ዓለማችን የደረሰችበትን የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ በእጅጉ የፈተነው፣ የፈጣሪን ህልውና እስከመካድ የደረሱ በርካታ ሳይንቲስቶችን ሃሳብ ያስቀየረው እና የብዙ በስልጣኔኣቸው የተመኩ መሪዎችን ፊት ወደፈጣሪ የመለሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዘላቂ መፍትሄ ሳይገኝለት ከአንድ ዓመት በላይ ዘልቋል። በአገራችንም ቫይረሱ ከተከሰተ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀሩታል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ቫይረሱ በዓለም ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት ከ111 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች በዚሁ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል። በአገራችንም ቢሆን እስካሁን የደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። ቫይረሱ ለመጀመርያ ጊዜ ከታየበት መጋቢት አራት ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከ151 ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ የታየባቸው ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥም 2 ሺህ 259 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
የኮቪድ 19 በዚህ ደረጃ በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ከማስከተሉም በላይ በኢኮኖሚ ረገድም ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። እንደነ አሜሪካ ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው አገራት ይህንን ወረርሽኝ ለመቋቋም ከሁለት ትሪሊየን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ኢኮኖሚያቸውን ለመደጎም የተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ሌሎች አገራትም ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል። በርካታ የኢኮኖሚ ተቋማትና ድርጅቶች በወረርሽኙ ሳቢያ እስከመዘጋት ደርሰዋል። ከነዚህም መካከል በዓለም ላይ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው የአየር መንገዶችና የቱሪዝም ተቋማት ይጠቀሳሉ።
ምንም እንኳን እስካሁን የጉዳቱ መጠን በጥናት ባይረጋገጥም በኢትዮጵያም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ አድርሷል። የተቀዛቀዙት የንግድ እንቅስቃሴዎችና በማበራዊ ዘርፉ ያጋጠመው ውጥንቅጥ ለዚህ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ቀድሞውንም በቋፍ ላይ የነበረው የአገራችን የትምህርት ዘርፍም በወረርሺኙ ምን ያህል በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደገባ የብዙዎቻችን ቤት ምስክር ነው።
ያም ሆኖ ግን መንግሥት የሄደባቸው የጥንቃቄ መንገዶች በሚጠበቀው ልክ ጉዳት ሳያስከትል ቆይቷል። በተለይ ድህነቱ እንዳይባባስ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር የተሠራው ሥራ ለዚህ ማሳያ ነው። ቫይረሱን እየተከላከልን ሥራችንን እንድንሠራ በተደረጉ ጥረቶች ቫይረሱ የሚጠበቀውን ያህል የኢኮኖሚ ጉዳት ሳያስከትል እንዲቆይ አድርጎታል።
በርግጥ በአገራችን የቫይረሱ ሥርጭት በታየበት ሰሞን በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው የፍራቻ ስሜት ከልክ ያለፈ ስለነበር፤ በመጀመርያው ዕለት መንገዶች ጭር ያሉበት እና በርካቶች ምግብና ልዩ ልዩ ሸቀጣሸቀጦችን በመግዛት ማከማቸት ላይ የተጠመዱበት፤ የተለያዩ ውዥንብሮች ውስጥ የተገባበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል። ይህ ግን በዚሁ ሁኔታ አልቀጠለም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነገሮች ተቀይረው ችግሩን የመልመድ ሁኔታው እያደገ መጣ። አልፎ መዘናጋቱ ከልክ ያለፈ ሆነ።
እናም ዛሬ ላይ ህብረተሰቡ የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ከዕለት ወደዕለት እየቀነሱ፤ በአንፃሩ ቫይረሱ የሚያስከትለው ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጣ። ወደፅኑ ሕክምና የሚገቡ ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን የሞት ምጣኔም ወደሰባት ከመቶ ከፍ ማለቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች እንደሚሳዩትም፣ በኮሮና ቫይረስ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እያለፈ ሲሆን፤ ለአብነት፣ በሚሊኒየም የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል ብቻ በ51 ሳምንት ጊዜ ውስጥ የፅኑ ሕክምና ፈላጊ ቁጥር በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት የአይ.ሲ.ዩ ክፍሎች በመሙላታቸው በመተንፈሻ ማሽን ለመረዳት ጥያቄ ያቀረቡ ታካሚዎችን ለመመለስ ተገድዷል። በተመሳሳይ በየካ ኮተቤ ማዕከል በፅኑ ህሙማን ክፍል ሆነው የአጋዥ መተንፈሻ ማሽን ከሚጠቀሙት አስር ታካሚዎች መካከል በአማካኝ ስምንቱ ህይወታቸው ያልፋል።
ስለዚህ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ከወዲሁ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ካልተቻለ ከባድ ፈተና መግጠሙ አይቀሬ ነው። መንግሥት በሁሉም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ማስክ መጠቀምን ግዴታ አድርጎ እየሠራ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ላይ ከፍተኛ ውስንነቶች ይስተዋላሉ። ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ በየቦታው የሚንቀሳቀሱ የህብረተሰብ ክፍሎችና አገልግሎት ሰጪዎች ጭምር ያለማስክ ሲሰሩ ማየት እየተለመደ ነው።
እንግዲህ እነኚህ ሁለት ተቃርኖዎች ከወዲሁ ሊታረሙ ይገባል። ምክንያቱም በአንድ በኩል የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ቢሆንም ከቁጥሩ ጋር የሚመጣጠን ቦታና ህክምና የለም። በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ቫይረሱ የጠፋ እስኪመስል ድረስ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ሆኗል። ስለዚህ ሁሉም ቆም ተብሎ ሊያስብ ይገባል።
ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የክትባት መድኃኒቶች ቢገኙም እነዚህን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ግን ገና ብዙ ፈተናዎች የተደቀኑበት ነው። የመድኃኒቱ ባለቤቶች አብዛኞቹ የሰለጠኑና የኢኮኖሚ አቅማቸው የጠነከረ አገራት በመሆናቸው መድሃኒቱን በቅድሚያ ለራሳቸው ዜጎች ለማዳረስ የተለያዩ ፍላጎቶችን እያሳዩ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የቫይረሱን ሥርጭት መግታት ካልተቻለና ሥርጭቱ እየተስፋፋ ከመጣ ክትባቱን ለመጠቀም ያለው ዕድል አናሳ በመሆኑ ለኛ ቅድመ መከላከል ላይ አተኩሮ መሥራት አማራጭ የሌለው ነውና አንዘናጋ።
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም