ኢያሱ መሰለ
ሕይወት የተለያዩ መልኮች አሏት ።ደስታና ሀዘን፤ ስኬትና ውድቀት፤ ድልና ሽንፈት ሌሎችም ዝብርቅርቅ መልኮች ይፈራረቁባታል ።ሰው የዚህችን ዓለም አየር መማግ ጀምሮ እስትንፋሱ እስኪቋረጥ ድረስ በርካታ የህይወት ውጣ ውረዶችን ያሳልፋል ።አንዳንዶች ገና በጠዋቱ የህይወትን መንገድ አንድ ብለው መጓዝ እንደጀመሩ በፈተና ይጠመዳሉ። አንዳንዶችም መልካም የስኬት ዘመን አሳልፈው ባለቀ ሰዓታቸው ለተለያዩ ችግሮች ይዳረጋሉ ።
የዛሬው እንግዳችን ገና ነፍስ ማወቅ እንደጀመረ በገጠመው ፈታኝ የጤና ችግር ምክንያት 13 ዓመታትን የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ያሳለፈ ነው ።የያኔው ብላቴና የአሁኑ ወጣት እስከ ሰባተኛ ክፍል በተማረባቸው ዓመታት ከክፍሉ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ይይዝ ነበር ። ውጤታማ ሯጭ ለመሆን ካለው ጉጉት የተነሳ ገና በጠዋቱ ልምምድ እያደረገ ተስፋ ሰጪ ውጤት ያስመዘግብ ነበር፡፡
ታዛዡ፣ ታታሪውና ባለብሩህ አዕምሮው ታዳጊ ያሰበውን የህይወት ጫፍ ለመንካት ሲጓዝ ይሆናል ተብሎ በማይገመት ምክንያት ጤናው ታውኮ ስድስት ጊዜ ያህል ቀዶ ጥገና አድርጓል ።ሌላ ቀዶ ጥገና ለማድረግም በቀጠሮ ላይ ይገኛል ።
እግሩ ላይ በወጋው እሾህ ሰበብ በተፈጠረ የህክምና ስህተት 13 ዓመታትን መተኛቱ ሳያንስ የግራ እግሩን ለመቆረጥ በቅቷል፡፡ተስፋ ያልቆረጠው ወጣት ከረዥም ቆይታ በኋላ ህልሙን ለማሳካት ክራንቹን ይዞ የትምህርት ቤት ደጃፍ መርገጥ ጀምሯል ።ባለታሪኩ የደረሰበት ፈተናና የህይወት ውጣ ውረድ አስተማሪ በመሆኑ የዚህ አምድ እንግዳ ለማድረግ ወደድን ።
ምህረቱ መንግስቴ ይባላል። ትውልዱና እድገቱ ምእራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ ዋንግዳ በሚባል ገጠራማ አካባቢ ነው። ነፍስ ካወቀ በኋላ ከአብሮ አደጎቹ ጋር እየተጫወተና ለቤተሰቡ እየታዘዘ ማደጉን ያስታውሳል። እድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ደግሞ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብቶችን እየጠበቀና የተለያዩ የግብርና ስራዎችን እየሰራ ቤተሰቦቹን በማገዝ ያሳልፋል ።
ጎን ለጎንም ትምህርቱን ይማራል ። ምህረቱ በትምህርቱ ውጤታማ ነበር ።የእስከ 7ኛ ክፍል በተማረባቸው ዓመታት ከክፍሉ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይይዝ እንደነበር የትምህርት ማስረጃው ያስረዳል ።
ልጅነቱን በትጋትና በብርታት እያሳለፈ የነበረው ብላቴና የ8ኛ ክፍል ትምህርቱን እንደጀመረ እንድ ክስተት ይገጥመዋል ።ምህረቱ አንድ ቀን እንደተለመደው ከብት እየጠበቀ ሳለ እግሩን እሾህ ይወጋዋል ።በእሾህ መወጋት በገጠር ህይወት ውስጥ ማንኛውንም ሰው ሊያገጥመው የሚችል ተራ ጉዳይ ነው ።
ተራ ጉዳይ በመሆኑም እሾህ በእሾህ ይወጣል ።ምህረቱም ለወጋው እሾህ ከዚህ ያለፈ ቦታና ግምት አልሰጠውም ።ነገር ግን ያለወትሮው የህመሙ ሁኔታ እየጨመረ ሲሄድ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ሐኪም ቤት ይሄዳል ።
ከዚያም ቴቲያነስ እንዳይሆንበት ሀኪሙ በሁለቱም ታፋዎቹ ላይ ለእያንዳንዳቸው አንድ መርፌ እንዲወጋ መድሃኒት ያዝለታል ።መርፌውን የወጋው ሙያተኛ ግን የታዘዘለትን ሁለት መርፌ በአንድ ታፋው ላይ ይሰጠዋል ።
ምህረቱ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን ይስታል፤ እግሩን ይደነዝዘዋል፤ መራመድ ይሳነዋል፤ ከዚያም መርፌ የተወጋበት ቦታ እያበጠ መሄድ ጀመረና ከስድስት ወር በኋላ ይፈነዳል ።ምህረቱ የአልጋ ቁራኛ ይሆናል ።
ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚኖሩት ቤተሰቦቹ ያላቸውን ንብረት እየሸጡ ልጃቸውን ለማሳከም እላይ ታች ማለት ይጀምራሉ ።ከባህርዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል እስከ ጥቁር አንበሳና ታዋቂ የግል ሐኪም ቤቶች ሳይቀር በርካታ ቦታዎችን ያዳርሳሉ፤ አንዳንዶቹ ጋር እየተኛ እንዳንዶቹ ጋር እየተመላለሰ መታከሙን ቀጠለ፤ ምህረቱ ግን ሊሻለው አልቻለም ።ጭራሽ ቁስሉ እዥ እያየዘ በቀን በቀን በርከት ያለ ፈሳሽ ማውጣት ጀመረ ።የቤተሰቦቹን ትእዛዝ በማከናወን ላይ እያለ እግሩን እሾህ የወጋው ጎበዝ ተማሪ እንደዋዛ አልጋ ላይ ወድቆ ቀረ ።ትምህርቱም ተቋረጠ ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ሌላ ችግር ተፈጠረ ። በግብርና ህይወት ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱትና ቤተሰቦቻቸውን በበላይነት የሚያስተዳድሩት በተለይም ምህረቱ ከአንዱ ሐኪም ቤት ወደ ሌላኛው እየተዟዟረ እንዲታከም ያላቸውን ሁሉ ሲያደርጉለት የነበሩት አባቱ በድንገት ታመው ይሞታሉ ።
ቤተሰቡ ሌላ ሀዘን እና ፈተና ውስጥ ገባ፤ ምህረቱን በማሳከም አቅማቸው የተዳከመው ቤተሰቦች እንደገና የአባወራውን ህልፈት ተከትሎ የገቢ ምንጫቸው በመቀነሱ ለችግር ይጋለጣሉ፤ የምህረቱ የህክምና ክትትልም በአቅም ማነስ ምክንያት መስተጓጎል ይገጥመዋል ።
በዚህን ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ ስራ ከጀመረ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላው ወንድሙ ፍቃዱ ምህረቴ የወላጆቹን ችግር ለመጋራትና ወንድሙን ለመንከባከብ ይዞት ወደ አዲስ አበባ ይመጣል ።
በመምህርነት የሚያገኘው ደመወዝ ከቤት ኪራይና ከምግብ አልፎ ወንድሙን ለማሳከም የሚተርፈው አልሆነም ።በተከራያት ጠባብ ቤት ውስጥ ምህረቱን እየተንከባከበና ስራውን እየሰራ ህይወትን ቀጠለ ።
ጧት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዱ በፊት ቁስሉን አጣጥቦ ምግቡን አስቀምጦለት ይሄዳል ።ማታም ሲመለስ እንዲሁ ተመሳሳይ እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ታዲያ ትምህርት ቤት ሆኖ ቀኑን ሙሉ የሚያስበው ስለወንድሙ ነው ።ምህረቱ የጤና መሻሻል ባለማሳየቱ ፍቃዱ የአዕምሮ እረፍት ሊያገኝ አልቻለም። ያ ታዛዥ እና በትምህርቱ ስመ ጥር የነበረ ታዳጊ እንደቀልድ አልጋ ላይ መዋሉ ያበሳጨዋል ።
ፍቃዱ ወንድሙ ጤናማ ሆኖ ትምህርቱን ቢማር ውጤታማ እንደሚሆን ያምናል፤ ያ ባለመሆኑም ያዝናል ።የቤተሰብ ቅርስ ተሟጦ አልቋል፤ የፍቃዱም ደመወዝ ከቤት ኪራይና ከምግብ ተርፎ ለህክምና የሚበቃ አልሆነም ።ፍቃዱ ወንድሙን ዝም ብሎ እያየው ከሚሞትበት የደረሰበትን የጤና ችግር እያስረዳ የሰዎችን እርዳታ መጠየቅ እንዳለበት ይወስናል።
ከዚያም ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ስለጉዳዩ ማስረዳት ጀመረ ።በዚሁ መሰረት በውጭም በሀገር ውስጥም የሚኖሩና ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች የድጋፍ እጃቸውን መዘርጋት ይጀምራሉ ።ከዚህም ከዚያም ያገኛትን ገንዘብ ይዞ በየሐኪም ቤቱ እያመላለሱ ማሳከም የፍቃዱ የዘወትር ስራ ሆነ ።ህመሙ ግን መልኩን እየቀየረና እየከፋ ሄደ ።
የህመሙ ጉዳይ ለሌላ ችግር ሊዳርገው ስለሚችል ምህረቱ አንድ እግሩን መቆረጥ እንዳለበት ከሀኪሞች ይነገረዋል ።ምህረቱ ከራሱ ጋር ከመከረ በኋላ እግሩን ለማስቆረጥ ይወስናል ።የህክምናውን ወጪ እንደሚሸፍኑለት ቃል ከገቡለት ሰዎች ጋር ይነጋገራል ።አንዲት እናት የቤት ኪራይ እንደምትከፍልለት እና ሌሎችም ሶስት ሰዎች የህክምና ወጪውን እንደሚሸፍኑለት ቃል ገብተውለት ህክምናውን ይጀምራል ። እናም የግራ እግሩ ይቆረጣል ።
በዚህም ከሚታዘዙለት መድኃኒቶች ጋር በአጠቃላይ እስከ ሶስት መቶ ሺ ብር የሚገመት ወጪ ይመዘገባል፤ ምህረቱ ህክምናውን ጨርሶ ከሆስፒታል ሊወጣ ሲል ያለበትን ሂሳብ እንዲከፍል ይጠየቃል ።ሊያሳክሙት ቃል የገቡለትን ሰዎች ተማምኖ ህክምና መጀመሩን በመግለጽ እርሱ ምንም እንደሌለው ይናገራል ።
ሀኪም ቤቱ ከሶስት መቶ ሺህ ብሩ መቶ ሺውን ትቶለት ሁለት መቶውን ብቻ እንዲከፍለው ቢያደርግም ሳይከፍል ይቀራል። እንከፍልልሃለን ያሉት በጎ አድራጊዎችም በገንዘቡ መብዛት ምክንያት ለመክፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ ።
በመጨረሻ መታወቂያውን አስይዞ ወደ ፊት ሰዎችን ተማጽኖ እንደሚከፍል ቃል በመግባት ከሆስፒታል ይወጣል።ምህረቱ እግሩን ካስቆረጠው በኋላ መጠነኛ እፎይታ ያገኛል ።13 ዓመታትን በአልጋ ላይ ያሳለፈው ብላቴና ዛሬ የ24 ዓመት ወጣት ሆኖ በድንገት ያቋረጠውን እና የሚወደውን ትምህርቱን ጀምሯል ።
የታከመበትን ብር አለመክፈሉ እና እዳ ተሸክሞ ትምህርት መማሩ የአዕምሮ ሰላም እንዳልሰጠው ይናገራል። ‹‹በህይወት እንድኖር ያደረገኝ የፈጣሪ ምህረት፣ የቤተሰቦቼ ጽናትና የሰዎች ድጋፍ ነው›› የሚለው ምህረቱ አሁንም ህይወቱ መስመር እንዲይዝ የሰዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይገልጻል ።
ምህረቱ በክራንች መንቀሳቀስ የጀመረ ቢሆንም ገና ልምድ ባለማዳበሩ ያሰበበት ድረስ መጓዝ አይችልም።የሚወደውን ትምህርቱን ላለማጣት ሲል በቀን በቀን ከአርባ እስከ 50 ብር እየከፈለ በባጃጅ ወደ ትምህርት ቤት ይመላለሳል ።አሁንም ለመድሃኒትና ቁስሉን በቀን ሁለት ጊዜ ለሚያጥቡት ባለሙያዎች በቀን እስከ ሰባት መቶ ብር ወጪ ያወጣል ።
ምህረቱ እግሩን እንደተቆረጠ ጥሩ ጥሩ ምግብ መመገብ እንዳለበት ከሀኪሙ ቢነገረውም እርሱ ግን ባለበት ኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት እራሱን ለመንከባከብ አልቻለም ።ይነስም ይብዛም ግን ወንድሙ የአቅሙን ሁሉ ያደርግለታል ።
ወንድሙ ትዳሩንና ልጆቹን እየበደለ ሙሉ ትኩረቱን ለእርሱ ሰጥቶ እዚህ ድረስ እንዳመጣው የሚናገረው ምህረቱ እራሱን ችሎ የሚኖርበትን ጊዜ ናፍቋል።
ምህረቱ አካል ጉዳተኝነት በማንም ላይ ሊደርስ እንደሚችል ያምናል ይልቁንም አንድ አካል ጉዳተኛ የሰው እጅ ላለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ያስፈልጋልም ይላል ።
የምህረቱ ህልም ይህን የችግር ሰዓት አልፎ ያሰበበት ቦታ ላይ መድረስ ነው ። ‹‹ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው›› የሰው ድጋፍና እርዳታ የቤተሰቦቹ ክትትልና እንክብካቤ እዚህ አድርሶታል ።
አሁንም ሰዎች ይህችን የችግር ወቅት ብቻ እንዲያሻግሩት ይማጸናል ።ህክምናውን ሳይጨርስ ወደ ናፈቀው ትምህርቱ የተመለሰው ምህረቱ የትምህርት፣ የምግብ፣ የትራንስፖርትና የህክምና ወጪዎቹ ፈተና ሆነውበታል ።
ከፊቱ ካለው ይልቅ ከኋላ ያሳለፈው ጊዜ ከባድ እንደነበር የሚናገረው ወጣቱ ።ሰዎች የአቅማቸውን እንዲያግዙት ይማጸናል ።በተለይም መንግስት የመኖሪያ ቤት ችግሩን ተረድቶ ማረፊያ ቤት እንዲሰጠውም ይማጸናል።
የተጎጂው ብላቴና ወንድም መምህር ፍቃዱ መንግስቴ በበኩሉ ከወንድሙ ጋር ያሳለፈውን የስቃይ ህይወት እንዲህ ይገልፀዋል ።መምህር እንደመሆኔ መጠን ሁል ጊዜ ትምህርት ቤት መገኘትና እያነበብኩኝ እራሴን ማብቃት ይጠበቅብኛል። እኔ ግን አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ወንድሜን በማስታመም ነው ።
ትዳሬንና ሁለት ልጆቼንም በምፈልገው ደረጃ መንከባከብ አልቻልኩም ።እግዚአብሄር ይመስገን ፈጣሪ ድካሜን ተመልክቶት አሁን ወንድሜ እራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ጀምሯል ።እንደውም ትምህርቱን ቀጥሏል ። በዚህም እፎይታ ተሰምቶኛል ።
ነገር ግን ከፊት ለፊቱ ሁለት ቀዶ ጥገና ይጠብቀዋል ።እስከ አሁንም ያገዙኝ ሰዎች ናቸው፤ አሁን የመጨረሻውን ምዕራፍ እንዳልፍ ወንድሜም የራሱን ህይወት እንዲኖር የሰዎች ድጋፍ ያስፈልገኛል›› ይላል ፍቃዱ።
ብዙውን ጊዜ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ድጋፍ የሚያደርጉት በማህበር ለተደራጁ ተጎጂዎች መሆኑን የሚናገረው ፍቃዱ ታማሚው ወንድሙ ግን በየሰዓቱ ክትትልና እንክብካቤ ስለሚያስፈልገው ቤት ውስጥ ለመተኛት መገደዱን ይናገራል። በዚህ የተነሳ በማህበር ታቅፎ የመረዳት እድል ስላላገኘ ፍቃዱ ሰዎችን እየተማጸነ እራሱም እየተፍጨረጨረ እዚህ አድርሶታል ።
ዛሬ ወንድሙ ባሳየው የጤና መሻሻል ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ታይተዋል ።ያም ብቻ ሳይሆን የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆነው ወንድሙ ነገ በትምህርቱ ውጤታማ ሆኖ ከራሱ አልፎ ለሌሎች እንደሚተርፍ ያምናል ።
ምህረቱ አብዛኛውን የስቃይ ዘመን በጽናት አልፎ እዚህ ቢደርስም አሁንም ፈታኝ ሁኔታዎች ከፊቱ እንዳሉ ይናገራል ።እነዚህም፤ ቀሪ ህክምናውን ማጠናቀቅ፣ ትምህርቱን መከታተል፣ ያለበትን እዳ መክፈል፣ የማረፊያ ቦታ ማግኘት ወዘተ ናቸው ።
አሁንም እነዚህን ችግሮች ተሻግሮ እራሱን ችሎ የሚኖርበት አዲስ ቀን እንደሚመጣ ያምናል ። እስኪሻገረው ድረስ ግን አሁንም የሰዎች ድጋፍና እርዳታ ያስፈልገዋል በማለት ተሰናበትን ።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013