አሥመረት ብሥራት
ወላጆች ልጆቻቸውን በማሳደግ ሂደት ውስጥ በጣም አስጨናቂ የሚሆንባቸው ነገር ህፃናት ሲያንቀላፉ የማይነሱ የሚመስላቸው ነገር ነው። ይህ ስጋት ዝም ብሎ የተከሰተ ሳይሆን ድንገተኛ የህፃናት ሞት በየአጋጣሚው ስለሚደመጥ ነው።
እናም ይህን ችግር በተመለከተ ዶክተር ከሚላ የህፃናት ህክምና እሰፔሻሊስት በቴሌግራም ገፃቸው ካካፈሉን ላይ በማከል በዶክተር መሐመድ በሽር የህፃናት ሐኪም የተፃፈውን ጽሁፍ እንዲህ አዘጋጅተነዋል።
ልጅ ወልዶ መሳም የሚወደድ የተፈጥሮ ፀጋ ነው ። በዚህ ፀጋ የተገኙት ፍሬዎች እስከሚያድጉ የተለያዩ ፈተናዎችን ማለፍ የወላጅ ግዴታ ነው ። ልጆች በእንክብካቤ ውስጥም ቢሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ። ከነዚህም መካከል ህፃናት ድንገትኛ ሞት የሚያጋጥማቸው በምን ምክንያት ነው የሚለውን ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ።
ድንገተኛ የሕፃናት ሞት (Sudden infant death syndrome) እና ሌሎች ከእንቅልፍ ጋር የተዛመዱ የሕፃናት የሞት አደጋን ለመቀነስ ሕፃናት ከተወለዱ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ከእንቅልፍ ጋር ለተያያዙ ድንገተኛ ሞት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሀኪሞች ከሰጡት ምክር ዶክተር መሀመድ ያካፈሉንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል።
በቀላሉ ልንከላከለው የምንችለው ነገር ግን ባግባቡ ካልተገበርነው እስከ የህይወት ማጣት አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ስለሕፃናት ድንገተኛ ሞት እና ሌሎችም ከእንቅልፍ ጋር የተዛመዱ ስለ ሕፃናት የእንቅልፍ ደህንነቶች ምን ያህል በአግባቡ ይታወቃል የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ሊያስረዱን ሞክረዋል ።
በየዓመቱ ከእንቅልፍ ጋር በተገናኘ በአሜሪካን ውስጥ ወደ 3,500 እድሜያቸው ከአንድ አመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲተኙ መሞታቸው ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ማሳያ እድርገው ያቀርባሉ ።
ከነዚህም በእንቅልፍ እያሉ ከሞቱት ሕፃናት ውስጥ አብዛኛዎቹ ይህ ሲከሰት የተገኘባቸው ነገሮች ሕፃን ከአልጋ ውጭ በሆነ ቦታ የተኙ ናቸው ። ከወላጆቻቸው፣ ከአያቶቻቸው ወይም ከሌሎች ተንከባካቢዎች ጋር አብረው የተኙ ያሉ ሲሆን ከወንድማቸው፣ ከእህታቸው ወይም ከሌሎች ልጆቻቸው ጋር ተኝተው በዛው እስከወዲያኛው አሸልበው የተገኙም አሉበት ።
እነዚህን አሳዛኝ የሞት አደጋ ለመከላከል፣ ልጆች በሚተኙበት ወቅት ሊወሰዱ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች በደንብ ተገንዝቦ በቀንም ሆነ በማታ የልጆች የእንቅልፍ ሰዓት ጥንቃቄ መደረጉን ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ያሳስባሉ።
ደህንነቱ የተጠበቀ የሕፃናት እንቅልፍ ABC ምንድን ነው?
ABC የሕፃናት እንቅልፍ ደህንነቶች: A for Alone ወይም ለብቻ ማስተኛት ማለት ነው የሚሉት ዶክተር መሀመድ ህፃናት ሲያስተኙ ሁሌም በእራሳቸው አልጋ ውስጥ ብቻቸውን መሆን እንደሚገባው ያሳስባሉ።
ትንንሽ ህፃናትን ከሌሎች ልጆች ወይም ጎልማሶች ጋር እንዲተኙ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ይህም በአጋጣሚ የህፃኑ አፍ ላይ በመተኛት ህፃን ማፈን ወይም በእንቅልፍ ጊዜ በእነሱ ላይ የመንከባለል አደጋ ሊፈጥር ስለሚችል ነው።
አልጋ ውስጥ ሲተኙ ሁሉንም ለስላሳ ዕቃዎች ከህፃኑ ማራቅ እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ ። ለምሳሌ የሕፃናት አሻንጉሊት፣ ትራሶች ወይም ለስላሳ ዕቃዎች አብሯቸው መተኛት የለባቸውም ። እነዚህ ለስላሳ ዕቃዎች በአጋጣሚ በሕፃኑ ፊት ላይ በመምጣት የማፈን አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ ።
ለእነሱ የተዘጋጁ መተኛዎች ወይም ብርድ ልብስ ህፃኑን በሚተኛ ጊዜ እንዲመቸው ያደርጋሉ ። ህፃኑን ከመጠን በላይ ሊያሞቁ የሚችሉ ከባድ ብርድ ልብሶችን ወይም መተኛዎች መጠቀም ከሚፈለገው በላይ ሙቀት በመፍጠር የህፃኑን ምቾት ይቀንሳሉ ።
ABC የሕፃናት እንቅልፍ ደህንነቶች:- B for Back ህፃናት በጀርባቸው መተኛት ይኖርባቸዋል የሚሉት ዶክተሩ በጀርባቸው የሚተኙ ሕፃናት ከእንቅልፍ ጋር በተያያዙ የድንገተኛ የሕፃናት ሞት አደጋ (sudden infant death syndrome) የመሞት ዕድላቸው በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል። በአቅራቢያዎ ያሉ እናቶችን ፣ አያቶችን እና እርስዎን የሚንከባከቡትን ሁሉ ህፃን ሲያስተኙ በጀርባ እንዲያስተኙ ማስተማር ያስፈልጋል ይላሉ ።
“በጀርባ ማስተኛት ” የሕፃንን የመታፈን አደጋ ወይም ትንታን ሊጨምር ይችላል ብለው ለደቂቃ እንዳይሰጉ ። ይልቁኑ ህፃኑ ታፍኖ እንዳይሞት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ነው ያስረዱት ።
ABC የሕፃናት እንቅልፍ ደህንነቶች:- C for Crib የህፃናት አልጋ ለልጆች መኝታ አስተማማኝ መሆኑን ለማመልከት መሆኑን ገልፀው የህፃናት አልጋ እና ካቢኔቶች ለህፃናት መተኛ ከየትኛውም ስፍራ በጣም አስተማማኝ ስፍራዎች መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
በህፃን አልጋዎች ላይ ትራሶች፣ ዳይፐሮች፣ የተለያዩ መጫወቻዎች፣ ብርድ ልብሶች መኖር የለባቸውም ። ምክንያቱም በአጋጣሚ የሕፃኑን ፊት በመሸፈን የማፈን አደጋ ሊያመጡ ይችላሉ ።
የሕፃን የአልጋ (እርዝመቱ 120 cm ጎኑ 60 cm ሲሆን) ፍራሽ ጠንካራ እና የማይሰረጉድ መሆን አለበት ። አልጋው ባዶ ቦታ ሳይኖረው በጥሩ ሁኔታ የሚስማማ መሆኑን ያረጋግጡ :: ሕፃኑን ጡት አጥብተው ከጨረሱ በኋላ ሁል ጊዜ ልጅዎን ወደ ራሱ አልጋ መመለስዎን አይዘንጉ ።
በማንኛውም ሁኔታ ልጆችን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ነገሮች በተቻለ መጠን ማራቅ ድንገተኛ የህፃናትን ሞት ለመከላከል አቻ የማይገኝለት ጉዳይ ነው ። ወላጆች ወይም ህፃናት ተንከባካቢዎች በቀላሉ ህፃናቱ እንዳይታፈኑ ጥንቃቄ ማድረግ ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን አለበት ።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013