በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ሰውዬው የእድር ጡሩንባ ነፊ ናቸው ።የእድሩ አባላት መካከል ሞት ሆኖ ጥሩምባ ለመንፋት ሲነሱ “ተመዝኖ መክበድ፤ ተመዝኖ መቅለል” የሚል ሰነድ ትዝ ይላቸዋል። ግለሰቡ የጥሩም ነፊነት ሃላፊነታቸውን ያገኙት በብዙ ጭቅጭቅ ነበር።
እንደሚባለው ከሆነ እድር ቤቱ ጥሩምባ ነፊ ለመቅጠር በእርሳቸው ላይ ያደረገውን አይነት ክርክር አድርጎ አያውቅም ነበር ይባላል። የእድሩ ሊቀመንበር ስብሰባውን መምራት የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቶ እስኪቸገር የሆነበት ስብሰባም በመሆኑ፤ ስብሰባውን ሊበትነው ጫፍ ደርሶም ነበር ሲባልም ሰምተዋል። በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፈው ያገኙት ሥራ የተመዘነበት ሰነድ ነው “ተመዝኖ መክበድ፤ ተመዝኖ መቅለል” የተባለው። የእድር ቤት ሰነድ ።
በወቅቱ በእርሳቸው ላይ አስተያየት የሰጡ ሰዎች አስተያየት በሙሉ ከስብሰባው በኋላ የእኔ በሚሉት ሰው አማካኝነት ሰምተዋል። እንደተናገራቸው በወሰን ጉዳይ የተጋጩት ጎረቤታቸው የሰጠው አስተያየት “ክቡር ሊቀመንበር ይቅርታ ያድርጉልኝና እኒህ ሰውን የእድራችን ጥሩምባ ነፊ ብናደርግ ድምፃቸው ጎልቶ ስለማይሰማ እድርተኛው መረጃው በአግባቡ ላይደርሰው ይችላሉ። ምናልባት ቤቱ ሃሳቤን የሚቀበል ከሆነ እራሳቸው በአካል ተገኝተው ጡሩንባ ሲነፉ ማየት ትችላላችሁ፤ እኔ ስለማውቀው ነው ።አዎን እርሱ አይሆንም፡፡”
ከዚህ ቀደም ብር ተቸግሮ እርሳቸው ያበደሩት ሌላኛው እድርተኛ ደግሞ ይነሳና “ክቡር ሊቀመንበር እኔ በእውነቱ በጣም ነው የማዝነው። አዎን በጣም ነው የማዝነው። እኒህ ሰው ከእድሩ መመስረት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በአንድም በሌላም እድራችንን ሲያገለግሉ የነበሩ ሰው ናቸው። ዛሬ ገና ለገና ገንዘብ ሊከፈላቸው የሚያስችል ሥራ ሆኖ ብንነጋገር የሚሆን የማይሆነውን እናነሳለን፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እንደ እርሳቸው ለእድራችን ተቆርቋሪ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ በፍፁም አላስብም፡፡ ስለሆነም ይቀጠሩ ባይ ነኝ።”
ልጄን ለልጅዎት የተባባሉት አንዲት እናት እንዲሁ ብድግ ይሉና “ኸረ ለመሆኑ ባለፈው ጊዜ ማናቸው ማዶ ቀበሌ 3 ያሉት እንጀራ በመሸጥ የሚተዳደሩት እድርተኛችን ባላቸው ባረፉ ጊዜ እኮ በበጎ ፈቃደኝነት ጥሩምባ የነፉት እኮ እርሳቸው ናቸው። እንደው ማን ይሙት እንደእዚያ ቀን ጥሩምባ ተነፍቶ ያውቃል።
የቀደመው ጥሩምባ ነፊ እንደምታውቁት ትቶን ከሄደ በኋላ የነበረውን ክፍተት የሞሉት እርሳቸው አይደሉም። ደግሞስ ከእኛ መሃል እንደ እርሳቸው የተማረስ አለ። ወይንስ ምንድን ነው ምክንያታችን ይህን ያህል እርሳቸውን ለመቅጠር የቸገረን፡፡”
ሌላው ተነስቶ ደግሞ ተቃውሞውን በወግ በወጉ አቀረበ። በአጭሩ ይቋጫል ተብሎ የታሰበው አጀንዳ ሰፊ የንትርክ ጊዜ ወሰደ ።የእድሩ ሊቀመንበር በምን ቀን ነው የዚህ እድር ሊቀመንበር የሆንኩት እስኪል ድረስ በልቡ አዘነ። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ለሦስት ወር ሙከራ ይቀጠሩ፤ በመጪው ሦስት ወር ውስጥ ግን የሚሞት ሰው ከሌለ በተጨማሪ ሦስት ወር ይታያሉ ተብለው ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተደረጉ።
ከሦስት ወር በኋላ አፈፃፀማቸው ሊገመገም እንደሚገባ፤ የግምገማ ሰነድን የሚያዘጋጅ ኮሚቴ መኖር ያለበት ስለመሆኑ እና የግምገማ ሰነዱም “ተመዝኖ መክበድ፤ ተመዝኖ መቅለል” ተብሎ እንዲሰየም ተስማሙ። ይህ የምናብ ታሪክ ምን ያስተምረናል? በቅድሚያ ምዝና ከየት እስከየትን እንመልከት።
ከየት እስከየት
አሁን ከቆምንበት በአራቱም አቅጣጫ ትንሽ እልፍ ብንል የበረከቱ የምዘና አይነቶችን እናያለን። ምዘና እንደ ተማሪ፤ ምዘና እንደ ሥራ ፈላጊ፣ ምዘና እንደ ሥራ ዕድገት፣ ምዝና እንደ ትዳር አጋር፣ ምዘና እንደ አባት፣ ምዘና እንደ ጉርብትና፣ ምዘና እንደ … ። ዘወትር እንደ ግለሰብ ራሳችንን እንመዝናለን። ስለ እከሌ ወይንም እከሊት ስናወራ በምዘና መንፈስ በተቃኙ ምልከታቸው ውስጥ ማለፋችን አይቀሬ ነው ።
በትዳራችን ውስጥ ምዘና አለ። በልጆቻችን ፊት እንዲሁም በጎረቤት ልብ ውስጥ ምዘና አለ። ለሥራ ለመቀጠር ሆነ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል በማለፍ ለሚደረግ ትምህርት ምዘና አለ። የኖርንበትን ዘመን ቆጥረን መልኩ ምን ይመስል እንደነበር ምዘና አለ። በአምላክ ፊት እንዲሁ ምዘና አለ። ቀሎ የመገኘት ወይንም ከብዶ የሚያሳይ ምዘና፡፡
በሕይወት ውስጥ የምናልፍባቸው የትኛዎችም ምዘናዎች ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል ካልን፤ በዋናነት ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ሁለት ዓላማዎች አሉ። ትላንትን ወይንም ያሳለፍነውን በአግባቡ በመገምገም ዛሬ መስተካከል የሚገባውን ለማስተካከል። ይቅር ማለትና ይቅርታን መጠየቅ እዚህ ጋር ዋናው ነው።
ትላንትን ባሰብን ጊዜ በጸጸት ዛሬን ከማበላሸት የሚረዳንን ተግባር ለማድረግ መነሳትም ማለት ነው፤ የንስሃ ፍሬም ልንለው እንችላለን። የትላንት ውስጥ የሆነውን ዛሬ ከማስተካከል ባሻገር ቀጥሎ ሊሆን ያለውን ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው ዓላማው፡፡ ግምገማ ሰውን መጉጃ ሳይሆን ማነፂያ ነው የሚባለውን ማለታችን ነው ።ለቀጣይ ጉዞ የሚሆነውን መቀመር መቻል ።
ጥሩምባ ነፊው ግለሰብ በትላንት ውስጥ ያለፉበትን የሚያስተካክሉት አለ፤ ፈጽሞ ሊያስተካክሉት የማይችሉትም እንዲሁ። ይህ የምዘና ዓላማ አንዱ ነው። የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ የሆነውን በመቀበል ውስጥ ቀጥሎ ሊሆን ያለውን ለማድረግ መነሳት ደግሞ ሁለተኛው ።
በዙሪያችን ያለው ሥርዓት እየመዘነ ትርጉም እንደሚሰጥ እንረዳለን። ከየት እስከየት ብንል በሁሉም ስፍራ ማለት የተሻለ መልስ ነው። በሁላችንም ሃይማኖት ውስጥ ከሞት ባሻገር ያለውን ምዘናንም ሳንዘነጋ። ተመዝኖ መክበድ ወይንም ተመዝኖ መቅለል እዚህም እዚያም ነውና። ዋናው ጉዳይ ግን ሚዛን ለመድፋት ዛሬ እንዴት እንኑር ነው፡፡
ሚዛን ለመድፋት
ቦክሰኛው ትጥቁን ታጥቆ ወደ መቦቀሻው ቀጠና ውስጥ የሚገባው በዝግጅት ነው። ያለ ዝግጅት ከባላንጣው ፊት ቢቀርብ የሚደርስበት ቡጤን ፈጽሞ መቋቋም አይችልም። ተማሪው ሆነ አትሌቱ፤ የመንግሥት ባለሥልጣኑ ሆነ ባለትዳሩ ሚዛን ለመድፋት ያስባል ።ሚዛን ደፊነቱም በእኛ ዘንድ ባለው አቅም ይገለጣል ።ዛሬ አብሮን ባለው ብቃት ውስጥ ሚዛን የመድፋታችን እውነታ አለ።
የገጠማቸውን ፈተና አልፈው በእግራቸው ቆመው ቀጣዩን የሕይወት ክፍል በድል አድራጊነት የተመለከቱ ብቃት የተገኘባቸው መሆኑ ጥርጥር የለውም ።በጦር ውሎ ድልን ተቀዳጅቶ የድል ብስራትን ለማሰማት የሚረዳ ብቃት በሠራዊቱ ውስጥ ያስፈለጋል። ብቃቱም በብዙ መንገዶች የሚገለጥ ነው። በኦሎምፒክ ሜዳ ሪከርድ የሰባበረ እንዲያው ብቃት የለሽ ሆኖ ሊገኝ የሚችል ትንግርተኛ ሰው ሊኖር አይችልም። ከብቃት የሚወጣ ድል አድራጊነት አለ።
ብቃትን መፍጠር፤ ብቃትን ማቆየት፤ ብቃትን ማባዛት ቢሆንልን በየዕለቱ ብንመኘው በተሰማራንበት ሁሉ ለፍሬ እንሆናለን። ከፍሬያችንም በልተው የሚጠግቡም ይበዛሉ። ተመዝኖ መክበድም ሆነ መቅለል ሚዛን መድፋት በሚያስችል ወይንም በማያስችል ብቃት ውስጥ እውነታነቱ አለ ።
በአገራችን ኢትዮጵያ የንግድ ሥራን ለመጀመር ፈቃድ ለመጠየቅ ወደ ሚመለከተው የመንግሥት አካል ሲኬድ ከሚጠየቁ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የብቃት ማረጋገጫ ነው። በእርግጥ አስፈላጊ ነው። ሁሉም ያሻውን እንደፈለገው እንዳይሠራ፤ ለገብያ የሚቀርበው እቃም ሆነ አገልግሎት ሚዛን የሚደፋ መሆን አለመሆኑን ለመለየት ብቃቱ ተፈትሾ ማረጋገጫ ይሰጥበታል።
ለትዳር የቀረበላትን ጥያቄ ሁሉ ከመቀበሏ በፊት በአስተውሎት መመዘን የምትችል ሴት እንዲሁ ምሳሌያችን ትሁን። ሚዛን ለሚደፋው የሚሰጠው ምላሽ እንዲያው አልተሰጠውም፤ ተመዝኖ ዋጋ የተሰጠው ነገሮች ስለተገኙ እንጂ። በጥቅሉ ብቃት የሚለውን ቃል አስምረንበት እንለፍ። ባል የመሆን ብቃት፣ ሚስት የመሆን ብቃት፣ መሪ የመሆን ብቃት፣ ልጅ የመሆን ብቃት፣ ጎረቤት የመሆን ብቃት፣ ጥሩምባ ነፊ የመሆን ብቃት ወዘተ፡፡
ሚዛን በመድፋት የሚኖሩ ሰዎች፣
1. መሆን ያለበትን ነገር ማየት የሚችሉ፣
2. መሆን ያለበትን ነገር እንዲሆን የሚያደርጉ፣
3. ይሠራ በሚባልበት ጊዜ ሥራዎችን የሚሠሩ ናቸው፡፡
ከሦስቱ የትኛውም የሚገልጽህ ይመስልሃል? አንተ አሳቢ ነህ? አከናዋኝ ነህ? ወይስ ሥራው እንዲሠራ አስተባባሪ? የሆንከውን በሆንክ መጠን ሰዎችን ይዘህ የተሻለ ተጽዕኖን መፍጠር ትችላለህ፤ ሚዛን መድፋት ይህን ማድረግ በሚያስችል ብቃት ውስጥ የሚገለጥ ስለሆነ። ዘወትር ተመዝኖ ከብዶ ለመኖር የሚያስፈልጉት ቁልፍ ነጥቦች ቀጥሎ እንመልከት፡፡
ተመዝኖ ከብዶ ለመኖር
ሁላችንም ብቃታቸውን በተግባር የሚያሳዩ ሰዎችን እናደንቃለን። ማድነቅ መቻል ራሱ ብቃት ቢሆንም። አናፂ ይሁን፣ አትሌት ወይንም የተሳካለት የንግድ ሰው በተግባር ሥራ ውስጥ የሚገልጠውን አቅም በተግባር አይተን እንደመማለን ደግሞም እንደሰታለን።
በብቃታቸው አንቱታን ያተረፉ ሰዎችን የቱንም ያህል አድናቂ ብንሆንም አስቸጋሪው ነገር ግን የታላቅ ብቃት ማሳያ የሆኑትን እንደ ቢል ጌትን፣ ማይክል ጆርዳንን ወይንም እንዲሁ ስለፈለግን መሆን አለመቻላችን ነው። እኒህ ሰዎች ያወቅናቸው በብቃታቸው እንጂ በመጠሪያ ስማቸው ልዩ መሆን አይደለም ።
ከእኒህ ሰዎች ህይወት ተምረን ተመዝኖ ከብዶ ለመኖር ብቃታችንን እንዴት ማጎልበትና ሥራ ላይ ማዋል እንዳለብን ለማወቅ ግን እንችላለን ።አይደለም በብቃታቸው አስከታዮችን ያፈሩትን ይቅርና በሳርቅጠሉ መማር ስለሚቻል። የሚከተሉት ነጥ ቦች በብቃታቸው ጎልተው ከወጡት የምን ማራቸው ናቸው፡፡
1. ሁሌም መሻሻልን የህይወት መርህ ማድረግ፣
በፈተና ውስጥ መጽናት አቅምን ይጠይቃል። በእያንዳንዱ ቀናት ውስጥ የተገነባ አቅም። ሁሌም ለመሻሻል ዝግጁ ከሆነ ልብ ውስጥ የሚገኝ አቅም። አስተውል ሁሌም ለመሻሻል ራሳቸውን ዝግጁ ያደረጉ ሰዎች ዘወትር በእድገት መስመር ውስጥ ናቸው። በምድራችን በብቃታቸው አንቱታን ካተረፉ ሰዎች የምንማረው ቀዳሚው ነጥብ ሁሌም ለመማር፣ ለማደግ እናም ለመሻሻል ጥረት የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው ።
ሁሌም መሻሻልን የህይወት መርህ ማድረግ አይደለም በግለሰብ ደረጃ በተቋም ደረጃም የሥራ ክፍል ኖሯት የሚሰራበት ሁኔታም አለ። በግልህም እንዴት ይበልጥኑ። ሁሌም መሻሻልን መርህ ማድረግ ሁሌም አቅም መጨመር ስለሆነ፡፡
ራሳችንን ስንመዝን በዙሪያችን ባሉ ሥራዎች ተወጥረን መሻሻልን ከማድረግ የዘገየን ሆነን እንገኝ ይሆን? ከሆነ ከመስመሩ የሳተውን ራሳችንን እንመልስ። ከመሻሻል ህይወት በአዕምሮህም ሆነ በስሜትህ የተለያየህ ከሆነክ ዳግም ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው ።በመጀመሪያ ዳግም ራስህን ወደ ሥራህ ምራው። ያልተከፋፈለ ትኩረት ለሥራህ ለመስጠት ቁርጠኛ ሁን። በመቀጠል ለምን ከመሻሻል እንደተነጠልክ አስብ። ሁሌም መሻሻልን የህይወት መርህ ማድረግ ሲመዘኑ ከብዶ ለመገኘት አሁንም ዋናው ነገር ነው ።
2. ዛሬን እንደ መድረክ፤
ሁሉም ነገሮች ወደሚጠብቃቸው ይመጣሉ የሚል አባባል አለ። ሃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች በየዕለቱ በሚጠበቁበት ቦታ ላይ የሚገኙ ናቸው ።ነገር ግን በጣም ተወዳዳሪ ያላቸው የብቃት ሰዎች ግን ከዚህም ደረጃውን ከፍ ያደርጉታል። እንዲህ አይነት ሰዎች በሚጠበቁበት የተወሰነ ቦታ ላይ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለሆነ ውስን ወቅት ሳይሆን በተከታታይ በየዕለቱ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በሚጠበቁበት ቦታ ላይ በብቃታቸው ይገኛሉ ።
በጊዜ እርቀት ውስጥ በሚመጣ መድረክ ላይ ብቻ የሚደምቁ ሳይሆን፤ እያንዳንዱን ቀን እንደ መድረክ የሚጠቀሙበት ናቸው። በተከታታይነት ብቃታቸውን ለማሳየትም ይጥራሉ ።ያሉበት የስሜት መዋዠቅ ምንም ይሁን ምን በሚጠበቁበት ቦታ ላይ ይገኛሉ። ዛሬን እንደ መድረክ በመጠቀም ለነገ መደላድልን ይፈጥራሉ። ዛሬ በትንሹ በመታመን ለነገ በትልቁ ለመሾም መዘጋጀት የተገባቸው እንደሆነ ስለሚያምኑ ።
3. የትም ፍጪው … ሳይሆን ልቀትን መከተል፣
አንድን ነገር በዚህም ተባለ በዚያ እንዲሠራ ማድረግ ይቻል ይሆናል። የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው እንደሚባለው። ነገር ግን ልቀትን በተከተለ መንገድ ማድረግና የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ፈጽሞውኑ ይለያያሉ። ጎበዝ ተወዳዳሪ ነው ተብሎ የሚጠራ ነገር ግን በተወዳዳሪነት ጎዳና ላይ በትጋት የማይሄድ ሰው ሊገኝ አይችልም። ፎስተር የተባለ ሰው እንዲህ አለ ጥራት በድንገት የሚገኝ ነገር አይደለም። ጥራት በታላቅ ትኩረት፣ ጥረት እናም ችሎታን መሰረት ካደረገ ሥራና የብልህ ምርጫ ውስጥ የሚገኝ ነው ። ሚዛን ደፊነት ማለትም ይኸው ነው ።
በከፍተኛ ደረጃ ልቀት ውስጥ መገኘት ሁልጊዜ የነፃ ፈቃዳችን ምርጫ ነው ።ብርቱው የሜዳ ውስጥ ንጉሥ ተጫዋች የቡድን አባላቱን የጫወታውን ኳስ እንዳቀበላቸው እንደዚያው በብቃት እንዲጠቀሙበት ይጠብቃቸዋል። እነርሱም እንደቡድን አባልነታቸው ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደ ውጤት የሚቀየር ኳስ እንድናቀብላቸው ይጠብቃሉ፡፡
ለራስህ የምትሰጠው ደረጃ የትም ፍጪው ሳይሆን መሆን ባለበት መንገድ ነገሮች መሆን እንዲችሉ ማድረግ ይሁን። ልታደርግ ያሰብከውን ያለመዋዠቅ በከፍተኛ ደረጃ መፈፀም ካልቻልክ ለሥራህ የሰጠኸውን ደረጃ ዳግም መርምረው፡፡
ብርቱው የኳስ ሰው ብቻውን ዋንጫ ማንሳት የሚችልበት ሊግ የለም። እንደ ኳሱም ሁሉም የህይወት መስኮቻችን እርስ በርስ እንድንፈላለግ የሆንባቸው ናቸው ።ስለሆነም ሚዛን መድፋትን ስናስብ ሌሎችን መነሳሳት ሌላው ቁልፍ ነጥብ ሆኖ እናገኘዋለን ።
4. ሌሎችን አነሳሳ፣
ከፍተኛ ተወዳዳሪ የሆኑ መሪዎች እራሳቸው በከፍተኛ ደረጃ ከማከናወን በላይ መሄድ የሚችሉ ናቸው። ከማከናውን በላይ መሄድ ማለት ሰዎችን ማነሳሳት እና ማበረታታት መቻልና ይህንም ወደ ውጤት መቀየር መቻል ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ግንኙነትን ማዕከል ባደረገ ችሎታ ላይ በማተኮር በደረሱበት ነገር በመርካት ይሄዳሉ ።
ውጤታማ መሪዎች ግን በተሻለ ብቃት የሚመሯቸውን አቅም በማሰባሰብ ወደ አዲስና የተሻለ ምዕራፍ ለመግባት ይሠራሉ። ሌሎችን በማነሳት አሁን ከደረሱበት ባሻገር ማየት መቻል እርሱ የብቃት መገለጫ ነውና፡፡
ተመዝኖ በመክበድ ውስጥ በተሳሳተ መንገድ የሚሄደውን መመለስ፤ ድካም ያለበትን ከድካም ለማውጣት ጥረት ማድረግ፤ ከሥራው ይልቅ አሻጥር ላይ የሚያተኩረውን ከተንኮሉ እንዲመለስ መንገድ መቀየስና ወደ ጤናማነት እንዲመጣ ማድረግ ወዘተ ተገቢ ነው። ሌሎችን አነሳስቶ ባለሚዛን በማድረግ ሚዛን መድፋት አለ።
በመጨረሻው የሚለከውን ስለምታውቅ ከሚለከው በላይ ተገኝ ።
5. ከሚለካው በላይ መገኘት
ከፍተኛ ተወዳዳሪ የሆኑ ሰዎች ሁልጊዜ ከሚጠበቀው እርቀት በላይ መሄድ የሚችሉ ሰዎች ናቸው ።ለእነርሱ ጥሩ የሚባለው ደረጃ በእውነትም ጥሩ አይደለም ።ጥሩ በሚባል ደረጃ የሚረኩ ሰዎች አዲስን ታሪክ ማስመዝገብ አይችሉም።መሪዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚመሩትን ጉዳይ ለማድረግ ከሚጠበቀው በላይ ማከናወንን መምረጥ አለባቸው።
ጥሩምባ ነፊው የሚመዘኑባቸው ነጥቦች “ተመዝኖ መክበድ፤ ተመዝኖ መቅለል” ውስጥ ይገኛሉ ።ከተጻፈው በላይ ለመሄድ ጥረት ባደረጉ ቁጥር ሥራቸውን ማጽናት ይችላሉ ።
ነገር ግን አንድ የተረሳ ነጥብ አለ በሰነዱ ውስጥ የሌለ መመዘኛ። “ተመዝኖ መክበድ፤ ተመዝኖ መቅለል” ሰነድ ውስጥ ጥሩምባ ነፊውን ለመመዘን ከገቡት ነጥቦች ባሻገር በመዛኞቹ ልብ ላይ ያለ ነገር ግን አለ ።
6. ለህሊና እረፍትን መስጠት
ጥሩምባ ነፊው በተቀጠሩ ጊዜ ለእርሳቸው መልካሙን የተናገሩት ከእድር አባልነታቸው ውጭ ባላቸው መልካም ግንኙነት ይመስላል ።የተቃወሟቸው ደግሞ ከእድር ሥራቸው ውጭ ባለ ጉዳይ ባላቸው ጉዳይም ይመስላል ።“ተመዝኖ መክበድ፤ ተመዝኖ መቅለል” የቱንም ያህል በጥራት የተዘጋጀ መመዘኛ ቢሆንም መመዘኛውን ተጠቅመው የሚመዝኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን መንፈስ አይገልጥም ።
መፍትሄው ለህሊናህ እረፍትን መስጠት ነው ። ልት ኖር የተገባውን ኑር። ሰዎች የሚሰጡት ምዘና ፍትሃዊ የማይሆንበት እድል እንዳለም ተረዳ። ለመሻሻልና ሁሌም የተሻለውን ለማድረግ የሚሰራ ሰው ሁን ።ከእዚያ ባለፈ ግን የህሊናህን ድምጽ አድምጥ ።ለህሊናህ እረፍት በተሰማህ ነገር ውስጥ ሰዎች ባይቀበሉትም እንኳን ልትኖር ግድ ነው ።ትልቁ ዳኛ – ህሊና!
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013