አንተነህ ቸሬ
ዛሬ በኢትዮጵያ ትያትር ቤቶችና ሌሎች የኪነ ጥበብ ተቋማት ውስጥ መልክ ይዞ ለሚታየውና ኢትዮጵያን ወክሎ በመላው ዓለም እየተዘዋወረ የባሕል አምባሳደርነት ተልዕኮውን በሚያኮራ ሁኔታ ለፈፀመውና እየፈጸመ ለሚገኘው የሐገረሰብ የሙዚቃ ቡድንና ጨዋታ የመጀመሪውን መሰረት የጣሉት አንጋፋው የኪነ-ጥበብ ባለሙያ በሻህ ተክለማርያም ናቸው::
በሻህ የሐገረሰብ ሙዚቃ መሰረት እንዲይዝ ያለፉባቸው መሰናክሎችና የተጠቀሟቸው ብልሃቶች አስደናቂና አስገራሚ ናቸው:: ሴቶች በአደባባይ መታየታቸው እንኳ ያልተለመደ በነበረበት ጊዜ ሴት ከያኒያንን ለማፍራት ያደረጉት ጥረትም አብዝቶ የሚያስመሰግናቸው ነው::
በሻህ ከግራዝማች ተክለማርያም አጥናፉ እና ከወይዘሮ የሺወርቅ ወልደጻድቅ በ1912 ዓ.ም፣ ባሌ ጎባ ውስጥ ተወለደ:: ግራዝማች ተክለማርያም ኦጋዴን አካባቢ በተደረገ ጦርነት ስለተሰው በሻህ ከእናቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ የመጣው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: በአዲስ አበባ የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያንም የቤተ ክህነት ትምህርት ጀመረ::
ለአራት ዓመታት ያህል ፊደል፣ ንባብና ጽሕፈት ሲያጠና ቆይቶ በስምንት ዓመቱ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገባ:: በመቀጠልም ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተዛውሮ ተማረ::
በሻህ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት ጋሪኮይስ የተባሉ ፈረንሳዊ የተለያዩ ድራማዎችን በሚያዘጋጅበት ጊዜ በድምፀ ሸጋነቱ ተመርጦ ይሳተፍ ነበር:: ከዚህ በተጨማሪም የአማርኛ መምህሩ የነበሩት ቀኝጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ በሚያዘጋጇቸው ተውኔቶች ላይም የመሳተፍ እድሎችን ያገኝ ነበር:: አቦነህ አሻግሬ ‹‹የሴት ተዋንያን ጉዞ ወደ ፕሮፌሽናሊዝም በኢትዮጵያ›› በሚለው ጽሑፋቸው ስለዚሁ ጉዳይ ‹‹ … በሻህ ተክለማርያም ተማሪ ሳለ በቀኝጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ ተውኔቶች ውስጥ ተውኗል።
‹በዚያን ዘመን ከዮፍታሄ ድራማዎች አንዱን ክፍል ሲጫወት፣ ኢትዮጵያ ባንዲት ቆንጆ ተመስላ የጥንቱን ጀግኖቿን ድፍረትና ወኔ በወጣት ልጆቿ መንፈስ ውስጥ ለመቅረጽ፣ጥንታውያኑን በፍቅር አምሳል ‹ ናናና … ናና ናና ናና! ና!ና!… እያለች የሰቀቀን ዜማዋን ለማሰማት እጇን በማርገብገብ በጠቀሰችው ጊዜ የጀግኖቹን መንፈስ የተመሰለው ተናፋቂ አርበኛ በሻህ እንደመረዋ የሚያስተጋባ ወንዳወንድ ድምጹን ዘለግ አድርጎ በመልቀቅ ‹ነይ! ነይ! ነይ!ነይ! ነይ! ነይ! ነይ! ነይ!.› እያለ በትካዜ ሲያንጎራጉር አድማጩን ሁሉ አፍዝዞ የግል ትዝታ ሰመመን አስይዞታል› የተባለለት ነው … ›› በማለት ገልፀዋል::
በዚያው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ አርመናውዊ ናልቫንዲያን የዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች ትምህርት ያስተምሩ ስለነበር በሻህ የሙዚቃ ሰው ለመሆን በር ተከፈተለት:: ይህ አጋጣሚም ከሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር እንዲተዋወቅና እንዲቀራረብ እድል ፈጠረለት:: ታዳጊው በሻህም ለሙዚቃ ልዩ ፍቅርና ፍላጎት አደረበት:: ቫዮሊንና ፒያኖንም መጫወት ቻለ::
በመሐሉ ግን፣ በ1927 ዓ.ም፣ ለወታደርነት ስለተመለመለ የሙዚቃ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ገባ:: በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሳለም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሙዚቃን ለመጫወትና ለመማር ጥረት ያደርግ ነበር::
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ታዳጊው በሻህ የጠላትን አገዛዝና ግፍ በፅኑ መቃወም ሲጀምር የፋሺስት ሹምንት በሻህን በቁጥጥር ስር አውለው ከባድ ግርፋትና ስቃይ አደረሱበት:: በበሻህ ልብ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት በግርፋት የሚሸረሸር አለመሆኑን የተገነዘቡት ፋሺስቶች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እንዲታሰር አደረጉ::
የፋሺስት ኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ኃይል በኢትዮጵያውያን አርበኞች ብርቱ ትግል ከኢትዮጵያ ተባረረ:: ወጣቱ በሻህም የሙዚቃ ትምህርቱን የመማርና ሙዚቀኛ የመሆን ተስፋው ዳግም ለመለመ::
በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ‹‹ቪዲዮ ኦርኬስትራ ዲ ምኒልክ›› በሚል ካርድ ላይ ቫዮሊን ሲጫወት የሚያሳይ ፎቶ በመገኘቱ ካለበት ቦታ ተፈልጎ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተወሰደ:: በማስታወቂያ ሚኒስቴርም የሸክላ ሙዚቃ እንዲያስቀርፅ ተጠየቀ:: በሻህም በጥያቄው ተስማምቶ ቀኝጌታ ቤተማርያም ዘወልዴ እያዜሙ፤ በሻህ ደግሞ በቫዮሊን አጅቦ እየተጫወተ ተቀረፁ::
በሻህ በስራው ባሳየው ችሎታና ትጋት በወቅቱ የትምህርትና ስነ ጥበብ ሚኒስቴር ተብሎ በሚጠራው መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ማገልገል ጀመረ::
በሻህ በትምህርትና ስነ ጥበብ ሚኒስቴር ተቀጥሮ እየሰራ ሳለ በየካቲት 1934 ዓ.ም የገንዘብ ሚኒስትርና የሐገር ፍቅር ማኅበር የበላይ ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ መኮንን ሀብተወልድ ጥሪ ቀረበለት::
ይህ ጥሪም ሕይወቱን ሙሉ ቢኖርበት ወደሚመኘው የኪነ ጥበብ ሙያ እንዲገባ ቀጥተኛና መልካም እድል የፈጠረለት አጋጣሚ ነበር:: የተመኘውን አገኘና በሐገር ፍቅር ማኅበር ተቀጥሮ መስራትም ጀመረ::
በሻህ ‹‹የሙዚቃና የትያትር ስራን ታስተባብራለህ›› ተብሎ ወደ ሐገር ፍቅር ትያትር ቢመጣም በወቅቱ ግን የተደራጀ የጥበባቱ ቁሳቁስና የሰው ኃይል አልነበረም:: ስለሆነም የጥበባቱን ቁሳቁስና የሰው ኃይል ‹‹ሀ›› ብሎ መጀመር ነበረበት::
ለዚህም ይረዳው ዘንድ የየብሔረሰቡን ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪዎችንና 200 ያህል የሙዚቃ ተጫዋቾችን አሰባሰበ:: ከእነዚህም በተለያዩ ደረጃዎች እያጣራ 40 ያህሉን አስቀረና ዋናውን ስራውን ጀመረ::
በመቀጠልም የሙዚቃ መሳሪያዎችን ድምፅ እየለካ ማቀናበሩን ተያያዘው:: መሰንቆ፣ ክራር፣ በገናና ዋሽንት ቃኝቶ ጥሩ ውጤት አገኘ:: የሐገረሰብ ሙዚቃ ለማቀናበር የሚረዳና ወፍራም ድምፅ የሚያወጣ የሙዚቃ መሳሪያ ባለማግኘቱ መላ ለማበጀት ለበለጠ ፈጠራ ተዘጋጀ::
ወደተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በማቅናት መሰንቆ፣ ከበሮ፣ በገና፣ ክራር፣ ዋሽንት፣ ነጋሪት፣ አታሞና ሌሎች የባሕል የሙዚቃ መሳሪያዎችን ውበት ባለው መልኩ በማሰራት አሰባሰበ:: በዚህ ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የማሰባሰብ ጥረታቸውን በተመለከተ አንድ ቆየት ባለ የሕትመት ውጤት ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል::
‹‹ … እናት መሰንቆ የተባለው የሙዚቃ መሳሪያ ተሰርቶ ሊያልቅ ሲቃረብ አንድ ችግር ተፈጠረ:: ይህም የሀገራችን ፈረሶች ጭራ ማጠሩ ነው:: ያጠረውን የፈረስ ጭራ መቀጠል ደግሞ በጭራሽ የሚታሰብ አልሆነም::
መፍትሔው ምን ሊሆን እንደሚችል በሚታሰብበት ወቅት ከአውስትራሊያ የመጡ ፈረሶች በጊዜው በነበረው የክቡር ዘበኛ ክፍል ውስጥ መኖራቸው ታወቀ:: ከዚያም ይህ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር የተፈጠረው ችግርን ማቃለል ተቻለ … ››
በሻህ በትምህርት ቤት ሳለ ያጠናቸው የውጭ አገራት የሙዚቃ መሳሪያዎችንና ስልቶችን በኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያዎች ለመለወጥ ፈጠራ የተሞላበት ጥረት በማድረግ ፍሉትን በዋሽንት፣ ጃዝን በከበሮና አታሞ እንዲተኩ አድርጓል::
ከዚህ በተጨማሪም በቅል ውስጥ ጠጠር በመጨመር ማራካሽ ከተባለው የሙዚቃ መሳሪያ የሚገኘውን ድምፅ እንዲሰጥ አድርጓል:: አንድ ወፍራምና አንድ ቀጭን ድምጽ የሚያወጡ ሁለት ክራሮችና ሁለት መሰንቆዎችን በመጨመር ኢትዮጵያዊ የሐገረሰብ ሙዚቃ ኦርኬስትራ አቋቋመ::
በሻህ ይህን ሁሉ የሙዚቃ መሳሪያ አደራጅቶና ከያኒያንን አሰልጥኖ፤ ዜማዎቹ ተጠንተው አስተማማኝ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ፣ ማለትም ስራውን ከጀመረ ከስድስት ወራት በኋላ፣ የስራ ፍሬውን ለማሳየት ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴንና ሌሎች እንግዶችን ወደ ሐገር ፍቅር ትያትር ትንሿ አዳራሽ በመጋበዝ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የሐገረሰብ ሙዚቃ ኦርኬስትራ አስተዋወቀ:: ንጉሰ ነገሥቱና ተጋባዥ እንግዶቹም በጣም ደስ ተሰኝተው በሻህን አበረታቱት፤ መረቁት::
በ1937 ዓ.ም የሐገር ፍቅር ማኅበርን የትያትር ቡድን በባለሙያ ለማደራጀት እንቅስቃሴ ጀመረ:: ትያትር ለማዘጋጀት ደግሞ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች ያስፈልጉ ነበር:: ይሁን እንጂ ሰዎቹን ማግኘት ቀላል አልነበረም::
በወቅቱ እነዚህን ሰዎች ማግኘት የሚቻለው ከቤተ ክህነት ነበር:: በሻህ ምልመላው እንዴትና ከየት እንደሚካሄድ ካውጠነጠነ በኋላ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ዲያቆናትን አሰባሰበ:: ኢዩኤል ዮሐንስ፣ መዝሙር ገብረወልድ፣ ከበደ ወልደጊዮርጊስና ሌሎችም ከተመረጡትና ከተሰባሰቡት መካከል ይጠቀሳሉ::
በሻህ የሐገር ፍቅርን የተቀላቀለበት 1930ዎቹ በኢትዮጵያ መቅረፀ-ድምጽ ስላልነበረ በወቅቱ የሚዜሙት የዘፈን ዜማዎች በመቅረፀ ድምፅ ተቀርፀው ሳይሆን ኦርኬስትራው ሬዲዮ ጣቢያው ድረስ በመሄድ በቀጥታ ስርጭት ነበር::
በሻህ የውዝዋዜ እና የዜማ ክፍል መሪ በመሆኑ ሙዚቃ ተጨዋቾችን ሬዲዮ ጣቢያው ስቱዲዮ ድረስ በመውሰድ ዘፈኖቹ በቀጥታ ለህዝብ እንዲተላለፍ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በኋላም ማስታወቂያ ሚኒስቴር መቅረፀ-ድምፆችን ሲያስመጣ ዘፈኖቹን በማሰባሰብ ተቀርፀው ለትውልድ እንዲቆዩ ትልቅ ሚና ተጫውቷል::
ማስታወቂያ ሚኒስቴር መቅረፀ-ድምፆችን አስመጥቶ ስራ ላይ ማዋሉ ለበሻህ ጥረትና ለአገሪቱ ጭምር ታላቅ ለውጥ አመጣ:: የሙዚቃ መሳሪያዎችን ተሸክሞ ወደ ሬዲዮ ስቱዲዮ መሄድ ቀረ:: የሐገር ፍቅር ማኅበርም የበሻህን ጨምሮ የኢዩኤል ዮሐንስንና የፍሬው ኃይሉን ዜማዎችን በግሪካዊ ተወላጅ ኮስታ ዴማስ አማካኝነት ‹‹ሂዝ ማስተር ቮይስ›› በተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ አስቀርፆ ለሕዝብ ጆሮ አድርሷል::
ከዚህ በተጨማሪም የሐገር ፍቅር ማኅበር የስራ እንቅስቃሴው እያደገ ሲመጣ የሙዚቃ፣ የውዝዋዜና የትያትር ቡድኖችን ይዞ በየጠቅላይ ግዛቱና በየአውራጃው በመጓዝ ትርኢቶችን በስፋት ለሕዝብ አቅርቧል፤ አስተዋውቋል::
በሻህ ተክለማርያም በብርቱ ትጋትና በጥልቅ ጥበብ አሰልጥነው ያደራጁት የኪነ ጥበብ ቡድን ወደ ውጭ አገራት ሄዶ ስራውን እንዲያሳይ ተፈልጎ ስለነበር በሻህ ይህንኑ ለመፈጸም እንዲዘጋጁ ተነገራቸው:: እርሳቸውም ትዕዛዙን ተቀብለው ቡድናቸውን በመምራት በ1953 ዓ.ም የመጀመሪያውን የኢትዮጵያን የኪነ ጥበብ ቡድን ይዘው ወደ ሶቭየት ኅብረትና ቻይና ተጓዙ::
በውጭ አገራት ቆይታቸውም የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ቡድን ከፍተኛ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን አተረፈ:: ሦስት ወራትን የፈጀው የባሕል ቡድኑ ጉዞ በወቅቱ በብዙ የውጭ አገራት መገናኛ ብዙኃን ጭምር ከፍተኛ ሽፋን አግኝቶ ነበር::
የበሻህ ተክለማርያም አሻራ ከሚታዩባቸው አበርክቶዎቻቸው መካከል የሚጠቀሰው ሌላው ጉዳይ ሴት ከያኒያንን ለማፍራት ያደረጉት ጥረት ነው:: ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው እንደተሾሙ፣ ኅዳር 11 ቀን 1925 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በተገነባው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ከፊል መደበኛ የትያትር አዳራሽ መድረክ ላይ በዳዲ ቱራ ተውኔት ላይ ቀጸላ አንዳርጌ እና አሰለፈች ማሞ የተባሉ ሴት ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተወኑ።
በወቅቱ ቀጸላ አንዳርጌ የጅፋሬን፤ አሰለፈች ማሞ ደግሞ የአያንቱን ገጸ ባህርያት ተላብሰው በመተወን ታዳሚውን አስደምመዋል። ከዚያ ጊዜ በኋላ እስከ 1930ዎቹ ድረስ በቀረቡ የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ የነበረው የሴቶች ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: ወቅቱ ሴት ከያኒያንን ለማሳተፍ ምቹ ስላልነበር ቀደም ባሉት ጊዜያት የሴት ተዋንያንን ሚና የሚወጡት ወንዶች ነበሩ::
በሻህ ተክለማርያም የሙዚቃና የትያትር ቡድን ሲያቋቁሙ ከመረጧቸው 40 ሰዎች መካከል 14 የሚሆኑት ሴቶች ነበሩ:: አቦነህ አሻግሬ በጽሑፋቸው እንዳብራሩት፤ በሻህ ተክለማርያም የመለመሏቸው ሴቶች በአብዛኛው በየመሳፍንቱና በየመኳንንቱ ድግስ ላይ፣ እንዲሁም በመጠጥ ቤቶች እየዘፈኑ በማዝናናት የሚታወቁ አዝማሪዎችን ሲሆን፤ እነሱም ንጋቷ ከልካይ፣ ሽሽግ ቸኮል፣ እታገኘሁ ኃይሌ፣ አሰለፈች ሙላት፣ ዘነበች ግዛው፣ ማናህሌ ማሞ፣ በየነች አሊ፣ አለሚቱ ተፈራ፣ ከበቡሽ ይመር፣ ዘነበች መንገሻ፣ በላይነሽ ውብአንተ፣ ደመቀች አሊ፣ ወርቄ መንገሻና አሰገደች ለማ ነበሩ። ይሁንና እነዚህ ሴት ከያንያን ከድምጻዊነትና ተወዛዋዥነት አልፈው በድራማ ውስጥ ለመተወን በወቅቱ የነበረው ማህበረሰባዊ ጫና ነጻ አላደረጋቸውም ነበር።
ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም ቢሆን ሴት ከያኒያን ከማኅበረሰባዊ ጫና ተላቅቀው በኪነ ጥበብ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አልነበረምና የሴቶች ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ነበር:: በሻህም ድፍረትን ገንብተዋል የሚሏቸውን ሴቶች እያግባቡ ጥቂቶችን ለማለማመድ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል::
በሻህ በርካታ ዜማዎችን ያቀናበሩ ሲሆን ‹‹ሙሽርዬ›› እና ‹‹ያይኔ ተስፋ›› የተሰኙት ስራዎቻቸው እስካሁን ድረስ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት አላቸው:: ‹‹ሙሽርዬ›› የሚለው ስራቸው በርካታ ወጣትና አንጋፋ ድምፃውያን የሚጫወቱት የሰርግ ዜማ ነው:: በሻህ የታወቁና የተደነቁ የባሕል ሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋችና ችሎታቸውን በሕዝብ ፊት ያስመሰከሩ የትያትር ተዋናይም ነበሩ:: ከዚህ በተጨማሪም በሳልና የማይዘነጉ የዘፈን ድርሰቶችን በመፃፍ ስማቸውን የተከሉ የጥበብ ፈርጥ ነበሩ::
እንዳለመታደል ሆኖ የአንጋፋው ባለሙያ የኪነ ጥበብ ሕይወት መጨረሻው ሊያምር አልቻለም:: ፍፁም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዲህ በማለት ያስረዳል …
‹‹ … የአቶ በሻህ የኪነ ጥበብ ሕይወት የሚቋጨው እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ነው:: ያን ያህል ደክመው ካሰባሰቧቸው የባሕል ተጨዋቾችና የትያትር ሞያኞች መካከል 43 ያህል ምርጥና ምትክ ያልነበራቸው አርቲስቶች ከስራ እንዲባረሩ ተደረገ:: የሕይወታቸውን ሙሉ ጊዜ ሰጥተው በሁለት እግሩ ያቆሙት የቴአትር ዘርፍ ፈረሰ:: የጥበብ ልጆቻቸው እንዲህ በቀላሉ ከጥበቡ ማዕድ እንዳይቋደሱ መደረጋቸው የአቶ በሻህን ጥንካሬ ፈተነው:: ከቶጎና ማርያም እስከ ሩቅ ምስራቅ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ፈጅቶ የፈካው የጥበብ አዝመራ በውርጭ ተመታ::
ይባሱንም ራሳቸው አቶ በሻህ ይወዱትና ሙሉ ጊዜያቸውን በመስጠት ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን እዚህ ካደረሱት ሙያ ተነስተው ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዛውረው እንዲሰሩ ተደረገ:: አቶ በሻህ ግን ‹አዲሱ መስሪያ ቤት ገብቼ አልሰራም› ብለው አሻፈረኝ አሉ:: ነገር ግን ከብዙ ውትወታ በኋላ በ1958 ዓ.ም በዋናው የኦዲተር መስሪያ ቤት የአንድ ክፍል ኃላፊ በመሆን ጡረታ እስከወጡበት 1967 ዓ.ም ድረስ አገለገሉ … ››
ለሐገረሰብ ሙዚቃ መሰረት የጣሉት አንጋፋው የግጥምና የዜማ ደራሲው እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋቹ በሻህ ተክለማርያም፤ ደማቅ አሻራቸውን ያሳረፉበት የሐገር ፍቅር ትያትር ቤት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት በሐምሌ ወር 1987 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል::
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013