውን ቅርፅና አወቃቀር ከመፈጠሩ በፊት የነበሩ የታሪክ ዑደቶችን፣ በወቅቱ የነበሩ ነገሥታቶችን እንዲሁም የሃይማኖት አመጣጦችን መረዳት የግድ ይላል::
የሀገርን ታሪክ ስናጠና ደግሞ ታላላቅ ሰዎችን እና የነፃነት ታጋዮችን ቅድሚያ ሰጥተን ልንመረምር ይገባል:: ይህ በሚሆንበት ወቅት ለሀገር ባለውለታ የሠሩ ሰዎችና የነፃነት ታጋዮች ለቀጣይ ትውልድ ስለ ሀገር መውደድ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ይኖራል። ይህ በሚሆንበት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ሀገሩን ማወቅና መገንዘብ ይችላል ማለት ነው::
ሌላው ደግሞ የሀገርን ባሕላዊ ሥርዓቶችን፣ ዜማዎችን፣ የአካባቢ ምግቦችን እና ቋንቋዎችን ማወቅና መረዳት ሀገርን እንድንወድ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል:: ለምሳሌ በሀገራችን በርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች ይገኛሉ:: የእነዚህን ብሔረሰቦች ባሕል፣ ቋንቋና አመጋገቦች ባወቅን ቁጥር ለሀገራችን ያለን ስሜት ይበልጥ ይጨምራል::
ሀገርን እንድንድወድ ከሚያደርጉን መንገዶች ሁለተኛው በማኅበረሰብ አገልግሎቶች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ነው:: ለምሳሌ በአካባቢ ልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የኔነት ስሜት ከመፍጠር ባሻገር ለቀጣይ ትውልድ ንፁህና ለመኖሪያ ምቹ የሆነ ሥፍራ ለማስተላለፍ ይረዳናል:: በሌላ በኩል ደግሞ አቅም የሌላቸውን አረጋውያን ቤት ማደስ፣ በቤት ውስጥ ሥራ መደገፍ እንዲሁም ወላጅ ለሌላቸው ተማሪዎች በየዓመቱ የትምህርት ወጪ መሸፈን ለሀገራችን የሚኖረንን ስሜት እንድናሳድግ ያደርገናል::
ወላጅ የሌላቸውን ልጆች የትምህርት መሳሪያዎችን በማሟላት እንዲማሩ መደረጉ ልጆቹ በጎ የሆነ ለሀገራቸው የሚኖራቸው ትርጉም ከፍ ያደርጋል:: በዚህም ልጆቹ ሲያድጉ በተመሳሳይ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ይነሳሳሉ ማለት ነው:: በተጨማሪም በዴሞክራሲያዊ ሂደቶች ማለትም ሀገራዊ ምርጫ ሲካሄድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ሀገርን ለመውደድ መንገድ የሚከፍት ነው::
ሶስተኛው ሀገርን እንድንወድ ከሚያደርጉ መንገዶች ሀገራዊ ንብረቶችን መጠበቅና መንከባከብ ነው:: ለምሳሌ የተፈጥሮ ሀብቶችን (እንደ አትክልት፣ ውሃ፣ የተፈጥሮ ተራሮች) መጠበቅና መንከባከብ የዜጎች ግዴታ ነው:: በተጨማሪም የሃይማኖት ቦታዎችን መጠበቅና ማክበር አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በተፈጥሮ አየርና ሀብት የበለፀጉ ሀገራት ዜጎቻቸውን በማስተባበር ከተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ:: ኢትዮጵያውያን ያለንን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅሞ መበልፀግ ላይ ድክመት ቢኖርብንም ጅምር ሥራዎች እንዳሉ ግን መመልከት ይቻላል::
የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም መበልፀግ ሲቻል ዜጎችን ወደ ሌሎች ሀገራት መሰደዳቸውን ያቆማሉ:: ለአብነት የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫን ብንመለከት ግንባታው ሲጀመር በሕዝብ አቅም እንደሚሠራ ሲነገር የሕዝቡ ስሜት የተለየ ነበር:: ይህን መሰል ሁኔታዎች እየሰፉ ሲመጡ ዜጎች ይበልጥ ሀገራቸውን እየወደዱ ይመጣሉ ማለት ነው::
በሌላ በኩል ብሄሔዊ ምልክቶች ሰንደቅ ዓላማ እና ታሪካዊ ቦታዎችን ማክበር ለሀገር መውደድ ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ ያደርጋል:: በሀገራችን በብዛት ሃይማኖታዊ እና የነገሥታት መኖሪያ የነበሩ ታሪካዊ ቦታዎች ይገኛሉ:: እነዚህን ሥፍራዎች በአዲስ መልክ በማደስና ዜጎችን በማስጎብኘት ቀደምት የታሪክ ዐሻራዎችን የማሳወቅ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል::
በአራተኛ ደረጃ የምንመለከተው ደግሞ ሀገርን እያስተዳደረ የሚገኘውን መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች መቀበልና መተግበር ሀገርን እንድንወድ ያደርጋል:: ለምሳሌ ሕጎችን መከተል፣ ግብር መክፈል እና በሕዝብ አገልግሎቶች (ለምሳሌ፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች) ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘመቻዎች ላይ መሳተፍ ያስፈልጋል:: በተጨማሪም የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲሻሻሉ የሚያደርጉ አስተያየቶችን በየጊዜው መስጠትም ተገቢ ነው::
በአምስተኛነት የምንመለከተው የሀገርን አንድነት ሊያስጠብቁ የሚችሉ ነገሮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ሀገርን ይበልጥ እንድንወድ ያደርጋል:: ለዚህ ደግሞ የብሔር፣ ሃይማኖት ወይም የፆታ ልዩነቶችን በማለስለስ የማኅበረሰብ አንድነትን መገንባት አስፈላጊ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶችን መሠረት ተደርገው ይፈጠሩ የነበሩ ሁከቶችና ግርግሮችን ወደ ጎን በመተው አንድነትን ሊጠናክሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በስፋት መሥራት ለሀገር መውደድ መሠረት ይጥላል:: በአንድነት ሆኖ በብሔራዊ በዓላት ለምሳሌ፣ የድል ቀን፣ መስቀል እና እሬቻ፣…ሌሎች የአደባባይ በዓሎችን በማክበር የጋራ ስሜት መፍጠር ተገቢ ነው።
ስድስተኛው ደግሞ ሀገርን በተግባር መውደድ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የሀገርን ምርቶች በመጠቀም የአካባቢ ኩባንያዎችን በመደገፍ እና ለሀገር እድገት በእውቀትና በሙያ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠቀሳል:: አብዛኞቻችን የውጭ ምርቶችን የምንጠቀም ሲሆን የሀገራችን ምርት የጥራትና ጥንካሬ ጥያቄዎች ይነሳባቸዋል። ነገር ግን ሀገራዊ አንድነትና መውደድ ለመፍጠር በሀገራችን ኩባንያዎች የሚመረቱትን መጠቀም እና ማበረታታት አስፈላጊ ነው::
እንደ አጠቃላይ ሁሉም ዜጋ ሀገርን ለመውደድ በቅድሚያ ከራሱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነቶች መወጣት አለበት:: ሀገር የሰዎች ስብስብ የሚፈጥረው እንደመሆኑ በሀገር ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች በጋራ ሆነው የሚያከናውኑት ተግባራት ለውድቀትም ሆነ ለእድገት ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ አለው:: ስለዚህ ሁሉም ሰው ሀገሩን በመውደድ ለቀጣይ ትውልዱ የሚሆኑ ዐሻራዎችን አሳርፎ ማለፍ አለበት። ሀገራችን ምን አደረገችልን ሳይሆን ለሀገራችን ምን ሠራን ምን አበረከትን የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ ሀገር ወዳድነታችንን አረጋገጥን ማለት ነው።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም