ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፎችን በማልማት ለዕድገቷ ለማዋል እንደምትሰራ ስታረጋግጥ የቆየች ቢሆንም፤ መሬት ላይ ጠብ ያለ የሚታይ ሥራ ግን የሠራችው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በአዲስ አበባው የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት፣ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ማድረግ እንደሚቻል ያመላከቱ ተግባሮችን በማከናወን አሳይቷል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አነሳሽነትና አስተባባሪነት አንድነት፣ የወዳጅነት እና የእንጦጦ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ከእነዚህ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ልምድ በመውሰድ እና በማስፋት በገበታ ለሀገር የቱሪዝም ሀብቶቿን ለማልማት ሰፊ ሥራ ውስጥ ገብቷል፡፡
እናም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በተፈጥሮ ሀብታቸው ውብ የሆኑትን ኮይሻን፣ ወንጪንና ጎርጎራን ለማልማት አቅዶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ፕሮጀክቱን ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶም ልማቱን ለሕዝብ ለባለሀብቶችና ለተለያዩ ተቋማት በማስተዋወቅ በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራትን በመቅረፅ እየተሠራ ይገኛል፡፡
ለፕሮጀክቶቹ ማስጀምሪያም ለሦስቱም ፕሮጀክቶች ዲዛይኖች ተዘጋጅተው ሶስት ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ሕዝቡም ተሳትፎውን እያረጋገጠ ሲሄድ፤ ባለሀብቶችም ከድጋፍ ባለፈ በፕሮጀክቶቹ ለመሳተፍ ጥያቄ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
የገንዘብ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በየጊዜው የደረሰበት ደረጃ ለሕዝብ ይፋ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ በተካሄደ መርሃ ግብር ላይ እንዳስታወቁት፤ በገንዘብ ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ ሶስት ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ የተጀመረ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡
ይሄን ተከትሎም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገበታ ለሀገር እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ለተወጡ በሀገር ውስጥ እንዲሁም በሀገር ውጭ ለሚገኙ መላው ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በምሥጋና መልዕክታቸውም፣ “3 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ አቅደን ጀመርን፤ እናንተ ደግሞ ኮይሻን፣ ወንጪን እና ጎርጎራን ለማልማት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እንዲሰበሰብ አደረጋችሁ›› ያሉ ሲሆን፤ የሆነው ሁሉ የኢትዮጵያውያን የመተባበር ውጤት እንደመሆኑም ‹‹በህብር ወዳሰብነው እንደርሳለን” ብለዋል፡፡
ከዚህ የምሥጋናና የጅሮጀክቶች ማስጀመሪያ የእራት ግብዣ መርሃ ግብር ማግስትም በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለትም በኮይሻ በመገኘት የመሰረት ድንጋይ በማኖር ፕሮ ጀክቱን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በሀብት አሰባሰብ የታየው ይህ ስኬት በብዙ መልኩ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ በሀገራችን ተሳኩ የሚባሉ ዕቅዶች ከመቶኛ በላይ የሚሆኑበት ዕድል ውስን እንደመሆኑ ይህ ዕቅድ ከአነዚህ ተርታ መሰለፉ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በቀጣይም በዚሁ ልክ መሥራት ከታቸለ በገበታ ለሀገር ሊከናወን የታሰበው ሁሉ እንደሚሳካም የዕቅዱ ስኬት ያመለክታል፡፡
እንደሚታወቀው ይህን ዕቅድ ለማሳካት ሲሰራ የነበረበት ወቅትም ሆነ ቀደም ያሉት ዓመታት ሀገራችን ከሰላምና ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ብዙ ፈተናዎች ውስጥ የነበረችባቸው ናቸው፡፡ ጁንታው የህወሓት ቡድን በያዘው የሴራ ፖለቲካ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን በመቀስቀስ ጥቃቶች በመሰነዘር ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ሠርቷል፤ በዚህም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡
ጁንታው ይህን ሁሉ ሲያደርግ የነበረው ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ለማድረግ እና መንግሥትን ከሕዝብ በማስጠላት ሥልጣኑን መልሶ ለመቆናጠጥ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማው መሳካት ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ እንዲገባ የሆነበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ አገር ምን ያህል ውድ ዋጋ እንደምትከፍል ይታወቃል፡፡
ለአብነት፣ ጁንታው በመሰረተ ልማት ላይ ያደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመተካት፣ ሰብአዊ ድጋፎችን ለማቅረብ እና ክልሉን መልሶ ለመገንባት ከፍ ያለ ሥራም ሀብትም የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ላይ የጁንታው ግብዓተ መሬት መግባት ያልተዋጠላቸው የጁንታው ርዝራዦች በውስጥና በውጭ አገር ሆነው በመንግሥትና በሀገሪቱ ላይ አሉቧልታ በመንዛት የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡
ይህ ሁሉ ፈተና ግን የመንግሥትን ትጋት፣ የሀገሪቱን የልማትና የሰላም ጉዞ ማስቀረት አልቻሉም፤ ለአፍታም እንኳን ሊያስተጓጉሉት እንዳልቻሉ ይህ የገበታ ለሀገር ስኬታማ ጉዞ አንድ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከመንግሥታቸው ጥሪ የሚያንገዋልሉት ወይም ይቆይ የሚሉት እንደሌላቸው ማረጋገጫ ነው፡፡
በሕግ ማስከበር ለተሰማራው ሠራዊት፣ በጁንታው አጥፊ ተልዕኮ ሳቢያ ለሰብአዊ ድጋፍ የተዳረጉ ወገኖችን ለመደገፍ ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን ሀገራቸውንና ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት የበኩሉን ሚና ለሚጫወተው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም ቀደም ሲል የገቡትን ቃል በወቅቱ በድጋፋቸው አረጋግጠዋል፡፡ ይህም የመንግሥት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን ኢትዮጵያውያን በሚገባ ተገንዝበው እየተሳተፉበት ስለመሆናቸው ማሳያ ነው፡፡
ስኬቱ ኢትዮጵያውያንና ሀገራቸው ኮሽ ባለ ቁጥር የያዙትን የሚለቁ እንዳልሆኑና ለአፍራሽ ሃይሎች አጀንዳዎች ቁብ እንደሌላቸውም ያመለክታል፡፡ ጁንታውና ተባባሪዎቹ ለኢትዮጵያ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመስጠት ከዋና የልማት አጀንዳዋ እንድትወጣ ሌት ተቀን ቢሠሩም፣ ኢትዮጵያውያን ልማታቸውን አጠናከረው መቀጠላቸውን አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን የብዙ ድሎች ማሳያ የሆነውን ይህን ፕሮጀክት ዳር ለማድረስ አሁንም ከመንግሥት ጎን መቆማቸውን አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013