ዋለልኝ አየለ
ወደ ቦታው የሚወስዱ መንገዶች አቧራማ ናቸው። እርግጥ ነው ከዋናው አስፓልት ያለው ርቀት ለማማረር የሚያበቃ አይደለም። እንዲያውም የቱሪዝም ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ የቱሪዝም መዳረሻ እስከ አፍንጫው ድረስ አስፓልት መሆን የለበትም። ትንሽ ርቀት በእግር መሄድ ያስፈልጋል። ተሽከርካሪ መግባት የለበትም ለማለት ነው።
የዚህን የቱሪዝም መዳረሻ አካባቢ አስተዳዳሪዎች ለመውቀስ የሚያስችል አንድ ሌላ ነገር ግን አለ። በአካባቢው ማረፊያ ቤቶች የሉም። በቅርብ ርቀት የሚታዩ የመኖሪያ ቤቶች ካልሆኑ በስተቀር ካፍቴሪያዎችና ሌሎች የመገልገያ ቦታዎች ይናፍቃሉ።
በቀጣይ የታሰበበት መሆኑን ግን የወረዳው የቱሪዝም ባለሙያ ነግረውናል። የቱሪዝም ቦታውን እናስተዋውቃችሁና የባለሙያውን ማብራሪያ እንደርስበታለን።
እዚህ ቦታ ላይ የጌዴኦ ህዝብ ጥበብ ይታያል። የሚታየው ታዲያ የተለመደው የእጅ ጥበብ ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ያለ ፍልስፍና ነው። እንዲያውም ዛሬ ላይ ‹‹ነውር ነው›› እያልን የምናልፋቸው ነገሮች ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ‹‹በግልጽ ይነገሩ ነበር ማለት ነው?›› ብለን እንድንጠይቅም ያስገድዱናል። ተፈጥሮን የመረመሩበት ምሥጢር ነው።
በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ጀምጀሞ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል። የአንደኛው ስም ቱቱ ፈላ ሲሆን የሁለተኛው ስም ደግሞ ጨልባ ቱቱቲ ይባላል። ቱቱ ይባል በነበረ ሰው እንደተሰየሙ ነው የአካባቢው ሰዎች የሚናገሩት።
በእነዚህ ቦታዎች ላይ በወንድና ሴት የብልት ቅርጽ የተሰሩ ጥርብ ድንጋዮች ቆመዋል። በትከሻ፣ደረትና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ቅርጽ የተሰሩም አሉ። በአጠቃላይ በዚህ ቦታ ላይ ያሉ ትክል ድንጋዮች ሰው ናቸው። በቦታው ላይ የተገኙ ሰዎች ሁሉ የሚጠይቁት ለምን በእነዚያ ቅርጾች እንደተሰራ ነው። አንዳንዶቹ በቀልድ አንዳንዶቹም በቁም ነገር ስለፍልስፍናው ይገረማሉ። ለብዙዎች አስገራሚ የሆነው ደግሞ በግልጽ የማይነገሩና የማይታዩ የሀፍረተ ሥጋ ቅርጾች መታየታቸው ነው።
እንግዲህ የሰሪዎች ፍልስፍና እዚህ ጋር ነው። የሰው ልጅ ልዩ ፍጡር ነው። ዓለምን የቀየራት የሰው ልጅ ነው። ዛሬ የተደረሰበት ቴክኖሎጂ ላይ ያደረሰን የሰው ልጅ ነው። ይህ የሰው ልጅ መራባት አለበት። የሚራባው ደግሞ በእነዚህ ‹‹ሀፍረተ ሥጋ›› በምንላቸው የሰውነት ክፍሎች ነው። በተለይም በጥንቱ ዘመን የሰው ልጅ ቁጥር አነስተኛ ነበርና መዋለድ እንደ ፀጋ ይታይ ነበር። አሁን የተደረሰበት የባህልና ወግ እሳቤ ውስጥ ላይሆኑም ይችላሉ። እንግዲህ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ጥበብና ፍልስፍናን አሳይተዋል።
በጌዴኦ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ባህል ታሪክና ቅርስ ጥናት ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ታደሰ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፤ በ1935 ዓ.ም በፈረንሳይ ባለሙያዎች በተደረገ ጥናት ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት የተወሰዱትን ጨምሮ በቦታው ላይ 247 ትክል ድንጋዮች አሉ።
በቦታው ላይ የሰው ልጅ አጽም ተገኝቷል። የመቃብር ሥፍራ እንደነበርም አጥኝዎች አረጋግጠዋል። በቁፋሮ የተገኙ ሌሎች ትክል ድንጋዮችም አሉ። በድምሩ ስድስት ሺህ ያህል ትክል ድንጋዮች ነበሩ። እነዚህ ትክል ድንጋዮች በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሰሩ ናቸው።
ሌላው የጌዴኦ ህዝብ ፍልስፍና እና ጥበብ ደግሞ ይሄኛው ነው። ጌዴኦ ከሌሎች የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለየ ተራራማነት የሚበዛው ነው። በብዙ የአገራችን አካባቢዎች የምናየው ተራራማ ስፍራዎች የተራቆቱና አፈር የሚሸረሸርባቸው መሆኑን ነው። በጌዴኦ ግን ይህ አይታሰብም።
ተራራ መሆኑን ማወቅ የሚቻለው አጠገቡ ሲደርሱ ብቻ ነው። ራቅ ብለው ሲያዩት ጠጠር ቢጥሉበት መሬት የማያሳርፍ የሚመስል ጥቅጥቅ ደን ነው። ከውስጡ ከገቡ ደግሞ ቀና ቢሉ ሰማይ ጎንበስ ቢሉ መሬት አይታይም። ማየት የሚቻለው አረንጓዴ ቅጠል እና መሬት ላይ የረገፉ ቅጠላቅጠልና ፍራፍሬ ብቻ ነው።
በዚህ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ በተሽከርካሪ እየተጓዙ ከሆነ ከአሽከርካሪው ፊት ለፊት ባለው መስታወት የሚታየው ጥቅጥቅ ያለ ዛፍ ከመሆኑ የተነሳ ከትንሽ ርቀት በኋላ መንገድ የማይኖር ይመስላል።
ከአሁን አሁን ተንደርድሮ ጫካ ውስጥ ገባ ብለው ይሳቀቃሉ። ይህ የጌዴኦ መልክዓ ምድር ነው። ለመሆኑ ይህ ተራራማ አካባቢ ለምን ጥቅጥቅ ደን ሆነ? ይህን ጥያቄ የሚመልሰው የጌዴኦ ሳይንሳዊ የሆነ ባህል ነው። ባህሉ ‹‹ባቦ›› ይባላል። ይህ ያልተጻፈ ህግ ‹‹የፀረ ሽብር ህግ›› በሉት። በዚህ አካባቢ የአንድ ዛፍ ቅርንጫፍ ከሰው ህይወት እኩል ዋጋ አላት። በዙሪያዋ ያለው ሰው ሁሉ ጠባቂዋ ነው።
በጌዴኦ ባህል ዛፍ መቁረጥ አደገኛው የወንጀል ድርጊት ነው። ይህ የሚሆነው በአካባቢ ሚሊሻ ወይም ፖሊስ አይደለም። ሲወርድ ሲወራረድ በመጣ የማህበረሰቡ ያልተጻፈ የባህል ህግ ነው። ሌላም አስደናቂ ነገር ልጨምርላችሁ።
በዚህ አካባቢ እጮኛ ሲመጣ ‹‹ስንት ከብት አለው? ቋሚ ሥራ አለው ወይ? ደመወዙ ስንት ነው?›› የሚባሉ የተለመዱ ጥያቄዎች አይደሉም የሚ ጠየቁት። ጥያቄው ‹‹ስንት ዛፍ ተክሏል?›› ‹‹ቪ8 አለኝ›› እዚህ አካባቢ አያዋጣም። የወደዳትን ኮረዳ ማግኘት የሚችለው ዛፍ ከተከለና ከተንከባከበ ብቻ ነው።
‹‹ዛፍ መቁረጥ ቢያስፈልግስ?›› ብለን የአካባቢውን ሰዎች ጠይቀናል። መልሳቸው አጭር ነው፤ መጀመሪያ ተክሎ ነው! መትከል ብቻም እንዳይመስላችሁ። የተተከለው ችግኝ መጽደቁ ተረጋግጦ ነው። ይህም የሚሆነው ታላላቅ ሰዎች ፈቅደው ነው። የተተከለው ችግኝ ከጸደቀ በኋላ አባቶች የይቁረጥ ፈቃድ ይሰጣሉ። የጌዴኦ ዛፎች ዕድለኞች ናቸው!
ይህ የጌዴኦ ጥምር ደን ዓለም አቀፍ ቅርስ ሊሆን ሂደቱን አጠናቋል። የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሊመዘግበው ሪፖርት ተደርጎ የባለሙያዎች አስተያየት እየተጠበቀ መሆኑን የነገሩን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ናቸው።
አቶ ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ የመጀመሪያ ዙር ጥናቱ ተጠናቆ ለባለሙያዎች ተሰጥቷል። እስከአሁን በተገኘው ግብረ መልስ ጥምር ደኑ በዓለም ቅርስነት እንደሚመዘገብ የሚያሳይ ሲሆን የመጨረሻው የባለሙያዎች አስተያየት ተሰጥቶ በቅርብ ጊዜ ይመዘገባል ብለዋል።
በነገራችን ላይ ወደ በይነ መረብ ጎራ ያለ ሰው ስለጌዴኦ ጥምር ደን ብዙ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያገኛል። የዛፎች አይነት ሳይቀር በምድብ በምድብ ተለይቶ ተጠንቷል። ጥናቶቹ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ስለሆኑ በአገርኛ ቋንቋዎች ተርጉሞ ለአካባቢው ህዝብ ማስረዳት ያስፈልጋል።
የጌዴኦ ህዝብ ለተፈጥሮ ያለው ክብርና ለተፈጥሮ ያለው ፍልስፍና ማህበራዊ ህይወቱንም አሳምሮለታል። የዓለም ኃያላን የሚባሉ አገራት ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለውን ቃል ከማወቃቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ‹‹ገዳ›› በሚባል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተዳደር ጀመረ። እነሆ ይህን የገዳ ሥርዓት ለሺህ ዘመናት አስቀጥሎ የጌዴኦ ህዝብ ዛሬም በገዳ አባቶች ማህበራዊ ህይወቱን ይከውናል።
በየትኛውም ጉዳይ ላይ ወጣቶች ለገዳ አባቶች ታዛዥ ናቸው። የገዳ አባቶች አማካሪ ናቸው። የመድረክ ዝግጅቶችም ሆኑ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች የሚጀመሩት በአባ ገዳዎች ምርቃት ነው። ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ የሚወጣ ሰው ሦስት ጊዜ ‹‹አባ ገዳ ዮያ፣ አባ ገዳ ዮያ፣ አባ ገዳ ዮያ›› ይላል። አባ ገዳዎች ሰላም እንደማለት ነው።
በጌዲኦ ብሄር ማንኛውም ማህበራዊ ችግር ሲከሰት የሚፈታው በአባ ገዳ ሥርዓት ነው። የእርቅ ስነ ሥርዓት የሚፈጸመው በአባ ገዳዎች ነው። በተለይም ‹‹ዴፋጬ›› የሚባለው ሥርዓት ግድያ ሲከሰት የገዳይና የሟች ቤተሰብ የሚታረቁበት ሥርዓተ ክዋኔ ነው።
የጌዴኦ ብሄር የራሱ የዘመን መለወጫ በዓል አለው። በዓሉ ‹‹ዳራሮ›› የሚባል ሲሆን አበባ ማለት ነው። የሚከበረውም ከጥር ወር መጀመሪያ እስከ የካቲት ወር መጀመሪያ ባለው ነው። ይህ ወቅት ደግሞ የጌዴኦ ህዝብ ቡናውን፣ ገብሱንና ሌሎች ምርቶችን ሰብስቦ ወደ ጎተራ የሚያስገባበት ነው። የዳራሮ በዓል በሚከበርበት ወቅት ከልጅ እስከ አዋቂ የሚይዙት የተፈጥሮ ስጦታ የሆኑትን የተክል አይነቶች ነው። በተለይም የቆጮ ቅጠል በብዛት ይታያል።
የቆጮ ቅጠል በጌዴኦ ብሄር የክብር መገለጫ ነው። በዘመነኛው ‹‹ቀይ ምንጣፍ›› እንደሚባለው በጌዴኦ ለክብር እንግዳ መንገድ ላይ እና የመግቢያ በር አካባቢየሚነጠፈው የቆጮ ቅጠል ነው። በተለያዩ ትርኢቶች ላይ ቅጠሉን በተለያየ ቅርጽ ይለብሱታል።
እንግዲህ የጌዴኦ ህዝብ ለተፈጥሮ ይህን ያህል ክብር አለው። ከሰው ልጅ እስከ ዕፅዋት አፈጣጠር ይፈላሰፋል፤ ይመራመራል፤ ይጠብቃል። ምድረ በዳ የመሆን ዕድል ያለውን ተራራማ አካባቢ ምድረ ገነት አድርጓል። በማህበራዊ ህይወት በኩልም በአባ ገዳ ሥርዓቱ የመከባበርን ልክ አሳይቷል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ ያገጠጠ ሀቅ አለ። ያ ለአገር የሚበቃ የተፈጥሮ ሀብት ያለበት አካባቢ የመሰረተ ልማት ችግር አለበት። በዞኑ ዋና ከተማ ዲላ ውስጥ እንኳን ዛሬም የውሃ ችግር አለ። በብዙ ሆቴሎች ውስጥ ውሃ የለም።
ከዋናው መስመር ውጭ ያሉ መንገዶች ከተሽከርካሪው በላይ በሚጨስ አቧራ የተሸፈኑ ናቸው። ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች የአካባቢው አመራሮች ተጠይቀዋል። የሰጡት ምላሽ ያው የተለመደው እየተሰራ ነው የሚለው ነው።
ይህ በተፈጥሮ የታደለ አካባቢ በሰው ሰራሽ ችግር እንዳይጎዳ ከፌዴራሉ መንግስት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013