ጌትነት ምህረቴ
በኢትዮጵያ የሚሰሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች በመጓተታቸው በአገር ደረጃ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትለዋል፤እያስከተሉም ናቸው፡፡ከእነዚህ መንገዶች መካከል አንዱ የቃሊቲ ማስልጠኛ- ቱሉ ዲምቱ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ለሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት ቢሆንም እስካሁን ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡
በመንገዱ ግንባታ የመዘግይት ከፍተኛ ቅሬታ የተሰማቸው ነዋሪዎች ጉዳዩ መቼ መፍትሄ እንደሚያገኝ የሚመለከተውን አካል አነጋግረን ምላሽ እንድንሰጣቸው ጠይቀውናል፡፡እኛም የሚመለከተውን አካል አነጋግረን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡
የቃሊቲ ማስልጠኛ- ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መዘግየት በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙ ቅሬታና እሮሮ እየቀረበበት መሆኑን የሚናገሩት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር እያሱ ሰለሞን፤ ይህ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በሚካሄድበት የግራ የመንገዱ መስመር ትልቅ የውሃ ማስተላለፊያ መስመር የሚገኝ በመሆኑ ለግንባታው መጓተት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰውልናል፡፡የመጠጥ ውሀ መስመሮች በወቅቱ አለመነሳት ለመንገድ ግንባታ መጓተትና አሁንም ግንባታውን ለማካሄድ እንቅፋት መፍጠሩን ነግረውናል፡፡
በተደጋጋሚ ህዝብ ስለጠየቀን የመንገዱ መጓትት ችግር መኖሩን አውቀናል የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ይህን የውሃ መስመር የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እንዲያነሳልን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ድረስ ፈጣን ምላሽ ልናገኝ ስላልቻልን የመንገዱን ግንባታ ማካሄድ አልቻልንም ይላሉ፡፡
ጉዳዩን ለውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ብቻ ሳይሆን ለከተማ አስተዳደሩ የበላይ አመራሮች ድረስ እንዳሳወቁ የሚገልጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አመራሮቹ የመጠጥ ውሃ መስመሩ እንዲነሳና የመንገዱ ግንባታ እንዲካሄድ አቅጣጫ ቢያስቀምጡም የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የውሃ መስመሩን ለማንሳት እስካሁን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊገባ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
የመጠጥ ውሃ መስመሩ በፍጥነት እንዲነሳ የስራ ተቋራጩ በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አመልክተው፤መስመሩ እንደተነሳ ስራ ተቋራጩ ወዲያው የመንገድ ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ዝግጁ እንደሆነና ይህንን ለማድረግም አቅም አለው ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የመንገዱ ግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸሙ ከ53 በመቶ በላይ ደርሷል የሚሉት አቶ እያሱ፤የመንገዱ የቀኝ ክፍል አብዛኛው ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና በመጪዎቹ ጊዜያት ሁለተኛውን ደረጃ አስፓልት የማልበስ ስራ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡
በአንጻሩ የመንገዱ ግራ ክፍል የውሃ መስመሩ ሊነሳ ባለመቻሉ የመንገድ ግንባታው እስካሁን የተጓተተ መሆኑን አውስተው ይህም በተጠናቀቀው የመንገዱ ቀኝ ክፍል ላይ ትልቅ የትራፊክ መጨናነቅ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባላሥልጣን በመንገዱ የግራ ክፍል የሚገኘውን ትልቅ የውሃ መስመር መቼ ያነሳው ይሆን የሚለው ለባለሥልጣኑ መልስ ሊያገኝበት ያልቻለ ጉዳይ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
እርግጥ ነው ውሃውም ሆነ መንገዱ ለህብረተሰቡ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ኢያሱ ለመንገዱ መጓተት ማነቆ የሆነው የውሃ መስመሩ ባለመነሳቱ እንጂ ሌላ ምክንያት አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
በተለይ በበጋው ወራት የውሃ መስመሩ ተነስቶ ከተጠናቀቀ ግንባታው በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል፡፡ሆኖም ባለሥልጣኑ መስመሩን ለማንሳት የሚወስድበት ጊዜ መንገዱ በፍጥነት ለመጠናቀቅም ሆነ ለተጨማሪ ጊዜ መጓተቱ ወሳኝና ምክንያት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ መስመሩ ከተነሳ በኋላ በዚህ ጊዜ የመንገድ ግንባታው ይጠናቀቃል ብሎ በርግጠኝነት ለመናገር ቀላል ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
ከቃሊቲ ማሰልጠኛ- ቱሉዲምቱ ድረስ እየተገነባ ያለው መንገድ ሦስት ዋና ዋና ማሳለጫዎችን የሚያካትት ሲሆን የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ መነሻ የሆነው የቃሊቲ ማሰልጠኛ አደባባይ ነው፡፡ ይህ ማሳለጫ ድልድይ ከሳሪስ አቦ የሚመጣውን ትራፊክ ተቀብሎ ወደ ቃሊቲ የሚያሸጋግር ነው፡፡
ማሳለጫ ድልድዩ 240 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከስር ያለው ነባሩ የቃሊቲ አደባባይ ደግሞ ወደ ሳሪስ አቦ እና ወደ ሀይሌ ጋርመንት አደባባይ የሚያቀባብል ይሆናል፡፡
ሁለተኛው ማሳለጫ ደግሞ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከደራርቱ ትምህርት ቤት ወደ አቃቂ ከተማ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ድልድዩ 90 ሜትር ርዝመት እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ማሳለጫ ቀደም ሲል ጋሪ ድልድይ እየተባለ የሚጠራው ሲሆን 20 ሜትር ስፋትና 50 ሜትር ርዝመት አለው፡፡
ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አጠቃላይ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 50 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን አጠቃላይ ዋጋውም ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ነው፡፡ የዚህ የፕሮጀክት ዋጋ 50 በመቶው ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከተማ መስተዳድሩ ለመንገድ ግንባታ በተመደበው ገንዘብ የሚገነባ እንደሆነና የግንባታ ስራው በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ እየተከናወነ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት በአገር ላይ ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት በብድር ተፈልጎ አልያም ከግብር ከሚሰብሰብ የህዝብ ገንዘብ መሆኑን ቶሎ ተገንብተው ካልተጠናቀቁ ለህብረተሰቡ እንግልትና በኢኮኖሚውም ኪሳራ የሚያስከትሉ ናቸው፡፡
ምክንያቱምፕሮጀክቶቹ ከተመደበላቸው በጀት ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃሉ፤ በብድር የሚሰሩ ከሆነ ተጨማሪ ወለድ እንድንከፍል ያስገድዳሉ ፤ ሌላ ብድር ለማግኘትም መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡ሁለተኛ ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ ተጠናቀው ይሰጡት የነበረውን ጥቅም ያሳጣሉ ይቀራሉ፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ በቂ የጤና ፣የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት የሌለባት አገር ናት፡፡እንዲሁም ኢንዱስትሪውና ግብርናው ወደኋላ የቀረ ነው፡፡አገሪቱ እነዚህ ሁሉ ፈርጀ ብዙ ችግሮች እያሉባት ውስን የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው የመንገድን ፕሮጀክቶችን በማጓተት ውስኑ የአገር ሀብት የሚባክን ከሆነ “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ በኢኮኖሚው ላይ ተጨማሪ ጫና ኪሳራ እንደሚያስከትል ይታወቃል፡፡
የመሰረተ ልማት መስመሮችና የግለሰብ ቤቶች ከመንገዱ ግንባታ የወሰን ክልል ውስጥ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ባለመነሳታቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ፍጥነት እንቅፋት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ስለዚህ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የመንገዶች ግንባታ መጓተት የህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ እንዳይሆኑና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ኪሳራ እንዳያስከትሉ ተናበውና ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለሚጓተተው የመንገድ ፕሮጀክትም ለዚህ ምክንያት የሆነው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር መበጀት አለበት፡፡
የቃሊቲ ቶታል- አቃቂ ድልድይ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አሁንም በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በተለይ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በለሥልጣን በመንገዱ በግራ በኩል ያለውን የመጠጥ ውሃ መስመር በፍጥነት ማንሳት ይኖርበታል እንላለን፡፡ ምክንያቱም የአገር ገንዘብ መባከን የለበትም፤ የህዝብ እሮሮም ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013