ተገኝ ብሩ
ኪነጥበብ በብዙ መልኩ አድምቃ ሁነትን ትገልፃለች። ያለፈን አቅርባ ታመላክታለች የሞተን ቀስቅሳ ህያው ታደርጋለች። ጥበብ ምልከታዋ ጥልቅ እይታዋ እሩቅ መጎናፀፊያዋ በውበት የደመቀ ነውና ሁሉንም ሰብስባ በአንድነት ገሀድ ታደርጋለች።
ይህች የጥበበኞች ምድር ኢትዮጵያ በጠቢባን ልጆችዋ ታሪኳ ተቃኝቷል። ነፃነትዋን ጠብቀው ያቆይዋት አባቶች ገድል፤ ክብሯ እንዳይደፈር የተሟገቱላት እናቶች መስዋእትነት በብዙ ተነስቷል።
ለአፍሪካዊያን የነፃነት ችቦ የለኮሰው የአድዋ ድል፤ ለኢትዮጰያዊያን ሉዓላዊነት አረጋጋጭ የጀግንነታቸው አመላካች የሆነው ታላቁ ታሪክ በጥበብና በጥበበኞች በተለያየ ገፅ ተከትቧል። አድዋ የጥቁር ህዝቦች የከፍታ ታሪክ የኢትዮጵያዊያን አንፀባራቂ ድል ከዘከሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች መሀል ለዛሬ ሁለቱን መርጠን ለእናንተ አቅርበናል መልካም ንባብ።
ከዛሬ 125 ዓመታት በፊት የሆነ በዚህ ምድር በበቀሉ ትንታጎች የተሰራ ታላቅ ገድል አድዋ የእጅጋየሁ ሽባባውን ያህል አጉልቶ ለዓለም የገለፀ ተቀኝቶ ልዕልናውን ያረጋገጠ የሙዚቃ ስንኝ ለማግኘት ብዙ መድከም ይጠይቃል።
ይህች ድንቅ አቀንቃኝ አድዋ በተሰኘ ዜማዋ የታሪካዊ ሁነቱ አጠቃላይ ገፅታ፣የኢትዮጵያዊያን ጀግንነት በጦርነቱ የከፈሉት መስዋዕትነት እና የድሉ ድምቀት በነጠሩና ብዙ በሚገልፁ ቃላት ተጠቅማ አቀንቅናዋለች።
መጠሪያው አድዋ በተሰኘው በዚህ ስራዋ የሰው ልጅ ታላቅነት የአዳም ዘርን ክብር አጉልታ በመጀመር ይህ ክብሩ ለታላቅና ከራሱ የበለጠ ለሚወዳትና ለሚያከብራት ሀገሩ እራሱን ቤዛ ያደረገበትን እውነት በዚህ መልክ ለማሳየት ተጠቅማበታለች።
የሰው ልጅ ክቡር፣… ሰው መሆን ክቡር፣
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፣ሰውን ሲያከብር፣
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ።
በወቅቱ እዚህ አገር ላይ በዚህ ጀግና ህዝብ የተፈፀመ ሀያል ድል በዘከረው የአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው ዜማ ለዚህች ምድር ክብር የተከፈለ መስዋዕትነት በነጠረ አገላለፅ ተሰኝቷል።
ከያኒዋ እያደር ሲሰሙት አዲስ፤ ከርሞ ሲያዳምጡት በብዙ የሚመነዝሩት ትርጓሜ የያዘ፤ ሲመረምሩት የሚደንቅ ፍቺ የሚሰጥ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ስራዋ ነው። ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ላከበራት ሀገሩ የከፈለው መስዋዕትነት ተወስቷል።
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣
ይች በደምና በአጥንት ነፃነትዋን ጠብቃ የቆየች ምድር ፤ጠባቂዎችዋ የዋሉላት ውለታ፤ የከፈሉላት መስዋዕትነት በብዙ ተገልፃል።
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ም ድር፣
ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።
መስዋዕትነቱ ልጆችዋ የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ ምክንያት ሆኗል። በማንነታቸውና በባህላቸው እንዲፀኑ ረድቷቸዋል። ኢትዮጵያዊያን ከሰው ፊት በነፃነት እንዲቆሙ መኩሪያ ሆኗቸዋል። ይሄንንም እጅጋየሁ በዚሁ ዜማዋ እንዲህ ስትል አዚማዋለች።
በኩራት፣ በክብር፣
በደስታ፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን፣
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን።
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣
ያኔ አፍሪካዊያን በነጮች ተወረው ነፃነታቸውን
አጥተው ሉዓላዊነታቸውን ተነጥቀው ነበርና ኢትዮጵያዊያን የተቀዳጁትን ድል ለጥቁር ህዝቦች በሙሉ በተለይ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ችቦ ለኩሷል። ድሉ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለተበደሉ ጥቁሮች ተንቀው ተደፍረው ለነበሩት አፍሪካዊያን ሁሉ ሆኗል።
የጥቁር ድል አምባ፣ አድዋ፣
አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ፣
ተናገሪ ……..ተናገሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ።
ከዚህች የሙዚቃው ዓለም ንግስት በተጨማሪ ይህንን ታላቅ ድል ከዘከሩ ድምፃዊያን መካከል ዝነኛው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) አንዱ ነው። “ጥቁር ሰው”ብሎ በሰየመው አልበሙ የአድዋን ታላቅ ድል ከጊዜው የኢትዮጵያ መሪ ንጉሰ ነገስት አፄ ሚኒሊክ ጀግንነት፣ ቆራጥነትና የኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ በጥበብ ኳሽቶ ባመረ ዜማ ገልፆታል።
ኑ አድዋ ላይ እንክተት..ያ የጥቁር ንጉስ አለና
የወኔው እሳት ነደደ…ለአፍሪካ ልጆች ድል ቀና
ባልቻ አባቱ ነፍሶ …መድፉን ጣለው ተኩሶ
ሳልል ወይ ሆሆ ሆሆ
ይህ የወቅቱ ታላቅ ታሪክ የኢትዮጵያዊያንን ድል የዘከረ፤ ዛሬ ላይ ትናንት የሆነውን በብዙ የገለፀ የጥበብ ስራ በከያኒው ተቀምሮ በሙዚቃዊ ጥበብ ተዋዝቶ ታሪክ አሳውቆናል።
አድዋ ላይ በጀግንነት የተዋደቁ ኢትዮጵያዊያን እዚያ ተራራ ላይ ለአገራቸው መስዋዕት የከፈሉ ታላላቅ የጦር መሪዎች ማንነት፣ ባህሪና ጀግንነት ምስል ከሳች በሆነ መልኩ አስደምጦናል። እነ ራስ አሉላን ከነጦር መሳሪያቸው የእነ መንገሻን ድል አድራጊነት ቴዎድሮስ ካሳሁን በሙዚቃው ጠቅሶ አሳውቆናል።
ፋኖው ኣባ ራስ አሉላ
ሳንጃ ጎራዴው ቀላ
አዛዥ የጦሩ ባሻ
ድል ነው ካለ መንገሻ
ጊዮርጊስ ፈረሱ ቆሞ ሳይ
ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ
አባቴ ወኔውን ተኮሰው
ምኒልክ ጥቁር ሰው
እያለ የጦር ሜዳው ተጋድሎ ለአገር የተከፈለው ታላቅ መስዋዕትነት ጥበብ መሰረት አድርጎ አሳይቶናል። በዚህ አላበቃም፤ እዚያ ታሪካዊው ተራራ አድዋ ላይ የተካፈሉ ጀግናው የጦር መሪ በቅፅል ስማቸው አባ መላ በመባል የሚታወቁትን ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን በዚሁ የታሪክ መዘክር በሆነው ስራው አንስቷቸዋል። በጦር ሜዳው ውሏቸው የሰሩትን ታላቅ ጀብድ ጠቅሷል።
ዳኛው ያሉት አባመላ
ፊት ሐብቴ ዲነግዴ
ሰልፉን በጦር አሰመረው
ፊት ሆኖ በዘዴ
ኢጆሌ ቢያኮ ጀጀባዳ መሌ
ጀዴቶ ከኤ ያገሬ ኮበሌ
ዱበት ኢንዴምኑ አልከን ተኤ ጉያ
ዲናፍ ሒላኑ ኢትዮጲያ
ኢጆሌ ቢያኮ
በህብር ያጌጠቸው በአድዋ ታላቅ ድል ነፃነቷን ጠብቃ ዛሬ ድረስ ሳትደፈር የቆየችው ኢትዮጵያ የብዙሀን እናት መሆንዋ እሙን ነው። አድዋ ላይ የተጋደሉ የመሀል አገር ጀግኖች እዚያ ቦታ ላይ ራሳቸውን ሰውተው አገራቸውን ያቆሙ ጀግኖች ዛሬም ድረስ በተለያየ መልኩ ይዘከራሉ።
ከምስራቅና ምዕራብ ከሰሜንና ደቡብ አንድ ላይ ዘምተው ከመሀል አገር ተነስተው አድዋ ላይ ትልቅ ጀብድ የፈፀሙት ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ባለሙያዎች በብዙ አንስተዋቸዋል። እኛም የድል ወር በሆነው ወርሀ የካቲት በዘመን ጥበብ አምዳችን የሁለቱ ዕውቅ ድምፃዊያን የአድዋ ዝክር የዳሰስንበትን ፅሁፋችንን በዚህ ቋጨን፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013