ሰላማዊት ውቤ
አቶ ንጉሴ ገመዳ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ያፈራቻቸው ውጤታማ አርሶ አደር ናቸው።ዕትብታቸው ከተቀበረበትና ልደታቸው ከተበ ሰረበት ከቡራ ወረዳ ከራሞ ቀበሌ ላይ ተነስተው ለብዙዎቹ አርአያ መሆን ችለዋል። አርአያነታቸው መላ ሲዳማን አዳርሶ ፣ደቡብ ክልልን ዘልቆ በሀገር ናኝቷል።
ወደ ባህር ማዶ ተሻግሮ ሀገራችንን ኢትዮጵያንም አስተዋውቋል። ስሟን ለማስጠራት ምክንያት ሆኗ ል። አርሶ አደር ንጉሴ በተለይ ኢትዮጵያን ወደ አስተዋወቁበት የቡና ንግድ ከገቡ ሰባት ዓመታቸውን አስቆጥረዋል። በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን ከተካሄደው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ ወይም የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር ከመሳተፋቸው በፊት ቡና ወደ ውጪ ልከው አያውቁም ነበር።
ከዚህ ውድድር በፊት አርሶ አደር ንጉሴ በቆሎና ሌሎች በአካባቢው ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማረስ የሚተዳደሩ ጠንካራ አርሶአደር ነበሩ። በእርግጥ ከዚህ ጎን ለጎን ቡና መሸጥ የጀመሩት ገና ከታዳጊነታቸው ጀምሮ በስኒ በመስፈር ለተጠቃሚዎች በችርቻሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሄ ሰርክ አልሞላ ብሎ ያስጨንቃቸው የነበረውን የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን በመደጎም ፍቱን መፍትሔ ሆኖላቸው ቆይቷል።
በቡና ጎጇቸውን የማድመቅና የማዘመን፤ ሕይወታቸውንም ከነቤተሰባቸው የማሻሻልና የመለወጥ ጥቅሙ እየበረታ መጣ። ዕድሜያቸውም እየጎረመሰ ሲሄድ በቡና ንግድ የጀመሩትም የሥራ ልምድ ጠበቅ አድርገው ያዙ። ዋናውን የሰብል ምርት ልማት ሥራን ሳይለቁ ፈጥኖ ለመለወጥ ያስቻላቸውን የቡና ሱቅ ከፍተው በመቸርቸር ጭምር ንግዱን ሰፋ ወደ ማድረጉ ገቡ።
እያሉም መቶ ኪሎ ቡና በጋራ ለሁለት ሆነው በፈረስ መጫን ቀጠሉ። ደግሞ ይሄንኑ መቶ ኪሎ ቡና በፈረስ እራሳቸውን ችለው ለብቻቸው መጫኑን ተያያዙት። ይሄ ጭነት ከመቶ ወደ ሁለት መቶ ኪሎ እያለ አይሱዙ መኪና የመግዛት አቅም ፈጠረላቸው።
ቡና እየሰበሰቡ ለቡና አቅራቢዎች ለመሸጥ የአይሱዙ አቅም እስከ ቻለ ድረስም ቡና ወደ መጫን የከፍታ ማማ ወጡ። የደረቅ ንግድ ቡና ፈቃድ ማውጣትም ቻሉ። ቡና ለምርት ገበያ በማቅረብ ወደ መሸጥም ተሸጋገሩ።
ይሄ የሆነው የዛሬ ሰባት ዓመት ነው። በዚህ መካከል ለሀገራችን የመጀመርያው የሆነው ቡና ቅምሻ ውድድር መጣላቸው። ቡና ለገበያ ቢያቀርቡና ቢሸጡም በምርት ገበያ በኩል ነበር። ሆኖም በተለይ ስድስቱን ዓመት ሙሉ እሳቸውም ሆኑ የአካባቢው ቡና አምራች አርሶ አደሮች በኪሳራ ነው ሲሸጡ የነበሩት። ምክንያቱም እንደ አካባቢያቸውም ሆነ እንደ ሀገር በቡና ምርት መጠቀም የሚችሉበት የተመቻቸ ዕድል አልነበረም።
ማንኛውም አርሶ አደር ቡናው ሲደርስ ለቡና አቅራቢዎች ነበር የሚያስረክበው እንጂ ቡናውን እራሱ በቀጥታ አያቀርብም ነበር። በዚህ ላይ የቡና ዋጋ ከበቆሎና ድንች በታች ዝቅ ያለበት አጋጣሚ አንደነበር ያስታውሳሉ።
በዚህ የተነሳ እሳቸውም ሆኑ ሌላው ቡና አምራች አርሶ አደር ትርፋማ አልነበረም። ከ2010 ወዲያ ባሉ ዓመታት የቡና ዋጋ ከአምስት እስከ አሥር ብር ድረስ ወርዶ የነበረበትንም ለማሳያ አንስተውልናል።
እርሳቸው እንደነገሩን አምና በውድድሩ ከመሳ ተፋቸው ቀደም ብሎ ይሄን የኪሳራ ታሪካቸውን የሚለውጥ አጋጣሚ ተከሰተ። ክስተቱ እንዲህ ነው። የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ አዘጋጆች ማሳቸው ወዳለበት ቀዬ ይዘልቃሉ።
በጥራት ካቀረባችሁ በጥሩ ዋጋ ትሸጣላችሁ ምርታችሁንም በቀጥታ ወደ ውጭ እስከ መላክና መሸጥ የሚያስችል ፈቃድ ይሰጣችኋል ይሏቸዋል። በዚህም ሳያበቁ ሃዋሳ ላይ ጥራት ያለው ቡና ማምረትና ማቅረብ የሚያስችል ስልጠና ይሰጧቸዋል።
ስልጠናው ቡናን በጥራት እንዲያመርቱ የሚያስችል ነበር። ከስልጠናው በፊት እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የቡና አምራች አርሶ አደሮች ቡና በብዛት መሰብሰብና ማከማቸት ላይ እንጂ ጥራት ላይ አትኩረው አይሠሩም ነበር።
ነገር ግን የወሰዱትን ስልጠና የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ ረዳቸው። ምርታቸውን በቀጥታ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችላቸውንም ፈቃድ ማውጣት አስችሏቸዋል። ለውድድሩ ጥራት ያለው ምርት እንዲያቀርቡም አግዟቸዋል።
በመጀመሪያ ዙር ከተወዳደሩት 1ሺህ 495 አርሶ አደሮች መካከል አንዱ እሳቸው ሆኑ። ከእነዚህ መካከል እርሳቸውን ጨምሮ 150 አርሶ አደሮች ውድድሩን አለፉ። ከ150ው ደግሞ 40 አርሶ አደሮች ተመለመሉ።
ከአርባዎቹ አርሶ አደር ንጉሴ ገመዳ ቡና አንደኛ ወጣ። በዚህ ውድድር ካቀረቡት ቡና መካከል 540 ኪሎ ግራም ተሸጠላቸው። የተሸጠው የቡና ዋጋ በህይወት ዘመናቸው አይተውት ቀርቶ ሰምተውት በማያውቁት ዋጋ ስምንት ሚሊዮን ብር ነበር።
ከሽያጩ ብር ላይ የሥራ ግብርን ጨምሮ ሌሎች ለመንግሥት የሚገቡ ወጪዎች ተቀናንሰው በእጃቸው የገባው 5 ሚሊዮን 930 ብር ነው። አንድ ኪሎ ግራም ቡና እንግሊዝ ለንደን ላይ የተሸጠላቸው በ407 ዶላር ወይም 14 ሺህ ብር ነው። አንድ ሲኒ የተፈላ ቡና ለንደን ላይ 64 ዶላር ወይም በኢትዮጵያ ብር 2 ሺህ 400 ብር ነው የተሸጠው።
ቀሪውን ቡናም በምርት ገበያ በኩል በፈረሱላ ሀገር ውስጥ ቸብችበዋል። ቡናቸውን አድንቀው ያልጠገቡት እንግሊዞች እኛ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ባነጋገርናቸው ከውድድሩ ዓመት በኋላ እንኳን ይሄን ዋጋ ያወጣውን ቡና ማሣ በግንባር ለማየት ከለንደን ድረስ መጥተው እየጎበኟቸው እንደነበር አጫውተውናል።
በዘንድሮው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድርም እየተሳተፉ ነው። የእርሳቸውን ተጠቃሚነት ያዩ በርካታ አርሶ አደሮች እንዲሳተፉም አርአያ ሆነዋል። አምናም ቢሆን ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያሸነፈው የእዚያው ለእርሳቸው የሚያቀርቡና የእሳቸው አካባቢ አርሶ አደሮች ያመረቱት ቡና ነው።
ለዘንድሮ ውድድር ያቀረቡት ቡና ናሙና ከደረሰ ሦስት ሄክታር ማሳ ላይ የተዘገነ ነው። በጥቅሉ ዘንድሮ ያላቸው ቡና በችግኝ ደረጃ ያለውን ጨምሮ 10 ሄክታር ነው። የደረሰውና ለውድድር የቀረበው ቡና ልዩ አዲስ ኦርጋኒክ ነው። የከብት አዛባ፣ፍግ እንዲሁም የአካባቢውን ቅጠላ ቅጠልና ግብዓት በመጠቀም የሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አፋፍቶታል።
እንደ አርሶ አደር ንጉሴ የቡና ምርት ከተከላውና ከአረሙ ጀምሮ አብዝቶ ከፍተኛ እንክብካቤ ይፈልጋል። የግድ በ22 ቀኑ መኮትኮት አለበት። የተከላ ሂደቱም እጅግ ከባድና አድካሚ ነው። የሚሰጠው ምርትም የእንክብካቤውን ያህል ነው።
አንድ የቡና ተክል የሚጎነደለው ከ25 እስከ 30 ዓመት ካገለገለ በኋላ ነው። የእሳቸው ቡና አዲስ በመሆኑ እዚህ ዕድሜ ላይ እስኪደርስ ምርት ሲሰጣቸው የሚቆይበት ገና ረጅም ዓመታት ስላለው ደስተኛ ናቸው።
ቡናው እስካለ ድረስ በየዓመቱ በውድድር የመሳተፍና ቡናቸውን በተሻለ ዋጋ የመሸጥ ፍላጎት እንዳላቸውም አርሶ አደሩ ይናገራሉ። በተለይ የውድድሩ ሂደት ማርኳቸዋል። ‹‹ያለፈው ዓመት የመጀመርያ ዙር ውድድር ፍትሐዊ ነበር›› ሲሉም እያሞካሹት ይገኛሉ።
‹‹ቡናውን የቀመሱት ከ17 የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ቀማሾች ናቸው። ውድድሩ ምንም ዓይነት አድሎ አልነበረበትም። የዘንድሮው ውድድርም ከዚህ የተሻለ ይሆናል›› የሚል ዕምነት አላቸው። አምና ለውድድር ያቀረቡት ቡና ስፔሻሊቲ ነው። እሸት ቡና በአልጋ ላይ ይሰጣና ይደርቃል። ይበጠራል።ስፔሻሊቲ የሚባለው በዚህ መልኩ በእንክብካቤ የመጣ ነው።
አርሶ አደር ንጉሴ የወደፊቱ ዕቅዳቸው ይሄን ቡና ከተፈላው አንድ ስኒ ቡና ጀምሮ 2ሺህ 400 ብር በተሸጠባቸው በለንደን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና አብዝቶ በሚወዳድበት በአሜሪካ ማቅረብ ነው።
ለሀገራችን የመጀመርያው የሆነው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ በዓለምና በአፍሪካ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእሳቸው ቡና በተሸጠበት ዋጋ የተሸጠ ቡና አለመኖሩ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው አኩርቷቸዋል።
በተለይ ለንደን ላይ አንድ ስኒ ቡና በ64 ዶላር የጠጣው ታዳሚ ለዘጠኝ ሰዓታት በአውሮፕላን በመጓዝ መሆኑ እጅግ አስደስቷቸዋል። ይሄ ለለንደንና ለአሜሪካ ለማቅረብ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።
በአጠቃላይ ዕድሜ በአምናው ውድድር አሸንፈው ላፈሱት ከፍተኛ መዋለ ነዋይና አርሶ አደር ንጉሴ በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ለውጥ አይተዋል። በዘንድሮው ዓመት የታጠበ ቡና ማቅረብ የሚያስችላቸው ሁለት የቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪም እዚያው የቡና እርሻ ማሳቸው ባለበት ቡራ ውዳ ውስጥ ተክለዋል።
የዚህ ኢንዱስትሪ ግንባታ ወጪ ከ10 ሚሊዮን በላይ ነው። የቡና ደረጃ መውጣቱ የኢንዱስትሪውን ተፈላጊነት የበለጠ ያጎላዋል። በዚህ ላይ ቡና የሚያመርቱበት ማሳ መሬት ከፍታ እስከ 2 ሺህ 400 የደረሰ ምቹ ነው።
ለእርሳቸው ቡና የሚያቀርቡላቸው አጋር አርሶ አደሮች ማሳም እንዲሁ ተመሳሳይ ከፍታ አለው።ከዚሁ ጋር ተዳምሮ ከሁለት እስከ አራት ሄክታር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የሰፈረው ኢንዱስትሪ በአካባቢው መተከል ተፈላጊነቱን አብዝቶ ያጠናክረዋል።
በሰብል ምርት ብቻ ለእራሳቸው የዕለት ጉርስ አልሞላ ብሏቸው ሲጨነቁና ኑሯቸውን ለመደጎም ከወዲያ ወዲህ ሲባክኑ የነበሩት አርሶ አደር ንጉሴ አሁን ላይ ቡና በፈጠረላቸው የማይቀለበስ አቅም ለሌሎች ጋሻ መሆን ችለዋል።
ለአካባቢያቸው ትምህርት ቤቶችን ፣ድልድዮችን፣ ለማስገንባት ደርሰዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች ሲቸገሩና ሲታመሙ አለሁ የሚሉም ለመሆን በቅተዋል። ቡናቸው ሲደርስ የሚከፍሏቸው እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ በማበደርም ኑሯቸውን ለማቅለል ድጋፍ እየሆኑላቸው ይገኛሉ። ለ80 ሴትና 70 ወንድ የአካባቢው ሕብረተሰብ ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠርም ችለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013