ጌትነት ምህረቴ
በቅርቡ በህግ ጥበቃ ስር የሚገኙ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች በፈለግነው የህክምና ተቋም ሂደት መታከም አለብን የሚል ጥያቄ አንስተዋል።ይህ ደግሞ ሁሉም በህግ ጥበቃና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች በፈለጉት የህክምና ተቋም ሄደው መታከም ይችላሉ ወይ? ማረሚያ ቤቶች ይህን ጉዳይ ማስፈጸም አይቸገሩም ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።ይህ መብት በህግ ጥበቃና በፍርድ ለታሰሩ ሰዎች የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ ለአንዱ ተሰጥቶ ለሌላው ሊከለከል አይችልም።
እርግጥ ነው በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 ንኡስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት በህግ ጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸው ያትታል።
እንዲሁም ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ከጓደኞቻቸው፣ከሀይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ከሀኪሞቻቸውና ህግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው ቢልም ሲታመሙ በፈለጉት የህክምና ተቋም ሄደው መታከም እንደሚችሉ በግልጽ አላስቀመጠም።
ከዚህ አኳያ በህግ ጥበቃና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች በሚፈልጉት ሆስፒታል ሄደው ከመታከም አኳያ ህጉ ምን ይላል በሚለው ዙሪያ በፌዴራል ማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ቁምላቸው ባልቻ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት በህግ ጥላ ስር ያሉ ታራሚዎች ወይንም የጊዜ ቀጠሮ አልያም የዋስትና መብት ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎችን በተመለከተ በመረጡበት የህክምና ተቋም መታከም ይችላሉ ወይንስ አይችሉም የሚለው ለመወሰን ብዙ ጉዳዮችን መመልከት ያስፈልጋል ይላሉ።
እንኳን በህገ መንግሥቱ በህግ ጥላ ስር ወይም ታራሚዎች ህክምና እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ባይቀመጥም እንኳን በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ
ቁጥር አንድና ሁለት በህግ ጥላ ስር ያሉና የታራሚዎች መብት ማለትም ከቤተሰቦቻቸውና ከግል ሀኪሞቻቸው ጋር የመገናኘት መብት አላቸው የሚለው ፍጹም መብት አለመሆኑን ሊታወቅ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ መብቶች በተወሰነ ደረጃ ሊገደቡ የሚችሉበት ሁኔታዎች አሉ።
በተለይ ለአገር ደህንነትና ስጋት የሚፈጥር ሰው ከሆነ ይህ አንቀጽ ይፈቅዳልና የግድ ለህክምና በሚል በሚፈልገው የህክምና ተቋም ሄጄ ልታከም ብሎ ጥያቄ የሚቀርብበት ሁኔታ ላይኖር ይችላል ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችንና በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን የሚያስተዳድርበት የራሱ የሆነ መመሪያና ደንብ አለው።ይህ መመሪያና ደንብ ደግሞ ከህገ መንግሥቱና ከሌሎች የወንጀለኛ መቅጫ ህጎችና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ጋር ባልተቃረነ መልኩ የሚወጡ ናቸው።
የህግ ታራሚዎች ወይንም በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች የፈለጉበት የህክምና ተቋም ሄደው መታከም ይችላሉ ወይስ አይችሉም ለማለት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን መመሪያና ደንቦች ማየት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
እንደዚህ አይነት ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜ የማረሚያ ቤቱ ስልጣን ምንድነው? የሚለው መታየት አለበት።ምክንያቱም የተሰጠው ስልጣን ላይ ታራሚዎችና በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን እንዴት ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው በመመሪያና በደንቡ ውስጥ ስለሚኖር ነው ይላሉ፤ሌላው አንድ ሰው ከማረሚያ ቤቱ ውጭ ህክምና ይሰጠኝ ብሎ ሲጠይቅ ምን ምን መስፈርቶች መሟላት አለባቸው የሚል በግልጽ መመሪያና ደንቡ ላይ ይቀመጣል።
ስለዚህ ታራሚዎችና በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በፈለጉበት የህክምና ተቋም ሄደው መታከም ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚሉ ነገሮች ሁሉ የሚያጠነጥኑት እነዚህ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
በህገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ አንድና ሁለት የተቀመጠው በህግ ጥበቃ ስር ያሉና ታራሚ ሰዎችን መብት ተግባራዊ ለማድረግ መጀመሪያ የአገር ደህንነትና ሰላም ቅድሚያ ይሰጠዋል።ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ባልተቃረነ መልኩ ነው ሊፈቀድ የሚገባው ሲሉ ያብራራሉ።
ፍርድ ቤቶች ለህግ ታራሚዎች ወይም በህግ ጥላ ስር ላሉ ስዎች በፈለጉት የህክምና ተቋማት ሄደው እንዲታከሙ የሚፈቅዱበት ሁኔታ ይኖራል ወይ ብለን አቶ ቁምላቸውን ጠይቀናቸዋል። እሳቸውም እንደገለጹትም፤ ፍርድ ቤቱ ታራሚዎች ወይንም በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በፈለጉበት የህክምና ተቋም ሄደው እንዲታከሙ ሊፈቅድ ይችላል።
ግን አንዳንድ ጊዜ ህጎች ሲወጡ ለትርጉም የሚጋለጡበት ሁኔታ ይስተዋላል።ከዚህ አኳያ አንዱ ዳኛ በህግ ጥላ ስር ያሉ ወይም ታራሚ ሰዎች ሲታመሙ በፈለጉበት የህክምና ተቋም ሄደው እንዲታከሙ ሊፈቅድ ይችላል ።
ሌላው ዳኛ ደግሞ ሊከለክል ይችላል።ምክንያቱም በህጉ ግልጽ የሆነ ውሳኔ የማይቀመጥበት ሁኔታ ይኖራል።እንደፈለክ የምትጫወትበት ሜዳ አለ።ስለዚህ ዳኛው ሲፈልግ ይፈቅዳል ሳይፈልግ አይፈቅድም።
ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሁኔታ የሚያጋጥመው ግልጽ የሆነ ህግ ስለሌለ ነው።ከዚህ አኳያ በእርግጠኝነት አስተያየት ለመስጠት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች መመሪያና ደንብን ማየት አስፈላጊ ነው።ግን ፍርድ ቤቱ የራሱን የሆነ ሁኔታዎች አይቶና በህግ ጥላ ስር ወይንም ታራሚው ሰው ያጋጠመውን የጤና እክል አይቶ በፈለገው የህክምና ተቋም ሄዶ እንዲታከም ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል።
ለምሳሌ ህክምና የጠየቀው ታራሚ ወይንም በህግ ጥላ ስር የሚገኝ ሰው በጣም አደጋ ላይ ሆኖ በሞትና በህይወት መካከል ከሆነ ዳኛው ታማሚው በሚፈልገው ህክምና ተቋም ተወስዶ ህክምናውን እንዲያገኝ ሊፈቅድ ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ዳኛው የህግ ታራሚው ወይንም በህግ ጥላ ስር ያለው ሰው በሚፈልገው የህክምና ተቋም ተወስዶ ይታክም ተብሎ ትዕዛዝ ሲሰጡ ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ትዕዛዞችም አብረው ይሰጣሉ ብዬ አምናለሁ።ግን ይህ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤቱ ትልቅ ጫና የሚፈጥር ከፍተኛ ወጪ ያለው መሆኑንም መገንዘብ ያሻል።
ታራሚውን ወይም በህግ ጥላ ስር ያለውን ሰው ለህክምና ወደሚፈልገው ሆስፒታል ስትወስድ ከፍተኛ የጥበቃ የሰው ሀይል ይጠይቃል።ከፍተኛ በጀትም ያስፈልጋል።
ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ታራሚዎች ወይም በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች የሚያመልጡት ከሆስፒታሎች ነው።ከዚህ አኳያ ሲፈቀድም ሆነ ሲከለከል ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግና ምክንያታዊ መሆንን የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ።
ከሚፈልጉት የህክምና ተቋም ሄደው እንዲታከሙ ከመፍቀድ ይልቅ የሚሻለው የተሻሉ ሀኪሞችን ወደ ማረሚያ ቤቱ አስገብቶ እዚያ ህክምና እንዲያገኝ ነው። ምክንያቱም በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ብዛት ላላቸው ታራሚዎች ወይም በህግ ጥበቃ ስር ለሚገኙ ህክምና ፈላጊዎች ሁሉ በሚፈልጉት የህክምና ተቋማት ሄደው እንዲታከሙ መፍቀድ ለአሰራር አመቺ ባለመሆኑ ነው ብለዋል።
ሁሉም ታካሚ እንዲህ አይነት ፈቃድ ያገኛል ብዬ አላስብም የሚሉት አቶ ቁምላቸው፤ሆኖም ለአንዳንድ ታራሚዎች ወይም በህግ ጥላ ስር ለሚገኙ ሰዎች የተለየ ጥቅምና መብት ሲከበርላቸው ይታያል።ይህ ደግሞ ህግ ለሁሉም በእኩልነት ይሰራል የሚለውን ፈተና ውስጥ ይከታል።
ምክንያቱም ለታራሚዎች ወይም በህግ ጥላ ስር ላሉ ታካሚዎች በፈለጉበት የህክምና ተቋም ተወስድው የሚታከሙበት ፈቃድ የሚሰጥ አስራር ወይም ህግ ካለ ሁሉም ታካሚዎች የፈለጉበት የህክምና ተቋም ተወስደው መታከም አለባቸው።አለበለዚያ ከተከለከለ ደግሞ ለሁሉም መከልከል አለበት።ምክንያቱም ህግ ወይም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ደንብና መመሪያ ለአንዱ ፈቅዶ ለሌላው እንደማይከለክል አመልክተዋል።
የግለሰብ መብቶች መከበርና መጠበቅ አለባቸው የሚሉት አቶ ቁምላቸው፤ ታራሚዎች ወይም በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች መብቶቻቸውን መጠየቅ እንደተጠበቀ ሆኖ የጠየቁትን ሁሉ ፈቃድ ሲሰጥ ግን የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013